July 1, 2009

እግድ የተጣለባቸው የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ስብሰባ አካሄዱ


Wednesday, 01 July 2009
እግድ የተጣለባቸው የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ስብሰባ አካሄዱ
- የኮሌጁ የበላይ ኃላፊ ለፌደራል ፖሊስ ደብዳቤ ፃፉ
በታምሩ ጽጌ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሣሙኤል የተመራ ስብሰባ በሃገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ ትናንት ለግማሽ ቀን ተካሂዷል፡፡
ትናንት በተካሄደው ስብሰባ ላይ በሃገረ ስብከቱ ስር የሚተዳደሩ አብያተ ክርስቲያናት፣ አስተዳዳሪዎች፣ ምክትል ሊቀመናብርት፣ ዋና ፀሐፊዎችና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተገኙ ሲሆን፤ በቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪዎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ ንግግር አድርገዋል፡፡

የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሣሙኤል ስብሰባውን በፀሎት ከከፈቱ በኋላ ባደረጉት የመግቢያ ንግግር ቤተክርስቲያኒቱ ላለፉት 17 ዓመታት የአዙሪት ጉዞ መጓዟን ተናግረው፣ ሕገ ቤተክርስቲያን በአግባቡ አለመከበርን አስመልክቶ በግንቦት ወር 2000 ዓ.ም. እና በጥቅምት ወር 2001 ዓ.ም. ሰፊና ጥልቅ ውይይት ተደርጐ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡

ቤተክርስቲያኗ በመልካም አስተዳደር እጦት የተነሳ ከሰባት ሚሊዮን በላይ አማኒያንን ማጣቷን፣ ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር መወዳደር አለመቻሏን የገለፁት ጳጳሱ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገነቡ ሕንፃዎች፣ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ላይ ለሠራ የተሰማሩና በየመንገዱ ስዕል አንጥፈው ልመና ላይ የሚገኙት የዚህችው የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ ሥርዓት በማጣት ሥራ ያላገኙ ምሁራን መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"የሾመኝ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ሊያወርደኝም የሚችለው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው" በማለት የተጣለባቸው እግድ እንደማይቀበሉት የተናገሩት አቡነ ሣሙኤል ሁሉንም ኃላፊነት ለቅዱስ ሲኖዶሱ መተዋቸውን ገልፀዋል፡፡

ከአቡነ ሣሙኤል የመግቢያ ንግግር በመቀጠል ከተለያዩ አድባራት የተገኙ አስተዳዳሪዎችና ፀሐፊዎች፣ የወንጌል ሰባኪያን ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሁሉም የአቡነ ሣሙኤልን መታገድ በማስመልከት "እንዴት ሙስናን የታገለ፣ ለቤተክርስቲያን እድገትና መስፋፋት የሠራ፣ በሁሉም ብሔር ብሔረሰብ መካከል ሠላም አውርዶ አንድ አድርጐ ፍቅርን ሠላምን እንዘምር የሚል አባት ይታገዳል?" በማለት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ተሰብሳቢዎቹ በአሁኑ ጊዜ በቤተክርስቲያን ዙሪያና በግለሰቦች ላይ የሚፃፉትን መፅሐፍት እና የሚበተኑትን መጣጥፎች ቅዱስ ሲኖዶሱ ተከታትሎ እርምጃ እንዲወስድ ካሳሰቡ በኋላ ባለ ዘጠኝ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡

የስብሰባው ታዳሚዎች አንድ በመሆን ያስተላለፉት የአቋም መግለጫ ቅድስት ቤተክርስቲያኒቱ ላለፉት 50 ዓመታት በራሷ ሊቀ ጳጳሳት መመራቷን፣ ከ1994 ዓ.ም. ወዲህ የሚታይና የሚዳሰስ ሥራ እየሰራች መሆኗን አበክረው ከመግለፃቸውም በላይ፤ ቤተክርስቲያኒቱ የምትመራበት ቃለ ዓዋዲ ሕገ ቤተክርስቲያን በመጣሱ ቅዱስ ሲኖዶሱ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድላቸው ጠይቀዋል፡፡

በአቡነ ሣሙኤል ላይ ሕገ ቤተክርስቲያንን በመጣስ የተወሰደው እርምጃም ቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲያነሳላቸው አሳስበው ሌሎችንም የአቋም መግለጫ ነጥቦች በማከል ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ለመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት፣ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት ጽ/ቤት፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ለፌዴራል ፖሊስ በግልባጭ አሳውቀዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የቅድስት ስላሴ መንፈሣዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ተላልፈዋል፣ ቤተክርስቲያኒቱ የምትመራበትን ሕገ ቤተክርስቲያን ጥሰዋል፣ ለመሻር ተንቀሳቅሰዋል ያሏቸውን ወገኖች በመኮነን የፌዴራል ፖሊስ ለኮሌጁና ለሃገረ ስብከቱ ለእያንዳንዳቸው ስድስት ፌዴራል ፖሊስ በአስቸኳይ እንዲመድብላቸው ለፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ለአቶ ወርቅነህ ገበየሁ የፃፉት ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

3 comments:

Anonymous said...

Is our church collapsing in its own internal fight?

Aba Samuel are you sure 6 million orthodox christians have left our church?

Teddy said...

Dear anonymous! According to Aba Samuel it is 7 million people who abandoned the church not 6 million. Still my question is: where our church is going?

Anonymous said...

Everything is going to be OK! Our Church will be triumphant, let's just keep our heads up and be positive!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)