July 23, 2009

‹‹ማርቆስ አባታችን እስክንድርያ እናታችን›› ብለን ወደ ቀደመው ድንኳን እንሂድ?

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 22/2009)

እስካሁን ድረስ ቤተ ክርስቲያንን እየመሩ ያሉ ጳጳሳትን በተመለከተ በአማኙ በኩል ከመንፈስ ቅዱስ በታች የቤተ ክርስቲያን መሪና ጠባቂ የጳጳሳት ጉባዔ ቅዱስ ሲኖዶስ እንደሆነ ይታመን ነበር፡፡ ሰሞኑን በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል ሲካሄድ የቆየውና በፓትርያርኩ ላይ ግልጽ ተቃውሞ ባሰሙ ጳጳሳት ላይ የጉዳት ማድረስ ሙከራ ከተደረገ በኋላ ሐምሌ 10 በስምምነት ተጠናቀቀ የተባለው ስብሰባ ሂደት ግን የሚያመለክተው ከዚህ የተለየ ነው፡፡በአንዳንድ የቅዱስ ሲኖዶሰ አባላት በሆኑ ጳጳሳት ዘንድ እየታየ ያለው መከፋፈል፣ ለእውነት አለመቆም፣ ከቤተ ክርስቲያኗ ሕግና ሥርዓት ይልቅ ለፓትርያርኩ ሃሳብ ተገዢ መሆን፣ የአባቶችን መንፈሳዊ ዝቅጠት የሚያመለክት ሲሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ እንደምትመራ ለሚያምን እና ለሚመሰክር ምዕመን ሁሉ አንገት የሚያስደፋ ጥቁር የታሪክ ክስተት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ሌላ የጨለማ ዘመን ውስጥ እንደምትገኝ በገሀድ ያየንበት ወቅት ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የምትመራው በቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ፓትርያርኩ ራሳቸውን እንደ ጣዖት ከሕግ በላይ ካደረጉ፣ አንዳንድ ጳጳሳትም ይህን የሳቸውን ፍላጎት እና የራሳቸውን ጥቅም ለማሟላት ቅዱስ ሲኖዶስን ሕልውናውን ለማሳጣት የሚያውኩ ከሆነ ቤተ ክርስቲናችን ቅዱስ ሲኖዶስ አላት ብሎ መናገሩ በዲያስጶራ ‹‹ሕጋዊ ሲኖዶስ›› ነኝ እያለ ምዕመናንን ግራ ከሚያጋባው አካል አይለይም፡፡ እስካሁን ድረስ አባቶች አሉን፣ “ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል” በማለት ነበር በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የቆየንው፡፡ እንግዲህ ቤተ ክርስቲያኒቱ በውስጥም በውጪም የወንበዴዎች ዋሻ ከሆነች፣ ወዴት እንሄዳለን?

ከሰሎሞን ቀጥሎ እስራኤልን ይመራ ዘንድ በዙፋኑ የተቀመጠው ሮብአም በላያቸው የተጫነውን ቀንበር እንዲያነሳላቸው እና በመልካም አስተዳደር ሕዝቡን እንዲያገለግል ሲመክሩት አልሰማም ብሎ የአብሮ አደጎቹን ክፉ ምክር በመስማት በላያቸው ባለው ቀንበር ላይ የባሰ ሸክም እንደሚያጸናባቸው ስለተናገረ ህዝቡ ‹‹ሕዝቡ በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም፡፡ እስራኤል ሆይ ወደ ድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ አሁን የራስህን ቤት ተመልከት፡፡›› በማለት ወደየድንኳኖቻቸው ተመልሰዋል፡፡ ብዙዎችም ዛሬ ይህን በመሰለ የፓትርያርኩ ሕገ ወጥነት እና በአንዳንድ ጳጳሳት ደካማነት ‹‹እግዚአብሔር ሆይ የራስህን ቤት ተመልከት›› በማለት ወደ ሌላ ድንኳን ለመመልከት እየተገደዱ ነው፡፡

ኧረ ለመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን ከመንበረ ማርቆስ፡ ከእስክንድርያ መንበር ተላቃ ራሷን እንድትመራ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ነገሥታትና ሊቃውንት በ50 ዓመት ታሪክ ውስጥ እንዲህ ዓይነት አሳዛኝታሪክ ሲታይ ምን ይሉ ይሆን? ፓትርያርኩ እንደሮብአም የሚሰሙት ምክር የመሰሎቻቸውን ከሆነ፣ ለእውነት በቆሙ አባቶች ላይ በሕይወታቸው እስከ ማስፈራራት ድረስ ቀንበር የሚጫንባቸው ከሆነ ፓትርያርኩ እና መሰሎቻቸው ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት እንኳን መንፈሳዊው ብቃት ዓለማዊ ጥበብም ይጎድላቸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲናችን ለ1600 ዓመታት ማርቆስ አባታችን፣ እስክንድርያ እናታችን ብላ ነው በብዙ ውጣ ውረድ ያለፈችው እና እዚህ የደረሰችው፡፡ አሁን ግን የእረኝነት ኃላፊነታቸውን በዘነጉ ፓትርያርክና ጳጳሳት ያለ አባት እና ያለ እናት ሊያስቀሩን በቀን የበቀል ኃይልን፣ በሌሊት ጨለማት ተገን አድርገው ደፋ ቀና እያሉ ነው፡፡ ታዲያ እስራኤላውያን ወደየድንኳኖቻቸው እንደተመለሱ እኛስ አባትና እናት እንደሌለው ሆነናልና ‹‹ማርቆስ አባታችን እስክንድርያ እናታችን›› ብለን ወደ ቀደመው ድንኳን እንሂድ?
(አንድ ደጀ ሰላማዊ እንደጻፉት)

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)