July 22, 2009

የወቅቱን የቤተ ክርስቲያን ችግር አስመልክቶ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ጥሪ አስተላለፉ


(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 22/ 2009

በወቅቱ በቤተ ክርስቲያናችን የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ የዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም መልእክት አስተላለፉ፣ ጥሪ አቀረቡ፣ አቋማቸውንም ገለፁ። መንግሥትም "በአሳለፍነው ወቅት ተናገረ እንደተባለውና አበው ሊቃነ ጳጳሳትም እንደመሰከሩለት የቅዱስ ሲኖዶስን ሕግና ደንብ በማክበርና በማስከበር እስከ መጨረሻው አቋሙን ሳይለውጥ የጥቅመኞችንና የራስ ወዳዶችን ወሬ ቦታ ሳይሰጥ ሊቀጥልበት ይገባል" ሲሉ ጠየቁ።

“የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሀሳብ ነው” በሚለው ሐዋርያዊ ቃል መግለጫቸውን “ ለቅድስት ተዋሕዶ እምነታችን ራሳችሁን ለሰጣችሁና ለመስጠት ዝግጁዎች ለሆናችሁ ወገኖቼ፤ የአብያተ ክርስቲያናት ሀሳብ ሀሳባችሁ፣ የአብያተ ክርስቲያናት ችግር፣ ችግራችሁ መሆኑን ለተረዳችሁና ለመረዳት ዝግጁዎች” ለሆኑ ሰዎች ያስተላለፉት ብፁዕነታቸው የችግሩን አጠቃላይ ሒደት ከቅዱስ መፅሐፍ ጋር እያመሳከሩ አቅርዋል። በቅዱስ ጳውሎስ ቃል ስንመዘን “ብዙዎቻችን ከመስመሩ ወጣ ብለን የራሳችንን ሀሳብና ፍላጎት ስነከተል ጥቂቶቻችን ደግሞ ስለ እውነት ስለ አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአቅማችንን ስንጥር እንታያለን። ሌሎቻችን ደግሞ በግላችን ካቋቋምነው ቤተ ክርስቲያንና ማህበር ውጪ እንደማይመለከተን ሆን አንዳንድ ጊዜ እንደ አስታራቂ ሽማግሌ፣ አንዳንድ ጊዜ እንደ ወቅቱ፣ እንደ ነፋሱ ስንወዛወዝ እንገኛለን” ብለዋል።

በጠቅላላው በአሁኑ ወቅት ለግል ዝናና ለስልጣን ተብሎ ወንጀል እየተሰራ መሆኑን፣ አበው ሊቃነ ጳጳሳት መንገላታታቸውን፣ የቤተ ክርስቲያን ችግር ሳይፈታ “በቀጠሮ ሰበብ” በይደር መተላለፉን፣ “እኔ ከሞትኩ” በሚለው እንስሳዊ ፈሊጥ “ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በልጆቿም ሆነ በተቃዋሚዎቿ ፊት የሀፍረት ካባን እንድትለብስ” መገደዷን” በሰፊው አብራርተው “ለወጋቸውና ለሥልጣናቸው፣ ለጥቅማቸውና ለክብራቸው ሲሉ የእግዚአብሔርን ትዛዝ እጅግ የናቁትን ለይተን እንወቅ” ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። በተለይም በሰሜን አሜሪካ ያለውን “የግል ቤተ ክርስቲያን የሚያስተዳድሩ” ሰዎች በተላለፈ በሚመስል አስተያየታቸው ደግሞ “በቤተ ክርስቲያን ስም የግል ጎጆ መቀለሱን ትተን ፣ ከውስጥ ሆነን በእውነትና በዓላማ እንሟገታቸው (ወንጀለኞቹን)፤ ስህተቶቻቸውንም በግልጽ እናሳያቸው” ብለዋል።

እውነትን ያ ፍርሃት በድፍረት እንመስክር ያሉት ብፁዕነታቸው “መንግስት በአሳለፍነው ወቅት ተናገረ እንደተባለውና አበው ሊቃነ ጳጳሳትም እንደመሰከሩለት የቅዱስ ሲኖዶስን ሕግና ደንብ በማክበርና በማስከበር እስከ መጨረሻው አቋሙን ሳይለውጥ፣ የጥቅመኞችንና የራስ ወዳዶችን ወሬ ቦታ ሳይሰጥ ሊቀጥልበት ይገባል” ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። አባቶችን በማስፈራራት፣ በአፈናና በዛቻ፣ በስም ማጥፋትና በአድማ የተከናወነውን የመጨረሻውን ስብሰባ የተቃወሙት ብፁዕነታቸው “እሳቱ ተዳፈነ እንጂ አልጠፋም” ብለዋል። “ጥቅምት (ጉባዔው የሚደረግበት ወቅት) ነገ ነውና የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዳይናጋ፣ ሥርዓቷ እንዳይበረዝ፣ ቀኖናዋ በሆያ ሆዬ እንዳይለወጥ፣ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆናችሁ ሁሉ ከዚህ ዕለት ጀምሮ በየአለንበት በጋራም ሆነ በግል እግዚአብሔርን በጾምና በጸሎት እንለምነው። … የተራራቅን ተቀራርበን፣ የተለያየን ተገናኝተን ለመጸለይና ለመዘመር እግዚአብሔርንም ለማመስገን እንድንችል የሚከብድብኝ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሀሳብ ነው እንበል” ሲሉ አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም ላለፉት ሦስት ዓመታት በኒውዮርክና በዲሲ አህጉረ ስብከት በሊቀ ጵጵስና በማገልገል የሚገኙ አባት ሲሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሙሉ በሙሉ የዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት በማስተዳደር ላይ ይገኛሉ። ብፁዕነታቸው ይህንን መልእክት በቀጥታ በማስተላለፋቸው ብዙ ምእመናንን አነገታቸውን ከደፉበት ቀና ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

(የመልእክቱን ሙሉ ቃል ለማንበብ የሀገረ ስብከቱን ድረ ገጽ እዚህ ይመልከቱ)
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)