July 14, 2009

ይህ ሁሉ ስለምን ደረሰብን? ምንስ እናድርግ?

ይህንን አጭር መልክት ሲታነቡት በፍጹም ቅንነትና በጎነት ታነቡት ዘንድና ይጠቅማል የምትሉ ከሆነ ለቤተክርስቲያን ዕድገት እንድታውሉት እና የጎደለውን እንድትሞሉበት በመጀመርያ በእግዚአብሔር ስም በትህትና እጠይቃለሁ። እኔም ይህንን ስጽፍ የድርሻዬን ተወጥቻለሁ ብዬ አይደለም፤ ነገር ግን ስሜቴን ላካፍላችሁ በማለት እንጂ።
በአሁኑ ሰዓት ሁላችንም እንደምናውቀው በእናት ሀገራችንም ሆነ በውጭ ሀገር ባሉት አብያተ ክርስቲያናት ከውስጥና ከውጭ የተለያዩ ፈተናዎች ተደቅነውባታል። ከውጭ የመናፍቃንና የአክራሪ እስልምና ከውስጥ ደግሞ ትምህርቷን ጠንቅቀው በሚያውቁ ነገር ግን በወንጌል እንደተገለጸው ሆዳቸው አምላካቸው በሆኑና ለጥቅም ባደሩ አይሁዳዊያንና ተሐድሶዎች ሥርዓቷ እየተበረዘ፤ አገልግሎቷ እንዳይስፋፋ እየተደረገ፤ ዶግማዋና ቀኖናዋ እየተበረዘ ፤ ምዕመኖቿም በመናፍቃንና በአሕዛብ እየተነጠቁ ይገኛሉ። በሌላም መልኩ ደግሞ ሌሎች አብያተ ክርስቲያንን ተገን አድርገው ለምድራዊ ዓላማቸው (ለሥጋዊና ፖለቲካዊ ጥቅም) ቤተ ክርስቲያንን ሲጠቀሙባት ይታያል። በተለይም ከሁሉም ዓላማዎች ውስጥ ይህ የመጨረሻው ዓላማ (ለሥጋዊና ፖለቲካዊ ጥቅም) በውጭ ሀገር ባሉት አብያተ ክርስቲያናት ላይ በጣም ጎልቶ ይታያል። በውጭ ሀገር ስላለው ችግር ግን ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ግን የማተኩረው በሀገር ቤት እየተከሰተ ስላለው ወቅታዊ ጉዳይ የተሰማኝን ነገር ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።
አንዳንድ በሐዋርያት ሥልጣን የተቀመጡ “አባቶች” ምዕመኑና ካህናቱ ያልለመደውን ባህርይ የሚያመጡ፤ አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት የመናፍቃንና የፖለቲካ ዓላማ መጠቀሚያና ማስፈጸሚያ ሲሆኑ ይስተዋላል። እዚህ ላይ ሳያውቁት የሚያደርጉ ቢኖሩም የቤተክርስቲያንን ትምህርት እያወቁ ነገር ግን ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ በቁጥር እንደሚበልጡ ማወቅ ያሻል። ቅዱስ ጳውሎስ በፊል. 3፤18 ላይ “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነሱ እላችኋለሁ፤ አሁንም እንኳን እያለቀስኩ እላለሁ መጨረሻቸው ጥፋት ነው ፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፣ ክብራቸው በነውራቸው ነው፣ አሳባቸው ምድራዊ ነው።” በማለት ገልጾታል። ዛሬም ባለንበት ዘመን አባቶቻችን ያወረሱንን ርስት (ማለትም እምነቷን፤ ትውፊቷን፤ ዶግማዋን፤ ቀኖናዋን እና ሥርዓቷን) አባቶች አስጠብቀው ሊያስጠብቁ፤ ምዕመኖቿም ሊከተሉትና ሊጠብቁት ይገባል። በሐዋ. ሥራ 20፤28 ላይ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው “እንናተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋውና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ እግዚአብሔር በደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ” ። የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ ሲል ምዕመኖቿንና እምነቷን፤ ትውፊቷንና ዶግማዋን ፤ ቀኖናዋን እና ስርዓቷን ያጠቃልላል። በአሁኑ ሰዓት እንደነ ሙሴ ፤ ናቡቴ እና እንደነ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ አባቶች ያስፈልጉናል። ሙሴ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን፤ ተስፋ ለሌለው ለአሕዛብ የተንደላቀቀ ኑሮ መሸነፍን ንቆ ፤ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው እግዚአብሔር ከልደት እስከ ጉልምስና ያደረገለትን ድንቃ ድንቅ ብድራቶች ትኩር ብሎ ተመለከተና የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እምቢ አለ። ናቡቴም የአባቶቼን ርስት አሳልፌ አልሰጥም፤ አልለውጥም በማለቱ ሰማዕትነትን ተቀብሏል። አቡነ ጴጥሮስም ስለሀገራቸውና ስለቤተክርስቲያን ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። በእርግጥ በቀራንዮ አደባባይ ላይ ለተመሰረተችው፤ መሰረቷና ጉልላቷ መስቀል ለሆነው ለቤተ ክርስቲያናችን ፈተና አዲስ ነገር አይደለም። በተለያዩ ጊዜያት በተነሱ አክራሪ ሙስሊሞች፣ መናፍቃንና ነገስታት ስትፈተን ቆይታለች፤ እየተፈተነችም ትገኛለች፣ ነገር ግን ሊያጠፏት አልቻሉም፤ ወደፊትም አይችሉም። ምክንያቱም “የገሀነም ደጆች ሊያናውጧት አይችሉም” ተብሎ በወንጌል ተነግሮላታልና።

በአሁኑ ወቅት “አባቶች” መንፈሳዊ ኃላፊነታቸውን ካለመወጣት የተነሳ ምዕመኑ ለአባቶች ያለው ክብር ማነስና በአባቶች ላይ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያለ ይመስለኛል። በሌላ መልኩ ደግሞ ተገልጋይ ምዕመን ትህትና ይዞት፤ በትዕግስት ከዛሬ ነገ ይስተካከላል ብሎ፤ በሃይማኖቱም ጸንቶ ነው እንጂ ስርዓቱ ሲበላሽ ድሮም ቢሆን ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም ብዬ እጽናናለሁ። ወንገልም “የጸኑትን አስቡ” ይላልና። ይህንንም ደግሞ ሁላችንም ማድረግ ያለብን ይመስለኛል።

ነገር ግን ሁል ግዜ በውስጤ የሚመላለሱ ጥያቄዎች አሉ፡- ይህ ሁሉ የውስጥና የውጭ ፈተና ባለበት ወቅት የቤተ ክርስቲያን “አባቶች” መከፋፈልና በቅን ልቡና ለማገልገል በሚፈልጉ አባቶችና ምዕመናን ላይ ለምን ይህ ሁሉ መሰናክል ለምን በዛ? ለምንስ ‘አባቶች’ ልጆቻቸውን በፍቅር፤ በትህትናና በመደማመጥ ስለ አገልግሎት ለምን መነጋገር አቃታቸው? መድረክ ላይ ወጥቶ መምህራኑ በራሳቸው በሕይወት የማይኖሩትን ማስተማሩስ ምን ያህልስ ለውጥ ያመጣል? “አባቶችስ” ለምን ያልለመዱትን ጸባይ አመጡት? እንደ ቅዱስ ዳዊት ሁሉ ሳዖል የጦር ልብሱን እንካችሁ ባለን ጊዜ “አልለመድኩም” በማለት ሊንሄድ አይገባም ነበር ወይ? የዓለም የሆነውንና የእኛ ቤት ልማድና ስርዓት ያልሆነውን ልንጥልና እንደዳዊት አገልግሎታችንን እንደጥንቱ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ሊሆን አይገባም ወይ? እንዲያው እኮ ሳስበው ምዕመኑ የአገልጋዮችን መልካም ስም ሰምተው ሰናይ ምግባራቸሁን አይተው ተሰብስበው ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡ እንጂ ስለ አባቶችና ስለሌሎች አገልጋዮች ስንፍና ወይም ግድ የለሽነት ሰምተውና አይተው መልካም የሆነው የቤተ ክርስቲያን ስርዓት እንዳማራቸውና እንደራባቸው እንዲቀሩ አልነበረም።

ቤተ ክርስቲያኗ ካሏት ምዕመንና ከመናፍቃን እንቅስቃሴ አንጻር ምዕመኑን በማስተባበርና የሰ/ት/ቤቶችን በማደራጀትና በማጠናከር ታላላቅ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት ብዙ ነፍስ ማትረፍ በተቻለ ነበር። በቅን ልቦና ከተነሳን የበለጠ ማድረግ በተቻለ ነበር። በሀገር ውስጥ ጧፍና ሻማ በማጣትና በአገልጋይ ካህናት እጥረት የተዘጉ በጠረፍ እና በገጠር ያሉትን አብያተ ክርስቲያናትን ማስከፈት በተቻለ ነበር። የሊቃውንት ምንጭ የሆኑትን ገዳማትን የበለጠ መርዳት በተቻለ ነበር። እኛ ግን ሆዳችን አምላካችን ሆኖብን በስጋዊ ነገር ተሸንፈን ማድረግ ያለብንን ነገር ሳናደርግ ቀርተናል ፤ የሚሰሩትንም አደናቅፈናል። ለዚህ መፍትሔ ከመስጠት በፊት እንዲህ እንዳናደረግ ያደረገንን ነገር ማወቁ አስፈላጊ ይመስለናል።

በመጀመሪያ የበጎ ነገር ጠላት የሆነው ጥንተ ጠላታችን ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑትን ግለሰቦች እና ተሐድሶ መናፍቃንን ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማስገባት እየተጠቀመ መሆኑን ማወቅና መገንዘብ፤ ከዚያም እስካሁን የሰውን ነፍስ በማዳን ረገድ እና ስብከተ ወንጌልን ከማስፋፋት አንጻር ምንም እንዳልሰራንና እንዳቀላፋን ማወቅና ጥፋት መሆኑን መቀበል ይኖርብናል። በመቀጠልም መንፈሳዊ ሕይወታችንን ከማሳደግ ጎን ለጎን ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ማቀድ አለብን። ምዕመኑም የአባቶችን ክብር ከቤተ ክርስቲያን ክብርና ስርዓት በመለየት ነገሮች ያለስርዓት ሲሄዱ ዝም ብሎ መመልከት እንደሌለበት ይሰማኛል። በተጨማሪም አንዳንድ ምዕመናን አባቶችን የጠቀመ ይመስል አላስፈላጊ የሆኑ እንክብካቤዎችን እያደረገና እያሞገሰ ከጸሎት እንዲርቁና እንዲፈተኑም ያደረጋቸው ይመስለኛል። ይህ ግን የሚስተካከለው ምዕመኑ አስቀድሞ ሲማር ነው። ለማንኛውም እንጸልይበት።

እግዚአብሔር አምላክ ደካምነታችንን በኃያልነቱ ፤ አላዋቂነታችንን በከሃሊነቱ አጥፍቶ ለሀገራችን፣ ለወገናችን፣ ለቅድስት ቤተክርስቲያናችን የምንበጅ ሙሴ ያድርገን።

እስቲ የጎደለውን እናንተ ደግሞ ሙሉበት።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክብር።
ZeTekiliye

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)