June 29, 2009

የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀጳጳስ አቡነ ሣሙኤል እና አቡነ ጢሞቲዎስ ከኃላፊነታቸው ታገዱ

(Reporter Sunday, 28 June 2009)
የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀጳጳስ አቡነ ሣሙኤል እና አቡነ ጢሞቲዎስ ከኃላፊነታቸው ታገዱ
የሐገረ ስብከቱ የባንክ ሒሳብ ታግዷል

በታምሩ ጽጌ

(DEJE SELAM) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀጳጳስ አቡነ ሣሙኤል እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ አቡነ ጢሞቲዎስ ከሰኔ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸውና ከሥራቸው መታገዳቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኙ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና ከሊቃውንት ጉባኤ ዕውቅና ውጭ መንፈሳዊ አገልግሎትን ስለማስተላለፍ የተሰራጨው ትምህርተ ቀኖና፤ ቤተ ክርስቲያንን የሚያፋልስና በቤተ ክርስቲያን ላይ የተሰነዘረ የድፍረት ድርጊት መፈፀማቸውን በመግለፅ፣ ጉባኤው ተጠንቶ በቅዱስ ሲኖዶስ እርማት እስከሚሰጥበት ድረስ ረዳት ሊቀ ጳጳሱ ከኃላፊነታቸውና ከሥራቸው ታግደው እንዲቆዩ በሚል ባስተላለፉት ጥሪ መሠረት መታገዳቸውን ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡

በብፅዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፀሐፊዎች ለአንድ ቀን ባደረጉት ስብሰባ፣ ለቤተ ክርስቲያኗ ሠራተኞች እየተላለፈ ያለ ህገወጥ ደብዳቤ በመኖሩ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መሆኑን፣ በሐገረ ስብከቱ በኩል ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የእምቢተኛነት መንፈስ ከመታየቱም በተጨማሪ፣ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሚተላለፉ መመሪያዎችም ሆኑ ውሳኔዎች ምላሽ በማይሰጥባቸው ደረጃ ላይ መደረሱን መግለፃቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤና በቋሚ ሲኖዶስ ተወስነው ያልተፈፀሙ ጉዳዮችን እየተከታተለ የሚያስፈፅም አንድ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቢቋቋምም የሐገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በኮሚቴው ስም ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ለመምሪያዎች፣ ድርጅቶችና ለሠራተኞች ባስተላለፏቸው ተደጋጋሚ ደብዳቤዎች፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቃለ ዓዋዲ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑና የመሥሪያ ቤቱ መዋቅር እንዲጣስ መደረጉን በስብሰባው ወቅት ትኩረት የተሰጣቸው ነጥቦች መሆናቸውን ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ በኩል እየታየ ያለው ችግር በቅርብ የተከሰተ አለመሆኑን የገለፁት የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ ድርጊቱ የቆየና የኖረ መሆኑን፣ ከላይ የመጣ መመሪያን ያለመቀበል ብቻ ሳይሆን ከታችም መመሪያን ተቀብሎ ማስተናገድ ባለመቻሉ፤ የአብያተ ክርስቲያናቱ አገልጋዮች ኑሮአቸው የሰቀቀንና "ነገ ምን ይገጥመን ይሆን?" የሚል የሥጋት ኑሮ መሆኑ በምሬት መወሳቱን ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎች ጨምረው እንዳስረዱት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ሀገረ ስብከት መሆኑ በሕግ መደንገጉን አስታውሰው "ፓትርያርኩም ሆኑ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ቢጠሯችሁ፣ መመሪያ ቢሰጣችሁም እንዳትቀበሉ" በማለት ከሐገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሕገ ወጥ ደብዳቤ ቢተላለፍላቸውም፤ ትዕዛዙን ጥሰው በጉባኤው ላይ ሊገኙ መቻላቸውን መግለፃቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

በሀገረ ስብከቱ በየአብያተ ቤተ ክርስቲያናቱ የተመደቡ ሠራተኞች፤ ለመዳቢዎቻቸው ጥቅም አሰባሳቢ ሆነው ካልተገኙ አኗኗራቸው አደጋ ላይ የወደቀ መሆኑን እንደሚገለፅላቸው የተናገሩት የስብሰባው ተሳታዎች፣ በሀገረ ስብከቱ የሕንፃ ግንባታና በሌሎችም ሙስና በተካሄደባቸው ዘርፎች ጥያቄ እንዳላቸው በመግለፅ ቅዱስ ሲኖዶሱ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎች በሀገረ ስብከቱ እየተከናወነ ያለውንና የእምነቱ ተከታዮች ምዕመናንን ያሳዘነ በርካታ አሳፋሪ ተግባራትና የስነ ምግባር ጉድለት በተለይም የጥንታዊ ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት በሚቃረን መልኩ ቅዳሴን፣ ፀሎትና ትምህርት በኢንተርኔት መረብ መከታተልና መፈጸም እንደሚቻል ያስተላለፉትን መልዕክት አበክረው እንደሚቃወሙት መግለፃቸውን ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ በብፁዕ አቡነ ይስሐቅ እና ንቡረዕድ አብርሃ የመክፈቻ ንግግር የተጀመረው የአንድ ቀን ውይይት ሰባት ነጥብ ያለው የአቋም መግለጫ በማውጣት መጠናቀቁን ምንጮች ገልፀዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ጋር የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ አቡነ ጢሞቲዎስም የታገዱ መሆናቸውን፣ ነገር ግን ሰኔ 19 ቀን 2001 ዓ.ም. ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ በመመለስ ይቅርታ ጠይቀው በመታረቃቸው ምናልባት እግዱ ሊነሳላቸው እንደሚችል ምንጮቹ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሣሙኤልን አግኝተን ለማነጋገር በተደጋጋሚ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ሊያነሱልን ባለመቻላቸው ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡

1 comment:

Anonymous said...

Pretty good FALSE!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)