July 10, 2009

በተዋሕዶ ነን ወይ ?

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 10/2009)
(ከብርሃናዊት)
ድምጼን አጥፍቼ ትንፋሼን ውጬ የሰሞኑን ዜና ከደጀ -ሰላም ስከታተልና : የማምሻውን የቪኦኤ ዜና ስሰማ : እንዲህ የሚል ጥያቄ መጣብኝ ::

የተከሰተው ምንድነው ?

- የሥልጣን ሽኩቻ ?
- [ለጊዜው ] ያልተሳካ የቤተክርስቲያን አስተዳደር ህዳሴ እንቅስቃሴ ?
- የተጠና ተቃዋሚዎችን የማስመቻ ድራማ ?
- ያልተቀደሰው የመንግሥትና የቤተ -ክህነት ተጣምሮ ማጋለጫ ታሪካዊ አጋጣሚ ?
- የጠንካራ ብሶት -ወለድ እንቅስቃሴ ጅማሮ ?
- የደካማ ብሶት -ወለድ እንቅስቃሴ ፍጻሜ ?
- ወይስ እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንዳልሰማን ማሳያ ?

ሁሉም ትንሽ ትንሽ ያለበት ይመስለኛል ... በተለይ ግን የመጨረሻው ነው ትክክለኛው የተከሰተው ነገር ብዬ አምናለሁ :: ነገሩ የጀመረ አካባቢ "እግዚአብሔር የዚህን ሕዝብ ብሶት ሊሰማው ይሆን ?" ብዬ ትንሽ ለራሴ ተስፋ ልሰጠው ሞክሬ ነበር ፡፡ ቢሆንም ... ብዙም ተስፋ አላደረግሁም ነበር :: የሆነው ሁሉ መልካም ነው :: ራሳችንን ለማየት ይጠቅመናል :: ጸሎታችን ከደመና በታች እየቀረ ለምን እንዳስቸገረንም ያሳየናል :: አዎ ! እኔ እንደዚያ ነው እላለሁ :: በአስተዳደር በደል ዙርያ ወደእግዚአብሔር መጮኽና ደኅና አባት እንዲሰጠን መጸለይ ከጀመርን እኮ ብዙ ዘመን ሆነን ? ግን እግዚአብሔር እየሰማን አይደለም :: መልስ ሊሰጠንም አልፈለገም :: ቢሰጠንም እንኳ : የሚሰጠን ምላሽ ሁሉ "ነገርኳችሁ እኮ ?! ከእቅፌ ከራቃችሁ ብዙ ጊዜ ሆኗችኋል :: ችግራችሁን እስክታምኑ እንዳትጠፉ እጠብቃችኋለሁ እንጂ : ጸሎታችሁን አልሰማም " የሚል ድምጽ ነው የሚሰማኝ ::

ምክንያቱ አንድ እና አንድ ነው :- ያም : አሁን በአስተዳደርና በአቋም መለዋወጥ እየወቀስናቸው ካሉት 'አባቶች ' ያልተሻለ መንፈሳዊ አቋም ላይ ስለምንገኝ ነው :: እነርሱ ማለት እኛው ራሳችን ስለሆንን : እኛ ስለነሱ የምናቀርበው ጸሎት "ክስ " እንጂ ጸሎት አይሆንም ::

ለመሆኑ ምናችን ነው እነርሱን የሚመስለው ? ብዙ ነገር ልንገምት እንችላለን :: ዋናውን ነጥብ ግን አናገኘውም :: ምናልባት - እኛም ውስጥ አድፍጦ ያለ ዘረኝነት ? የሥልጣን ፍላጎት ? ትዕቢት ? ልግምተኝነት ? ፍቅረ -ነዋይ ? .... ብለን ልንዘረዝር እንችላለን :: ልክ ነው ! በብዙ የሥነ -ምግባር ጉድለት ከ”አባቶቻችን” ጋር ልንመሳሰል እንችላለን :: ነገር ግን እነርሱን ይበልጥ የምንመስልበት ዋና ነጥብ : ንጹሕ ሃይማኖት በውስጣችን ባለመኖሩ ነው :: "እኔ የተዋሕዶ እምነት ተከታይ ነኝ " ብለናል እንጂ : በተዋሕዶ በሙሉ ልብ አናምንም :: ተዋሕዶን በሙሉ መልኳ አናውቃትም - ጥምቀቷን ተጠምቀናል : ቁርባኗን ተቀብለናል : ጣዕሟን በጥቂቱ ቀምሰናል .... ቢሆንም ጥቂት ገጿን ጨረፍ አድርገን አይተናታል እንጂ : ሙሉ እርሷነቷን በግልም : በቤተሰብም በማኅበረሰብም ደረጃ አልኖርናትም :: በርሷ ሆነን ተገኝተን ቢሆን : አንዳችን እንበቃ ነበር - ጸሎቱን ከደመና ለማሳረግ :: ግን አልተገኘንም ::

"እንዴታ ?! አምላክ ሰው መሆኑን አምናለሁ ! መለኮትና ሥጋ ከሁለት ባሕርይ ወደአንድ ባሕርይ : ከሁለት አካል ወደአንድ አካል ያለመለየት ያለመለወጥ ያለትድምርት : ያለመቀላቀል : ያለመከፋፈል : በመዋሐዱ አምናለሁ :: በ 5ቱ አዕማደ ምሥጢር : በ 7ቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን አምናለሁ :: ታድያ በተዋሕዶ ውስጥ አይደለሁም ?" ልንል እንችላለን - ያውም በቁጣ ::

መልሱ ግን "በመንፈስ ያለነው በተዋሕዶ ውስጥ ላይሆን ይችላል፡ እንዲያውም በተዋሕዶ ውስጥ አይደለንም! " የሚል ቁርጥ ያለ መልስ ነው ::

- በተዋሕዶ ሆነን ቢሆን ኖሮ : በምስጢረ ሥጋዌ ሙሉ ትርጉሙ እናምን ነበር፡፡ ለዓለም ሕግ (ለሰው ሠራሽ ካፒታሊዝም : ዲሞክራሲ : ሊበራሊዝም : ኢንዲቪጁዋሊዝም : ወ ዘ ተ ...) ፍልስፍና ራሳችንን አናስገዛም ነበረ :: ተዋሕዶ ማለት መለኮት ሥጋ ሆነ ማለት አይደለም ወይ ? መለኮት ሥጋንም ገንዘብ ሲያደርግ እኮ : ሥጋም በመለኮት ፈቃድ ራሱን ሊያስመራ ተስማምቶ ነው እንጂ - ያ ሥጋዊ : ይሄ ደግሞ መንፈሳዊ ብሎ ለይቶ : አንዴ ለዓለም ሰው ሰራሽ ሕግ : አንዴ ለእግዚአብሔር መለኮታዊ ሕግ ሊገዛ አይደለም :: ፈቃድ አንዲት ናት - ያችውም የመለኮት ፈቃድ ናት :: የእግዚአብሔር ፈቃድ በሰማይ እንደሆነች ሁሉ : እንዲሁም ደግሞ በምድር እንድትሆን የተጸለየችው ጸሎት : በክርስቶስ ቤዛነት ተቀባይነት አግኝታ : መንግሥቱ በምድር ሆናለች :: ያችውም - በኢትዮጵያ ሲሠራባት የኖረችው የመንግሥት ወንጌል ናት :: ከካህናት እና ከምዕመናን ሎት፡ ከምሥጋና፡ ከነግህ ከሰዓት፡ ከሠርክ መስዋዕት ሌላ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ፡ የመሣርያ ፖለቲካ፡ የገንዘብና የኢኮኖሚ አምልኮ፡ ወይም በሥነ-ጥበብና ባሕል ልውውጥ ስም የዝሙት፡ የትውፊት ንቀትና የባሕል ማንኩዋሰስ በይፋ በጸሓይ ብርሃን አይደረግም ነበር፡፡ ሁል ጊዜ እጇን ወደእግዚአብሔር በምትዘረጋው በኢትዮጵያ ምድር : የሰይጣናዊ የአውሮፓ ፍልስፍና የሆነው የባሩድ ሕግ ምን ይሰራል ? ከናካቴው በኢትዮጵያ ምን ይሰራል ? አስርረሽ ምቺውና ዝሙት በኢትዮጵያ ምን ይሠራል ? ጫትና ቡና በኢትዮጵያ ምን ይሠራል ? (ለውጭ ምንዛሪ ? ኢኮኖሚ ነው ወይ አምላካችን ?) ይህ ሁሉ በአረጋዊቷ : በሃይማኖት ታላቅ በሆነችው በኢትዮጵያ ምድር ምን ይሰራል ? ይህን ለማጥፋት ሰርተናል ወይ ? ምድርና ሰማይ እኮ ተዋሕደዋል - እውን በተዋሕዶ የምናምን ከሆነ ? ሰው እኮ በበጎ ፈቃዱ (ነጻ ምርጫው ) የእግዚአብሔርን መንግሥት በምድርም ላይ ሆነ ከምድራዊ ሕይወቱ በኋላ ሊኖርበት ተስማምቷል - ያውም ያኔ ክርስቶስ ተወልዶ ስብሐት ለእግዚአብሔር ብለን ስንዘምር ?! መላእክት እኮ የነገሩን እርሱን ነበር ? ኢትዮጵያም እኮ ለዘመናት ያመነችበት እርሱን ነበር ? ተዋሕዶ ስትል እርሱንም ጨምራ እኮ ነው እንጂ ስለ ብረትና እሳት ውሕደት ብቻ ስትፈላሰፍ አይደለም የኖረችው ? እና ካህኒቷ አረጋዊቷ ኢትዮጵያ ምን ሆና ነው ሲጋራና ሀሺሽ : ሽጉጥና የዝሙት ወጋ ወግ የታጠቀችው ? ጳጳሱ ሽጉጥ ይዘው ታዩ እንላለን - ኢትዮጵያ ሽጉጥ ታጥቃ የለ ? ጳጳሱ ቢዮንሴን አቀፉ እንላለን - ኢትዮጵያ በየ 5 ሜትሩ ርቀት መሸታ ቤትና የፊልም ቤት ከፍታ እየደነሰች አይደለ ? ጳጳሱ እኮ የኢትዮጵያ ነጸብራቅ ናቸው ? እኛ ያለንበትን ሁኔታ ነው እርሳቸው ላይ የምናየው እኮ ?! (ደግሞ በጠመንጃ ጠላት አትከላከሉ የሚል መጣ እንዳትሉ - አድዋ ላይ ያሸነፍነው በጊዮርጊስ ጽላት እንጂ በጠመንጃ አይደለም :: )

እና እኛና ሀገራችን በተዋሕዶ ነን ወይ ? መንፈስና ሥጋ ተዋሕደዋል ወይ ? አልተዋሐዱም እኮ ? ለሥጋችን የሚያመቸውን ሁሉ በኢኮኖሚ : ንግድ : ሥልጣኔ : የባሕልና ኪነጥበብ ሙያ : ወዘተ ... ስም ከሰኞ እስከቅዳሜ እናመቻቻለን :: ለመንፈስ ደግሞ እሑድ ቤተክርስቲያን እንሄዳለን :: በሃገራችን ሥጋዊ ኑሮዋችን ከሃይማኖታችን ጋር አይሄድም፡፡ በሁለት ሕግ ነው ያለነው፡፡ ከሁለት ባሕርይ ወደአንድ ባሕርይ መምጣት ስላልቻልን : በተግባር በሁለት ባሕርይ እምነት ነው ያለነው :: ለዚያ ነው ፓትርያርካችን ሮማ ለሮማ ሲዞሩ የምናያቸው :: ምክንያቱም ሁለት ባሕርይ ቤቱ እዚያ ነዋ :: ሁላችንም እዚያ ሮማ ቤት ነው ያለነው :: ባንሆንማ ኖሮ ፓትርያካችን የት አግኝተውን ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ይገዙናል ? በሁለት ባሕርይ ሆነን ስላዩን አይደለም ? እግዚአብሔር፡ በኛ ዘመን፡ በግልም ሆነ በሃገር ደረጃ ወዲትዋ ልጁ ኢትዮጵያ፡ በሁለት ባሕርይ ሆና ስላያት፡ ለሁለት ባሕርይ እናት ለሮማ አሳልፎ ሰጣት፡፡

- በአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት አምነን ቢሆን ኖሮ : ምሥጢረ ሥላሴን ከልብ እናምንበት ነበር :: ያም - አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ - በአካል ሦስት : በመለኮት አንድ የምንለው : አብ የነፍስ : ወልድ የሥጋ : መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የመንፈስ ምሳሌ ሆነው : አንድ እግዚአብሔር እንደሚሆኑ ሁሉ : ሰውም ሥጋው ነፍሱና መንፈሱ በአንድ ተደምሮ አንድ ሰው እንደሚሆን እናምን ነበር :: ነገር ግን : ይህን ባለማድረጋችን የተነሳ : ሥጋ - በሥጋ ፍልስፍና : በገዳይ መርዛማ ትምህርት : በሥጋዊ ፍልስፍና በተደገፈ ሕክምና : በማሕበረሰብ ኑሮ ፍልስፍና እና ምዕራባዊ መዝናኛ እንዲጠመድ ስንፈቅድለት : መንፈሳችንን ደግሞ በሳምንት አንድ ቀን እሑድ ብቻ ቤተክርስቲያን እየመጣን "ልናዝናናው " እንሞክራለን :: ሥላሴ ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው ብለን የለ ? ሰውም ሥጋ : ነፍስና መንፈስ ቢኖረውም : አንድ ሰው ነውና : ከአንድ በላይ በሆነ ሕግ አይመራም ነበር :: ትምህርት ቤቶቻችን : እርሻችን : ሐኪም ቤቶቻችን : እድሮቻችን : ጽዋ ማኅበሮቻችን : ውትድርናችን : ኪነ -ጥበባችን :... ባጠቃላይ : ለሥጋና ለነፍስ ያስፈልጋል የምንለው ሁሉ : በመንፈስ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ : አገራዊና ትውፊታዊ ሥርዓት እንዲተካ ለማድረግ እንተጋ ነበር :: ግን አላደረግንም :: ስለዚህ : እኛ ከቤተክርስቲያን ወጥተን ይህን ሁሉ የኑሮ መልካችን መንፈሳዊ ልናደርገው ሲገባ : የተገላቢጦሽ እርሱ ቤተክርስቲያን ገብቶ እኛንና ቤተ-እምነታችንን ሥጋዊ አደረገን :: እና በመንፈስ ሕግ ሳይሆን በሌላ ሌላ ሕግ ራሳችንን አጦዝነው :: አንድ ሕግ አልሆንንም - ለሥጋ ለነፍስ ለመንፈስ የተለያየ ሕግ እየሰራ ነው :: እና በተዋሕዶ ነን ወይ?

- በምሥጢረ ጥምቀት አምነን ቢሆን ኖሮ : ክርስትናን የምንኖረው : ሞቱን በሚመስል ሞት ክርስቶስን መስለን : ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ከርሱ ጋር እንደምንነሳ በማሰብ ይሆን ነበር :: ግን : ሞቱን ሳንሞት ትንሣኤውን ብቻ እንናፍቃለን :: ሞቱ ከግል ሰማዕትነት ይጀምራል :: ሰማዕትነት በሰይፍ ብቻ አይደለም : እውነትን በመናገርም ነው እንጂ :: ሰማዕትነት በመታሰር ወይም በመገደል ብቻ አይደለም : 'ለዓለም የሞትኩ ነኝ " በማለትም ጭምር ነው እንጂ :: ለዓለም የሚሞተው መነኩሴ ብቻ ነው የምትል ኢትዮጵያ የለችም :: ኢትዮጵያውያን : ከምዕመኑ እስከ መነኩሴው : ለዓለም በመሞት በትህርምት ለመኖር ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን የተገባቡ ሕዝቦች ናቸው :: ስለሆነም : በተዋሕዶ ሆነን ቢሆን ኖሮ : ሞቱን በሚመስል ሞት ከክርስቶስ ጋር እንተባበር ዘንድ : ለምቾታችንና ለድሎታችን እንሞት ነበር :: በምትኩም : በሀገራችን ኖረን : ልጆቻችንን መልካም ዲያቆናት እንዲሆኑ : መልካም ቀሳውስት እንዲሆኑ : መልካም ጳጳሳት እንዲሆኑ እያስተማርን : ሀገራችን በሃይማኖቷ ኖራ : ለዓለም የምትተርፍበትን መንገድ በማሰብ ዕድሜያችንን እንፈጅ ነበር :: ነገር ግን : ይህን ፈጽሞ አናስብም :: ለሃይማኖቱ አንኖርም : ለሃይማኖቱም አንሞትም :: ከዚያ ይልቅ : ሃይማኖቱ ለእኛ እንዲኖርልን ለማድረግ ብቻ : ትንሽ ትንሽ ብር አናዋጣለን : በተዋጣውም ብር : ሌሎች ሃይማኖቱን ኖረው : ለሃይማኖቱ ሞተው : ለኛ ትርፍ ጊዜ መዝናኛ ሃይማኖቱን እንዲያኖሩልን እንፈልጋለን :: እናም ... አረማዊው ልክ ነው ለሚለው ሃይማኖቱ እየሞተ እኛን ሲቀድመን : እኛ ለራሳችን ኑሮ ስንሞት ትዝብት ላይ ወደቅን :: ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸው ነበር የሚኖሩት :: ሞቱን በሚመስል ሞት ጌታን ይመስሉት ዘንድ ይሻሉና :: ከዚያ የሚቀድም ምንም ነገር ለነርሱ አልነበረም :: ያ ነበር የሚያምኑበት ምሥጢረ ጥምቀት:: Religious tolerance በሚል ሽፋን ቸልተኝነት አጥቅቶን እንጂ : ያኔ ገና እነ አለቃ አያሌው እንዳሉት : ከሮማ ጋር ሲጨባበጡ 'አይ በፍጹም !" እንል ነበር :: አሁንም መንገዱንና ድራማውን ሁሉ የሚያቀናብርልን ሮም ይሁን ወይም ኒውዮርክ : ወይም ቱርክ ምን እናውቃለን ? በጠመንጃ አፈሙዝ የሚያምን እኮ ከነዚ መሃል ከአንዱ ጋር በማይበጠስ የጥቅም ሰንሰለት የተቆራኘ ብቻ ነው :: አልያማ በ 80 ሚልየን ሕዝብ ፊት ደረቱን ነፍቶ ምን ያስቆመዋል ?

እና በተዋሕዶ ነን ?

እስቲ ሌላውንም ምሥጢራት እናሰላስል ?

በተዋሕዶ ነን ወይ ?

2 comments:

ፍቅር said...

amen to that!!

Anonymous said...

በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው?
ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥
ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።
በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ።

1ጴጥ3;14
k mn

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)