July 15, 2009

በመንግሥት አደራዳሪነት ዝግ ስብሰባ እየተደረገ እንደነበረ ታወቀ

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 15/2009)
ለብዙ ቀናት በመስማማትና ባለመስማማት መካከል ሲንከባለል የነበረው አጀንዳ በአባቶች መፈረሙን ተከትሎ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሁለት በመከፈላቸው ይህንኑ ለአንዴም ለመጨረሻውም እልባት ለመስጠት ዛሬ በመንግሥት ባለ ሥልጣናት ሰብሳቢነት የተጠራ ስብሰባ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ (ከሰዓት በሁዋላ) መካሄዱ ታውቋል። ስብሰባው ይህንን ዘገባ እስካዘጋጀንበት ጊዜ ድረስ የቀጠለ ሲሆን ውጤቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ አልቻልንም። የፓትርያርኩ ቡድንም ሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ አባቶች በሌላ በኩል በገቡት ፍጥጫ አንዱ የሌላውን ቁጥር ዝቅ ለማድረግ አድፍጠው እየሠሩ ነው ተብሏል። የዚህ ስብሰባ ውጤት ትልቅ ትርጉምና ወሳኝነት እንደሚኖረው ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትናንትናው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትርት በረከት ስምዖን መንግሥት ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተለ መሆኑን ተናግረዋል። በረከት ለቤተ ክርስቲያን ጤናማ አመለካከት ከሌላቸው ባለስልጣናት መካከል አንዱ መሆናቸው መዘገቡ ይታወቃል።
የስብሰባውን ሂደትና ውጤት እንደደረሰን እናቀርባለን።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

2 comments:

orthodoxawit said...

ፍኖተ ዘኢይሃልቅ

Anonymous said...

ሳይነገር የታወቀ ሳይታለም የተፈታ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መንግሥት በእጁ ካላደረገ ህልውናው ከዜሮ በታች እንደሆነ ሳይነገር የታወቀ ሳይታለም የተፈታ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተለየው መንግሥት በዚያች በቅድስት ምድር ላይ ለአንዲት ቀን እንኳን አያድርም። ለዚህም ነው መንግሥት በሩን ቆልፎ ድርድር የጀመረው። በእርግጠኝነት መንግሥታችን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተጸጽቶም አያውቅ ወደፊትም አይጸጸትም፤ በብዙ ሚድያ ሃይማኖታችንን ሲያጣጥሉ የነበሩም ሆኑ አሁን በሥልጣን ወንበር ላይ የተቀመጡት ባላሥልጣኖች ለሃይማኖታችን እንደማይገዳቸው ከልቦናቸው ሌላ አንደበታቸው ብዙ ጊዜ ፈር ስቶ ተደምጧል። በብዙዎች የተሳሳተ አመለካከት ሃይማኖታችንን ለአገራችን ለኢትዮጵያ ለውድቀቷ ምክንያት ያደርጓታል፤ ለረሐብና ለችግርዋም ተጠያቂ አድርገው ይፈርጇታል። አምላክ በውስጧ እንደሌለ እና ኋላ ቀር የሆነ አካሄድ ነው የምትሄደው ያሉን ሰዎች ዛሬም የፖለቲካው ዋነኝ አቀንቃኞች ናቸው። ታዲያ ምን ተገኝቶ መንግሥት በሩን ዘግቶ ስብሰባ ጀመረ? በእርግጠኝነት ከአባ ጳውሎስና ከተከታዮቻቸው ወይንም ከሲኖዶስ አቋም ተከታዮች የትኞቹ ይሻሉኛል በማለት ለስብሰባ ተቀመጠ፤ ዝግ ችሎት ያዘ እንጂ ይህቺ ታሪካዊ ሃይማኖት በምንም ምክንያት መጥፋት የለባትም በሚል ቁጭት አይደለም። የሆኖ ሆኖ ለጊዜው የተፈቀደልን መስማት ብቻ ስለሆነ ምን እንደሚሉ ደግሞ እንስማ እንጂ መፍትሔው መንግሥት እንዳልሆነ አጠራጣሪ አይደለም። እኩል ለሁለት የተከፈለ ሲኖዶስ ያለን ይመስለኛል። እንደ ፈርዖን ልብ የደነደነውን፤ እውነትን ደብቆ በሐሰት መንገድ ያለውን ቡድን ልዑል እግዚአብሔር መልሱን ይስጥልን።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቅሟን ማሳየት ብትችልና የሃይማኖት መሪዎቿ ለመንግሥት ሁለመናቸውን ባያስረክቡ እንዲሁም ለትንሽ ጥቅም ባይደለሉ ኖሮ ማን ከላይ ማን ከታች እንደሚሆን ግልጽ ነበር። አሁን ግን የተገላቢጦሽ ሆነና ሃይማኖታችንን የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲሰድቡብን ዝም በማለታችን እንደ ፈሪ ተቆጠርንና መጫወቻ ሆንን። መንግሥት ግን በአፉ ይሳደብ እንጂ ያለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምንም መሆን እንደማይችል ሲያውቀው ለዝግ ስብሰባ ተቀመጠ። መልሱን አብረን እንስማው።

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)