July 17, 2009

የቤተ ክህነቱ ማፊያ ቡድን አሁንም አልተያዘም፤ የመንግሥት ደህንነቶች ሳይኖሩበት አልቀሩም

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 17/2009)

ረቡዕ ከምሽቱ አራት ሰዓት ጀምሮ በአካባቢው ያለውን የመብራት መጥፋት ተገን ባደረጉ ሰዎች በብፁዓን አባቶች ላይ አደጋ ለመጣል በተደረገውና በንብረት ውድመትና አባቶችን በማጎሳቆል እንዲሁም አፍኖ በመውሰድና በማስፈራራት በተፈጸመው ወንጀል ቤተ ክህነቱን የተቆጣጠረው የፓትርያርኩ “ቤተ ዘመዶች ቡድን” እንዲሁም በጉቦ የተገዙ “የመንግስት ደህንነት ሠራተኞች” እንደሚገኙበት ውስጥ አዋቂዎች እየተናገሩ ነው።

“ሊቀ ኅሩያን” የሚል የማዕረግ ስም ተሰጥቶት ታላቁን የቤተ ክርስቲያኒቱን የሰበካ ጉባዔ ማደራጃ መምሪያ ሃላፊነት የተቆጣጠረው የፓትርያርኩ እህት ልጅ በሆነው በአቶ ያሬድ ከበደው መሪነት የሚንቀሳቀሰው የማፊያ ቡድን የተጠናከረና መሳሪያ የታጠቀ ሲሆን አደጋ በመጣልና በማስፈራራት ከዚህ በፊትም ልምድ አለው። ከዓመታት በፊት በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ታቦተ ሕጉ በቆመበት የአንድ ባህታዊ ነፍስ በጠፋባት ዕለት “ጥይቲቱን ያስወነጨፈው እርሱ ነው” እየተባለ ሲታማ የኖረው ያሬድ የቤተ ክህነቱ ቁጥጥር ክፍል ሀላፊ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱ የጀርባ አጥንት የሆነው የሰበካ ጉባዔ መምሪያ የበላይ ነው። ይህ መምሪያ በተወዳጁ መንፈሳዊ አባት በሊቀ ጉባዔ አባ አበራ በቀለ መሪነት ለአስርት ዓመታት ሲተዳደር የነበረ ሲሆን አባ አበራ ከፓትርያርኩ በደረሰባቸው መገፋት የሕክምና ርዳታ ሳያገኙ፣ በአንዲት ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት ውስጥ ኖረው በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ሊለዩ በቅተዋል።


ስለ ረቡዑ አደጋ አስተያየት የጠየቅናቸው የቤተ ክህነት ሠራተኞች እንደሚናገሩት “እነ ያሬድ የጠሉትን ሰው በማንኛም መልኩ ከማጥቃት ወደ ሁዋላ” እንደማይሉ ገልጸው በዚህ ወንጀላቸው ደግሞ በመንግስት ደህንነት ውስጥ የሚሰሩ ወይም ይሰሩ የነበሩ ሰዎች እንደሚተባበሯቸው ተናግረዋል። ደህንነቶቹ ለምን በዚህ ወንጀል እንደሚሳተፉ ምክንያታቸውን የሚዘረዝሩት ውስጥ አዋቂዎቹ “ሰዎቹ በገንዘብ ይደለላሉ፣ የቤተ ክህነት ቤቶች ይሰጧቸዋል፣ ወይም ፓትርያርኩ የሥጋ ዘመዶች ይሆናሉ” ሲሉ አብራርተዋል።

በግንቦት 2001 ዓ.ም ለቅዱስ ሲኖዶስ በቀረበና የፓትርያርኩን አስተዳደራዊ በደሎችና ወንጀሎች በዘረዘረ አንድ መረጃ ላይ ፓትርያርኩ “በሙስናና በተለያዩ ከፍተኛ ችግሮች በደል ተገኝቶባቸው ከመንግሥት በግምገማ የሚባረሩ አካላትን ከጥፋታቸው ሳይታረሙ ከነችግራቸው በማቅረብ ቤተ ክርስቲያኒቱን የዘራፊዎች ዋሻ አድርገዋልታል፡፡” የሚል ክስ ቀርቦባቸው እንደነበረ ታውቋል።
በርግጥም መንግስት የደህንነት ሃይሎቹ በፈለጉት መልክ ወንጀል ሲሰሩ ሊቆጣጠር የሚችልበት ዘዴ ከሌለው አገራችን የድህረ-አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ ዕጣ እየገጠማት ነው የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ ፈጥሯል። ፓትርያርኩ ከዚህ በፊትም የሚቃወሟቸውን ሰዎች በመንግስት ስም እንደሚያስፈራሩ ይታወቃል።

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)