July 9, 2009

ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔው ላይ ሳይፈርም ቀረ፤ ጋዜጠኛው ተደበደበ

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 9/2009)
• የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዘጋቢ ተደበደበ፣
ትናንት ውሳኔ በማሳለፍና ቃለ ጉባዔ በማጽደቅ ስብሰባውን የበተነው ቅዱስ ሲኖዶስ ቃለ ጉባዔው ላይ በመፈራረም ተግባራዊ ያደርጋል ተብሎ ሲጠበቅ ያንን ሳያደርግ ቀረ። ስብሰባው ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን ተጨባጭ ውሳኔ ሳያልፍ ቀርቷል። ቅዱስነታቸው በበኩላቸው ቅ/ሲኖዶስ ያዋቀረውንና እርሳቸው ያገዱትን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን እግድ በማንሣት ነገሮችን እንዲያቀዘቅዙ በድጋሚ ቢጠየቁም አሁንም አሻፈረኝ ብለዋል። ይልቁንም አዲስ ሕግ ለራሳቸው ያወጡ ይመስል “የፓትርያርክ ትዕዛዝ በፓትርያርክ ብቻ ነው የሚሻረው” በሚል ከቅዱስ ሲኖዶስ በላይ መሆናቸውን አሳይተዋል። ቅዱስ ሲኖዶስ ሐሳቡን ቀልብሶ ስለ ጉዳዩ እንደገና እንዲነጋገር ያስገደደው ውስጣዊ ጉዳይ ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም። በርግጥ ትናንት ጉባዔው ሲበተን የዚህ ሁሉ ድራማ ዋና ተዋናይ የሆኑት ወ/ሮ እጅጋየሁ ጳጳሳቱን ሲያስፈራሩ እንደነበር ታውቋል። ሴትዬዋ እንዴት ከሕግ በላይ ሊሆኑ እንደቻሉ ለብዙዎች ግራ የሚያጋባ ነገር ሆኗል።
በተያያዘ ዜና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባልና የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የፌዴራል ፖሊስ ልብስ በለበሱ ሰዎች ጥበቃ በቤታቸው ተገድበው እንደሚገኙ ምንጮቻችን ገልጸዋል። እገታው ለክፋት ይሁን ወይም እርሳቸውን ከክፉ ነገር ለመጠበቅ እስካሁን የታወቀ ነገር ለም። ምንጮቻችን እንደተናገሩት አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ሊቀ ጳጳሱን ያገተው ክፍል ማን እንደሆነ እንደማያውቁ ተናግረዋል ተብሏል። በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ በመንግሥት ባለሥልጣናት በኩል አንድና ወጥ የሆነ አቋም እንደሌለ ይታወቃል። የኢሕአዴግ ክፍል የሆነው ሕወሐት በለዘብተኝነት፣ የአማራው ክፍል ክንፍ ነው የሚባለው የነበረከትና ተፈራ ዋልዋ ቡድን ደግሞ በፀረ-ቤተ ክርስቲያንነት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ይታወቃል። የብአዴን አመራሮች ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዲህ የሚጠሉበትና የሚያዋርዱበት ምክንያት ግን አሁንም ግልጽ አልሆነም። በቅርቡ በደሴ የቅድስት አርሴማን ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የተንቀሳቀሱ ምእመናን የፖለቲካ ስም ተሰጥቷቸው ጥቃት እንደደረሰባቸው ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቤተ ክህነቱ አካባቢ በመካሄድ ላይ ያለውን ውጣ ውረድ ከመጀመሪያው ጀምሮ በማቅረብ ላይ የሚገኘው የአማርኛ ጋዜጣ “አዲስ ነገር” ሪፖርተር ስብሰባውን ለመከታተል ከሄደበት ከቤተ ክህነት ወደ ቢሮው ሲመለስ መንገድ ላይ አድፍጠው በጠበቁት ሰዎች መደብደቡ ታውቋል። ጋዜጠኛው “አብርሃም በጊዜው” አንድ ሰው ቀኑን ሙሉ ይከታተለው እንደነበረ ከተገነዘበ በሁዋላ መንገዱን ቀይሮ ወደ ቢሮው ለመግባት ሲሞክር ከፊት አድፍጠው ይጠብቁት በነበሩ ሰዎች በብረትና በብረት ቦክስ መደቆሱ ተገልጿል። ጋዜጠኛው የሕክምና ርዳታ ካገኘ በሁዋላ በደህና ሁኔታ ላይ ይገኛል። ከዚህ በፊት ያልታወቁ ሰዎች የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ የሆነውን አማረ አረጋዊን በዚሁ መልኩ መደብደባቸው ይታወሳል።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)