July 29, 2009

በደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ በአስተዳደር ቦርዱና በአባቶች ካህናት የወጣ የአቋም መግለጫ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ሐምሌ ፲፱/፳፻፩ ዓ.ም. (July 26, 2009)
በደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ በአስተዳደር ቦርዱና በአባቶች ካህናት የወጣ የአቋም መግለጫ፦
(Read in pdf here)

በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁሐዋ.፳፥፳፷
ይድረስ፦ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ በሙሉ።
ጉዳዩ፦ የቅዱስ ሲኖዶስ ሉዐላዊነት መከበር ስለሚገባው እና ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት በተመለከተ።
መግቢያ፦

ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመባል የምትታወቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ እጅግ ሊስተዋል የሚገባው ሥራ አከናውናለች፤ ወደፊትም ለማከናወን ተዘጋጅታለች። ቃላት ሊገልጸው፣ አንደበት ሊተርከው፣ ሕሊና ሊያሰላስለው፣ አእምሮ ሊያወጣውና ሊያወርደው ከሚችለው በላይ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽማ የተሰጠች እምነትን፣ በአምላካችን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተዋጀችውን፣ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት የታነጸችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖትና ሥርዓት፣ ትውፊትና ቀኖናን በመቀበል፤ ለሃይማኖቷ ተቆርቋሪ፣ ለሥርዓቷ ተገዥ የሆኑ ካህናትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ዲያቆናትና መዘምራንን እንዲሁም ጠቅላላው ምእመንን በውስጧ በመያዝ ለተሠሩትም ሆነ ወደፊትም ለሚሠሩት አበይት ክንውኖች መሠረት መጣልዋ ከምንም በላይ ሊጠቀስና ሊዘከር የሚገባው አብይ ጉዳይ ነው።

በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሠረተቸውን እና ዋጋ የተከፈለባትን እምነት ከመናፍቃን እና ከከሀዲያን ጠብቀውና ተከላክለው በማቆየት ለእኛ ያስረከቡንን የሃይማኖት አባቶቻችንንና እናቶቻችንን አደራ ለመጠበቅና ለማስጠበቅ መዘጋጀት፤ የተቀበልነውንም ታላቅ አደራ ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ በሚኖረው ሒደት ብዙ ውጣ ውረድ፣ ብዙ ፈተና እና ድካም መኖሩ ሳይነገር የታወቀ ሳይታለም የተፈታ ነው። ሆኖም ግን የሃይማኖት መገለጫና ዋነኛው መንገድ በጠባቡ በር ማለፍ ስለሆነ ፈተናውን ተቀብሎ፣ መከራውን ችሎና ታግሦ የሰይጣንን ደባ እያፈራረሱ በድል መጓዝ አባቶቻችን ያለፉበት በመሆኑ እኛም በዚያው መንገድ ልናልፍ ግድ ነው። በመሆኑም ከቤተ ክርስቲያናችን ምሥረታ ጀምሮ በየትኛውም መልኩ የልዩነት ኅብረት ሳናደርግ የብፁዓን አባቶቻችንን ቡራኬ በመቀበል ዛሬ የደረስንበትን ሥፍራ ለማየት ችለናል።

መልእክት፦

እንደሚታወቀው የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥር ፲፫ እና ጥር ፳ ፲፱፻፺፱ ዓ.ም በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እና በካናዳ ቶሮንቶ የጳጳሳት ሹመት ሲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ በአገራችን በኢትዮጵያ የለም ፤ መንበሩም የመንበሩም ጠባቂዎች በምድረ አሜሪካ ይገኛሉ፤ በማለት ሃይማኖታችንና ሥርዓታችን ከሚፈቅደው ውጪ ሕጋዊ ሲኖዶስ በስደት ያለው ነው በማለት በቅድስት አገር ኢትዮጵያ ሲኖዶስ እየተባለ የሚጠራ አካል እንደሌለ አድርገው በተነሡት ሰዎች ላይ ይህ ሁኔታ በተፈጸመ ማግስት ያለማንም አነሳሽነት ትክክለኛው መንገድ የትኛው እንደሆነ በመረዳት ጥር ፳፭/፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ባወጣው አቋም ላይ ሲኖዶስ አንድ እንደሆነ፤ መንበሩም በቅድስት አገር ኢትዮጵያ እንደሆነ ለሕዝባችን አበክረን መግለጻችን የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በመልእክታችንም ሰዎች ይሰደዳሉ እንጂ አገር አይሰደድም፤ አገር እንደማይሰደድ ሁሉ መንበርና ሲኖዶስም አይሰደዱም፤ ስለዚህም እንዲህ ያለውን አካሄድ እንደ እምነታችን በፍጹም የማንቀበለው ነውበማለት መጥቀሳችን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ከማስጠበቅ አንፃር የበኩላችንን አደራ መወጣታችን እንደነበር ግልጽ ነው።
ቤተ ክርስቲያናችንም በቅድስት አገር ኢትዮጵያ የአስተዳደር ብልሹነት እንዳለ በመግለጽ በዚያው ቀንና ዓመተ ምሕረት ለቅዱስ ሲኖዶሱ መልእክቷን አስተላልፋለች። በመልእክቷም ቤተ ክርስቲያኒቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ በተቀመጠበት ወንበር ማድረግ የሚገባውን ሳያደርግ ቀርቶ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተለያዩ ፈተናዎች ሲቃጡ ዝም ብሎ ሁኔታዎችን በቸልተኝነት መመልከት አግባብ አይደለም። ታፍራና ተከብራ የኖረችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አቅጣጫ አለመቃኘት ቸልተኛነት ነውና ሊታሰብበት ይገባል። በመሆኑም ፍትህ ያልሰፈነበት፣ የአስተዳደር ድክመት የሚታይበት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ የበላይነት ያልተረጋገጠበት እና የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ቸል የተባለበት ሁኔታ በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ እየተንሰራፋ እና እየተንጸባረቀ የመጣ በመሆኑ እርምት ሊወሰድበት ይገባዋል በማለት መልእክታችንን ማስተላለፋችን የሚታወስ ነው። በመጨረሻም የአስተዳደር ችግር ተወግዶ አስተማማኝ ሁኔታ ሲፈጠር በብቸኛና በአንድ ሲኖዶስ ሥር ታቅፈን እምነታችንን እንደምናራምድ ቃል ስንገባ ለቤተ ክርስቲያናችን መፍትሔ ከሚፈልጉ ጋር አብረን ተሰላፊ በመሆን ይህን መላ-ቅጡ የጠፋ አካሄድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ እንሰለፋለን፤ የጅምራችን ስኬታማነት እና የሕልማችን ገሃድነት ቅርብም ባይሆን ሩቅ አይደለም በማለት ነበር።

ልዑል እግዚአብሔር ሁሉን በጊዜው ውብ አድርጎ ይሠራልና ትናንትና የቤተ ክርስቲያን ሉዐላዊነት ተደፍሯል፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተንቋል፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ፈርሷል፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ጠፍቷል፣ የሲኖዶስ የበላይነት ተዘንግቷል፤ በማለት እናሰማው የነበረውን ድምጽና እየጮህን ያለውን ጩኸት ዛሬ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል ያሉ ብዙኻን ብፁዓን ጳጳሳት፤ በየአብያተ ክርስቲያኑ ያሉ ካህናትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ዲያቆናትና ዘማርያን፣ እንዲሁም መላው ምእመናን የሚያስተጋቡት ሆኗል። ይህም ሁኔታ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች መነጋገሪያ አጀንዳቸውን አንድ ብቻ አድርጎታል፤ ይኸውም የአስተዳደር በደል የሌለበት የሲኖዶስ የበላይነት ይከበር የሚል ነው።

ባለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ እጅግ ታሪካዊ የሆነው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሞትም ሽረትም፣ ትግልም ሽንፈትም፣ ውደቀትም መነሣትም ከአገር ሸሽቶ ሳይሆን እዚሁ ባለንበት ሥፍራ ነው በማለት ቆርጠው በመነሣት የአስተዳደር በደል አለ፤ ያለ አግባብ የሚባክን የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ አለ፤ ሁኔታዎች በቅዱስ ሲኖዶስ ሳይሆን የሚመሩት በፓትርያርኩ ብቻ ነው፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቀና የሆነ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ሐሳብ ሲያቀርቡ ከቦታቸው እንዲነሡ ይደረጋሉ፤ ለእውነት የቆሙ ሰዎች ብዙ መከራ እየደረሰባቸው ይታያል፤ በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል። የዚህ የእውነት ድምጽ ግን የተነሡበትን ዓላማ እና እየተጓዙበት ያለውን መንገድ አልጋ በአልጋ አላደረገውም፤ ይልቁንም ይህንን በማለታቸው ማስፈራራትና ዛቻ እንዲሁም ድብደባ ደርሶባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የስም ማጥፋት ዘመቻ እየተደረገባቸው መሆኑ ለሁላችን ገሐድ ሆኖ ተደምጧል። ቅዱስ ሲኖዶሱ የአንድ ነገድ መሰባሰቢያ፣ የዝምድና ሥራ የሚሠራበት ሥፍራ፣ ገንዘብ ያለአግባብ የሚባክንበት ቦታ፣ ለእድገት የሚቀርቡ ሐሳቦች ተዳፍነው የሚቀሩበት መስክ እየሆነ መጥቷልና ፍጹም ክርስቶሳዊ የሆነ ሥራ ይሠራበት የሚሉ ብፁዓን አባቶች ተነሥተዋል። ይህም በቆራጥነት የተነሡበት ዓላማቸው መክኖ እንዳይቀር፤ በውስጣቸው የተዳፈነው የእውነት መንፈስ በተለያዩ ፍርሀቶች እንዳይገታ፤ ለአባቶቻችን ልንጸልይ እና በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ልንረዳቸው የሚያስፈልግበት ጊዜ አሁን መሆኑን ከመቼውም የበለጠ ልናስብበት ይገባል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያን ያህል አገር አና ኦርቶዶክስን ያህል ፍጹም እምነት የያዘች ቤተ ክርስቲያናችን ለአያሌ ዘመናት ለግብፅ እንደ አገረ ስብከት እየተሰጠች ቡራኬ ስትቀበል ኖራለች። የሃይማኖት መሪዎቿ ብቻ ሳይሆኑ የአገር መሪዎቿ ጭምር ኢትዮጵያ እራሷን ችላ የእራሷን ፓትርያርክ ልትሾም የሚያበቃትን ሲኖዶስ እንደ እምነት ቀዳማዊነቷ እንድታገኝ ሲሞክሩላትና ሲታገሉላት ኖረዋል። ይህ ጥያቄም መልስ ያገኘው የዛሬ ሃምሳ ዓመት በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. ነው። ኢትዮጵያ ለዘመናት ትመኘው የነበረውን የሲኖዶስ መንበር የያዘችውና ያገኘቸው በጾም በጸሎት እና ቆራጥ በሆኑ የሃይማኖት አባቶቿ እና እናቶቿ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። በእግራቸው ሲጓዙ በግብጽ በረሐ ወድቀው የቀሩት አባቶቻችን የደከሙበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ የበላይነቱን ጠብቆ እንዲኖር እንጂ ቅዱስ ሲኖዶሱን የበታች አድርጎ በመቁጠር የሰዎችን ሉዐላዊነት ለማንጸባረቅ አለመሆኑ ግልጽ ነው።

ሲኖዶሱ ዘላለማዊ በመሆኑ እስከ መጨረሻው ይኖራል፤ ተሿሚዎቹ ግን አላፊዎች በመሆናቸው ከመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ጀምሮ እስከ ዛሬ አምስት ፓትርያርኮች ተሾመዋል። ቋሚና ዘላለማዊ የሆነውን መንበር የበላይነቱን ማስከበርና ማስጠበቅ የሁላችን ኃላፊነት በመሆኑ ዛሬም እንደ ትናንት የልዩነት ኅብረት ሳናደርግ ለአንድ ሲኖዶስ ህልው መሆን እስከ መጨረሻው እንታገላለን። ተቃውሟችን ከሰዎች ጋር ሳይሆን ሲኖዶሱን የበታች አድርጎ ከሚመለከተው አስተሳሰባቸው ጋር ነው። ምን ጊዜም ቢሆን የሲኖዶሱ የበላይነት በጥያቄ ውስጥ መግባት አይኖርበትም። አባቶቻችንና እናቶቻችን የደከሙበትና የሕይወት መሥዋዕት የከፈሉበት ቅዱስ ሲኖዶስ የበላይነቱ ተጠብቆ እንዲኖር እንጂ የአገር መሪ ሲቀየር አብሮ የሚቀየር ፓትርያርክ እንዲፈራበት አልነበረም። እዚህ ላይ በደንብ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባው አብይ ጉዳይ ቢኖር ሲኖዶስ ያለፓትርያርክ መኖር ይችላል፤ ፓትርያርክ ግን ያለሲኖዶስ መኖር አይችልም። ይህ ዓረፍተ ነገር ለሁላችን ግልጽ ከሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ የበላይነትም አሻሚ የሌለው፤ በምንም ሁኔታ ለድርድር የሚቀርብም አይደለም።

ይህ እውነታ የገባቸው በዘመናት መካከል የተገኙ ቆራጥ አባቶች መከራ ቢመጣ እንወጣዋለን፤ ሞት ቢመጣ እንጋፈጠዋለን፤ የሲኖዶስ የበላይነት ይከበር፤ ሙስና ለአንዴም ለዘላለምም ይጥፋ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትደግና ትስፋፋ፤ በማለት ተነሥተዋልና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን እግዚአብሔር እንዲታደግልን በጸሎት፤ ሕሊናም ተሰጥቷናልና በማስተዋል እንድንመላለስ በቆራጥነት እንነሣ። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የፓትርያርክነትን ሥልጣን በተረከቡበት ጊዜ እንዲህ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፦ በዘመናት መካከል ወደ እምነታቸው ምንጭ ለመድረስ ወደ እስክንድርያ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በምድረበዳ ወድቀው የቀሩ ኢትዮጵያውያን አሁን በዓፀደ ነፍስ ሆነው የዚህ ክብር ተቀባዮችና ተካፋዮች ናቸው። ይህ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ንግግር እንኳንስ በሕይወት ያለነውንና በዓፀደ ነፍስ ያሉትን ኢትዮጵያውያንን የክብር ተካፋይ እንደሚያደርጋቸው ሲያስረዳ አሁን ይህን ክብር ያለአግባብ ለመጠቀም እና የበላይነቱን ከማጉላት ይልቅ ገዢውን ተገዢ፣ መሪውን ተመሪ፣ ቋሚውን ጊዜያዊ አድርጎ ማቅረብ ከሥርዓት ውጪ መሆን ነው። በመጨረሻም ለረጅም ዓመታት እየታየ ያለውን ይህን የመለያየት መንፈስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልዑል እግዚአብሔር ከእኛ ሊያስወግደው መንገድ እያሳየን በመሆኑ ለእውነት በእውነት ቆመው የቅዱስ ሲኖዶስ የበላይነትን ለማስከበር ከሚታገሉት ጋር አብረን እንሰለፍ። ይህ የሲኖዶስ የበላይነት ሲረጋገጥ እኛም ያለፉት ጥቂት ዓመታት ጥያቄአችን ይመለሳልና ለዚህ ትግል በጸሎትም በገንዘብም በእውቀትም የሚገባንን ያህል ድርሻችንን እንወጣ።

ማጠቃለያ፦

በደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ በአስተዳደር ቦርዱ እና በካህናተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በጠቅላላው ምእመን የወጣው ይህ የጋራ መግለጫ ከዚህ በታች በሰፈሩት ነጥቦች ላይ የተመሠረተ ነው።

፩- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ እድገት ለማይሹትና በእኛም መለያየት የሚፈጠረውን አጋጣሚ ጠብቀው ለሚነሡ መናፍቃን ምንም ዓይነት መግቢያ ቀዳዳ ላለማበጀት በጽናት እና በቆራጥነት መቆማችንን ለማሳየትና ብሎም ቤተ ክርስቲያን በኛ ዘመን ፈተና ላይ ስትወድቅ አላፊ ለሆነ ጊዜያዊ ሥልጣን ብቻ የሚረባረቡትን የሥልጣን ሰዎች ድርጊታቸው ተገቢ አለመሆኑን አበክሮ ለመግለጽ ነው።

፪- የቤተ ክርስቲያን አደራችንንና የእምነት ድርሻችንን በተገቢው መንገድ ከመወጣት አኳያ ለተተኪው ትውልድ የተስተካከለ እና ወጥ የሆነ የአሠራር መንገድ ትቶ ለማለፍ፤ ተተኪው ትውልድም የአባቶቹን አርአያ በመከተል የታሪኩን ምንነት እና የሲኖዶስን ሁኔታ ጠንቅቆ እንዲያውቅ ለማትጋት ነው። በተለይም እንዲህ ያለው ሁኔታ ሲፈጠር ዝምታን ገንዘብ ከማድረግ ይልቅ እውነታው የቱ እንደሆነ በገሐድ በመናገር የሕሊና እረፍት ለማግኘትም ጭምር ነው።

፫- ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ሊያመጣ የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ከሁሉም የበለጠ በመሆኑ እንቆቅልሻችን እንዲፈታ የሲኖዶስ የበላይነት እንዲከበር ማስደረግን ቦታ በመስጠት ነው። ሁሉ ነገር እያለን የጎደለን ነገር ቢኖር ተከባብሮ መኖርና ፍቅር ማጣት በመሆኑ ሥርዓትን አስከብሮ እና ሃይማኖትን ጠብቆ ለመኖር ከወዲሁ ለመዘጋጀት በማሰብ ነው።

በመጨረሻም ይኼን የእውነትና የሰላም የደወል ጥሪ ያደመጣችሁ ካህናትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ዲያቆናትና መዘምራን፣ እንዲሁም ጠቅላላ ሕዝበ ክርስቲያን ጸሎትን እና ልመናን ወደሚሰማ ወደ ልዑል እግዚአብሔር ልመናችሁን አቅርቡ። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ፣ የቅዱሳን ጸሎት እና የመላእክት ተራዳኢነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፤ አብሳሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል የሰላም የፍቅርና በአንድነት ለአንድነት መሥራትን ገንዘብ እንድናደርግ የተለመደ ብሥራቱን ያሰማን አሜን!!


ወ ስ ብ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር!!

ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ

ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ
ደጀ-ሰላም መዝሙር ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ (U.S.A.) www.debreselam.net
Debre Selam Medhanealem Ethiopian Orthodox Tewahedo Church 4401 Minnehaha Avenue South Minneapolis, Minnesota 55406
Tel. (612) 721‐1222 (U.S.A) www.debreselam.net Page 1
ሐምሌ ፲፱/፳፻፩ ዓ.ም. (July 26, 2009)
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)