July 6, 2009

በዘመናት መካከል የተገኘ ዘመን የማይሽረው ልዕልና

በዘመናት መካከል የተገኘ ዘመን የማይሽረው ልዕልና
(አብርሃም ሰሎሞን)

እሑድ ሰኔ ፳፰/፳፻፩ ዓ.ም. JUNE 25, 2009 በደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ ተነበበ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእራስዋ ልጆች መካከል የሃይማኖቷ መሪ
የሆነ ፓትርያርክ የሾመችበት የ፶ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል

 ገና በሥነ ፍጥረት ስሙ ግዮን የተሰኘ የኢትዮጵያን ምድር የሚከብ ወንዝ ገነትን
ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር ተብሎ የተነገረላት፣
 አርባ ሦስት ጊዜ ስሟ በመጽሐፍ ቅዱስ ኢትዮጵያ ተብሎ የተገለጠ፣ የሴም እና የኩሽ ነገድ መኖሪያ የሆነች ባለብዙ ታሪክ፣
 እግዚአብሔር በጣቶቹ ጽፎ በሚያስፈራ፣ በሚያስደነግጥ እና በሚያንቀጠቅጥ ሁኔታ ሙሴ ከሲና ተራራ ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበላቸው ሁለቱ የምስክር ጽላቶች እና የታቦተ ጽዮን ማረፊያ፣
 ነብዩ ኢሳይያስ ሦስት ዓመት ሙሉ ለምልክትና ለተአምራት ሊሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን የሄደባት፣
 ነብዩ ኤርምያስ በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? ብሎ ስለ ሃይማኖቷ የተናገረላት፣
 ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቍርባኔን ያመጡልኛል፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች በማለት ነብያት በራእይ የተመለከቷት፣
 እናንተ እስራኤላውያን ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ብሎ ልዑል እግዚአብሔር ያገነናት፣
 የክርስቲያን ደሴት በመባል በዓለም የምትታወቀው እና የጌታ ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀሉ የሚገኝባት ታላቅ ምድር የእኔና የእናንተ አገር ኢትዮጵያ ነች።
ከብዙው በጥቂቱ፣ ከሰፊው በጠባቡ፣ እነኝህ ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች ኢትዮጵያ ቀደምትነት ያላት አገር ለመሆንዋ ዓይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው። ኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ገንዘብ ያደረገችውና እግዚአብሔርን በማወቅ አስቀድማ በሕገ ልቡና ከዚያም በሕገ ኦሪት አሁን ደግሞ በሕገ ወንጌል እየተመራች መገኘትዋ አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ የዳዊት ሥር ነኝ ብሎ እንደተናገረው አገራችን ኢትዮጵያም የሃይማኖት ሥር እንጂ ቅርንጫፍ አለመሆኗን በውል ያስረዳናል።
እንደሚታወቀው ለአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመታት ማለትም ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከመጀመሪያው አባት አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን (ቅዱስ ፍሬምናጦስ) ሌላ ኢትዮጵያ ከእራስዋ ልጆች የእራስዋን ጳጳሳት እና ፓትርያርክ እስክትሾም ድረስ አንድ መቶ አሥራ ዘጠኝ ግብፃውያን አባቶች ከእስክንድርያ እየተላኩ ኢትዮጵያን በሊቀ ጵጵስና ሲያገለግሉ እና ሲባርኩ ቆይተዋል። ኢትዮጵያውያን ከሳቴ ብርሃን (ብርሃን ገላጭ) ብለው ስያሜ ያወጡላቸው ቅዱስ ፍሬምናጦስ እጅግ ሊያስተውሉት የሚገባ ታላቅ ሥራ መሥራታቸው እንዲሁም ከእሳቸው በኋላ እየተሾሙ በመምጣት ኢትዮጵያ እንደ ሀገረ ስብከት እየተሰጠቻቸው ቡራኬ በመስጠት የኦርቶዶክስ እምነትን ያስፋፉ ለመሆናቸው ጥርጥር የለውም። ቢሆንም ግን ኢትዮጵያ ከእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ እንዲላክላት እና የአባቶቿን ቡራኬ ለመቀበል ያላፈሰሰችው ገንዘብ፣ ያልገበረችው ወርቅ፣ ያላሳለፈችው መከራ እና ያልከፈለችው መሥዋዕትነት የለም። እንዲህ እንደ ዛሬው መጓጓዣ አመቺ ባልነበረበት ሰዓት እና ከኢትዮጵያ ወደ ግብፅ ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ አጋሰስ እና የእግር ጉዞ ብቻ የመጓጓዣ መሣርያ በሆኑበት ዘመን ታሪክ ለአንዳፍታ እንኳን የማይዘነጋቸው አባቶቻችን በበረሐ ለመኖር እና ለመጓዝ ብቃትና ችሎታ ያላት ግመል እንኳን የምትደክምበትን የግብፅን በረሐ ባዶ እግራቸውን ለብዙ ወራት በመጓዝ ጉዳይ ለማስፈጸም ከኢትዮጵያ ወደ እስክንድርያ ሲመላለሱ ለመኖራቸው የዓይን ምስክሮች ባንሆን ታሪክ የዘገበውን አንብበን፣ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን የነገሩንን አሰላስለን በውስጣችን ከሚነደው የሃይማኖት ስሜት ጋር እውነታውን ለማወቅ እና ለመመስከር እንችላለን።

የዛሬ ሰማንያ ዓመት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእራስዋ ልጆች ጳጳሳት ተሹሞላት ሃይማኖቷን በመጠበቅና በማስጠበቅ ብትኖርም ከሁሉ የበለጠው ደስታ ግን የተፈጸመው የዛሬ ሃምሳ ዓመት በዚሁ በያዝነው ወር ሰኔ ፳፩/፲፱፻፶፩ ዓ.ም. ከመጨረሻው ግብፃዊ አባት አቡነ ቄርሎስ በኋላ ከእራስዋ ልጆች መካከል የመጀመሪያ ፓትርያርኳን አቡነ ባስልዮስን ስትሾም ነው። ይህ ፕትርክና የተገኘው በጾም በጸሎት፣ በብዙ ድካም እና ጥረት፣ በታላቅ መሥዋዕት ለመሆኑ ከላይ እንደገለጽነው ገና በአንድ ሺህ ሰባ ሰባት ዓ.ም. ንጉሥ ሐርቤ ኢትዮጵያ ከእራስዋ ልጆች ጳጳሳትን መምረጥ አለባት ብሎ ድምፁን ካሰማበት ጊዜ ጀምሮ ነው።

ታሪክ እንደሚነግረን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያለማቋረጥ ኢትዮጵያውያን ከእስክንድርያ እየተሾሙ የሚመጡትን ጳጳሳት ስለሁኔታው አስፈላጊነት ሲጠይቁና ሲሞግቱ ኖረዋል። የብዙ ዓመት ትግል መልስ ያገኘው ግን ምንም እንኳን ልዑል እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ቢሠራውም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፍጹም ባለውለታ በመሆን ባላቸው ዲፕሎማሲያዊ እውቀትና ችሎታ ሁኔታውን አመቻችተው ያስፈጸሙት የአገር መሪ ንጉሥ ብቻ ሳይሆኑ የሃይማኖት መሪም በመሆን ሕይወታቸውን ለቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያስገዙት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው። መልካም ስማቸው ከመቃብር በላይ ሕያው ሆኖ ይኖራል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የረጅም ዘመናት ኅልሟ እና ራዕይዋ እውን የሆነበት ይህ ታላቅ ምስጢር የዛሬ ሃምሳ ዓመት ተከናውኗልና።

ለአንዲት ሃይማኖታቸው እና ለቅድስት አገር ኢትዮጵያ ሲሉ በጥይት ተደብድበው የሞቱት፣ ሃይማኖትን ለማቅናት እራሳቸውን ጥለው፣ በጾም እና በጸሎት ተጠምደው ሚዛን የማይመዝነው፣ ቁጥር የማይወስነው እና አንደበት የማይገልጸው ተጋድሎን የተጋደሉት፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሕዝበ ክርስቲያን አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች
በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ። የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። እንዳለው በብዙ ስቃይ እና መከራ ውስጥ ያለፉት አባቶቻችን እና እናቶቻችን የከፈሉት ዋጋ ክቡር ንዑድ በመሆኑ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ወርቅነቱን የሚያረጋግጠውን ያህል ኢትዮጵያም እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትና ወርቅ ለሆነ ሃይማኖቷ ከልጆቿ መካከል የሃይማኖት መሪዎቿን አፍርታለች፤ እራስዋንም ችላለች። ጳጳሳቷ አቡነ ጴጥሮስ እና አቡነ ሚካኤል ከሰባ ዓመታት በፊት በውጭ ወራሪ የቀመሱትን የግፍ ሞት ፓትርያርኳም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከሠላሳ ዓመታት በፊት በውስጥ ምንደኞች ቀምሰውታል። ይህን መከራ እና ስቃይ በውል የተረዱት እና የሚያውቁት ታላቁ የጸሎት ሰው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ዕለት ዕለት የከበደባቸው የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ሆኖ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እንዲታደጋት፣ በከንቱ ይፈስ የነበረውን የልጀቿን ደም እንዲገታላት፣ መሪዎቿ እና ሕዝቦቿ እንዲስማሙላት ጫማ ሳይጫሙ እና ማለፊያ ምግብ ሳይመገቡ ቀንና ሌሊት በጸሎት ተግተውላታል። ዛሬም የአባቶቻቸውን ፈለግ የተከተሉ ስውር ባህታውያን በምድራችን አሉና እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ይስማላቸው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ እንደዛሬው እራስዋን ችላ ከእራስዋ ልጆች ጳጳሳት መሾም የሚችል ፓትርያርክ እስከምታገኝ ድረስ ለዘመናት ከግብፅ አሌክሳንድርያ ጳጳሳት እየመጡላት ታስተናግድ ነበር። ለዘመናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከገዛ ልጆችዋ እና ሊቃውንቶችዋ ጳጳሳት ለመሾም ሳትታደል ቀርታ በመጨረሻው ሰዓት ያሰበችውን ስታሳካ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ የተናገሩት የተዋጣለት እና የተሳካለት ንግግር <አዲስ ሕይወት> ከሚለው መጽሐፍ እንዲህ ይነበባል፦
<ለአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመታት ከእስክንድርያ ግብፅ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ማርቆስ መንበር ጋር ያላት መንፈሳዊ ግንኙነት እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ልጆች በጵጵስና ማዕረግ እየሾመች በነፃነት እንድትኖር ስንደክምበት የቆየነው ተፈጽሞ በማየታችን ዛሬ የመላው ኢትዮጵያ ደስታ ነው። የኢትዮጵያ ታላቅነትና የሥልጣኔ እድገት ከሃይማኖት ጋር የተባበረ እንዲሆን ያስፈልጋል። ሃይማኖት ከሌለ ምንም ዓይነት ኃይል ቢኖር ምንም ዓይነት ሥልጣኔ ቢገኝ ሥልጣኔም ሆነ ኃይል በግፍ የተሸፈነና በግፍ የታወረ ይሆናል።

የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን እና ልጆቿን ለማገልገል ቃል የገባችሁ ጳጳሳት ሁሉ የሃይማኖትን እና የበጎ ምግባርን ትምህርት ለማስፋፋት ከባድ አደራ ያለበትን ኃላፊነት ተቀብላችሁ የሐዋርያነት ሥራችሁን ጀምራችሁ በእግዚአብሔር ስም የምትፈጽሙት ሁሉ ሰማያዊ ክብር እንዲያስገኝላችሁ ከልብ እንመኝላችኋለን፤ ለነፃይቱ አገራችን ነፃ የሆነች ቤተ ክርስቲያን
ያስፈልጋታል። እግዚአብሔር የሚሠራውን ሥራ በፈቀደ ጊዜ ስለሚፈጽም ኢትዮጵያ አገራችን ነፃ ሕዝቦችን መንግሥታችን ራሷን የቻለች ቤተ ክርስቲያን እንድትኖራቸው ይመኙት የነበረው ሁሉ ተፈጸመ፤ ይኽም በዓለም ዘንድ እንዲታወቅ ሆነ። ይኽም ደግሞ በዘመናችን ስለተፈጸመ እኛም ሕዝባችንም እኩል የምንኮራበት ነው። ያለፉት አባቶቻችን ይኽንን ተመኙ፤ በተስፋም ተመለከቱ፤ በኃይማኖት የጸናች ተስፋቸው ግን በእኛ ዕድሜ ስትፈጸም ለማየት በቃን።

አገራችን ከጥንት ጀምሮ ታላቅ ታሪክ ያላት አገር ናት፤ ነገር ግን በመካከሉ ታሪኳ እንደጠፋ ያህል ተቆጥሮ ቤተ ክህነት በሰው እጅ የሚተዳደር ሆኖ ነበር፤ አሁን በቅርቡ በእኛው ዘመን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ስብሰባ አድርገው በሚነጋገሩበት ጊዜ አለቃዋ እያለች(ግብፅን ነው)ጭፍራዋ አትጠራም (ኢትዮጵያን ነው) የሚል ምክንያት በመሰጠቱ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በጉባዔው ውስጥ መግባት አይገባትም ስለተባለ ግብፆች ተጠርተው ሲሄዱ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ወገኖች እንደ ጭፍራ ተቆጥረው ከጉባዔው ሳይሳተፉ በመቅረታቸው በጣም አዝነን ተጸጽተን ነበር፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ ጸጸት የሚወገድበትን ከማሰብ ሳንቆጠብ የእግዚአብሔር ፈቃዱ እስኪሆን ድረስ ውጤቱን በመጠባበቅ እየደከምንበት ቆይተን ነበር፤ ምስጋና ለእርሱ ይሁንና አሁን ያሰብንበትንና የደከምንበትን ሁሉ ተፈጽሞ ስላገኘነው ለእግዚአብሔር ምስጋና ከማቅረብ አንቆጠብም፤ ብዙዎች ጳጳሳት ይቅሩና አንድ ጳጳስ እንኳን ከኢትዮጵያውያን ወገን በጵጵስና ማዕረግ ሊሾም አይገባውም እየተባለ የሚነገርበት ጊዜ አልፎ ከኢትዮጵያውያን መካከል ፓትርያርክ ተሾሞ ጳጳሳትም እንዲሾሙ ተደረገ፤ ለአገራችን ለኢትዮጵያ ጥንታዊ የሆነ ታሪካዊ ክብሯ ሲመለስላት በማየታችን እና የኢትዮጵያም ምእመናን ይኸንን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ እምነታቸውን በከፍተኛ ማዕረግ በማግኘታቸው እኛም በዚሁ ቀንና ሰዓት የዚሁ ደስታ ተካፋይ እንድንሆን የተቀደሰ ፈቃዱ ስለሆነ ውለታው በዋጋ ሊከፈል ለማይቻለው አምላክ ምስጋናችንን እናቀርባለን። በዚህም እግዚአብሔር በቸርነቱ ለሚሠራው ሥራ ምክንያት ስላደረገን በጊዜው ይኽንንም ለማየት አብቅቶ የኢትዮጵያን የቤተ ክህነት ደረጃ ከፍ አድርጎ ጳጳሳትና ፓትርያርክ በአንድነት ሆነው እንዲመሩ ስላደረገ ለእኛ ከዚህ የበለጠ ደስታ አይኖረንም። እግዚአብሔር ለሚያደርገው ምክንያት አድርጎን የዚህ ዕድል ተካፋይ ሆነን እንድንገኝ ለፈቀደልን አምላካችን ምስጋና እያቀረብን ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዕድገት ለምንጊዜም ከልብ የምንመኝ ስለሆነ ያሰብነውን ሁሉ ያስፈጽመን እያልን ቸሩ ፈጣሪያችንን እንለምነዋለን።> በማለት ንግግራቸውን አሰምተዋል። መንግሥቷና ሕዝቧ ሃይማኖቷን በእምነት ይጠብቁላት
የነበረችው ምድራችን ዛሬም እንደ ትናንት ተደስታ የደስታዋን ፍጻሜ ማየትን እንሻለን። ዛሬ ይህ ታላቅ ድል ከተገኘ ሃምሳ ዓመት ሆነው ስንል ዓመታት ለመቁጠር ሳይሆን ከሃምሳ ዓመታቱ በፊት የነበረውን የታሪክ ጉዞ ለማሳሰብ ነው። የቀደምት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ታሪክ ሕያው የሚሆነው ይህን መሥዋዕት የተከፈለበትን ሃይማኖትና ሥርዓት እንዲሁም ማንነታችንን ለትውልድ ማስተላለፍ ስንችል ብቻ መሆኑንም ለማዘከር ነው። ቅዱሳን አባቶች የደም ዋጋ የከፈሉበትን ይህን ሃይማኖት እና መንበር መጠበቅም ሆነ ማስጠበቅ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። ይህ በዓል የሁላችን በዓል ነውና እያንዳንዳችን አስበነው እንድናልፍ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ከእራስዋ ልጆች ፓትርያርክ በሾመችበት ማግስት ጀምሮ በዓለም እራስዋን በማሳወቅ ቤተ ክርስቲያናትን ከፍታለች። ለዚህም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በኒው ዮርክ፣ በጃማይካ፣ በሱዳን፣ በትሪላንድና በብርትሽ ጉያና አገሮች ላይ ቤተ ክርስቲያን ታንጸዋል።

አሁንም በተራራ ላይ ያለች ፋኖስ አትደበቅምና ሃይማኖትን በማሳደግና ቤተ ክርስቲያንን በማስፋፋት ረገድ እየተደረገ ያለው ነገር እጅግ አመርቂ ነውና ጠማማውን ነገር ሳንመለከት ቀናውን እያሰብን በጸሎት እና በምልጃ ወደ እግዚአብሔር እናሳስብ። እኛ ደረሰብን የምንለው መከራ እና ችግር በአባቶቻችን ላይ ከደረሰው መከራ ጋር ሲነፃፀር የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አለው። ያለተስፋ ያልተወን አምላክ ተስፋ ቆርጠን እንዳያገኘን በውል ልናስብበት ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ። ብሎ እንደተናገራቸው እኛም ነጻነትን ካገኘን በኋላ ዳግም ወደ ባርነት እንዳንሄድ የተከፈለውን ዋጋ ዞር ብለን የምንመለከትበት አንገት እና አርቀን የምናይበት የሃይማኖት መነፅር ያስፈልገናል። በጠባቡ በር ለመግባት በብዙ መፈተናችን ዳግም ባርነትን እንድንመኝ ሊያደርገን አይገባም። ልዑል እግዚአብሔር በብዙ መፈተናቸውን እና መቸገራቸውን አውቆ ከግብፅ ባርነት እና ከፈርዖን ሠራዊት ያስጣላቸው እስራኤላውያን ወደፊት የሚያገኙትን ተስፋ ከተስፋ ሳይቆጥሩት ለዕለት ያጋጠማቸውን ፈተና ብቻ ለመወጣት ሲሉ ወዳለቀሱበት እና ወደተዋረዱበት ምድር ለመመለስ ጉምጉምታን አሰሙ።በግብፃውያን ፊት ተንቀው እና ተረግጠው፤ ልጆቻቸውን በግፍ አጥተው እና ጉልበታቸውን ጨርሰው የበሉትን ምግብ ዳግም ሊበሉት አስፈለጋቸው። እግዚአብሔር ያዘጋጀላቸው ምድር ማርና ወተት የሚያፈስ መሆኑን ማስተዋል ተሳናቸው። በግብፅ ያለ ዋጋ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዱባውንም፥ በጢኹንም፥ ኩራቱንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት እናስባለን፤ አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀች፤ ዓይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም አታይም። ማለትን ጀመሩ። ዛሬም በብዙ መሥዋዕት ለዚህ የደረስንበትን ነፃነታችንን ጥቂት ፈተና አሸንፎን ከሃምሳ አመታት በፊት እንደነበረው ዓይነት ኑሮን ዳግም ለመኖር መመኘት አያስፈልገንም። ትናንት የገበርነውን ግብር ዛሬም ለመገበር፤ ትናንት የኖርነውን ኑሮ ዛሬም እንደገና ለመኖር መመኘት ከችኩልነት የመጣ ውሳኔ እንጂ ከማስተዋል የመጣ አይደለም። ወደ ግብፅ ሲሄዱ በግብፅ በረሐ ወድቀው የቀሩትን የቅዱሳን አባቶቻችንን ድካም በዓይነ ሕሊና ማየት ይኖርብናል። በመጨረሻም ልዑል እግዚአብሔር ዮርዳኖስን እያሻገረ የሕይወት መንገድ እንደሰጣቸው ባለታሪኮች፣ በዮርዳኖስ ባሕር ገብተው ከቁስላቸው እና ከለምጻቸው እንደተፈወሱት አገልጋዮች ለኢትዮጵያ ምድር እና ለኦርቶዶክስ እምነታችንም ዮርዳኖስን በደረቁ እያሻገረ ወደ ሕይወት እና ወደ ሰላም መንገድ ይምራልን። አለበለዚያም ቁስለኛው እንደተፈወሰበት ለምፃሙ እንደነጻበት የዮርዳኖስ ባሕር እኛም ከባሕሩ ገብተን ከጸብ እና ከክርክር፣ ከመለያየትና ከአለመግባባት፣ ካለመተማመንና ካለመከባበር፣ ቁስል እንፈወስ። በእጃችን
ያለውን ወርቅ እንደ ተራ ነገር ቆጥረነው ከጣልነው በኋላ ሌላ አንሥቶ ሲያጌጥበት እንዳንመለከት የእጃችንን ወርቅ ልንንከባከበው ያስፈልገናል።

በዘመናት መካከል የተገኘ ዘመን የማይሽረው ልዕልና ከፍ ከፍ ሊል ይገባዋልና የሰላም እና የፍቅር አምላክ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ዓይን ሞታለች የተባለችውን የኢያኢሮስን ልጅ ለማዳን እመን እንጂ አትፍራ ብሎ እንደተናገረ አሁንም አለቀ፣ ተቆረጠ፣ ተሰበረ የተባለለትን አንድነት እመን እንጂ አትፍራ ብሎ ወደ ቀደመ ክብራችን ይመልሰን። ታሪክ ተቀብለን ታሪክ የማናወርስ ሰዎች እንዳንሆን እግዚአብሔር ይርዳን።
ወ ስ ብ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር ! !
አብርሃም ሰሎሞን
ሰኔ ፳፰/፳፻፩ ዓ.ም. JULY 25, 2009
slat6@yahoo.com__

9 comments:

Anonymous said...

"እግዚአብሔር በጣቶቹ ጽፎ በሚያስፈራ፣ በሚያስደነግጥ እና በሚያንቀጠቅጥ ሁኔታ ሙሴ ከሲና ተራራ ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበላቸው ሁለቱ የምስክር ጽላቶች እና የታቦተ ጽዮን ማረፊያ፣ ነብዩ ኢሳይያስ ሦስት ዓመት ሙሉ ለምልክትና ለተአምራት ሊሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን የሄደባት፣" የሚለው አባባል ታሪካዊነት ቢኖረው መልካም በሆነ ነበር። እውቁ የታሪክ ሊቅ ዶክተር ታደሰ ታምራት እንኳ የማይቀበሉት ነው። ልብ ወለድና አፈ ታሪክነቱ ለአገር በማድላት የተደረገ ጥረት በመሆኑ እያፈርንም ቢሆንም እስቲ ይሁና ብለናል።

Anonymous said...

"እግዚአብሔር በጣቶቹ ጽፎ በሚያስፈራ፣ በሚያስደነግጥ እና በሚያንቀጠቅጥ ሁኔታ ሙሴ ከሲና ተራራ ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበላቸው ሁለቱ የምስክር ጽላቶች እና የታቦተ ጽዮን ማረፊያ፣ ነብዩ ኢሳይያስ ሦስት ዓመት ሙሉ ለምልክትና ለተአምራት ሊሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን የሄደባት፣" የሚለው አባባል ታሪካዊነት አለው። የታሪክ ሊቅ ዶክተር ታደሰ ታምራት ሊቅ መሆናቸው አሁን ከላይ ከተጻፈው ኃይለ ቃል ጋር አይዛመድም። ነብዩ ኢሳይያስ ሦስት ዓመት ሙሉ ለምልክትና ለተአምራት ሊሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን የሄደባት፣ የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነውና ትንቢተ ኢሳይያስ ምእራፍ ሦስት ቁጥር ሃያን መመልከት ግድ ይላል። የታቦተ ጽዮን ሁኔታ አጠያያቂ ስላልሆነ አፈ ታሪክ ተብሎ አያስነግረውም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ሌላ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልምና የተጻፈው ጽሑፍ እስቲ ይሁና የሚያስብል አይደለም። ቸር ይግጠመን።

Anonymous said...

Mr Anonymous,
It is good to ask for historical evidence. But, you are trying to disprove the facts( presented by Abrham Solomon,) which is endorsed by countless local and foreign historians.
My friend, you may not belive it niether does Dr.Tadesse that is okay. However, that would not change the reality.
Little John

Anonymous said...

Anon4
Could the last Anon please cite one historical fact? Or are you inviting the viewer not to ask questions but to just believe whatever you or someone says? I think it is this reasoning that is working against the teachings and credibility of our mother church.

Anonymous said...

ትንቢተ ኢሳይያስ ፫፡፳ ተብሎ የተጻፈው ፳፡፫ ተብሎ ይስተካከል። ሊቅም ይሁን ፈላስፋ፣ ምሑርም ይባል ተመራማሪ ከመጽሐፍ ቅዱስ የወጣ ቃል ወይም መጽሐፍ ቅዱስን መነሻ ያላደረገ ታሪክ አይኖረውም፤ በተለይም ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ ሃይማኖቷ መናገር ከፈለገ። የነብዩ ኢሳይያስ በኢትዮጵያ ምድር መመላለስን እግዚአብሔር ከመሰከረለት እውቁ የታሪክ ሊቅ ዶክተር ታደሰ ታምራት ያልዳሰሱት እና ያላወቁት ታሪክ አይኖርም ማለት የዋህነት ነው። እውነትን እውነት ብሎ ማለፍ እና ተማርኩበት ብሎ መመስከር ሲገባ የእግዚአብሔርንም ምስክርነት መቃወም ተገቢ አይሆንም። ለማንኛውም ቃሉ ከቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይነበባል፦
እግዚአብሔርም አለ። ባሪያዬ ኢሳይያስ በግብጽና በኢትዮጵያ ላይ ሦስት ዓመት ለምልክትና ለተአምራት ሊሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን እንደ ሄደ፥ (ትንቢተ ኢሳይያስ. ፳፡፫)

Anonymous said...

The teaching and credibility of our mother Church doesn't stand against God's word. As for me there can be no historical proof except the words of the Bible. I wish Dr. Taddese would say some thing about this fact.

Anonymous said...

Anon7
ከላይ የተለጠፉትን አስተያየቶች አነበብሁ። "እግዚአብሔር በጣቶቹ ጽፎ በሚያስፈራ፣ በሚያስደነግጥ እና በሚያንቀጠቅጥ ሁኔታ ሙሴ ከሲና ተራራ ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበላቸው ሁለቱ የምስክር ጽላቶች እና የታቦተ ጽዮን ማረፊያ፣" የምትለዋ እየተረሳች ነውና አንድ ላይ ይነበቡ። በነገራችን ላይ ልቡ ለመማር ያልተከፈተለት ምን ቢሠሩት አያምንም። ጌታችንን የዳሰሱ ሙታንን ሲያስነሳ ተአምራቱንም ያዩ እንኳ አላመኑበትም። መማር የሚቻለው የተሻለ ማስረጃ ሲቀርብ የያዙትን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሲኾን ነው። ቅንነትን ይጠይቃል። እንደ ሕጻን ካልሆናችሁ የሰማይን መንግሥት አታዩም ያለው ለዚሁ ነው።

Anonymous said...

I have seen and read thoroughly what Abraham Solomon has written. Yes, of course it is our historical upcoming of Ethiopia.

Anonymous said...

What do you mean "it is our historical upcoming of Ethiopia?"

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)