July 14, 2009

የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ዛሬ ማክሰኞም ይቀጥላል


(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 14/2009)

የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ዛሬ ማክሰኞ በበዓለ ቅድስት ሥላሴ ዕለትም ይቀጥላል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ደጀ ሰላም ያነጋገረቻቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንደተናገሩት “ቅዱስነታቸው ቢሰበስቡም ባይሰበስቡም ስብሰባው ይኖራል፣ ውሳኔም እናሳልፋለን” ብለዋል። “ታዲያ እንደዛ ከሆነ ትናንትስ እንዳትወስኑ ያደረጋችሁ ምንድር ነው?” ለተባሉት ሲመልሱ “ችግሩን በስምምነት ለመፈጸም ከመፈለግ” የመጣ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትናንት ሰኞ ስብሰባ በሕመም ምክንያት ሳይሳተፉ የቀሩት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ዛሬ ማክሰኞ እንደሚገኙ ምንጮቻችን ገለጹ። በመልካም ሥነ ምግባራቸው፣ በሐዋርያዊ አቋማቸው፣ ለቤተ ክርስቲያናቸው ባላቸው ፍቅርና ትጋት እንዲሁም ጀግንነት በብዙዎች ዘንድ የሚመሰገኑት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ባላፈው ሳምንት የተደረገውን ስብሰባ መምራታቸው ይታወሳል። አረጋዊው አባት በዛሬው ስብሰባ ላይ መገኘታቸው ውጤቱን ምናልባት ከትናንቱ የተሻለ ሊያደርገው ይችላል የሚል ተስፋ ጭሯል።

ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት ወር ባደረገው ስብሰባ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች ምክንያት ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር አለመስማማት ውስጥ በመግባቱ ፓትርያርኩ ከሥልጣናቸው በላይ ቅ/ሲኖዶሱ ያቋቋመውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊያግዱ ችለዋል። ቅ/ሲኖዶሱ ይህንኑ ተከትሎ ዕገዳውን በመሻር የበላይ መሆኑን ማሳየት ሲገባው ወደ ታች ዝቅ ብሎ ፓትርያርኩን በመለመን ላይ ይገኛል።

በርግጥም ስብሰባው ዛሬ የሚቀጥል ከሆነ የሚነጋገርባቸው አጀንዳዎች እንደ ሰሞኑ ሁሉ በፓትርያርኩ የሥልጣን አያያዝና አስተዳደር ድክመት ዙሪያ እንደሚሆን ይጠበቃል።
++++++++++++++++++
መልካም ምክር (ምክር ሠናይት) ከአንዱ ደጀ ሰላማዊ የተበረከተ

እግዚአብሔርን የሚያውቅ ሰው ስለ እምነቱ ፈሪ አይደለም። በተደረገው ውሳኔ ውስጥ እግዚአብሔር አለበት ማለት አልደፍርም። እግዚአብሔር ሰውን ፈጥሮ ሕሊናንም አብሮ ሰጥቶታል። ሕሊናው እውነት ለማይስማማው ሰው ተገዥ በመሆን ዝምታን ለመረጠ ተሰብሳቢ ከማዘን ሌላ ምንም አይባልም። ሥጋን መግደል የሚቻላቸውን አትፍሩ ይልቅስ ሥጋንም ነፍስንም ማጥፋት የሚችለውን እግዚአብሔርን ፍሩ የሚለውን ጥቅስ ወደፊት ማን ይሆን ደፍሮ የሚጠቅሰው። መንግሥት ታዛቢ ሆኖ የውስጡን በውስጡ ይዞ ቢቀመጥም ይኼንን እውነታ ሸሽገው ምንም እንዳልተፈጠረ ጆሮ ዳባ ልበስ ላሉትም ሆነ ላሰኙት ፍርድ የሚያውቅ መንፈስ ቅዱስ የፈረደ ዕለት እንዴት ይኮን ይሆን!! ዛሬ ደስ የተሰኛችሁ እና ነገም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወትሮው ለመዝረፍ ለተዘጋጃችሁ ሁሉ የጌታ መለስ የምትመጣበት ዋዜማ ላይ እንዳላችሁ እወቁት።
የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ በሚለው መርሆ የጥፋት ተባባሪ የሆናችሁ ሁሉ አሁን ወደ ማስተዋላችሁ ተመለሱ። የዛሬ ተሰብሳቢዎችም ላይሆናላችሁ ነካክታችሁ፣ ላትጨርሱት ወጥናችሁ፣ ላትገፉበት ጀምራችሁ ጉድ ሠራችሁን። አባታችን አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ሃምሳ ሰው በምድሪቱ ላይ ብታገኝ አትምርልኝምን በማለት ጀምሮ አሥር ብታገኝስ ብሎ ጨረሰ። ዛሬም በዘመናችን እንኳን ጥቂት ሰው ሊገኝና አንድ ሰው እንደ አብርሃም ያለ ተገኝቶ ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገር ጠፋ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በውጭ ባሉትማ ለመፍረድ ምን ገዶኝ እንዳለው እኛም ምን ገዶን እያልን መፍረድ ጀምረናል። የፈረድነውን ግን የተቀመጡበት ወንበር የቅዱሳን ወንበር በመሆኑ ነው። ትናንት የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እና የቅዱስ ጳውሎስን በዓል ባከበርን ማግስት ገድላቸውን የተረክን ሁሉ የመሥዋዕትነቱ በሩ ሲከፈት እንደ ጴጥሮስ የሚሆን አንድም ጠፋ። ጴጥሮስ ጌታን ካደው ለማለት አንደኞች ነበርን፤ ዛሬስ እኛ ማንን እየካድን ነው?
በመጨረሻም ልዑል እግዚአብሔር ሆይ ይኼን ጸሎት ስማን እያልን እንማጸንኻለን፦ በምድር ላይ ዳግም ዮሴፍ የሚባል ሰው ይከሰታል ብሎ የማይጠብቅና ተስፋውን ሙሉ ለሙሉ ያሟጠጠ፤ አፈር ምሶ ባይቀብረውም የልጆቹን ቃልና የተቀዳደደ የዮሴፍን ልብስ ተመልክቶ እርሙን ያወጣ ያዕቆብ ከዘመናት በኋላ የሚወደውን ልጁን አግኝቶ ዮሴፍንና ልጆቹን መርቆ በሰላም እንዳንቀላፋው እንደ ያዕቆብ ለእኛም ተስፋችን ተሟጠጠ ስንል እና አለቀ አከተመ ብለን ስናወራ የምስራቹን ቃል አንተ በወደድከው ቀን አሰማን። አቤቱ የሆነብንን አስብ ከማለት ሌላ እኛም ጸሎት የለንምና ልመናችንን ስማን።

July 14, 2009


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)