May 4, 2009

ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ


የእውነት መንገድ የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአጽራረ ቤተክርስቲያን ቅሰጣና ትንኮሳ ለዘመናት ስትጎነትል ኖራለች፡፡ ትንኮሳውና ቅሰጣው መልኩን እየቀያየረና ዘመናዊነትን እየተላበሰ ቀጥሎ አሁን ያለንበት ዘመን ድርሷል፡፡ ይህን እንድናነሳ ያደርገን በቅርቡ በአንድ የፕሮቴስታንት ድርጅት በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ክብርና ልዕልና የሚነካ ተግባር በመፈጸሙ ነው፡፡
ጉዳዩ እንዲህ ነው በቤተክርስቲያን ሥርዓት፣ የትምህርት ዝግጅት፣ የክህነት መዓረግ እና አገልግሎት የማይታወቅ አንድ ሰው በአንድ የፕሮቴስታንት ድርጅት ጉባኤ ላይ በመገኘት «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ነበርኩኝ፤ ስሜም «ብፁዕ አቡነ ያሬድ ጥላሁን እባላለሁ» በአዲስ አበባ በተለያዩ አድባራት ለ17 ዓመት በአስተዳዳሪነት አገልግያለሁ፡፡ በመድኃኒት አሳብደውኝ በሽተኛ ሁኜ ነበር፤ አሁን ግን በጌታ ድኛለሁ» በማለት በቤተክርስቲያኒቷ ሥልጣነ ክህነትና መዐርግ ያልኖረበትን፣ እና ያላገለገለበትን ተግባር ነበርኩ በማለት የቤተክርሰቲያኒቱን ስምና ልዕልና የሚያጎድፍ «ምስክርነት ሲሰጥ» ተደምጧል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ምስጢረ ክህነት ከፍ ያለ ምስጢር ነው፡፡ የማሠር የመፍታት ሥልጣን ያለው፤ ሌሎችንም የቤተክርስቲያን ምስጢራት ለማክበር ለመፈጸም ችሎታ ያለው /የተመረጠ/፤ ክርስቶስ የመሠረተውና የሠራው ሥርዓት ነው፡፡ ከእርሱም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያላማቋረጥ የሚሰጥ ጸጋ ነው፡፡ ይህንንም ሥልጣን ክርስቶስ ለሐዋርያት በንፍሐት በአንብሮተእድ ስጥቷ ቸዋል፡፡ ዮሐንስ 20 ፣ 21 እና 23፣ ሉቃስ 24.50፣ ከዚያም ሐዋርያት ከጌታ የተቀበሉትን ለተከታዮቻቸው በመስጠት ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ከሐዋርያት የተቀበለችውን ሥርዓት ይዛ ዛሬ ድረስ ክርስቶስ ለመረጣቸው /ለለያቸው/ ስልጣነ ክህነትን ስትሰጥ ቆይታለች፡፡ ወደፊትም እስከምጽአት ይቀጥላል፡፡

ሊቃነ ጳጳሳት ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ ክርስቶስ የሾማቸው የሐዋርያት ተከታዮች ናቸው፡፡ /የሐዋርያት ሥራ 20:28/ አንድ ጳጳስ ሲሾም ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ይገኛሉ፡፡ ይህም ሹመት ያለ ኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤ አይደረግም፡፡ የሚሾመውም ሰው ነውር የሌለበት የተማረ በልቡናው ከሐኬት የነቃ፣ እንግዳ መቀበልን የሚወድ፣ አብዝቶ የማይጠጣ ወዘተ መሆኑ የተመሠከረለት ሲሆን ነው፡፡
ስለዚህም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተመርጦ በአንብሮተ ዕድና በቅብዐተ መንፈስ ቅዱሰ የሚሾመው አባት «ብፁዕ» የሚል ቅጽል ይሰጠዋል፡፡ ከጳጳሳት በታች ያለ ማንኛውም ሠልጣነ ክህነት ያለው ሰው ይህ ቅጽል አይሰጠውም፡፡ በመሆኑም ይህ ሰው «ብፁዕ...» እባላላሁ ሲል ጳጳስ ነበርኩ እያለ ነው፡፡

የዚህ ሐሰተኛ ግለሰብ ድርጊት ግን ዐይን ያወጣ ውሸት መሆኑን ሁሉም ሊያውቀው ሊረዳው ይገባል፡፡ ግለሰቡ ብፁዕ የሚለው ቅጽል ለማን እንኳን እንደሚሰጥ ያልተረዳ ዋሾ /ብልጣ ብልጥ እበላ ባይ/ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ይህ ግለሰብ እንኳን ካህን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመን ሆኖ እንደማያውቅ ከአነጋገሩ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በቤተክርስቲያናችን አንድ ሰው ራሱን ብፁዕ ብሎ አይጠራም፤ ከላይ በመግቢያችን ለማሳየት እንደሞከርነው በቤተክርስቲያናችን በጸሎትና በቅብዐ መንፈስ ቅዱስ ብፁዕ ይባላል እንጂ፤ በየቦታው በየአጋጣሚው ራሱን ብፁዕ ብሎ አይገልጽም፡፡ የቤተክርሰቲያንችንም ሥርዓት፤ የአባቶቻችን ትምህርት ይህን አያስተምረንም፡፡ ግለሰቡ ግን የዕለት ምግብና ጊዜያዊ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ የአንዲትን ሉዐላዊት ቤተክርስቲያን ስምና መልካም ዝና ማጉደፍ፤ እንዲሁም ክብር በሚነካ ሁኔታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ሥርዓት ማፍለስ፣ የአባቶችን ስም ማጥፋት በሕግ ከመጠየቅ እንደማያድነው ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

የዚህን ህሊና ቢስ ተረታ ተግባር እና ውሸት በቪሲዲ፣ በኢንተርኔትና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ማስራጨት ወንጌልን አስተምራለሁ፤ ሞራልና ሥነ ምግባር አለኝ ከሚል የእምነት ድርጅት የማይጠበቅ መሆኑንም ለመናገር እንፈልጋለን፣ ድርጊቱ የአንድን ልዑላዊት ቤተክርሰቲያን ክብርና ልዕልና የሚጎዳና የሚያጎድፍ እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነውና፡፡

ድርጊቱም በሃይማኖት መካከል ግጭትን የሚያነሣሣ አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡ ይሄን አሳፋሪና አስነዋሪ ተግባር ማሰራጨት ከአንድ የሃይማኖት ድርጅት ይጠበቃልን) ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት እየደጋገሙ አባዝቶ መሸጥ እና በኢንተርኔት ማሰራጨት ምን ዓይነት ሥነ ምግባር ነው) የሃይማኖት ድርጅቱ በእውነት በሕግ እንደሚጠየቅ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡ ድርጊቱንም ሊመረምር፣ ስርጭቱንም ሊያስቆምና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በግልፅ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ በመሆኑም የቅሰጣና የማጥላላት ተግባር በሕግ የሚያስቀጣ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

የደርጊቱ ፈጻሚንም ሆነ በሃይማኖት ተቋም ስም ቪሲዲውን የሚያባዛ ካለ ለሕግ በማቅረብ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድበት መደረግ አለበት፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም ድርጊቱን ተከታትለው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱበት እንጠቁማለን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን በዚህ ድርጊት መሸበር እንዳሌለባቸው ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን መሪዋ ከሆነው ክርስቶስ ትዕግስት፣ ጽናትና ፍቅርን ለተከታዩቿ ስታስተምር ኖራለች፡፡ ወደፊትም ትኖራለች ተከታዮቿም ትምህርቷን ይዘው በቤተክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ፈተና በትዕግስት ሲያልፉት፣ በእምነት ከማይመስሏቸውም ጋር በፍቅር ሲኖሩ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡

ምእመናንም በጉዳዩ ሳይደናገጡ ተመሳሳይ ድርጊቶችን እግዚአብሔር እንዲገሰጽ በጸሎታቸው እንዲተጉ፤ በእምነት ያልጠነከሩትም ድርጊቱ እንደተለመደው በቤተክርስቲያን ላይ የተቃጣ የቅሰጣ ተግባር መሆኑን ተረድተው በእምነታቸው ሊጠነክሩ ይገባል እንላለን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ያሬድ የሚባሉ የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ አባት ያሏት እንጂ፤ ወደ ሌላ የእምነት ድርጅት የገባ ሊቀ ጳጳስ የላትም፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)