July 17, 2009

የሁለቱ ወር የቅ/ሲኖዶስ ውጣ ውረድ ሲጠቃለል፤ ሪፖርታዥ

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 17/2009)

ከግንቦት 6/2001 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ሁለት ወራት ሲተረማመስ የነበረው ጉባዔ በመጀመሪያ የተነሳበትን ጉዳይ ከግቡ ሳያደርስ፣ “በስውር እጅ” ድል አድራጊነት፣ በፓትርያርኩ የበላይነት ተጠናቋል። ለመሆኑ ችግሩ ከመጀመሪያው ምን እንደነበር ማንሳት ይገባል። ቤተ ክርስቲያን በተለይም በፓትርያርክ ጳውሎስ መንበረ ፕትርክና ከመቼውም ጊዜ በላይ ውድቀት ላይ እንደምትገኝ የቅ/ሲኖዶስ አባላት ተገንዝበዋል። መገንዘብ ብቻ ሳይሆን በዚህ ዓመት በአንድነት መናገርም ጀምረው ነበር። ችግሩ የተረዱ አባቶችም ለቅ/ሲኖዶስ ባቀረቡት ባለ 21 ገጽ ዶኩሜንት ችግሩን በዝርዝር አቅርበው ነበር። ይኸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋና ዋና አንገብጋቢ ችግሮች እና መፍትሔዎች፦ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ” በሚል ርዕስ የቀረበው ዶኩሜንት በሚከተሉት ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጥናል።

1 ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚፈጽሟቸው ስሕተቶች፣
(ይህም 23 ነጥቦችን ያዘለ ነው፤ እንደ አስፈላጊነቱ ወደፊት በዝርዝር እናቀርበዋለን፤)
2 ጠቅላይ ጽ/ቤቱን በተመለከተ አሉ ችግሮች (ባለ 9 ነጥብ ሐሳብ)፣
3 የችግሮቹ ማጠቃለያ፣
4 የአጭርና መካከለኛ ጊዜ የመፍትሔ ሐሳቦች፤

የነገሩን አካሄድ የተረዱት ፓትርያርኩ ጉዳዩን ለማኮላሸት “የነገሩ ጠንሳሽ” ናቸው ያሏቸውን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በማንሳት በምትኩ በከፋፍለህ ግዛው ዘዴ ሀ/ስብከቱን ለአራት ጳጳሳት ሊሰጧቸው ቃል ገቡላቸው። ከነዚህም መካከል አንደኛው አቡነ ገብርኤል ናቸው። ይህንን እጅ መንሻ የተቀበሉት አቡነ ገብርኤል ዛሬ ጉባዔው እስከተፈጸመበት ዕለት ድረስ የቤት ሥራቸውን በትጋት ሲሰሩ ሰንብተዋል። ከዚህም ባሻገር የተነሳውን ነውጥ አቅጣጫ ለማስቀየር ፓትርያርኩ አዳዲስ ጳጳሳትን “መሾም እፈልጋለሁ” ብለው አቀረቡ። ሊሾሙ የተዘጋጁት “አባቶች” በአብዛኛው የእርሳቸው ጋሻ ጃግሬነታቸውን ገና ከጠዋቱ ያስመሰከሩ ናቸው። ቅ/ሲኖዶሱ ይህንን ሹመት አልቀበልም በማለት ላለፉት 17 ዓመታት ያላሳየውን ድፍረት አሳየና ፓትርያርኩንና “የማፊያውን ቡድን” አስደነገጠ። ማፊያው ቡድን በፍጥነት ወዲያዉኑ በመንቀሳቀስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን “የሚያዋርድ መጽሐፍ” ኣሳትሞ ማሰራጨት ጀመረ። የመጽሐፉ “ደራሲም” አዲስ መኪና ተሸለመ። መጽሐፉም በቤተ ክህነት ግቢ እና በመስኪድ አካባቢ በስፋት መሰራጨት ይዟል። ይህ መጽሐፍ እየተሰራጨ ሌላ መጽሐፍ እንዲዘጋጅ ተደረገ። አዲሱ መጽሐፍ የ10 ጳጳሳትን ስም ለማጥፋት የተዘጋጀ ሲሆን ከነዚህም አንደኛው ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ነበሩ። የመጽሐፉ ይዘት ለነዚህ አባቶች እንዲገለጽላቸው ከተደረገ በሁዋላ አፋቸውን ዘግተው እንዲቀመጡ ወይም የፓትርያርኩ ደጋፊዎች እንዲሆኑ ተደረጉ። አቡነ እስጢፋኖስም ይህንኑ ተቀብለው ሲኖዶሱን በማፍረስ ረዱ። ይህንን በማድረጋቸው የራሳቸውን “ጉድ” ለመደበቅ ቤተ ክርስቲያንን “ጉድ አደረጓት”። ቤተ ክርስቲያን በንስሐ ያጠበችላቸውን ሃጢአት ሰዎች ስላልረሱት እነርሱን ለማስደሰት ብለው “ይቅር” ያለቻቸውን ቤተ ክርስቲያን” አሳዘኗት። ያተረፉት ነገር ለጊዜው መጽሐፉ ታትሞ እንዳይሰራጭ ማድረግ ብቻ ነው።

ከዚአ ማፊያው ቡድን በአንድ በኩል፣ ፓትርያርኩ በአንድ በኩል በብፁዓን አባቶች ላይ ዘመቱባቸው። ስማቸውን ማጥፋት፣ ማስፈራራት፣ መዛት ቀጠሉ። እንዲያውም ፓትርያርኩ መስመር አልፈው “ሕገ ቤተ ክርስቲያንን አልቀበልም” ብለው የክህደት ቃል ተናገሩ። ለዚህ ቃላቸው ሳይገሰጹ፣ ሳይቀጡና ኢቅርታ ሳይጠይቁ፣ ማፊያው ቡድን አበውን ቤት በመሰባበር በርግጥም ዛቻው በቃላት ብቻ እንደማይገታ አሳየ። አባቶችም ማንም እንደማይደርስላቸው ካረጋገጡ በሁዋላ “እሺ እንደቃሎ ታዛዥ ነን” ብለው ለፓትርያርኩ እጃቸውን ሰጡ። በዚሁ ተጠናቀቀ። አዲስ ምዕራፍ ተጀመረ ማለቱ ይሻላል።

የሰውን አየነው አሁን የእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ ይጀምራል። ሁሉም በቤተ ክርስቲያን የጭንቅ ቀን ተመዘነ። የቀለለው ቀለለ፤ የተዋረደው ተዋረደ። በዚህ ውስጥ ለቤተ ክርስቲያናቸው የቆሙት በሙሉ ዋጋ ከፋይ በሆነው አምላክ መመስገናቸው አይቀርም። ለሌሎቻችን ግን ይብላኝልን!!! ስለዚህ ተስፋ እንቁረጥ? “ምን ጳጳስ አለ?” ብለን በቀቢጸ ተስፋ ወደየቤታችን እንግባ፣ ወደ ኣለሙ እንሰማራ፣ ወደ መናፍቁ አዳራሽ እንሂድ፣ ከስደተኛው እንደመር? በጭራሽ!!!!! ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገላችን ሰማዕትነትም ቢሆን እንቀበል ዘንድ መዘጋጀት ካለብን ጊዜው አሁን ነው። በተለይም በኢትዮጵያ ያሉ አበው፣ ወንድም እህቶች በሙሉ “የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ነው” እየተባሉ የፓትርያርክ ጳውሎስንና የማፊያውን ውሳኔ እንዲቀበሉ ይገደዳሉ እምቢ ካሉም “መንግሰት ሰላም ለማስከበር” ደረታቸውን በጥይት፣ እጃቸውን በብረት፣ ጉልበታቸውን በእንብርክ ማድቀቁ አይቀርም። ምዕመናን ቤተ ክርስቲያናቸውን ለማዳን መነሣት ካለባቸው ጊዜው አሁን ነው። በመሸሽ፣ ከቤተ ክርስቲያን በመቅረት፣ ገለልተኛ ሆኛለሁ.ተሰድጃለሁ በማለት ሳይሆን ቤቱን እንዲያጸዳ አምላክን በመለመን የዘመናችን “ልዮናውያን” መታገል አለብን።

ዛሬ ቤተ ክህነታችን ያለበት ሁኔታ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የካቶሊኮች ሁኔታ ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው። በአባቶች በኩል ያለው ሥርዓት አልበኝነቱ፣ ገንዘብ ወዳድነቱ፣ እግዚአብሔርን አለመፍራቱ፣ ለምንኩስና ክብር አለመስጠቱ፣ ምዕመናንን አለመጠበቁ ወዘተ የዘመነ ሉተርን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያስታውሰናል። ካቶሊክ ቤተ ክርስቲአን እንዲያ በብልግና በመበሻቀጧ ምን መጣባት? ሉተር ተነሳባት። እኛስ እግዚአብሔር በምን ይቀጣን ይሆን? በእስላሞች ሰይፍ? በመናፍቃን ወረራ? እርሱ ባለቤቱ ያውቃል። ለሃጢአታችን ግን ዋጋ ሳንከፍል አናመልጥም። ንስሐ እስካልገባን ድረስ። ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መናገሻ የሆነውን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ያስደፈሩት ፓትርያርክ እንደ አቡነ መርቆርዮስ እንኳን ዕድሜ ለንስሐ ሳያገኙ እንዳይቀሩ በጣም ያሰጋቸዋል። እግዚአብሔር የሰጣቸውን ዕድል አልጠቀም አሉ። 17 ዓመት ሙሉ ያዋረዷት ቤተ ክርስቲያን እንደ ደካማ ተቆጥራ በድል የወጡ መሰላቸው። የምጥ ጣር እንደሆነ ማን በነገራቸው። መቸም ይህንን ማን ይነግራቸዋል። እርሳቸውስ ምን ጆሮ አላቸውና። (“ነባዕነ ነባዕነ፤ ከመ ኢነባዕነ ኮነ፤ ጮኽነ ጮኽነ፣ እንዳልጮኽነ ሆነ” አለች አሉ ውሻ!!!)

ታሪክን የሚለውጥ አምላክ ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)