July 18, 2009

የግርግሩ ፍጻሜ ማግሥት

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 18/2009)
• የተመዘበረው የብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ቤት አልተሠራም፣
• ቅ/ሲኖዶስ የሰየማቸው የሥ/አስፈጻሚ አባላት ለቀዋል፣
• በግርግሩ ፍጻሜ መንግሥት እፎይታ አግኝቷል፣

በትናንትናው ዕለት “በስውሩ እጅ” እርዳታ ፓትርያርኩ ቅ/ሲኖዶስን ካሸነፉ ጀምሮ በቤተ ክህነት አካባቢ ያለው ግርግር ፀጥ ማለቱ ታውቋል። ለሁለት ወራት ሲታወክ የሰነበተው ግቢ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ በደርግ ዘመን እንኳን ሆኖ የማያውቀውን፣ አባ ጳውሎስ ካስደፈሩት በሁዋላ ጸጥታ ሰፍኖበታል ተብሏል።


በችግሩ ውስጥ መፈናፈኛ አጥቶ የነበረው መንግሥት አዲሱ የለውጥ ሒደት ምንም እርምጃ አለማምጣቱን ከተረዳና ጳጳሳቱም በእጃቸው የገባውን ዕድል መጠቀም እንዳልቻሉ ሲገነዘብ አቅጣጫውን በመቀየር ከፓትርያርኩ ጋር መቆምን እንደመረጠ ተንታኞች ገልጸዋል። መንግሥት እውነተኛ የለውጥ ፍላጎት ቢኖረው እንኳን ብፁዓን አባቶች ግን የሚጠበቅባቸውን ያህል በተጠናከረና በዲሲፕሊን ላይ በተመሠረተ አሠራር የተካኑ ባለመሆናቸው በቆረጣ የገባው የማፊያው ቡድን ሊበታትናቸው ችሏል። ፓትርያርኩን ለሕገ ቤተ ክርስቲያንና ለቅ/ሲኖዶስ የበላይነት ለማስገዛት ይቻል ዘንድ ዋዜማው ላይ ከተደረሰ በሁዋላ በአባቶች መከፋፈልና ጠንካራ አቋም ማጣት ነገሩ እንደከሸፈ ያስረዱ አንድ ውስጥ አዋቂ “አውሬው ከቆሰለ በሁዋላ አመለጠ” ሲሉ ነገሩን በምሳሌ አስረድተዋል። የቆሰለው አውሬ ቁስሉን እየላሰ እንደማይቀመጥ ያብራሩት እኒሁ ሰው ያቆሰሉትን ለማጥፋት ተመልሶ መምጣቱ አይቀርም ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ረቡዕ ሌሊት በማፊያው ቡድን ቤታቸው የተሰባበረባቸው ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ከዘመድ ተጠግተው እንደሚገኙ ምንጮቻችን ገለፁ። ብፁዕነታቸው የተሰበረውን በር ጠግኖ ወደ ቤታቸው የሚመልሳቸው “አናጢ” በሀገር በመጥፋቱ ዛሬም በሰው ቤት ይገኛሉ ተብሏል። የወንጀሉ ፈጻሚዎችና ግብረ አበሮቻቸው ፍንጭ እስካሁን ያልተገኘ ሲሆን ጉዳዩን የአዲስ አበባ ፖሊስ እየተከታተለው መሆኑም ተሰምቷል።

በተያያዘ ዜና ቅ/ሲኖዶስ አቋቁሞት የነበረውና በፓትርያርኩ የታገደው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሥራውን እንዲሠራ “ዕግዱ ተነስቶለታል” ቢባልም ሊቆጣጠረው ይገባ ለነበረው አካል ማለትም ለፓትርያርኩና ለሥራ አስኪያጁ ተጠሪ እንዲሆን በመደረጉ የኮሚቴው አባላት እንደማይቀጥሉ ታውቋል። ፓትርያርኩ ዕግዱን አንስቻለሁ ያሉት ኮሚቴው በስም ብቻ እንጂ በግብርና በሥራ እንደማይኖር ካረጋገጡ በሁዋላ እንደሆነ የቅርብ ሰዎች ገልጸዋል። በዚህ ግርግር ውስጥ መከራ የደረሰባቸውና ማስፈራሪያ ያገኛቸው አባቶች ግን “ቤተ ክርስቲያናችንን ጥለን የትም አንሄድም፤ ፓትርያርኩንም አናኮርፋቸውም” ሲሉ ተሰምተዋል። ሕዝቡ ግን በነገሩ ሁሉ መበሳጨቱ ታውቋል። መንግስት በበኩሉ በቀላሉ የተጀመረውና ወደሁዋላ የጦዘው ውጥረት ለጊዜው መርገቡ ቢያስደስተውም ትልቅ ቤት ሥራ መውሰዱን ማወቅ እንዳለበት ተንታኞች ጠቅሰዋል።

እስቲ ቸር ወሬ ያሰማን እንበላ!!!
አሜን ብለናል።

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)