July 10, 2009

ምርጥ ንግግሮች ስለ ወቅቱ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 9/2009)
“እርስዎ (ቤተ ክርስቲያኒቱን) ገደሏት እኛ ደግሞ አፈር አልብሰን ቀበርናት” (ብፁዓን አባቶች ፓትርያርኩን የገሰፁበት አባባል)
“ጳጳሳትም ካልተባበሩ፣ መንግሥትም ይህንን ሁሉ ችግር እያየ አንድ መፍትሔ ካልሰጠ፣ እግዚአብሔር ይፍታው ማለት ነዋ… እርሳቸውም (ፓትርያርኩ) እምቢ ካሉ፣ ሲኖዶሱም ፍርክርክ ካለ፣ መንግሥት ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ተለይታለች ብሎ አንድ አስታራቂ ነገር ካልሰጠ፣ የቤተ ክርስቲያኗ ጳጳሳት በአንድ ዓላማ ካልሄዱ፣ እግዚአብሐየር ይፍታው እንጂ ማን ይፈታዋል ታዲያ? 17 ዓመት ሙሉ በወሰንነው ውሳኔ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አልሄድንም … ቤተ ክርስቲያናችንን ሕዝባችንን እስከ መቼ ድረስ ለምን እናሳዝናለን? ቤተ ክርስቲያናችንንስ ለምን እንጎዳለን?”
ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ መጨረሻው ምንድርነው ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ ከተናገሩት፤
ቅዱስ ሲኖዶስ፦ የትናንት ታሪኩ፣ የዛሬ ፈተናው

By (ቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን)

Source:- From Mahibere Kidusan Website.
ሲኖዶስ የሚለው ቃል የግሪክ ሲሆን ትርጉሙም የተቀደሰ ጉባኤ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠብቁ በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ጳጳሳት እና ሊቃነ ጳጳሳት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጽናት እና ለመጠበቅ የሚደርጉትን ስብሰባ ያመለክታል፡፡ ይህ የጳጳሳት እና የሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ (ሲኖዶስ) በቤተ ክርስቲያን ከፍተኛው አካል ሲሆን የጉባኤው ሰብሳቢ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወይም ፓትርያርኩ ነው፡፡ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ማሻሻል እና መደንገግ የሚችል፣ አኅጉረ ስብከቶችን የሚያቋቁም፣ የጳጳሳት እና የኤጲስ ቆጶሳትን ሲመት የሚያጸድቅ፣ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ውጪ የሆኑ ወቅታዊ ፍልስፍናዎችን እና ግኝቶችን በመለየት እና ለምዕመናን በማሳወቅ ቤተ ክርስቲያን በንጽሕና እንድትጓዝ የሚያደርግ የቤተ ክርስቲያን ጉባዔ ነው፡፡

‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዜአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው እና ለራሳችሁ ተጠበቁ›› (ሐዋ. 20፡28) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጸው ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሐዋርያት እና በእነርሱ እግር የተተኩ ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ የተለያዩ ጉባዔዎችን አድርገዋል፡፡

ሐዋርያት በ54 ዓ.ም ክርስትናን በተቀበሉ በአይሁድ እና በአሕዛብ መካከል የነበረውን ልዩነት ለመፍታት በኢየሩሳሌም ያደረጉት ጉባኤ፣ በ325 ዓ.ም ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› (ሎቱ ስብሐት) ብሎ በተነሳው በአርዮስ የክህደት ትምህርት ምክንያት በኒቅያ የተደረገው ጉባዔ፣ በ381 ዓ.ም ‹‹መንፈስ ቅዱስ አካል የለውም (ሕጹጽ ነው)›› የሚል የክህደት ትምህርት ይዞ በተነሳው በመቅዶንዮስ ምክንያት በቁስጥንጥንያ የተደረገው ጉባዔ፣ በ451 ዓ.ም ‹‹እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ ሰብእ እንጂ ወላዲተ አምላክ አትባልም›› የሚል የክህደት ትምህርት ይዞ በተነሳው በንስጥሮስ ምክንያት የተደረገው ጉባዔ ኤጲስ ቆጶሳት እና ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ያደረጓቸው ዓለም አቀፍ ሲኖዶሶች ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን ላለው አገር አቀፍ ሲኖዶስ መሠረቶች ናቸው፡፡

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከዓለም አቀፍ ጉባዔ በተጨማሪ በየቦታው በቤተ ክርስቲያን ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታትና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጽናት የተደረጉ ብሔራዊ ሲኖዶሶች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ በ314 ዓ.ም በሃይማኖት በሚደርስባቸው መከራ ምክንያት ከክርስትና ወጥተው የነበሩ ክርስቲያኖች በንስሐ እንዲመለሱ እና ሌሎች ቀኖና ቤተ ክርስቲያናትን ለመደንገግ በእንቆራ የተደረገው የኤጲስ ቆጶሳት ሲኖዶስ፣ በ341 ዓ.ም ስለ መብል እና ስለ ጋብቻ የተነሱ ውዝግቦችን ለመፍታት በጋንግራ የተደረገው የኤጲስ ቆጶሳት ጉባዔ፣ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ በጳውሎስ ሳምሳጢ የክህደት ትምህርት ምክንያት በአንጾኪያ የተደረገው ሲኖዶስ፣ በ345 ዓ.ም በማኒ የክህደት ትምህርት ምክንያት የተደረገው ጉባዔ፣ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ብሔራዊ ሶኖዶሶች ናቸው፡፡

ሲኖዶስ ሲባል የጳጳሳት ጉባዔን የሚያመለክት ቢሆንም የጳጳሳት ስብሰባ ሁሉ በራሱ ግን ሲኖዶስ ነው ማለት አይደለም፡፡ ማንኛውም አገር አቀፍ የኤጲስ ቆጶሳት እና የጳጳሳት ጉባዔ ሲኖዶስ የሚባለው ቅዱስ አትናቴዎስ ባስቀመጠው መሥፈርት በመጀመሪያ የሐዋርያትን ትውፊት ሲጠብቅ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚገልጽ እና የሚያጸና ሲሆን እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸውን ጉባዔያት፣ ቀኖናዎች ሲደግፍ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊት ብትሆንም ብሔራዊ አስተዳደር እና ገጽታ አላት፡፡ በዚህም መሠረት በአገር አቀፍ ደረጃ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እና ሕልውና የሚጠብቅ አንድ አገር አቀፍ ሲኖዶስ ብቻ ይቋቋማል፡፡ በዚህም መሠረት ቀደም ብለው ይታወቁ የነበሩት የሲኖዶስ መንበሮች የእስክንድርያ፣ የሮም፣ የቁስጥንጥንያ፣ መንበሮች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የምትቀበላቸውም የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ዓለም ዓቀፋዊ ሲኖዶሶችም የተካሄዶት በእነዚህ መንበር ሥር ከነበሩ ኤጲስ ቆጶሳት እና ጳጳሳት የተሰባሰቡ ናቸው፡፡ በ451 ዓ.ም የተደረገው የኬልቄዶኑ ጉባዔ ግን ቅዱስ አትናቴዎስ ያስቀመጣቸውን ከፍ ብለን የጠቀስናቸውን መሥፈርቶች ያልተከተለ በመሆኑ በምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት የለውም፤ እንዲያውም በተለየ ስሙ ‹‹ጉባዔ ከለባት›› በመባል ይታወቃል፡፡

ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያን ላይ መከፋፈል በማምጣቱ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የነበረው ግንኙነት ተቋርጧል፡፡ በዚህም ምክንያት ብሔራዊ ሲኖዶሶች እያደጉ የመጡ ሲሆን የኢትዮጰያ ኦርዶቶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ ሲኖዶስ ሳይኖራት በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሥር ከ1600 ዓመታት በላይ ቆይታለች፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ለዚህ የረጅም ዘመናት የራሷ ሲኖዶስ ሳይኖራት የቆየችው የሊቃውንት እጥረት ኖሮባት ሳይሆን የራሷን መንበረ ጵጵስና እና ሲኖዶስ ለማቋቋም መሠረቱ የክርስቲያች ፍቅር እና አንድነት መሆኑን በማመን ነበር፡፡ ለዚህም ነው በተለያዩ ወቅቶች የኢትዮጵያ ነገሥታት ያቀረቡት ጥያቄ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት ባያገኝም ብዙ ሥጦታዎችን በመላክ ጳጳሳትን ከግብጽ ሲያስመጡ የኖሩት፡፡

ግብጽ በሙስሊሞች የምትተዳደር በመሆኑ ሙስሊም መሪዎች በግብጾች ክርስቲያኖች ላይ በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምክንያት ኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ያለ ጳጳስ ቆይታለች፡፡ በርዳታ ስም በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ፖርቱጋሎችም የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በሮም ሥር ለማድረግ ብዙ ጥረዋል፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ማርቆስ ሥር ጸንታ ቆይታለች፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በ1928 ዓ.ም ስትወር ቤተ ክርስቲያናችን ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበራትን አንድነት ለማጥፋት ሌሎች ጳጳሳት እንዲሾሙ አድርጋ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ራሷን የቻለች ሉዐላዊት አገር ብትሆንም ፋሺስት ኢጣሊያ ድል ከሆነ በኋላ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የነበረው ውዝግብ ተፈትቶ በአንድነት ተጉዘዋል፡፡ በመጨረሻም እግዚአብሔር ፈቅዶ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጋር በተደረገ ስምምነት በ1951 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ (ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት) ለመሆን ቻሉ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በራሷ መንበረ ጵጵስና እና ሲኖዶስ የምትመራ ቤተ ክርስቲያን ለመሆን በቃች፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በራሷ መንበር መመራት ከጀመረች ገና 50 ዓመት ያህል ቢሆንም ከዚያ በፊት ለ1600 ዓመታት የታየው የአባቶቻችን ጽናት ግን በዚህ የአጭር ጊዜ ታሪክ መታየት ባለመቻሉ ቤተ ክርስቲያናችን እስከዛሬ ከገጠማት አስከፊ ችግር የባሰው ላይ ትገኛለች፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ኃላፊነት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓት፣ ትውፊትና ሁሉን አቀፍ አንድነት መጠበቅ እና ማስጠበቅ ቢሆንም ይህንን የቅዱስ ሲኖዶስ ተልዕኮ መፈጸም እና ማስፈጸም ግን ከምዕመናን እስከ ጳጳሳት የቤተ ክርስቲያኗ አካል ከሆኑ ሁሉ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡

ዛሬ ለምናየው መከፋፈል እና መለያየት ብዙ ምክንያቶች መስጠት ቢቻልም ወሳኝ የሆነው ምክንያት ግን ተቀራርቦ አለመወያየት እና ችግሮችን በራስ ለመፍታት መሞከር ነው፡፡ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች የምንማረው ችግሮችን በጋራ መፍታትን እና ለዚህም የእግዚአብሔርን ረዳትነት ማመን ነው፡፡ ክርስትናን በተቀበሉ በአይሁድ እና በአሕዛብ መካከል በነበረው ልዩነት ተቸግሮ የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ለጉዳዩ መፍትሔ ያመጣው ችግሩን ወደ ሐዋርያት ጉባዔ በማምጣት ነው፡፡ ‹‹ወንድሞች ሆይ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ፤ እኔ ከሰው አልተቀበልኩትም፡ አልተማርኩትምም›› በማለት የተናገረው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጌታ ገልጾልኛል›› በማለት አልተመጻደቀም (ገላትያ 1፡11 - 12)፡፡ ሐዋርያትም በጉዳዩ በአንድ ልብ ሆነው በመወያየት ለነበረው መለያየት መፍትሔ ሰጥተዋል፡፡ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ በአንድ ልብ በመሆናቸው ውሳኔው የመንፈስ ቅዱስ መሆኑን ለመግለጽ ‹‹እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል›› በማለት ውሳኔአቸውን ‹‹ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሳቸውን ከሰጡት›› ከጳውሎስ እና ከበርናባስ ጋር በአንጾኪያ፣ በሶርያ እና በኪልቅያ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ልከዋል (ሐዋ 15፡19-29)፡፡

በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል፣ በካህናት እና በምእመናን መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ታይቶ እና ተሰምቶ የማይታወቅ ነው፡፡ ዐፄ ሱስንዮስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በካቶሊክ መንበር ሥር ለማድረግ ቢሞክሩም አባቶቻችን በብዙ መስዋዕትነት ቤተ ክርስቲያኗን ጠብቀው አቆይተዋል፡፡ ፖርቱጋሎች የተከሉት የቅባት እና የጸጋ ኑፋቄ በዘመነ መሳፍንት አከራካሪ ሆኖ ቢቆይም ቤተ ክርስቲያንን ተፈታተናት እንጂ አልከፈላትም፡፡ ግራኝ አህመድ በቤተ ክርስቲያን ላይ ባካሄደው የጥፋት ዘመቻ አባቶቻችን እንደዘመነ ሰማዕታት አበው ሰማዕትነትን በጸጋ በመቀበላቸው ደማቸው የፈሰሰበት፡ አጽማቸው ያረፈበት መካናት እስከዛሬ የገዳማዊ ሕይወት እና የመንፈሳዊ ትምህርት፡ እና የክርስትና ቅርስ ማዕከላት ናቸው፡፡ ስደትም ቢገጥማቸው እንኳ የአካል እንጂ የመንፈስ ስደተኞች አልነበሩም፡፡

ቅዱስ አትናቴዎስ በአርዮሳውያን ተንኮል የተነሣ ቢያንስ ለአምስት ጊዜ ያህል ከመንበሩ ተሰዷል፡፡ የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፣ ሌሎችም ታላላቅ አባቶች ከመንበራቸው ላይ እንዲነሡ እና እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሄዱበት አገር ሲኖዶስ ለማቋቋም ያሰቡ ወይም በተግባር ያሳዩ የሉም፡፡ እንዲያውም በስደት ካሉበት ቦታ ሆነው መልእክት በመላክ ምእመናንን ያጸኑ፣ ያጽናኑ እና ያበረቱ ነበር፡፡ በሄዱበት ቦታ ሁሉ የሚጨንቃቸው የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንጂ የሥልጣን ጉዳይ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ‹‹ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው›› (2 ቆሮ 11፡28)፤ ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ደግሞ ‹‹ምሳሌ እንድንሆናችሁ ነው እንጂ ያለ ሥልጣን ስለሆንን አይደለም›› (2 ተሰ 3፡9) በማለት የተናገረው፡፡ በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያናችን ለገባችበት ለዚህ ችግር ዋና እንቅፋት የሆነው ይህንን የሐዋርያትንና የቀደምት አበውን አሠረ ፍኖት አለመከተል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ለዚህ ልዩነት መፈጠር እና እየተባባሰ መምጣት፣ ለችግሩም እልባት ለመስጠት በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ችግር ሆነው የሚገኙ በርካታ ነገሮች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ዐበይት ናቸው ማለት ይቻላል፡-

1. ፖለቲካ፡- በውጪው ዓለም የሚገኙ አንዳንድ ፖለቲከኞች ቤተ ክርስቲያንን የፖለቲካ መድረክ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት ለምዕመናን መከፋፈል እና በአባቶች መካከል አንድነት እንዳይፈጠር ዋናው ዕንቅፋት ነው፡፡ ስለ አገር አንድነት እየተናገሩ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት የማይጨንቃቸው፣ ስለ ሀገር ደኅንነት ቆመናል እያሉ ለቤተ ክርስቲያን ራስ ምታት የሆኑ፣ ቤተ ክርስቲያን የምትመራው በመንግሥት ነው እያሉ የሚኮንኑ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያንን በፖለቲካ ፍልስፍናቸው ለመምራት የሚሞክሩ ፖለቲከኞች ቤተ ክርስቲያንን የፖለቲካ ለማድረግ ሙከራ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡

ሰዎች በፖለቲካ የራሳቸው አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ግን እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ እና ፈቃድ እንጂ እንደራሳቸው አመለካከት ሊጓዙ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ለፖለቲካ ጥማቸው ሰውን ማግኘት የሚችሉት ቤተ ክርስቲያን ስለሆነ ፈጽሞ እምነት የሌላቸው ሰዎች በሃይማኖት ካባ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተው የመከፋፈል ሥራቸውን ተያይዘውታል፡፡ ዛሬ በመልካም ሥራ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚመላለሱ ምዕመናን ከፖለቲከኞች በገሀድ እና በስውር የሚቀርበው ጥያቄ ‹‹የኬፋ ወይስ የአጵሎስ›› የሚል ዓይነት ጥያቄ ነው፡፡ ስለማያምኑበት ‹‹የክርስቶስ ነኝ›› ወይም ‹‹የቤተ ክርስቲያን ነኝ›› የሚል መልስ ተቀባይነት ካጣ ሰንብቷል፡፡ ስለዚህ ምዕመናን በቤታቸው ባይተዋር ሆነዋል፤ ‹‹የርኩሰት ምልክት በተቀደሰው ቦታ ቆሞ ባያችሁ ጊዜ አንባቢው ያስተውል›› እንደተባለው ዘላለማዊ የእግዚአብሔር መንግሥት የሚሰበክበት ሥፍራ የፖለቲካ መድረክ ሆኗል (ማቴ 24፡15)፡፡

ፖለቲካ ምን ያህል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደገባ የሚያመለክተው ፖለቲካው ከምዕመናን አልፎ አንዳንድ አባቶችንም ማሳተፍ መጀመሩ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያጠፋን የምትገስጽ እና የምትመክር፡ ያዘነን የምታጽናና፡ የተጣላን የምታስታርቅ ናት፤ ነገር ግን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኗን መስቀል የያዙ፡ የሃይማኖት ካባ የለበሱ አባቶች ከፖለቲከኞች ጋር በመሰለፍ አንዱን በማወደስ፡ ሌላውን በማውገዝ ቤተ ክርስቲያንን የፖለቲካ መስተናገጃ አድርገዋታል፡፡ ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፡ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት›› የሚለውን የጌታን ቃል በማስታወስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በእምነት እና በጸሎት ልንመላለስ ይገባል፡፡ ጌታ ‹‹የቄሳርን ለቄሳር›› እንዳለው ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች መተው ይገባል፡፡ ፖለቲከኞችም ቤተ ክርስቲያንን ሊተዉአት ይገባል፡፡ ‹‹ስለ ሥራችሁ ክፋት ቁጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ፡ የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳያቃጥል ለእግዚአብሔር ተገረዙ፡ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ፡፡›› በማለት እግዚአብሔር እንደተናገረው ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ፡ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላለማዊ ጸጋን የምንጎናጸፍባጽ ቤት መቅሰፍትን እንዳንዘራ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ እና ፈቃድ ልንመላለስ ይገባናል፡፡ (ኤር. 4፡4)

2. መናፍቃን፡- ቤተ ከርስቲያችን በየዘመኑ የነበሩትን ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ተቋቋቁማ ዛሬ ካለችበት የደረሰችው አባቶችና ምዕመናን ባሳዩት የዓላማ አንድነት እና ጽናት ነው፡፡ በዚህ አቃማቸው የሕይወት መስዋዕትነትን ሳይቀር ከፍለው ቤተ ክርስቲያንን ከመናፍቃንና ከከሃድያን ወረራ ታድገዋታል፡፡ ዛሬ የተፈጠረው ክፍተት ግን ቤተ ክርስቲያንን ለመናፍቃን ዘመቻ አጋልጦአታል፡፡

‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል›› እንዲሉ የተፈጠረውን መለያየት በመጠቀም ቤተ ክርስቲያን ሳትልካቸው ራሳቸውን ያሰማሩ፡ ቤተ ክርስቲያን ብታወግዛቸውም ዓላማቸውን ለማስፈጸም በቤተ ክርስቲያን ስም መሸሸጊያ ያገኙ፡ በሃይማኖት መስፈርት ሳይሆን በሥጋ ጥቅም የቤተ ክርስቲያን ሸክም የሆኑ፡ የተደበቀ ዓላማቸውን ለማራመድ እና ጥቅማቸውንም ለመጠበቅ ሲሉ አንድነትን ሳይሆን ልዩነትን የሚሰብኩ፡ የእግዚአብሔር ሳይሆን የሰው ተገዢዎች የሆኑ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ጥንት የክርስትና ማዕከል የነበሩ እንደ ቁስጥንጥንያ፡ ኤፌሶን፡ ሶርያ እና ግብፅ ያሉት አገሮች ዛሬ ታሪካቸው ተረስቶ፡ ቅርሳቸው ጠፍቶ የእስልምና ማዕከል የሆኑት፡ በክርስትና ስም የሚንቀሳቀሱ ከሺ በላይ ድርጅቶች የተፈጠሩት፡ በክርስትናው ዓለም በተፈጠረው መከፋፈል ነው፡፡ ዛሬ በአባቶች መካከል የተፈጠረው ልዩነት በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ እየተንፀባረቀ ነው፡፡ በውጪው ዓለም በተፈጠረው መከፋፈል የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ስለተናጋ የተጣላን የሚያስታርቅ፡ ያጠፋን የሚገስጽ፡ አካል ባለመኖሩ ወይም ያለውም አካል ተቀባይነት በማጣቱ ከምዕመንና እስከ ካህናት ድረስ ‹ቤተክርስቲያን› እንደሱቅ መክፈት የኩርፊያ ውጤት ከሆነ ሰንብቶአል፡፡ የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ይህን የመሰለ መከፋፈል በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተፈጠረው በአብዛኛው በመናፍቃን የመከፋፈል ሚና ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንን ከመናፍቃን ቅሰጣ፡ ለመታደግ እና ከአባቶቻቸን የተረከብነውን ለልጆቻችን ለማስረከብ ወደ አንድነት መምጣት አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው፡፡

መፍትሔ
1/ የአባቶች ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆን
ካልተነጋገሩ መግባባት አይፈጠርም። በማንኛውም ግጭት ውስጥ መግባባት የሚኖረው መነጋገር፣ ሐሳብ መቀያየር ሲኖር ነው። ከቅዱስ ሲኖዶስ የተገነጠሉት አባቶችም ሆነ በሀገር ቤት አሉ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መነጋገር ቢችሉ መልካም ነው። ዛሬ እንደቀልድ የተፈጠረው ክፍተት ነገ ታሪክ ይሆናል። አንድ እንሁን ቢባል እንኳን ዋነኞቹ አልፈዋል እና በምን አቅማችን የሚባልበት ዘመን ይመጣል። ያለምንም ምክንያት የተፈጠረው የልዩነት ጉዞ ነገ በዶግማና በቀኖና እስከመለየት ያደርስና አስተዳደር ሳይሆን የሃይማኖት ልዩነት ይፈጠራል።፡አባቶች የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገን ተመልክተው ለመነጋገር ፈቃደኛ ቢሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከመለያየት አደጋ ይጠብቋታል። “የእግዚአብሔርን መንጋ ጠበቅዩ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በግድ ሳይሆን በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳኢሆን ጎብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ” (1ኛጴጥ. 5፡2-3)።

2. የምዕመናን ግንዛቤ መዳበር
ብዙ ምዕመናን የተፈጠረውን ልዩነት በተለያየ መልኩ ሲተረጉመው ይታያል። አንዳንዱ የፖለቲካ አቋም የለያያቸው፣ ሌላው ተራ በሆነ አለመግባባት የተከፋፈሉ እየመሰለው ጉዳዩን በቸልተኝነት ይላፋል። በመሠረቱ ምዕመናን ከተለያየ ቦታ ከሚሰሙት ውዥንብር የበዛበት አሉባልታ ይልቅ ጉዳዩን በትክክል ቢያጤኑት መልካም ነው። የጨው ክምር ሲናድ ሞኝ ይስቃል፣ ብልጥ ያለቅሳል እንዳይሆን ያስፈራል። እየሆነ ያለው ሁሉ ለዚህች ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን ከባድ ጠባሳ ነው። ችግሩን ለመፍታት ቆም ብሎ ማሰብ፣ መፍትሔ መፈለግ እንጂ አይቶ እንዳላየ መሆን የትም አያደርስም።

ምዕመናን ሃይማኖታቸወን አውቀውና ተረድተው ለአንድነት ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን መወጣት እንጂ መለያየትን በዕልልታና በጭብጨባ ማጀቡ መልካም አይደለም። ለሀገር አንድነት የምንቆረቆረውን፣ የምናዝነውን ያህል ቤተ ክርስቲያን ስትነገነጣጠልም ልናዝን ይገባናል።

በመጨረሻም ሁሉን ማድረግ የሚችል የሰላም አምላክ ስላለን ለሰላምና ለአንድነት ወደ እግዚአብሔር ልንጸልይ ያስፈልጋል፡፡ ተወያይቶ ወደ አንድነት ለመምጣት ጥበቡ ሊጎድለን፡ ትእግስቱ ሊያጥረን ይችላል፡፡ ነገር ግን ‹‹ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል›› (ያዕ 1፡5) በማለት ሐዋርያው ያዕቆብ እንደተናገረው ጥበቡን፡ ትዕግስቱን፡ ሰላሙን እና አንድነቱን እንዲሰጠን እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ልንጓዝ ያስፈልጋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ “መጽሔተ ተዋሕዶ” ጆርናል፤
አሳታሚ በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል
(2000 ዓ.ም)


4 comments:

Anonymous said...

“ ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።” ት. ዕንባቆም ፫፤፲፯-፲፰

Anonymous said...

jeje selam thanks for the letest devlopment,however you maheber keluan flamming the fire, i want to tell you one thing you will not get any thing form this because you ar not the part of the church. this is my advie to you g and start your carrier in dead politics

Anonymous said...

ደቂቀ እምየ ተበአሱ በእንቲአየ (የእናቲ ልጆች ተጣሉብኝ)አይድነቀን ምክኒያቱም ማስተዋሉን ላደለው ሰው ሲኖዶስ፤ ፓትሪያሪክ ቀኖና የሚለው ቃልም ሁነ የስልጣን ተዋረድ ትርጉም ያሚኖረው የአንድ እናት ልጆች ለአንድ አላማ እንደ ሓዋርያት አንድ ልብ ሆነው ሲሰለፉ ብቻ ነው።
ቅዱሳን ሐዋርያት ልመናቸው ወንጊልን አደራ ይሰጣቸው ዘንድ ነበር
1ተሰ፤2፡3

ልቦና ይስጠን

hiwot said...

Letera sel Yedefersal yelalu seteritu.
Let us pray.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)