July 9, 2009

ቅ/ሲኖዶስ የፓትርያርኩን “ሁሉን አቀፍ ሥልጣን” ገፈፈ፣ “እንደራሴ” ሾመ


(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 8 እና 9/2009)
ትናንት ማታ የተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ታሪካዊ ስብሰባ በእምቢተኝነታቸው የጸኑትን ፓትርያርክ ሥልጣን በመግፈፍ እንደራሴ ሾመባቸው። ትናንት የስብሰባው ቃለ ጉባዔ በተነበበበት ጊዜ እንደተገለጸው ቅዱስነታቸው ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች በሙሉ ተገልለው፣ በጸሎት ብቻ ተወስነው እንዲኖሩ፣ ለዚህም አስፈላጊው ነገር ሁሉ እንዲሟላላቸው፣ በእንደራሴነት ደግሞ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ እንዲሰየሙ ወስኗል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ሰሞኑን ባደረገው ሙከራ ቅዱስነታቸው ነገሮችን በጥሙና እንዲመለከቱና በሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዲመሩ አባቶች በእንባ ጭምር የለመኗቸው ቢሆንም ቅዱስ ፓትርያርኩ ግን ማንንም ለመስማት ሳይችሉ ቀርተዋል። በርግጥም ቃለ ጉባዔው በሚፈረምበት ቀን ማለትም ሐሙስ ጁላይ 9 ጠዋት ውሳኔው ቀድሞ እንደተነበበው ሆኖ ካለፈ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉ ሥራው በእንደራሴው ይመራል ማለት ነው። ይህ ማለት ግን እንደ ቀድሞ ፓትርያርክ ከሥልጣናቸው ወርደዋል ማለት እንዳልሆነ አንድ አባት ለደጀ ሰላም አብራርተዋል። ምናልባት ግን ቅዱስነታቸው በተለመደው ጠባያቸው (የነ ወ/ሮ እጅጋየሁን ምክር ተከትለው) ከሄዱ የአቡነ መርቆርዮስ ዓይነት መጨረሻ ይገጥማቸው ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል።
ከእንደራሴው ሹመት በተጨማሪ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሹም ሽር የሚደረግ ሲሆን በተዋረድም በቅዱስነታቸው ቤተ ሰቦች ተይዘው የነበሩ ታላላቅ የአገልግሎት መምሪያዎች ሃላፊነቶች በሙሉ ለቦታው በሚመጥኑ ሊቃውንት ይሰጣሉ ተብሏል። ይህንኑ አጠቃላይ ሒደት የተመለከቱ አንድ አባት “እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሥራውን እየሠራ ነው” ብለዋል።
እንደራሴነት ምን ማለት ነው የሚለው ጉዳይ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተመሳክሮ ማብራሪያ መሰጠት እንዳለበት እያመንን ለጊዜው ግን ከዚህ ቀደም የነበረ አንድ ታሪክ ለማስታወስ እንወዳለን። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ (የመጀመሪያው ፓትርያርክ) በዕድሜና ጤና ምክንያት ሥራቸውን መሥራት ባልቻሉባቸው የመጨረሻ ዓመታት ሁዋላ 2ኛ ፓትርያርክ የሆኑት ሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ “እንደራሴ” ሆነው ቤተ ክርስቲያንን ሲመሩ ቆይተዋል። መንበሩ ግን የፓትርያርኩ እንደሆነ ዘልቋል። በቅዳሴ ወቅት የሚነሣውም የእንደራሴው ስም ሳይሆን የፓትርያርኩ ስም ነበር።
መጨረሻውን ያሳምረው!!!!!

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)