July 24, 2009

ጉዞ ወደ እስክንድርያ በድጋሚ? እንዴት ተደርጎ!!!

(ደጀ ሰላም፣ ጁላይ 23/2009)
የተወደዳችሁ ደጀ ሰለማውያንና ደጀ ሰላማውያት፣
አንድ ጦማሪ ወዳጃችን ‹‹ማርቆስ አባታችን እስክንድርያ እናታችን›› ብለን ወደ ቀደመው ድንኳን እንሂድ? ብለው መጣጥፍ ማቅረባቸው ይታወሳል። በዚሁ መነሻነት ሁልጊዜ “ጦማሪያችን” ብርሃናዊት በበኩሏ የሚከተለውን ጽሑፍ ልካልናለች። ሁለቱም ጸሐፍት የሚያነሷቸው ሐሳቦች የግላቸው እንጂ “ደጀ ሰላም ተቀብላ ያጸደቀችው” እንዳልሆነ በማስታወስ ወደ ምንባቡ እንጋብዛችሁዋለን።
ቸረ ወሬ ያሰማን
+++++++++++++++++
ጉዞ ወደ እስክንድርያ በድጋሚ? እንዴት ተደርጎ!!!
(ከብርሃናዊት )

እስክንድርያ፡ ከአትናቴዎስ ማረፍ በሁዋላ፡ እናታችን ሆና አታውቅም፡፡ እውነተኛ እናትነትዋ፡ በደጋጎቹ በነቄርሎስ፥ በነዲዮስቆሮስ ጊዜ አብቅቶዋል፡፡ ከአትናቴዎስ ስደት በሁዋላ መተካት የጀመሩት የእስክንድርያ ጳጳሳት ሁሉ ኢትዮጵያንና ቤተክርስቲያኑዋን በሁለት ቢላዋ ሲበሉዋት ነው የኖሩት፡፡ ቀድሞ፡-

• የኢትዮጵያውያንን ቅድመ-ታሪክ የያዙ መሕፍት ሁሉ ከምድረ ኢትዮጵያ ጠፍተው፡ በምትኩ ዐረብኛና የግብውያንን ገድል የሚተርክ መሓፍት ብቻ እንዲበዙ በማድረግ፡

• ግዕዝኛን አጥፍቶ፡ በምትኩ፡ ዐረብኛ ብቻ እንዲተካ ለማድረግ፡ ብዙ የቤተክርስቲያን የግዕዝ መሕፍትን፡ (የተወሰኑ የሃይማኖት መሕፍት ብቻ ሲቀሩ) የታሪክ፥ የፍልስፍና፥ የዕደ ጥበብ፥ የትውፊት መጻሕፍትን በደካማ ነገሥታት እያደሩ በማስጠፋት፡

• እንደ አፄ ዐምደ ጽዮን የመሳሰሉ፡ የዚህን ነገር አደገኛነት የተረዱ ነገሥታት፡ ወደቀደመ ሥርኣት ለመመለስ ያደረጉትን እርምጃ አምርሮ በመቃወም፡ ታሪካቸውን ገልብጦ በመጻፍና ያለስማቸው ስም በመስጠት፡ “ያባታቸውን ሚስት ያገቡ” በማለት፡ ኢትዮጵያውያን የነርሱን ፈለግ እንዳይከተሉ በመከላከል፡ ሌሎች ነገሥታትም የርሱን ፈለግ ሲከተሉ፡ ወይም ቀድሞ የተከተሉ ከነበሩ፡ “በዘመኑ ንጉሥ እከሌ የግብን ጳጳስ በመቃወሙ እግዚአብሔር ተቆጥቶ ረሃብ ሆነ” የሚሉ እንቶ ፈንቶ ተረቶችን በመፍጠር፡ የኢትዮጵያውያን ምዕመናንን ሥነ-ልቦና በፍርሃት በመያዝ፡

• ከዚህም አልፎ ተርፎ፡ “ሥጋ በመለኮት ፀጋ ሲበቃ ሊሰወር አይችልም፡ ስውር ባሕታዊ የሚባል ነገር የለም፡ ክርስቶስም ረቂቅ መለኮት ቢኖረውም፡ ሥጋውን ሊያረቅቀውና ስውር ሊያደርገው አይችልም” እያሉ ኢትዮጵያውያንን ለዘመናት ከኖሩበት ክርስቶሳዊ እምነታቸውና ሥውር ባሕታውያንን የማናገር ፀጋቸው ለማላቅቅና፡ በምትኩ፡ የነርሱን ሁለት ባሕሪ የመሰለ አስተምህሮ እንዲቀበል በማስገደድ፡ በ5ኛው ክፍለ ዘመን በዋልድባ ላሉ መነኮሳትና ሊቃውንት መበታተንና መጨፍጨፍ ምክንያት በመሆናቸው (ዛሬ የግብጽ ኦርቶዶክስ “ተዋሕዶ” ቤተክርስቲያን እያልን ስንጠራቸው ይገርመኛል፡፡ የሃይማኖት ቃላቸው በተግባር ሲገለጥ ምን እንደሆነ ስለማያውቁ፡ በኢትዮጵያ ምድር ከባሕታውያን ጋር ሲጣሉ ኖሩ፡፡ ለመሆኑ፡ ግብውያን “ሥላሴ በስም ሦስት ናቸው እንጂ በአካል ሦስት አደሉም” እንደሚሉ ስንቶቻችን እናውቃለን? የኛ ቤተክርስቲያን ግን፡ በተረዳ ነገር “አብ የራሱ የሆነ ፍጹም አካል አለው፡ ወልድ የራሱ የሆነ ፍጹም አካል አለው ፡መንፈስ ቅዱስ የራሱ የሆነ ፍጹም አካል አለው፡ ወልድ ሰው የሆነው በተለየ አካሉ ነው” ብለን ስናምን፡ ግብጻውያኑ ግን አካል ያለው ወልድ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ የአባ ሕርያቆስን ቅዳሴ የት እንዳገቡት እንጃ፡፡ ምናልባት አባ ሕርያቆስ ግብጦች በሁዋላ በሓሰት እንዳጻፉት ሳይሆን፡ በዋልድባ የነበረ ኢትዮጰያዊ ነው የሚለው የአባ ተስፋ ሥላሴ argument ትክክል ሆኖ ይሆን? ይመስላል!)

• ኢትዮጵያውያን፡ ከማንም በፊት፡ በመልከ-ጼዴቅ በኩል የክህነት ፀጋ ተቀብለው ሳለ፡ ሁዋላም፡ በታቦተ ጽዮን መምጣት ጊዜ፡ በሌዋውያን ካህናት በኩል “እስራኤል ዘነፍስ” ተብለው፡ ክህነታቸውን አጽንተው፡ የክህነት ግምጃ ቤት ሆነው ሳለ፡ ግብጻውያኑ ለነርሱ ዐረባዊ ተንኮል እንዲያመቻቸው፡ መልከ ዴቅንና ከንግስተ ሳባ በፊት ያሉ የኢትዮጵያ ካህናትን አስደናቂ መንፈሳዊ ኑሮና እግዚአብሔራዊ ትምህርት የሚዘክሩ መሕፍት እንዳይነበቡ በማውገዝና፡ “የማንም ደብተራ የጻፋቸው ድግምቶች” የሚል ስም በማሰጠት፡ ከኢትዮጵያ ምድር ወጥተው በሜሮዌና ኑብያ እንዲሰደዱ በማድረግ፡ ኢትዮጵያውያን ከሳባ በፊት ያለውን ታሪካቸውን እንዳያውቁ በተቻላቸው መጠን በመታገል፡

• እግዚአብሔር “ኢትዮጵያውያኑ የሰጠሁዋቸውን ሃብተ-ክህነት ንቀው፡ ባላልኩዋቸው መንገድ ሄደውብኛልና፡ ትቀጣቸው ዘንድ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ፡ ነገር ግን ጠላቶቻቸውን (ዐረባውያን ግብጦችንና ሌሎች ስደተኛ ክስርቲያን ነን ባዮችን) እንጂ እነርሱን አትንካ” በማለት ለዮዲት ጉዲት አይሁዳዊ ቅድመ አያት የቅጣትን ፈቃድ በመስጠቱ፡ ትልቅ ችግር በኢትዮጵያ ተከስቶ፡ ኢትዮጵያን እርስ በርስ ብቻ ሳይሆን ከአምላክ ጋር ጭምር እንዲጣሉ ምክንያት በመሆን፡

• በኢትዮጵያ የነበሩና፡ በሰላም ወደ ክርስትና መቀላቀል የጀመሩ ቤተ እስራኤላውያንን፡ “ሰቃልያነ እግዚእ” እያሉ ነገሥታቱ ሁሉ እነርሱን ለማጥፋት እንዲተባበሩ በመቀስቀስና፡ ነገሥታቱ እምቢ ካሉም “የክርስቶስ ወዳጅ አይደለህም” እያሉ ከሌሎች ስደተኛ የሮምና የሌሎች የውጭ ሃገር ተወላጅ ክርስቲያኖች ጋር በመተባበር፡ ቅስቀሳ በማካሄድ፡ በኢትዮጵያ ምድር ቤተ እስራኤላውያንን እንደማርያም ጠላት እንዲታዩ በማድረግ፡

• በዚህ ድርጊታቸው ተከፍቶ፡ ከበዙ ሙከራ በሁዋላ፡ ጥምቀቱን ሁሉ ትቶና ማተቡን በጥሶ ወደሁዋላ እየተመለሰ ጭምር፡ ራሱን ለማደራጀት የበቃው የቤተ እሥራኤልና የሌሎችም የተገፉ ኢትዮጵያውያን ጦር፡ በዮዲት ጉዲት አማካኝነት ተነስቶ፡ ዐረብ-ነክ የሆኑ ቅሪቶችን ለማጥፋት በመነሳቱ፡ በሰበቡ ለብዙ የቤተክርስቲያን ሃብት መውደምና ብዙ ካህናት መታረድ ምክንያት በመሆን፡

• ኢትዮጵያ በሕገ-ልቦና እና በሕገ-ኦሪት ጸንታ የነበረች በመሆንዋ፡ ሊቃውንቶችዋ ሁሉንም ከሕገ-ወንጌል ጋር አስተባብረው በሚያስተምሩበት ወቅት፡ “የምታስተምሩት ኑፋቄ ነው” በማለት በመቃወምና፡ ልክ እንደዘመኑ ተሃድሶ መናፍቃን “ገና ከኦሪት ያልተላቀቃችሁ” በማለት ትልቅ ረብሻ በማስነሳት፡ ከ700 በላይ መተኪያ የሌላቸው ሊቃውንት፡ በአክሱም ዘመነ መንግሥት፡ በኢትዮጵያ ምድር በማስጨፍጨፍና በማሳደድ፡

• ኢትዮጵያዊው የሥዕል አሳሳል ዘይቤ ጠፍቶ፡ በምትኩ በነርሱ መልክ ዐረባዊ መልክ ያለው ሰው እንዲሳል በመጎትጎት፡ እምቢ ካሉም፡ ኢትዮጵያውያን ሰዓሊዎችን ምላስና እጃቸውን ከነገሥታት ጋር በመተባበር በማስቆረጥ፡

• “የብሕትውና ሁሉ ጀማሪ አባ እንጦንስ ነው” በማለት ያለማዕረጉ ከሚገባው በላይ ማዕረግ ሰጥተው፡ በኢትዮጵያ ላይ ድንቅ ተአምራትን ያደርጉ የነበሩና ብዙ ገዳማትን በኢትዮጵያ ዙርያ ክልሎች ያቀኑ ናዝራውያን ባሕታውያንንና ካሕናትን በማሳደድ፡ ክርስቶስን ሲወለድ እጅ መንሻ የሰጡትንና ከነርሱ ተምሮ የመነነውን ሁሉ እንደሌለ በመቁጠር፡ እስከዋልድባ በማሳደድና የአክሱምን ቤተ ክህነት ከእጃቸው ፈልቅቆ በመውሰድ የኢትዮጵያን ቤተክህነት ለዘላለሙ በመለወጥ (የኢትዮጵያ አብነት ትምህርት ቤት ግን ኢትዮጵያዊውን ሥርዓት በመጠበቅ፡ የቤተክህነቱን ያህል ሳይበገርላቸው እስከዛሬ በእግዚአብሔር ቸርነት ዘልቆዋል፡፡)

• ንጉሥ፡ ሁሉ “አል…” በሚል ቅጥያ እንጂ “አፄ” በሚል ቅጥያ እንዳይጠራ ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ በመሥራት: ለዛሬዎቹ አረማውያንና ዐረባውያን ወገኖቻቸው “አልነጃሺ የተባለ ሙስሊም ንጉሥ ነበር”… ቅብርጥሶ የሚል የፈጠራ ታሪክ መንገድ በመክፈት፡

• ለዚህ ጥፋትን አዘል አገልግሎታቸው፡ ሓዋርያዊነቱ ቀርቶ ንግድ እስኪመስል ድረስ፡ ነብዩ በትንቢቱ እንዳለው፡ ኢትዮጵያውያንን ለግብጽ ጉስቁልና በመንዳት፡ ብዙ ወርቅና ብር እጅ መንሻ ከኢትዮጵያውያኑ ሲጎርፍና ሲቸገሩ፡ “ይህ መንፈሳዊ አገልገሎት እንጂ ሥጋዊ አደለም” ብሎ እንኩዋን ሃይ ያለ አንድም ግብጣዊ ክርስቲያን ባለመኖሩ፡ እንዲያውም፡ እጅ መንሻው በድብቅ “እከሌን ትተህ እከሌን አንግሥልኝ” ለሚል መማጠኛ ጭምር እንዲውል በመፍቀድ፡ የለየለት የዛሬውን ቤተ ክህነትና መንግሥት ትስስር የሚመስል የማፊያ አሠራር በመንደፍ፡ ነገሥታቱን በሥልጣን ሽኩቻ በማባላት፡ እነርሱ ግን በመሃል ቤት ወርቃቸውን በማጋበስ፡

• ከዚህም የባሰው ደግሞ፡ ምንኩስናቸውን ያፈረሱ እና አንዱ ደግሞ ሃይማኖቱ እስላም የሆነ ከአንድም ሁለት ሦስት ጋጠወጥ ግብጣውያን ጳጳሳት፡ ወደኢትዮጵያ መጥተው የቻሉትን ያህል ሃይማኖታዊ ቅርስና ወርቅ ዘርፈው ሲሄዱ፡ ግብጥ ላይ የሚያወግዛቸው እንኩዋ አለመኖሩ፡ ይልቁንም “ደግ አረግህ ልጄ” የሚል በሚመስል አኩዋሁዋን ምንም ሳይባሉ ኑሮዋቸውን እንዲቀጥሉ በማድረግ


አሁን በዘመናችን ደግሞ፡-


• በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያን ይዞታ በመቀናቀንና መነኮሳቱን በማስቸገር

• አንድ ተአምር መሰል ነገር የተሰራላቸው እንደሆን፡ በየኢንተርኔቱ በየመጽሐፉ በየምናምኑ በማስነገር፡ ውስጠ-ኑፋቄ የሆነ አደገኛ ትምህርታቸውን በተሃድሶዎች በኩል በማስፋፋት- አዎን! ያንን እስኪበቃኝ ታዝቤያለሁ፡፡ ተመሳስለው ቤተክርስቲያን የገቡ ተሃድሶዎች በሙሉ ወይ አፍቃሬ-ግብጽ፡ ወይ አፍቃሬ-ግሪክ ናቸው፡፡ ስብከታቸውን፡ አንድምታቸውን፡ መጽሓፋቸውን ማዳነቅና የኢትዮጵያውን ግዕዛዊ ስብከትና አንድምታ ደግሞ እንከኑን በማብዛት፡ የምእመናንን ልብ መሸርሸር የዕለት ተዕለት ሥራቸው ነው፡፡ ያም፡ እውነት ግብጽን ወይም ግሪክን ወደው ሳይሆን፡ ኢትዮጵያዊውን ትምህርትና ትውፊት ለመደምሰስ፡ በቅድሚያ እርሱን የማይተካ፡ በስም ግን ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ሥርዓት ወደቤተክርስቲያን ማስገባት እንዳለባቸው፡ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው፡፡ (በሚያሳዝን ሁኔታ፡ የዘመኑ መንፈሳዊ መጽሓፍ ጸሓፊ ሁሉ፡ ያለ ሽኖዳ አባት ያለ ግብጽ ገዳማት የማያውቅ ይመስል፡ “አስቄጥስ”…. “አስቄጥስ”….. “ሽኖዳ”…. “ሽኖዳ” የሚል መጽሓፍና ኅትመት ብቻ በማባዛት፡ በኢትዮጵያ የሕይወት ቃልን እየተናገሩ፡ ግን ሰሚ አጥተው እያለፉ ያሉ ባሕታውያንንና ያብነት ትምህርት ቤት መምህራንን ትምህርትና ቃለ ምዕዳን እየተከታተሉ በጽሑፍ በማስፈር ፈንታ፡ የቲዮሎጂ ምሩቅና ጋዜጠኛ ሁሉ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተከርስቲያን ተከታይ እስኪመስል ድረስ፡ ቅኔያዊውና ወዝ ያለው የኢትዮጵያውያን ቃለ እግዚአብሔር ከትውልዱ ጆሮ እንዳይደርስ ደንቃራ እየሆነ ይገኛል፡፡ በግብጽ አስቄጥስን አስቄጥስ ያደረጉዋት፡ ቁስቁዋምን ቁስቁዋም ያደረጉዋት እኮ ቀደም ሲል የነበሩ ኢትዪጵያውያን መናንያን ነበሩ እንጂ ሌላ አደለም!)

• በግብጽ ስደት ወቅት፡ እመቤታችን በኮቲባና ትዕማን የደረሰባትን እንግልት፡ በልዋጩ ለኢትዮጵያውያን ለመስጠት በመዳዳት፡ “ግብጾች እንዲህ አደረጉ የሚለው የኢትዮጵያውያን ፈጠራ ነው” በማለት ራሳቸውን በትዕቢት በመኮፈስ፡ ምግባር ጉድለታቸውን ሁሉ በኢትዮጵያውያን ላይ በማላከክ

• የእግዚአብሔር ካህን ዮቶርን (የሙሴ አማትን) ለሙሴ በሕገ- እግዚአብሔር ፈንታ ጥንቆላን ያስተማረ እርሱ ነው በማለት፡ የአረማውያን ፈርኦኖቻቸውን ስምና ዝና ሳይቀር በካህኑ ዮቶር ፈንታ በመከላከል፡ በውዳሴ ማርያም ትርጉዋሜ እንዲገባ በማድረግ፡

• የቀስተ ደመና እና የባንዲራችንን ትስስር ለማስቀረት፡ በዚሁ መጽሓፍ ላይ፡ በቀስተ ደመናው ጎልቶ የሚታየው አረንጉዋዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ቀርቶ፡ ጎልቶ የማይታየውን በመውሰድ፡ የቀስቱ ቀለም ጥቁር፡ ነጭ፡ ቀይና ብጫ ነው በማለት፡ ከራሳቸው ባንዲራ ቀለማት ጋር ተጠጋግቶ ተተክቶ እንዲነበብ በማድረግ፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ፡ አረንጉዋዴ ቢጫ ቀይ የሆነውን የተለመደውን የኢትዮጵያውያንን ማተብ፡ በራሳቸው ባንዲራ ቀለማት በመተካት፡ ጥቁር ነጭ ቀይ በማድረግ፡ “ነጩ ሕይወት፡ ቀዩ የክርስቶስ ደም፡ ጥቁሩ የገሃነም ምሳሌ ነው” በማለት እንዳፈቀዳቸው ትርጉም በመስጠት ሲያቄሉን በመኖር፡ (ከማንኛውም ቀለም፡ ተለዋጭ ትርጉም መስጠት የሚቻል መሆኑን አንዘንጋ)

….ይህንና ይህን በመሳሰለው፡ ፈጽሞ የማንግባባባቸው የእስክንድርያዎች ዲስኩርና ውስጠ-ጠላትነት ምክንያት፡ ዳግም በግብጽ ቅኝ ግዛት እንድንገዛ ለተመኘህበት ደጀሰላም ንስሓ ግባ፡፡ የደጀ ሰላምን ጽሑፍ አንብቦ በልቡ የተመኘም ሁሉ ንስሓ ይግባ፡፡

እስክንድርያ አደለችም፡ ኢትዮጵያ ናት እናታችን፡፡ ትናንት አቦ አቦ ስንላቸውና ስንክባቸው የነበሩትን አባቶች፡ በሥራቸው ምክንያት ዛሬ መሬት ስናወርዳቸው፡ አለቃ አያሌው ታምሩ በመንፈስ እያዩ ምን ይሉ ይሆን? እውነተኛው ጠንቅ መቼ እንደጀመረና ምን እንደሆነ ግልጽ አድርገው ተናግረውት ነበር እኮ? እነ ንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ምን ይላሉ? እስክንድርያ ምን ያስኬደናል ቅኝ ግዛት ፍለጋ? ከላይ የተዘረዘረው የግብጻውያን ወንጀል ሁሉ ከሌሎች የኛ ስንፍናዎችና አላዋቂነት ጋር ተደማምሮ የት ድረስ እንዳዘቀጠን በደንብ የተረዱ፡ የአሁኑ ቤተ-ክህነት ችግርም እንዴት እንደሚፈታ በደንብ የሚያውቁ፡ እነርሱን የመሰሉ ሊቃውንት፡ ታሪክ አዋቂዎችና የክህነት ባለቤቶች እያሉ፡ እስክንድርያ የምንሄደው አል ነጃሺን ፍለጋ ነው ወይ? ወይስ አሁን ደሞ እጅ መንሻ አባይን አንደኛችንን አስረክበን ሌላ 1600 ዓመት ከግብጽ ውሃ ስንለምን ልንኖር ነው? ወይስ ዴር ሱልጣንን እጅ መንሻ እንስጥ? እግዚአብሔር ሌላ ግራኝ፡ ሌላ ዮዲት ያስነሳ ወይ? እሱ ነው ያማረን? ምን ችግር አለ? እኛ ብቻ ያማረንን እንግለጥ እንጂ እነርሱ እንደሆን ዝግጁ ናቸው- እንደጥንቱ ሊግጡንና ከቻሉ ሊያጠፉን የኛዎቹ ፍልስጤማውያን ራሳቸው አሰፍስፈዋል፡፡

መድሓኒቱን አፍንጫችን ሥር አስቀምጠን፡ ወንዝ ተሻግሮ የሰው ቤት መቀላወጥ፡ ያውም የማይመስሉንን ሰዎች ቤት መቀላወጥ፡ ራስን የመጥላትና የራስን ሊቃውንትን የመናቅ አባዜ እንጂ ሌላ ስም የለውም፡፡

ሌላውም የተዋሕዶ ልጅ ነኝ የሚል ሁሉ፡ ኢትዮጵያን ሳይሆን ግብጽን በኢትዮጵያ ላይ ከመስበክ መቆጠብ ይገባዋል፡፡ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ናት- ሥርኣቱዋና ከአምላክ የተቀበለችው አደራም 7 ቃልኪዳናት እንጂ አንድ ብቻ የሥጋ ወደሙ ቃል ኪዳን አደለም፡፡ ታቦትን፡ ግርዛትን፡ ጠበልን፡ ብሕትውናን፡ የተቀደሱ እንስሳትን መብላትን፡ ሥርዓተ መንግሥትን፡ የቀስተ ደመና ሰንደቅ ዓላማችንን፡ የቤተልሔምን ምሳሌያዊ ህንጸትና የንጹህ ስንዴ ሕብስት የመፈተት ምሳሌያዊ ሥርዓትን… ይህን ሁሉ ገና ለግብጾች ስናስረዳ መኖር የለብንም፡፡ የምንሰዋው ቁርባን እንኩዋ ተምሳሌቱ የኛ ምሉዕ እና ሦስቱንም ሕግጋት (ሕገ-ልቦና፡ ሕገ-ኦሪትና ሕገ-ወንጌል) አጠቃልሎ የያዘ ነው- ሁለቱን በተምሳሌትነት፡ አንዱን በአማናዊነት፡፡ እንደመናፍቅ “ዋናው ክርስቶስ ነው” እያልን መቅለጥ ካልፈለግን በቀር እስክንድርያ የሚያዞረን ጉዳይ የለም፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)