July 6, 2009

"ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊነት የሚጠበቅብንን ሁሉ በማድረግ እንትጋ"

"ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊነት የሚጠበቅብንን ሁሉ በማድረግ እንትጋ" ማኅበረ ቅዱሳን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን የምታስፈጽምበት፣ የውስጥም ሆነ የውጪ ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎቷን በአግባቡ የምታቀናጅ በትና የምታከናውንበት፣ ማዕከላዊውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልናና
የሥልጣን እርከን ተዋረድ ጠብቃ ራሷን የምትመራበትና የምትገለገልበት የአስተዳደር ሥርዓት ባለቤት ናት፡፡

አስገኝዋ እግዚአብሔር በመሆኑ የመንፈሳዊ አስተዳደር ሥርዓቷም እግዚአብሔር ነው፡፡ ለዚህም በዓለመ መላእክት የነገደ መላእክትን የሥ ልጣን እርከን፣ የአገልግሎት ስምሪትና አሠፋፈር፤ የእግዚአብሔር ሰዎች በሕገ ልቡና የተመሩበት፤ ከዚያም በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል እስከ አሁን የተደረሰበት የአስ ተዳደር ሥርዓትና አፈጻጸም ለአብ ነት የሚጠቀስ ነው፡፡

በዘመነ ብሉይ በሕገ ኦሪት የሙሴ አማት ኢትዮጵያዊው ዮቶር ለሙሴ፤ ሕዝቡን እንዴት ማስተዳደር እንዳ ለበት፤ መንፈሳዊውን የአስተዳደር ሥርዓትና አፈጻጸም ጭምር፤ «ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችንኮ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፣ የታመኑ፣ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎችን ምረጥ፤ ከእነርሱም የሺሕ አለቆችን፤ የመቶ አለቆችን፣ የዐምሳ አለቆችን፣ የዐሥር አለቆችን ሹምላቸው፡፡ በሕዝቡ ላይ ሁል ጊዜ ይፈርዱ፤ አውራውንም ነገር ሁሉ ወደ አንተ ያምጡት፤ ታናሹ ንም ነገር ሁሉ እነርሱ ይፍረዱ፤» በማለት አስተምሮታል፡፡ ሙሴም በፈቃደ እግዚአብሔር ሥርዓት አበጅቶ አስፈጽሟል፡፡ «ሙሴም ከእስ ራኤል ሁሉ አዋቂዎችን መረጠ፤ በሕዝቡም ላይ የሺሕ አለቆች፤ የመቶ አለቆች፣ የዐምሳም አለቆች፣ የዐሥርም አለቆች አድርጐ ሾማቸው፡፡ በሕዝቡም ላይ ሁልጊዜ ፈረዱ፤ የከበደባቸውንም ነገር ወደ ሙሴ አመጡ፡፡» /ዘጸ.18፡21-26/

በሐዲስ ኪዳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሥርዓት አበጅቶ፣ ለመረጣቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም የቤተ ክርስ ቲያን አስተዳደር መሪ በመሆን ትምህርተ ሃይማኖትን አጽንተዋል፡፡ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ደንግገዋል፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ እንዲፈጸምና እንዲዘልቅ በመልμም ሥራቸው የተመሰከረላ ቸውን በሕዝበ ክርስቲያኑ የተመረጡ አገልጋዮች ሥልጣነ ክህነት ሰጥተዋል፡፡ /የሐዋ.ሥራ.6፡1-7/ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ተከፋፍለው ሥምሪት በማድረግ በርμታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር በሥርዓት መርተዋል፡፡

ይህንኑ በማስተማር፤ የቀደሙት ቅዱሳን ሐዋርያትና አበው አጽንተው ያቆዩትን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሥርዓትና አገልግሎት ጠብቃ በተግባር ስትፈጽም የቆየች፤ ከራሷ መንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር ለአገርና ሕዝብ አስተዳደር ሥርዓት አርአያ በመሆን ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከተች፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናዊ አስተዳደርና ውጤታማ አፈጻጸም እንግዳ እንደማትሆን ሁሉም የሚገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፋዊና አገራዊውን ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ፣ የሕዝቡን መንፈሳዊ ሕይወትና አኗኗር ታሳቢ አድርጐ ትውልዱን ይዞ ለመቀጠል የሚያስችል፤ ዘመኑን የዋጀ በተጠና ዕቅድና አፈጻጸም የሚከናወን፤ ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ለቤተ ክርስቲያናችን አስ ፈላጊ መሆኑ የሚያያይቅ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለተቋማዊ እንቅስቃሴዋ የተቀላጠፈ ዘመናዊ አሠራርና ውጤታማ አፈጻጸም መመሪያ የሚሆን መርሕ ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ እን ዳለባት በየአጋጣሚው በየቦታው የሚነoe የወቅቱ ጥያቄ ሆኗል፡፡ ይህንን እንደ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የምእመናን ሁሉ አጀንዳ የሆነ ጉዳይ በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቅርቡ ከብፁዓን አባቶች የመረጠው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የወቅቱን የቤተ ክርስቲያን ችግር ተገንዝቦ ዘላቂ ውጤት ሊያመጣ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተገኘው ማስረጃ እንደሚያመለክ ተው፤ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ስለአለው ችግርና ድክመት መፍትሔ ለመፈለግ፤ በቤተ ክርስቲያናችን መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ሕጓና ሥርዓቷ እንደተጠበቀ ሆኖ የተቀላጠፈ አመራርና አሠራር እንዲኖር ለማድረግ፤ ስብከተ ወንጌል ትኩረት ተሰጥቶት በሠለጠነ የሰው ኃይል ተደራጅቶ ብቃትና ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ እንዲጠናከር የኢትዮጵያ ኦር ቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ግንቦት 6 ቀን 2001 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በሰፊው ተወያይቶበታል፡፡ በውይይቱም ችግሩ ዘለቄታ ያለው መፍትሔ እንዲያገኝ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤና በቋሚ ሲኖዶስ እየተወሰኑ የሚተላለፉ ጉዳዮችን እየተከታተለ የሚፈጽምና የሚያስፈጽም፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚታየውን የአስተዳደር ችግር በጥልቀትና በስፋት የሚከታተልና መፍትሔ የሚሰጥ፤ ለወደፊቱም የሚሠሩ ሥራዎችን ሁሉ የሚገመግምና የሚቆጣጠር እንዲሁም መፍትሔ የሚ ሰጥ ሰባት ብፁዓን አባቶች አባላት ያሉት ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የሆነ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰይሟል፡፡ ለዚህ ውሳኔ እና ኮሚቴ መሰየም መሠረት የሆነው ጥቅምትና ግንቦት 15 ቀን 2001ዓ.ም በተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተላለፈው ውሳኔ ነው፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ለተላለፈው ውሳኔ ምክንያት የሆኑ ዋና ዋና ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ከጽ/ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የፋይናንስ አጠቃቀም፣ የሰው ኃይል አደረጃጀት እና የልማት እንቅስቃሴ ወዘተበሲኖዶስ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የአፈጻጸም ችግር ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድገት ዋና ማነቆ በመሆናቸው ቅዱስ ሲኖዶስ እነዚህን ችግሮች የሚፈታ ሥራ አስፈጻሚ እንዲቋቋም አድርጓል፡፡
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖቷን፣ እምነቷን፣ ሥርዓቷን፣ ትውፊቷን ጠብቃ፤ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷን ለመፈጸም ለዘመናት የተጠቀመችበትን አስተዳደራዊ ሥርዓትና አሠራር በየጊዜው በመፈተሽ ዘመኑን የዋጀ የተሻለ የአሠራር ለውጥ ማምጣት ይጠበቅባታል፡፡ ሆኖም ለውጥ ሲባል ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ሳይጣስ፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቷ እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕከላዊነት የሥልጣን እርከን ተጠብቆ የማንነቷ መገለጫ ሳይቀየር ሥርዓቱን ተከትሎ ነው፡፡

ስለዚህ ዘመኑን የዋጀ የተሻለ ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓትና አሠራር ለውጥ ያስፈልጋል ሲባል፤ ቋሚ የሆነውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓተ አምልኮዋንና ቀኖናዎን በአግባቡ ለማስፈጸም በሚያስችል መልኩ የተደራጀ ሊሆን ይገባል፡፡ የካህናትንም ሆነ የምእመናንን ተግባራዊ ተሳትፎ የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችል፤ ቃለ ዓዋዲው በተሟላ ሁኔታ በትክክል ተግባራዊ መሆኑን የሚያረጋግጥ፤ እንዲሁም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻ ወሳኝ አካል አፈጻጸሙን ለመከታተልም ሆነ ለመቆጣጠር በሚያስችለው መልኩ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ እስከታች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለውን አμል የሚያሳትፍ እንዲሆን ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ማኅበረ ቅዱሳን በዓላማውም ሆነ በአገልግሎቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ እምነት ሳይጣስ ቀኖናዋ ተጠብቆ እንዲዘልቅና ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ በማይናወጽ እምነት ጠንከሮ ይሠራል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔዎች ለማስ ፈጸም በሚደረገው ጥረትም ቤተ ክርስቲያን የምትጠብቅበትን ሁሉ ለማበርከት ማኅበረ ቅዱሳን ዝግጁ ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንደሚያስረዳው እየተባባሰ የመጣው የአስተዳደር ችግር ቅድስት ቤተ ክርስ ቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በአግ ባቡ እንዳትወጣ አድርጓታል፡፡ በም ልዓተ ሲኖዶስና በቋሚ ሲኖዶስ የሚሰጡ ውሳኔዎችና የሥራ መመሪያዎች አይፈጸሙም፡፡ ለአፈጻጸሙም አስፈላጊው ክትትል እየተደረገና በየወቅቱ በሚቀርብ ሪፖርት እየተገመገመ የቤተ ክርስቲያኒቷ ዘርፈ ብዙ ሥራ አለመከናወኑ በየጊዜው የሚጠቀስ ችግር ነው፡፡ ማዕከላዊ የፋ ይናንስ አስተዳደር ሥርዓት አለመኖሩ፤ የሰው ኃይል አመዳደብ፣ የሀ ብትና የሥራ መመሪያ አጠቃቀም በዕቅድና በተደራጀ ሁኔታ አለመፈጸሙ፤ የትምህርት ዝግጅትን ሞያና የሥራ ልምድን ታሳቢ ያደረገ ሥራና ሠራተኛን የሚያገናኝ የምደባ ሥርዓት ተግባራዊ አለመሆኑ ጐልተው የወጡ ችግሮች ናቸው፡፡ ሓላፊነትና ተጠያቂነትን በአግባቡ ለማስፈጸም በማያስችል ሁኔታ የሚደረግ የሠራተኛ አመዳደብና ሙስና የተንሠራፋበት አሠራር ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት እንቅፋት ሆኗል፡፡ ስለዚህ ይህ ችግር መልካምና ገንቢ ለውጥ ሊያመጣ በሚያስችል ሁኔታ መሠረታዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት ያስፈልጋል፡፡

በየገጠሩ አገልጋይ ካህናት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ አልባሳትና ንዋያተ ቅድሳት ተቸግረው፣ የዕለት መቀደሻ ጧፍ እጣን አጥተው አገልግሎታቸው የሚታጐል፣ ከዚያም በባሰ ሁኔታ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ገዳማትና አድባራቱ የችግራቸው ጽናት ከፍቶ እየተፈቱ፤ በዘላቂ ልማት ገቢያቸውን በማሳደግና ራሳቸውን ችለው ለአካባቢያቸውም በማትረፍ አርአያ ከመሆን ይልቅ በመዘጋት አደጋ ጠርዝ ላይ ተንጠልጥለው በአሳሳቢ ስጋት ውስጥ ያሉት ብዙዎች ናቸው፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቤተ መቅደስ ውስጥም ሆነ የውጭ አገ ልግሎት መሠረት የሊቃውንቱ፣ የአ ገልጋይ ካህናቱና መምህራነ ወንጌል መፍለቂያ ምንጭ የሆኑት አብነት ትምህርት ቤቶች ሕልውና እጅግ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የሆኑት ታላላቅ መምህ ራንና ደቀመዛሙርቱ የዕለተ ጉርስ የዓመት ልብስ በማጣት ችግር እየጠናባቸው ጉባኤያቱ እየተፈቱ ነው፡፡ በርቀትና ጠረፋማ አካባቢዎች የሚ ገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖ ቻችን ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በወንጌል ብርሃን እንድትደርስ ላቸው በተስፋ ይጠብቃሉ፡፡

ስለዚህ ከዕለት ወደ ዕለት እየሰፋ፣ እየከፋና እየተባባሰ የመጣውን የቤተ ክርስቲያን ችግር ለመቅረፍ እንዲቻል የመፍትሔው አካል በመሆን፤ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ የድርሻችንን ለማበርከት መዘጋጀት አለብን፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ የተሰየመው ሥራ አስፈጻሚ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከሆኑ ብፁዓን አባቶች ገለጻ ለመረዳት እንደተቻ ለው፤ ኮሚቴው በቤተክርስቲያን ለተፈጠሩት የአስተዳደር ችግሮች መፍትሔ በመፈለግ ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓትና አሠራር ለማምጣት የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

በሥሩ አምስት ንዑስ ኮሚቴዎችን ለማቋቋም በሒደት ላይ ነው፡፡ እነዚህ ኮሚቴዎች የቤተ ክርስቲያኒቷን አስተዳደራዊ ሥርዓትና አሠራር የተሻለና ዘመናዊ አድርጐ ለማጠናከር፤ በአስተዳደርና ሥራ አመራር፣ የሰው ኃይል እና ሀብት አጠቃቀም፣ በፋይናንስ አስተዳደር፣ በኢኮኖሚ፣ በሕግ፣ በምሕንድስና ዘርፎች ተዋቅረው የሚሠሩ ናቸው፡፡ በየመስኩ ባለሞያ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን አካተዋል፡፡ ኮሚቴው በተሰጠው ተግባርና ሓላፊነት መሠረት ከዚህ በፊት በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስነው ተግባራዊ ያልሆኑትን ውሳኔዎች ተከታትሎ በተግባር ለማስፈጸም የሚያስችል ዕቅድ አውጥቷል፡፡ ለአፈጻጸሙም እንዲያመች በጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያው ሓላፊዎች እና በየደረጃው ያሉትን ሠራተኞች ለማወያየት ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ የሥራ አስፈጻሚ ቋሚ ኮሚቴው የሥራ ጊዜው ለአንድ ዓመት እንዲሆንና የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲያቀርብ ሓላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ኮሚቴው ሥራውን በይፋ ጀምሯል፡፡ ኮሚቴው ሥራውን እየሠራ የመተዳደሪያ ደንቡን አርቅቆ በሐምሌ ወር በ2001 ዓ.ም ለሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲያቀርብ ተወስኗል፡፡ ለሥራ አስፈጻሚ ቋሚ ኮሚ ቴው የተሰጠው ተግባርና ሓላፊነት ይህ ሆኖ እያለ፤ ከዚህ በተቃራኒ « የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ ፓትርያርክ አንሥቶ ፓትርያርክ ለመተካት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው » በማለት የሚናፈሰውን መሠረተ ቢስ አሉባልታ /ቅስቀሳ/ አጥብቀው እንደሚቃወሙ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውስጥ ያሉ ብፁዓን አባቶች ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚያጋጥሟትን ችግሮች ለመቅረፍ እንዲቻል በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የተለያዩ ኮሚቴዎች መቋቋማቸው አይዘነጋም፡፡ ሆኖም ኮሚ ቴዎቹ የተቋቋሙበትን ዓላማ ሳያስፈጽሙና ውጤታማ ሥራ ሳይሠሩ በተለያዩ ምክንያት ሥራቸው የሚስተጓጎለው በርካታ ናቸው፡፡ ነገር ግን ግንቦት 6 ቀን 2001 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአንዳንድ ቦታዎች በሚናፈሱ መሠረተ ቢስ ቅስቃሳዎች ምእመናን ግራ እየተ ጋቡ መሆናቸውን እየገለጹ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት በሌላቸው መድረኮችም ሆኑ ቦታዎች ላይ በተዛባ ሁኔታ እያነሡ የሚተቹ አሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን የሚመለከታቸው አካላት በትክክል በመካሔድ ላይ ያሉትን ጉዳዮች፤ ባልተሟላ እና በተሳሳተ መረጃ ላይ በተመሠረተ የተዛባ አስተሳሰብ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በየራሳቸው አመለካከት በመተንተን ያሰራጩት ወሬ በተለይ ምእመናንን እያደናገረ ነው፡፡

በፈቃደ እግዚአብሔር ተመሥርቶ እስከአሁን የደረሰውን የማኅበረ ቅዱሳንን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማደናቀፍና በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ የማኅበሩን መልካም ገጽታ ለማጉደፍ የሚንቀሳቀሱ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታዛ ሥር የተሸሸጉት አጽራረ ቤተ ክርስቲያንም፤ ማኅበሩ የተዛባው አሉባልታ መሪ እንደሆነ አድርገው መሠረተ ቢስ ቅስቀሳ እያናፈሱ ነው፡፡

አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ የተሰጠውን ከባድ ሓላፊነትም በቁርጠኝነት እንደሚወጣና የቤተ ክርስቲያንን አጠቃላይ ችግሮች ለማስወገድ ቅዱስ ሲኖዶሱን እና ምእመናንን ይዞ እንደሚሠራ እናምናለን፡፡ ሆኖም የቅዱስ ሲኖዶሱን ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ ተከትሎ በሚናፈሱት መሠረተ ቢስና የተዛቡ ቅስቀሳዎች ምእመናን ግራ እንዳይጋቡ ለተሰየመው ቋሚ ኮሚቴ ጥርት ያለ የአገልግሎት ጉዞ እና ስኬታማ የሥራ አፈጻጸም ያመች ዘንድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየወቅቱ ያለውን እንቅስቃሴ በማሳወቅ አስፈላጊውን መረጃ መስጠት ይጠበቅባ ታል፡፡ ምእመናን ተግባራዊ ተሳትፎአቸው የበለጠ ተጠናክሮ፤ ችግሮችን በመጠቆም፣ መፍትሔ በማመላከት፣ ሞያዊ የምክር አገልግሎት በመስጠት፣ ወዘተ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ በማበርከት በቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ አህጉረ ስብከት፣ ወረዳ ቤተ ክህነት፣ በየአጥቢያው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሰበካ ጉባኤያት በየደረጃው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አካላትና አገልጋዮች ሁሉ፤ ለተሻለ ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓትና ውጤታማ አሠራር በቁርጠኝነት ለለውጥ መነሣታቸው አስፈላጊ ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔን ተቀብሎ መረጃ በመስጠት፣ ውሳኔውን በማስፈጸም ንቁ ተሳታፊ መሆን ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ተግባራዊነት ለማረጋገጥ የየድርሻችንን እናበርክት፡፡


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)