July 13, 2009

ቅዱስ ሲኖዶስ በፓትርያርኩ ሰብሳቢነት እየተነጋገረ ነው

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 13/2009)
ባለፈው ሳምንት በቅዱስ ሲኖዶሱና በቅዱስ ፓትርያርኩ መካከል በተነሣው አለመግባባት ሲታመስ የነበረው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በመንግሥት አሸማጋይነት ከተረጋጋ በሁዋላ ዛሬ ሰኞ ጠዋት ስብሰባውን በድጋሚ ጀምሯል። የመንግሥት ባለሥልጣናት በመካከል ገብተው “ተዉ፣ ተዉ” ብለው ያረጋጓቸው ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አባቶች ዛሬ ሲገናኙ ስብሰባውን ማን ነው መምራት ያለበት የሚለው ጥያቄ ሳይነሳ ፓትርያርኩ ቦታቸውን መያዛቸው ታውቋል።
“ጉዳዩ ስለርስዎ አስተዳደራዊ ብልሹነት ስለሆነ እርስዎ መምራት የለቦትም” ያላቸው አንድም አባት ባለመገኘቱ የልብ ልብ የተሰማቸው ቅዱስነታቸው ስብሰባውን በፈለጉት መልክ ሲያስኬዱት አርፍደዋል ተብሏል። ይልቁንም ብፁዓን አባቶች ሲለምኗቸው፣ “በገጸ ምሕረታቸው” እንዲመለከቷቸው ሲለማመጧቸው ውለዋል ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ችግሩን ይፋ ካወጡትና ለሕዝብና ለመንግሥት እንዲደርስ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል የሆኑት የሥራ አስፈጻሚና የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ዕገዳ ደብዳቤዎች ጉዳይ ቢነሣም ቅዱስነታቸው ሁለቱንም ደብዳቤ አላነሣም በማለታቸው እንደጸኑ ምንጮቻችን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በዛሬ ውሏቸው ምንም የልብም የምግባርም ለውጥ ሳያመጡ እንዲያውም በያዙት አቋም ጸንተው እንደተገኙ የታወቀ ሲሆን በሌሎቹ አባቶች በኩል ግን መፍረክረኩ መቀጠሉ ታውቋል። “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ አላት ማለት አይቻልም” ያሉ አንድ የቤተ ክርስቲያን አባት “ችግሩ የአቡነ ጳውሎስ ሳይሆን የጳጳሳቱ ነው። እርሳቸውማ አቋማቸውንና ፍላጎታቸውን እያስፈጸሙ ነው። ለቤተ ክርስቲያን መቆም ያቃታቸው ብፁዓን አባቶች ናቸው” ብለዋል።
ስብሰባው ዛሬ ከሰዓትም የቀጠለ ሲሆን በጠዋቱ መልክ ቀጥሎ ከፍጻሜ ከደረሰ ፓትርያርኩ በአሸናፊነት በመውጣት ከዚህ በፊት ከነበረው ወደ በለጠ አምባ-ገነን አስተዳደር እንደሚሸጋገሩ፣ ተቃዋሚዎቻቸውን በሙሉ አንድ በአንድ እንደሚመነጥሩ ተገምቷል።

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)