August 4, 2009

ቅዱስ ፓትርያርኩ ሕገ ቤተ ክርስቲያን የማሻሻል ርምጃ ጀምረዋል

• ቋሚው ሲኖዶስ የፓትርያርኩን ሕግ የማሻሻል ጥያቄ አልተቀበለውም ነበር፤
(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 3/2009)፦ በግንቦት 2001 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ከብፁዓን አባቶች በተነሣባቸው ጥያቄና አስተያየት ተቃውሞ የገጠማቸው ቅዱስ ፓትርያርኩ “ሕገ ቤተ ክርስቲያን” ተባለውን የቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ለማሻሻል እንቅስቃሴ ጀመሩ። ታማኝ ምንጮች ለደጀ ሰላም እንደገለፁት በ1991 ዓ.ም ወጥቶ በሥራ የሚገኘውንና ፓትርያርኩ ከብፁዓን አባቶች ጋር ክርክር በገጠሙበት ወቅት አላፈናፍናቸው ያለውን ሕግ ለመቀየር ቆርጠው መነሣታቸው ታውቋል።

ከጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በፊት ሕጉን ለውጠው ለመቅረብ የወሰኑት ቅዱስነታቸው ይህንኑ እንዲያስፈጽሙ ለሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በደብዳቤ መመሪያ ሰጥተዋል ተብሏል። ጉዳዩን አስቀድመው ለቋሚ ሲኖዶስ ያቀረቡት ቅዱስነታቸው ቋሚ ሲኖዶሱ “ሕጉን ለማሻሻል መብት የለኝም፣ ሕጉን ለማሻሻልም አሁን በቂ ምክንያት አላገኘሁም” በማለቱ ነገሩ ወደ ሌሎች ሊቃውንት ሊመራ እንደቻለ ተጠቁሟል።

“ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ማጥናት ስለማስፈለጉ” በሚል መሪ አጀንዳ በቅዱስነታቸው የተጻፈው ይኸው ደብዳቤ ፓትርያርኩ የቁልቢ ገብርኤልን በዓል ለማክበር ከመሄዳቸው በፊት ተጽፎ ተሰራጭቷል። ደብዳቤው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥርዓት ባልጠበቀ መልኩ ግልባጭ ሊደረግላቸው የሚገቡ ግለሰቦችንና ቢሮዎችን ሳይጠቅስ አልፏል ተብሏል። ደብዳቤው ለሥራ አስኪያጁ ለብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ብቻ ግልባጭ የተደረገ ሲሆን ለቋሚ ሲኖዶስ እንኳን ግልባጭ አልተደረገም ተብሏል።

የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖናዊ ሥርዓት የሚጥስ፣ የቤተ ክርስቲያኗን አንድነት የሚያደፈርስ አዝማሚያና ችግር ሲገጥም ሊቃውንት ተሰብስበው ዕቅድ አውጥተው፣ ለተከሰተው ችግር መንስዔ የሆነውን ሕገ ደንብ በመመርመር ሕጉን በማሻሻልና አስፈላጊውን መፍትሔ በማሳለፍ መፍትሔን እንደሚያስገኙ ይታወቃል።

“እንደሚታወቀው ሁሉ የሰሞኑ ዘርፈ ብዙ ችግር ጊዜያዊ መፍትሔ ያገኘ ቢሆንም የዘለቄታውን የሥራ ደህንነት በተመለከተ ከፍትሕ መንፈሳዊ፣ ከሌሎች ቀኖናዊ ሥርዓት ካላቸው መንፈሳዊ መጻሕፍት፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተጨባጭ የሥራ እንቅስቃሴና ቀደምት አበው ሲሰሩባቸው ከኖሩት የታሪክ መዛግብት አንጻር አሁን እየተሠራበት ያለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በማየት ወጥ ሕገ ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅታችሁ ታቀርቡ ዘንድ ይህ የቤተ ክርስቲያናችን የጥሪ መልእክት እንዲደርሳችሁ ማድረግ አስፈልጓል”

የሚለው የቅዱስነታቸው መመሪያ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የኮሚቴው ሊቀ መንበር ሆነው ተሰይመዋል።

ደብዳቤው የተጻፈውም
1. ለቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል፣
2. ለመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ፣
3. ለሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ አማኑኤል፣
4. ለንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ፣
5. ለመላከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን፣
6. ለዶ/ር አዲስ የሻነው (የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር)፣
7. ለአቶ ይስሐቅ ተስፋዬ፣
8. ለመጋቤ ሠናያት አሰፋ ሥዩም (የዚህ ኮሚቴ ፀሐፊ ሆነዋል)፣ እና
9. ለብፁዕ አቡነ ገሪማ መሆኑ ታውቋል

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)