July 6, 2009

ግልጽ ደብዳቤ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በእስዎም በኩል ለቤተ ክርስቲያኗ ሲኖዶስ

ግልጽ ደብዳቤ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በእስዎም በኩል ለቤተ ክርስቲያኗ ሲኖዶስ
(ምንጭ፦http://azekiri21.blogspot.com)
(ደጀ ሰላም፤ ጁን 6/2009) ከሰሞኑ መንበረ ጴጥሮስ ወÔውሎስ በልዮናውያኑ ወደ ተነጠቀባት ሮሜ ከተማ /ጣልያን/ ጎራ ብለው ተናገሩ የተባለው የታቦተ ሙሴ ጉዳይ እኛ ልጆችዎ ብቻ ሳንኾን ዓለም በጠቅላላ እየዳከመበት /እየተነጋገረበት/ ያለ ጉዳይ እንደኾነ የተሰወረብዎት እንዳልኾነ ይገባኛል፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን አባት የተናገሩት ምን ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል አስቀድመው ማሰብ ቢሳንዎትም ስሕተቱ እርስዎ እንዳሉት ከጋዜጠኛውም ይሁን /ብዙዎቻችን እንደ ምንገምተው/ ከራስዎ አስጨንቆዎት ጋዜጠኞችን ወደ መንበረ ፕትርክናዎ ጠርተው «እባካችሁ አስተባብሉልኝ» ዓይነት ጥሪ አድርገዋል፡፡ ጣልያናዊው ጋዜጠኛ ያላሉትን እንዳሉ አድርጎ በማቅረቡ «I am deeply disappointed that the Italian media misquoted me and disseminated false information about me unveiling the Ark of the Covenant to the world´ ብለዋል፡፡ [ሮይተርስ.ጁን 30]፡፡ በዚያ መግለጫዎ ሁለት ነገሮችን ዘንግተዋል፡፡ አንዱ አሁንም የሚያስጠይቅዎ ሌላው የሚያስወቅስዎ፡፡

የሚያስጠይቅዎ በዚያው ግራ ባጋባን የሮም መግለጫዎ በቤተ ክርስቲያኗ ረጅም የታሪክ ጉዞ ተነግሮም ተጽፎም በማያውቅ ሁናቴ በእግዚአብሔር ፈቃድ ለሦስት እስራ ምእት /millenium/ ኢትዮጵያ የሚገባትን አክብሮት እየሰጠች በምሥጢር የያዘቻትን ታቦተ ሙሴ በዓይኔ ዐይቼአታለሁ ያሉ የመጀመሪያና ምናልባት እንደስዎ ያለ ካልመጣ የመጨረሻ ሰው መኾንዎ ነው፡፡ ይኸንንስ መቼ አልኩኝ ብለው ሌላ ውሸት ይናገራሉ ብዬ አልገምትም፡፡ የማይዋሽ ሁላችንም ተርጓሚ በማያሻን ሁኔታ በቋንቋችን የተናግሩትን ዶቼ ቨለ ሬድዮ የአማርኛው መርሐ ግብር ቀድቶ በሞገዱ ሲረጨው በጆሮአችን ሰምተነዋል፡፡ እንደብዙዎቻችን እምነት ከኾነ ይኸኛውም ወይ ታቦተ ጽዮን እኛ አገር ናት የሚለውን ክርክርዎን ጥንካሬ እንዲሰጥ የተናገሩት ወይም ብዙ ጊዜ እንደ ሚያደርጉት የግል ስም ለማሰር ብለው የዘባረቁት ውሸት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ታሪካችንንና ማንነታችንን በእውነት ስለ እውነት ማስረጃ በጠገበ ሁኔታ አስረድተን የሚቀበል እንዲቀበል የማይቀበል እንዲቀርበት እናደርጋለን እንጂ በውሸት ታሪካችንን አናስረዳም፡፡ ማንነታችንንም ሌላው እንዲያውቅ አናደርግም፡፡ ስለዚህ ታቦተ ጽዮንን የሚጠብቃት አንድ ሰው እንዴት እንደሚመረጥ ያ ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ተተኪው እንኳን እንደማያይ ምናልባት እርስዎም የሚያውቁት ለሦስት ሺ ዘመናት የቆየ ጠንካራ ሥርዓት አለና እርስዎ በምንም መልኩ ስላላዩት በአስቸኳይ ይህንንም ውሸትዎን ያስተባብሉ፡፡ አላልኩም ብለው ሳይኾን ተሳስቼ ነው በማለትÝÝ
የሚያስወቅስዎ ደግሞ በመግለጫዎም ኾነ መግለጫውን ከመስጠትዎ በፊት እዚህ ሁሉ መዘላበድ ወደ ከተትዎ ጉባኤ ሲሔዱ የራስዎን አካላት ከቁብ አለመቁጠርዎ ነው፡፡ እንደ ሰማነው ምሽት የምትኾን መንበርዎን ለቀው ወደ ሮሜ በመምጣት ከዚያ ሁሉ መዘላበድ ውስጥ የገቡት . ከልዮናዊው ¬¬ ጋርም ወደ መንበሩ ሔደው እጅ ነስተው የተመለሱት እርስዎን ከመንበርዎ ጋር ያጋባው ቅዱስ ሲኖዶስ ሳያውቅና ሳይፈቅድልዎ ነው፡፡ ይኸ እርስዎ በሚመሯት ቤተ ክርስቲያናችን ቋንቋ ሚስትን በግብታዊነት ትቶ ከሌላ ጋር እንደ መወስለት ይቆጠራል፡፡ ተወቃሽ ነዎት፡፡ ከምሽትዎ ያጋባዎትን ሲኖዶስ ይቅርታ ይጠይቁ፡፡ ሌላው የሚያስወቅስዎት ጉዳይ እርስዎ ሙቀት እንዲሰማዎ ብቻ በመላ አውሮ¬ና መካከለኛው ምስራቅ ልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚያገለግሉ ካህናት እርስዎ ሮሜ ሲገቡ አብረው እንዲገቡና እንዲያጅቡዎት ቀላጤ ወረቀት በመበተን ጥሪ አድርገው የቤተ ክርስቲያኗ ንብረት እንዲበዘበዝ ከዚያም በላይ ካህናቱ ማደሪያ ፍለጋ የምእመናን ፊት እንዲገርፋቸው ማድረግዎት ነው፡፡ እነዚህን ካህናት ሲጠሩ አበል እንዲቆረጥላቸው አላደረጉም፡፡ ያም ቢቀር የሚያገኙትን ቀማምሰው ጎናቸውን የሚያሳርፉበት ቦታ እንኳን አላስፈቀዱላቸውም፡፡ እርስዎ የተደላደለ ሆቴልዎ ላይ ቁጭ ብለው «በነበር» በምናወሳው ፊውዳላዊ ሁናቴ እርስዎን ለማጀብ ከየቦታው የተሰባሰቡት ካህናት /የግማሹ አውሮ¬ ሊቀ ÔÔS ጭምር/ በየጥጋጥጉ እንዲወድቁ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ካህናት ብዙዎቹ ከእርስዎ የአስተዳደር ስብራት የተነሣ በያሉበት በሚፈጥሩብን ንቅዘት እኛ ምእመናን የምንወቅሳቸው ብንኾንም እርስዎ ወደ ሮሜ ጠርተው ስላሰቃዩአቸው ተወቃሽ ነዎት፡፡
ለጊዜው የሚያስወቅስዎትን ትቼ ያስጠይቅዎታል ባልኩት ነጥብ ምክንያተ ነገር (cause) ላይ በማትኮር የልጅነት ምክሬን ልለግስዎ፡፡ የተነሳውን «ታቦተ ጽዮንን በዓይኔ አይቼአታለሁ፣ ለዓለምም አሳያለሁ አሉ» ግርግር ተከትሎ ቤተ ክርስቲያኗን የሚወዱትም ኾነ የሚጠሉት እንዲሁም የታቦተ ጽዮን ባለቤቷ እኛ ነን በሚሉ አካላት ዙሪያ በሳይበሩ ዓለም ምን ዓይነት ሁካታ እንዳለ የምንከታተል እያየነው ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ግለት መንበረ ፕትርክናዎ ኹነው የሰጡት መግለጫ ቶሎ የሚያበርደው አይመስልም፡፡ እርስዎ ቢሉም ያሉትን ይዞ ሌላውም እያለ ነው፡፡ ለምን እዚህ ጣጣ ውስጥ ከተቱን) ምነው በቃልም በመጣፍም ስንተርከው የኖርነውንና እርስዎም የማያጡትን ብቻ ተናግረው አፍዎን በሰበሰቡ ኖሮ) ምነው እርስዎ መጥፎ ተናግረው ንጽሕቷን ቤተ ክርስቲያን «ark of the covenant confusion makes Ethiopian church look bad» እያሰኙ ዓለም ከፍታ እንድትታየው አደረጉ) [http://zeebs19.wordpress.com/2009/06/29/ark-of-the-covenant-confusion-makes-ethiopian-church-look-bad/]. ምነው ያኔ ሲምስቶኒያን ከተሰኘው መጽሔት ወደ መንበረ ፕትርክናዎ መጥቶ ለጠየቀዎ ራፋኤል ለተባለው ጋዜጠኛ “Can you believe that even though I’m head of the Ethiopian church, I’m still forbidden from seeing it?” [http://www.smithsonianmag.com/people-places/ark-covenant-200712.html] ብሎ እውነት በተናገረ ምላስዎ ዛሬ ሌላ አየሁ ያለ ደባል ምላስ በቀለ) ምነው ምን ኾነዋል) የሚከተሉትን እመክርዎታለሁ፡፡
1. እንደ ¬ትርያርክ ያስተውሉ
በርቀት ኾኖ ለሚያይዎ ካልኾነ ጠጋ ብሎ ለሰማዎ ንግግርዎ ዘለፋና ሳቅ ይበዛዋል፡፡ ከፍሬ ነገሩና ከምክሩ ተግሳጹና ወቀሳው ያመዝናል፡፡ ለመናገር አይፍጠኑ፡፡ ለመኾኑ እንደስዎ ያለ አባት የእግዚአብሔርን ቃል ለማስተማር እንጂ እንደኔ እንደጨዋው የኾነ ያልኾነውን ለመናገር ምን ያስቸኩለዋል፡፡ በዚህ ጠባይዎ ቤተ ክርስቲያናችን ችግር ላይ መውደቋን ያስተውሉ፡፡ በአስተዳደሯ ከሚደሰተው የሚያዝነውና ተስፋ የሚቆርጠው በዝቷል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ መሶብ ሳይራቆት በአስተዳደርዎ ስብራት የተነሳ ሊቃውንቱ የሚበሉ የሚጠጡት እያጡ ወንበራቸው ታጠፈ፤ ተማሪዎቻቸው ወደ ከተማ ገብተው ሎቶሪ አዟሪ . ኦቾሎኒና ማስቲካ ቸርቻሪ ኾኑ፡፡ እኛም ይኸንን እያየን አንገታችንን በሐዘን ደፋን፡፡ በዘመነ ወረራ ከተዘረፈው የበለጠ ዛሬ በእርስዎ ዘመን ቤተ ክርስቲያኗ የተዘረፈችው ቅርስ ይበዛል፡፡ እርስዎም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እንዲዘረፍ መንገድ የሰጡት ብዙ ነው፡፡ የእርስዎ ወዳጅ ፈረንሳዊው Ïክ መርሴ እርስዎ ካለ ሲኖዶሱ ፈቃድ /ገና መጣራት ባለበት ሁኔታ. አገርን ከዘረፈ ወንጀለኛ ጋር ስለተባበሩ/ ፈርመው የቤተ ክርስቲያኗን ጓዳ ጎድጓዳ ሁሉ በርብሮ ያወጣውና ዛሬም በእስዎ ሽፋን ሰጪነት እያወጣው ያለው ቅርሳችን ብቻ ዬትዬለሌ ነው፡፡ አሁንም ከሌሎች ጋር ሊፈርሙ ብርእዎን እየፋቁ ነው ይባላል፡፡ ዛሬ በእርስዎ ዘመን አንድ ኾና የአገርን አስተዳደር አንድ አድርጋ የኖረች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በእርስዎ ዘመን ተሰነጣጥቃለች፡፡ ምን ያልኾነችው አለ በእርስዎ ዘመን) የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ብዙ ቢኾንም ዋናው ግን የእርስዎ አስተዋይ አለመኾን ነው፡፡ የተቀመጡበት ወንበር ከቅድስናው የተነሳ ፈተና የማያጣው ቢኾንም መንበሩ ካማጣብዎ ፈተና ይልቅ የእርስዎ የግል ጠባይ ያመጣው ፈተና ቤተ ክርስቲያኗን እያወካት ይገኛል፡፡ ስለዚህ በፈጠረዎ ጠባይዎን ያስተካክሉ፡፡ ደግሞ ጠባይዎን ያስተካከሉ ያለዎትን ሁሉ እንደ ፖለቲከኛ አንዳች ስም ሰጥተው ሳይፈርጁና ድራሽህ ይጥፋልኝ ሳይሉ በአዋልድ መጻሕፍት ዜና ሕይወታቸው ተጽፎ እንደ ምናነባቸው አባቶች አቅርበው የሚነግርዎትን ይስሙ፡፡ እንደ ¬ትርያርክ ባለማስተዋልዎ ብዙ ተጎዳን፡፡
2. ለቤተ ክርስቲያኗ ሕግ ይገዙ
በመሠረቱ /እንደ አማኝ እግዚአብሔር ፈቅዶልዎ ልበልና/ እርስዎ ከዚህ መንበር የተቀመጡት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው እንዲያስጠብቁ ነው፡፡ እንጂ እርስዎ በአደባባይ እየጣሱ ሌላውም በማን አለብኝነት እየጣሰ ቤተ ክርስቲያኗ እንድትፈርስ አይደለም፡፡ በነቢብም ኾነ በገቢር ለሚሠሩት ነገር ሁሉ ሚዛንዎ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይሁን፡፡ እስከ አሁን በፈላጭ ቆራጭነት የተጓዙት ጉዞ እራስዎንም ቤተ ክርስቲያኗንም አልጠቀመ፡፡ እስዎን የመንፈስ ልጆችዎ ከምንኾን ምእመናን ነጥሎም ብቻ አላስቀረዎት፡፡ እራስዎ በአንብሮተ እድ የሾሟቸው አባቶችም እየተነሱብዎት ነው፡፡ ዛሬ እየተቃወሙዎት ያሉት ጥቂት ይኾኑ ይኾናል፡፡ ነገ ግን ሁሉም አንቅረው ይተፉዎታል፡፡ የእስዎ አንቅሮ መተፋት እንዳላዋቂ ካየነው የግልዎ ጉዳት ነው፡፡ ነገር ግን የተቀመጡበት ወንበርና የተሾሙባት ቤተ ክርስቲያን በእርስዎ የተነሳ እንዲንገላቱ አንፈልግምና ሕግ አክብረው እርስዎን ለዚህ ክብር ያበቃውን ሲኖዶስ እየፈሩና እያማከሩ ይንቀሳቀሱ፡፡ በሲኖዶሱ እንደርስዎ ረዘም ላለ ጊዜ አሜሪካ የቆዩ . ፕሪንሲተንን በመሰሉ ዩኒቨርሲቲዎች ባለመማራቸው እንግሊዝኛ የማያውቁ ይኾናሉ፡፡ ከጥቂቶቹ በስተቀር ብዙዎቹ ናቸውም፡፡ ግን የሲኖዶስ አባላት ናቸው፡፡ በመኾኑም ያክብሯቸው፤ ለሚያወጡት ደንብና ለሚደርሱበት ውሳኔ ተገዥ ይሁኑ፡፡ ወዲያውም ቤተ ክርስቲያን ቋንቋዋ ግእዝ እንጂ የአፍርንጁ ልሳን አይደለም፡፡ ወደዚያ ያተኩሩ ከተቻለ፡፡
3. ጥሩ አማካሪዎችን /ባለሙያዎችን/ በዙሪያዎ ያኑሩ
እስዎን የከበቡዎት እየበሉ የሚተኙ . የሚሠራውን የሚነችፉ እንጂ እየበሉ የሚሠሩ . እነሱ ሠርተው ሌላውን ለሥራ የሚያተጉ ሰዎች እንዳልኾኑ ተብሎ ተብሎ የወሬ ቅራሬ የኾነ እውነታ ነው፡፡ ያንን እርስዎም አያጡትም፡፡ የዘመኑን አሠራር የተረዳ ወሬና ነገርን አጣፍጦ ማቀበልን ሳይኾን ሥራ የሚያውቅ ባለሙያ በአጠገብዎ ቢኖር ኖሮ የሰሞኑን ዓይነት የሚያስጠይቅና የሚያስወቅስ ስሕተት ባልፈጸሙ ነበር፡፡ ሮም ላይ ወደ መንበሩ ሔደው እጅ እንደነሱት ¬¬ ወይም እንደ ብዙዎቹ ዘመናዊ አሠራርን እንደ ሚከተሉ የአብያተ ክርስቲያን መሪዎች አሠራር ቢኾን ኖሮ እርስዎ የሚናገሩትን አርቅቆ የሚሰጥዎ ሲያስፈልግም የሚናገርልዎ ባለሙያ ሊኖርዎ ግድ ይል ነበር፡፡ እርስዎ ሁሉንም ልሁን ሲሉ ይኸውና እንደዚህ ዓይነት ግርግር ውስጥ ቤተ ክርስቲያናችንን ከተቱ፡፡ ዘመናዊነትዎ እንግሊዝኛ በማልፋት ብቻ ኾነሳ) ቤተ ክርስቲያናችን ማንነቷን ጠብቃ ዘመናዊ አሠራርን እንድትከተል ያድርጉ እንጂ) የእርስዎ የቆብ ወንድም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ የሚጽፏቸው መጻሕፍት በረሃ አቋርጠው ለእኛ ወጣቶች መማሪያ ሲኾኑ ይመለከቱ የለም እንዴ) የተማሩ ሰብስበው በመንበራቸው ዙሪያ ስለያዙ እኮ ነው፡፡ እርስዎም ዘመዳ ዘመዶችዎን ምናምን እያስያዙም ቢኾን ራቅ ያድርጓቸውና በሙያቸው ቤተ ክርስቲያኗ ዘመኑን እንድትዋጅ የሚያደርጉ ዘመናዊ ምሁራንን ያቅርቡ፡፡ ዘመናዊነቱ ቤተ ክርስቲያኗን የማይጠቅም መኖሩን ተረድተውም ምርጫዎ ላይ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን ዘመናዊ አሠራር እንድትከተል የማያደርጓት ከሰዎች ጋ ላለመጣላት ነው የሚል የጅል ግምት ባይኖረኝም መጠላት መወገዝዎ ካልቀረ ምነው ቤተ ክርስቲያኗን ወደ ፊት ሊያራምድ የሚችል ጥሩ ሥራ ሠርተው ቢጠሉ) ይንቀሳቀሱ እንጂ እስከመቼ ዝም ብለው ይቀመጣሉ)
ምክሬን ሳጠቃልል ሁሉም እንዲሰምር ይጸልዩ ብዬ አልደፍርዎትም፡፡ ይልቅዬስ በርእሱ ተነስቷልና እርስዎን ከመንበርዎ ያጋባ ሲኖዶሱ የእስዎ ዘመን ድክመት ሲነሣ ነገ ታሪክ የሚያጮኸው የወቀሳ ጅራፍ እሱም ላይ እንደሚያርፍ አስተውሎ ጀምሮታል እንደተባለው በመረጋገጥም ይሁን በመፋጠጥ መፍትሔውን ያስቀምጥልን የሚል መልእክቴን በአጭሩ ወርውሬለት ላብቃ፡፡
ማስተዋሉን ከልቡና ጋር ይስጥልኝ፡፡
የሮሜው ልጅዎ ከካታኮምቡ አጠገብ


1 comment:

Anonymous said...

selam dejeselamoch
yihe homepage yekefetachihut be enqirt lay...endilu betekristyanachinin mezebabecha litaderguat new?melikam eyerserachihu yale yimesilachihual?eyegenebachihu weyis eyaferesachihu? SEWOCHIN EYEGEDELU LE AMILAKACHEW MELIKAM YESERU YEMIMESILACHEW ZEMEN YIMETAL. yetebalewun astewulu...negerun bataragibu melikam yimesilegnal.
amilak betekristyanachnin yitebik

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)