July 24, 2009

ፓትርያርኩ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ኃላፊዎችን ሰበሰቡ፤ መመሪያ ሰጡ

• መንግሥት ገለልተኛ ባለመሆኑ እየተወቀሰ ነው፣
(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 24/2009)
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ከሥልጣናቸው በማንሳት አስተዳደሩን ጠቅልለው የያዙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ትናንት ሐሙስ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችን፣ ፀሐፊዎችንና ሌሎች ሃላፊዎችን በመሰብሰብ መመሪያ ሲሰጡ መዋላቸው ተሰማ።


በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ለግማሽ ቀን በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞችም እንዲገኙ የተደረገ ሲሆን በዚህ መልክ ፓትርያርኩ የሀገረ ስብከቱን ሃላፊዎች የመሰብሰብ ልምድ እንዳልነበራቸው ታውቋል። ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከስልጣናቸው ከወረዱ በሁዋላ አውሮፓ ውስጥ ትምህርት ላይ የሚገኙትን ቀሲስ ፋንታሁን ሙጬን በሥራ አስኪያጅነት የመደቡት ቅዱስ ፓትርያርኩ እርሳቸውን ለማስተዋወቅ በሚል በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ መገኘት የመረጡት “ለማስፈራራት እና የአቡነ ሳሙኤል ደጋፊዎችን ደግሞ ለማናደድ” መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። መጪው የመስቀል በዓል እንደከዚህ ቀደሙ በድመቀት እንዲከበር ቅዱስነታቸው በዚሁ ስብሰባ ላይ መመሪያ መስጠታቸውም ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅዱስ ሲኖዶስ ከቅዱስ ፓትርያርኩ በገጠመው ሁነኛ ፈተና ምክንያት ችግር ላይ በወደቀባቸው ባለፉት ሁለት ወራትና በችግሩ አፈታት ወቅት መንግሥት ገለልተኛ ከመሆን ይልቅ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር በመወገን መቆሙን የሚቃወሙ ሰዎች ሐሳባቸውን በማቅረብ ላይ መሆናቸው ታወቀ። እነዚሁ ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው አንዳንዶቹም በመንግስት ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች እንደሚናገሩት መንግሥት በዚህ ግርግር ወቅት ገለልተኛ ሆኖ መቆም ሲገባው ድንበሩን በማለፍ የአቡነ ጳውሎስ ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሆኑን አጥብቀው ተከራክረዋል። በተለይም የደህንነት ክፍሉ በፍፁም የተሳሳተ መረጃና አቅጣጫ የአቡነ ጳውሎስ ደጋፊ ሆኖ መዝለቁን የሚናገሩት እነዚሁ ወገኖች መንግስት ይህንን ጉዳይ እንዲያጣራ በመጠየቅ ላይ ናቸው ተብሏል:፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)