May 31, 2009

ታሪካዊው የ2001 ዓ.ም የቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ ሒደት “አዲስ ነገር” ጋዜጣ እንደዘገበውከግንቦት 6-13/2001 ዓ./ም የተሰበሰበው የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ሥራዎች ሰባት አባላት በሚገኙበት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቱ የበላይነት እንዲመራ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል። አዲሱ አሠራር ፓትርያርኩ በማናቸውም አስተዳደራዊ ሥራዎች ጣልቃ እንዳይገቡ ያደርጋል ተብሏል።
43 የቅ/ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በዚህ ጉባዔ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ አልፏል። ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የተባሉት አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አሁን ያለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ አሠራር እና የፓትርያርኩን አመራር በመተቸት ያቀረቡት ሐሳብ የሞቀ ክርክር እንዳስነሣ ለመረዳት ችለናል። ቅዱስ ፓትርያርኩ በበኩላቸው “የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሙስና ተስፋፍቶበታል” በማለት ሀገረ ስብከቱን ለአራት ለመክፈል ያቀረቡት ሐሳብ ከብዙ ውይይት በሁዋላ እንዲቀር መደረጉም ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ፓትርያርኩ 18 ተጨማሪ ጳጳሳትን ለመሾም ያቀረቡት ሐሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱም ታውቋል። የሹመቱ ሐሳብ ውድቅ የተደረገው በበጀት እጥረት እና በአቀራረቡ የተሟላ አለመሆን ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ “የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ መነጋገሪያ መሆን ያለበት ሹመት ሳይሆን ሌላ ነው” ያሉት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አንገብጋቢ ችግሮችን እና የመፍትሔ ሐሳቦችን አያይዘው ያቀረቡ ሲሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ተፈጸሙ ያሏቸውን የሙስና ግባራት እንዲሁም በቅዱስ ፓትርያርኩ ፈጽመዋል የሚሏቸውን የአስተዳደር ጣልቃ ገብነቶች በዝርዝር ማቅረባቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔዎችም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች በፓትርያርኩ ላይ “ይህን የመሰለ ግልጽና የተብራራ ወቀሳ ቀርቦ አያውቅም” ያሉት ምንጮች እንደሚያስረዱት የውይይት ሐሳብ ያቀረቡት ሊቃነ ጳጳሳት በርካታ ጉዳዮችን ማንሣታቸውን ገልጸዋል። ሐሳብ አቅራቢዎቹ በጉባዔው ላይ እንደተናገሩት ከሆነ የቀድሞውን ፓትርያርክ ጨምሮ አሜሪካ በሚገኙት እና አገር ቤት ባለው ዋናወ ሲኖዶስ መካከል የተፈጠረው ችግር እንዳይፈታ እንቅፋት የሆኑት ፓትርያርኩ ናቸው ብለዋል።
ፓትርያርኩ ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ሊቃነ ጳጳሳትን ከአንዱ አገረ ስብከት ወደ ሌላው ያዛውራሉ፤ የቤተ ክህነቱን ውራ አስኪያጅ ስልጣን በመጋፋት በተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሾመዋል፣ ሽረዋል፣ ቀጥረዋል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሚዲያዎች ግልጽ አሠራርና ኤዲቶርያል ፖሊሲ የሌላቸው የግል መጠቀሚያ አድርገዋቸዋል፣ አሠራሩ ከሚፈቅደው ውጪ ቨግል ትእዛዛቸው ገንዘብ ሠጪ አድርገዋል የሚሉት ወቀሳዎች ለሲኖዶሱ ከቀረቡት በርካታ ሐሳቦች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
ሐሳብ አቅራቢዎቹ ቅ/ፓትርያርኩ ያለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ፈቃድ አሜሪካ ለሚገኘው “የሀገር ፍቅር ሬዲዮ” አዘጋጅ አንድ መቶ ሺህ ብር እንዲሰጥ ማድረጋቸውን ከመጥቀሳቸውም በላይ በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያኒቱ በከፍተኛ የገንዘብ ችግር ውስጥ እንደምትገኝ ለጉባዔው አስረድተዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ያሏት ተከታዮች ብዛትና ግዴታ ያህል የሚጠበቅባትን እያበረከተች አለመሆኑን የገለጹት ሐሳብ አቅራቢዎቹ መሠረታዊ የሠራር ለውጥ ልታካሂድ እንደሚገባት መጠየቃቸውም ታውቃል።
በዘመድና በሙስና የሚፈጸም የሠራተኛ ቅጥር፤ ቁጥጥር የማይደረግበት የንብረት እና የገንዘብ አስተዳደር እንዲወገድ የአሠራር ለውጥ እንደሚያስፈልግ በዚሁ የውይይት አጀንዳ የተጠየቀ ሲሆን ከአስተዳደሩም ባሻገር ቀኞናዊ ጉዳዮችን እና ጥያቄዎችን የቤተ ክርስቲያኒቱን ተውፊትና አንድነት በማይጻረር መልኩ የሚያስተናግድና መልስ የሚሰጥ አሠራር መፈጠር እንዳለበት ማሳሰባቸውን የምንጮቻችን ዘገባ ይጠቁማል።
እነዚህን እና በጉባዔው የተጠቀሱትን በርካታ ችግሮች ለመፍታት ውዱስ ፓትርያርኩ ጣልቃ የማይገቡበት፣ ሙሉ ሥልጣን ያለው “የቅዱስ ሲኖዶስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ” በሲኖዶሱ እንዲቋቋም፣ የሥራ ዘመኑም አንድ ዓመት እንዲሆን በውይይት ሐሳብ ቀርቧል።
በቀረቡት ወቀሳዎችና የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ውይይት ያደረገው ሲኖዶሱ በመጨረሻ አባት አባላት የሚገኙነበት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ማቋቋሙ ታውቋል። ቤተ ክርስቲያኒቱ በራሷፓትርያርክ መመራት ከጀመረች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ “የፓትርያርኩን አስተዳደራዊ የበላይነት በማስቀረትመንፈሳዊ አመራር ብቻ እንዲሰጡ ያደርጋል” የተባለለት ይህ አሠራር በተግባር ላይ ከዋለ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ተገልጿል። በአዲሱ አሠራር የመጀመሪያው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በመሆን የተመረጡት ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነመልከ ጼዴቅ፣ ብፁዕ አቡነእስጢፋኖስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ብፁዕ አቡነሳሙኤል እና ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ናቸው። ከዚህ ኮሚቴ በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚሰጡ ከፍተኛ ሹመቶችን የሚከታተል ልዩ ኮሚቴም ተቋቁሟል””
ይህ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በየመስኩ ሞያዊ ምክር የሚሰጡት አማካሪዎች እንደሚኖሩት ምንጮቻችን ገልጸዋል። አዲሱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሥራውን መቼና እንዴት እንደሚጀምር እንዲሁም ተግባራዊ እንቅስቃሴው ምን መልክ እንደሚኖረው ጥናት ካደረገ በሁዋላ በቅርቡ መግለጨቫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል። እነዚህ የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች በቅርቡ ለመንግሥትና ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚተላለፉ ታውቋል።

May 27, 2009

ቅዱስ ሲኖዶስ የፓትርያርክ ጳውሎስን ሥልጣን ገደበ፤ ታሪካዊ ውሳኔ አሳለፈ


(አዲስ አበባ)፦ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ባካሄደው ታሪካዊና ወሳኝ ጉባዔው በቤተ ክርስቲያን ወቅታዊና ወሳኝ ዩዳዮች ላይ በመነጋገር ውሳኔ ሲያሳልፍ፣ ቤተ ክርስቲያንን በሙስና (ኮራፕሽን) ዘፍቀዋል፣ ክብሯን አዋርደዋል፣ አንድነቷን አደጋ ላይ ጥለዋል፣ ሚዲያዎቿን ለግል ጥቅማቸውና ጠላቶቻቸውን ለማዋረድ ተጠቅመውበታል ያላቸውን ፓትርያርኩን “ከቡራኬ ውጪ” በየትኛውም ዓይነት አስተዳደርና የሹመት ሥራዎች ውስጥ እንዳይገቡ አግዷቸዋል።
በቤተ ክርስቲያኒቱ የቅርብ ዘመን የአባቶች ታሪክ ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ መልኩ በመንፈሳዊ አርበኝነት ፓትርያርኩን የተቋቋሟቸው ብፁዓን አባቶች እንደቀድሞው ለማስፈራራት፣ “ጉዳችሁን ነው የማፈላው” ያሉትን ፓትርያርክ ሳይፈሩ በመንቀሳቀስ ቤተ ክርስቲያኒቱ “አበቃላት፣ አከተመላት” የተባለው የተቀናቃኞቿን ጉራ የሚያከሽፍ ተግባር ፈጽመዋል። በተለይም የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በፓትርያርኩ የተደገሰላቸውን የሽረት አዋጅ ወደ ጎን በማለት፣ “በሙስና ያቀረቡባቸውን” ውንጀላ በማለፍ ኢልቁንም ዋነኛው የሙስና አባትና መሪ እርሳቸው ራሳቸው ፓትርያርኩ መሆናቸውን ለጉባዔተኛው በማስረዳት ይህንን ታሪካዊ ውሳኔ ለማሳለፍ ችለዋል። በዚህም መሠረት ፓትርያርክ ጳውሎስ እንደከዚህ በፊቱ የፈለጉትን መሾም የጠሉትን መሻር የማይችሉ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኒቱን “በዝምድና፣ በአምቻ፣ በጋብቻ” የተቆናጠጧት ዘመዶቻቸውም እንደለመዱት ሀብቷን ለመዝረፍ እንደማይመቻቸው ምንጮቻችን ገልጸዋል።
ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል (ከቀድሞው ፓትርያርክና ከሌሎች አባቶች ጋር ያለውን)ልዩነት ከማጥበብ ይልቅ እይሳፉ ቤተ ክርስቲያን እንድትከፈል የሚያደርጉት ጥረት ሳያንስ በሀገር ቤት አስተዳደርም ዘመዶቻቸውን በመሾም ሀብቷ እንዲባክን ማድረጋቸው በተጠቀሰበት በዚህ ጉባዔ ዝናውን በውጪ ሀገርም ለማስነገር አሜሪካ ለሚገኘው የሀገር ፍቅር ሬዲዮ አስር ሺህ ዶላር መስጠታቸው ተገልጿል። አቶ ንጉሴ ወ/ማርያም ለተባለ ዲሲና አካባቢው ጋዜጠኛ 100 ሺህ ብር ሰጥተዋል የተባሉት ፓትርያርክ ጳውሎስ በርግጥም ይህንን አድርገው ከሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ገዳሞችና አድባራት እንዲሁም ሊቃውንት በችጋር እየተሰደዱ ሳሉ ገንዘቡን ያለ ርህራሄ ያባከኑ መሪ ያሰኛቸዋል።
የዚህን ታሪካዊ ጉባዔ ዝርዝር እንደደረሰን እናቀርባለን።

ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን


May 5, 2009

ለሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ሊደረግ የነበረው ሽልማት ውዝግብ አስነሳ

Sunday, 03 May 2009 20:41
Ethiopia Zare (እሁድ ሚያዝያ 26 ቀን 2001 ዓ.ም. May 3, 2009)፦ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጳጳስና ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ረዳት ለሆኑት አቡነ ሣሙኤል ተግዝቶ ሊሰጣቸው የነበረው የ1.5 ሚሊዮን ብር ሽልማት ውዝግብ አስነሳ።

የቤተክህነት ምንጮች ለኢትዮጵያ ዛሬ እንደገለጹት፤ ከሁለት ወራት በፊት የከምባታ፣ ሃዲያ፣ ጉራጌና ስልጤ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ለሆኑት አቡነ መልከጸዲቅ የክልሉ ተወላጆችና የታወቁ ነጋዴዎች ናቸው የሸለሟቸው በሚል የ1.3 ሚሊዮን ብር ሞዴሉ ቶዮታ የሆነ ፕራዶ መኪና የሸለሟቸው ሲሆን፤ “በርካታ ቤተክርስቲያናት በተቸገሩበት ወቅት ለአንድ የኃይማኖት መሪ እንዲህ ያለ ሽልማት መስጠቱና መቀበሉ ከኃይማኖት ሰዎች የሚጠበቅ አይደለም” የሚል ትችት አስነስቶ ነበር።


ከሁለት ሣምንት በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ በንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ ሰብሳቢነት አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኙ ቅርንጫፍ ቤተክርስቲያናት፤ “… በቅርቡ አራት ኪሎ ብርሃን ሠላም ማተሚያ ቤት ጀርባ የሚገኘው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያሠራውን ህንጻ ያስመርቃል። በዚህ የምረቃ በዓል ላይ የአዲስ አበባውን የሀገረ ስብከት ጳጳስና የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ረዳት አቡነ ሣሙኤልን ሳያውቁት ሽልማት አዘጋጅተን ልንሰጣቸው ስለሆነ ከየአጥቢያችሁ የ15 ሺህ ብር እንድታዋጡ …” የሚል ነው።

አቡነ ሣሙኤል በአንዳንድ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች የተወደዱ በመሆናቸው ደብዳቤው ከደረሳቸው አጥቢያዎች የአንዱ አስተዳዳሪ ጠጋ ብለው ሳያውቁ ተዘጋጅቶ ሊሰጣቸው ስለታሰበው ሽልማትና አጥቢያዎቹ አዋጡ ስለተባሉት ገንዘብ ሹክ ይሏቸዋል።

አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ አጥቢያ ቤተክርስቲያኖች ወደ 100 ደርሰዋል፣ እነዚህ እያንዳንዳቸው 15 ሺ ብር ቢያዋጡ ወደ 1.5 የኢትዮጵያ ብር ይደርሳል። ሊገዛ የታሰበው መኪና ዋጋ ደግሞ 1.3 ሚሊዮን ሲሆን፣ አንደኛ፦ የተከበረ ስማቸው እንደአቡነ መልከጸዲቅ እንዳይጠፋ፣ መዋጮው ለሙስና የሚጋብዝ መሆኑን በመጠቆምም ወዳጆቻቸው ምክር ይለግሷቸዋል።

አቡነ ሣሙኤልም “አለመስማቴ ነው እንጂ ብሰማ እስካሁንም ዝም አልልም ነበር” በማለት እጅግ ተቆጥተው የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃን በማስጠራት፤ “በኔ ስም የጀመራችሁትን መዋጮ በአስቸኳይ እንድታቆሙ እኔ ሳላውቅስ እንዲህ ያለ ሥራ እንዴት ይሠራል በርካታ ቤተክርስቲያናት በችግር ላይና በምዕመና ዕርዳታ ላይ እያሉ እንዴት ይህን ያህል ገንዘብ ለማስወጣት ትንቀሳቀሳላችሁ?” ብለው እንዲያቆሙ ትዕዛዝ አስተላልፈውላቸዋል።

የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ በበኩላቸው ሽልማቱን ለማዘጋጀት የወሰኑት እሳቸው እየሠሩ ላሉት ሥራ ድጋፍ ይሆናል ብሎ በማሰብ መሆኑን በመግለጽ ይቅር ካሉ ማስቀረት እንደሚቻል ማስረዳታቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም አቡነ መልከጸዲቅን የክልሉ ተወላጆችና የታወቁ ነጋዴዎች ናቸው ያዘጋጁት በሚል የ1.3 ሚሊዮን ብር መኪና ሰጥተዋቸዋል። ሽልማት የሚጠላ ባይሆንም ስንት የሚሠራ ሥራ እያለ ያውም ለኃይማኖት አባት እንዲህ ያለ ስጦታ ገዝቶ መስጠቱ አግባብ አልነበረም ሲሉ ይደመድማሉ።

May 4, 2009

ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ


የእውነት መንገድ የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአጽራረ ቤተክርስቲያን ቅሰጣና ትንኮሳ ለዘመናት ስትጎነትል ኖራለች፡፡ ትንኮሳውና ቅሰጣው መልኩን እየቀያየረና ዘመናዊነትን እየተላበሰ ቀጥሎ አሁን ያለንበት ዘመን ድርሷል፡፡ ይህን እንድናነሳ ያደርገን በቅርቡ በአንድ የፕሮቴስታንት ድርጅት በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ክብርና ልዕልና የሚነካ ተግባር በመፈጸሙ ነው፡፡
ጉዳዩ እንዲህ ነው በቤተክርስቲያን ሥርዓት፣ የትምህርት ዝግጅት፣ የክህነት መዓረግ እና አገልግሎት የማይታወቅ አንድ ሰው በአንድ የፕሮቴስታንት ድርጅት ጉባኤ ላይ በመገኘት «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ነበርኩኝ፤ ስሜም «ብፁዕ አቡነ ያሬድ ጥላሁን እባላለሁ» በአዲስ አበባ በተለያዩ አድባራት ለ17 ዓመት በአስተዳዳሪነት አገልግያለሁ፡፡ በመድኃኒት አሳብደውኝ በሽተኛ ሁኜ ነበር፤ አሁን ግን በጌታ ድኛለሁ» በማለት በቤተክርስቲያኒቷ ሥልጣነ ክህነትና መዐርግ ያልኖረበትን፣ እና ያላገለገለበትን ተግባር ነበርኩ በማለት የቤተክርሰቲያኒቱን ስምና ልዕልና የሚያጎድፍ «ምስክርነት ሲሰጥ» ተደምጧል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ምስጢረ ክህነት ከፍ ያለ ምስጢር ነው፡፡ የማሠር የመፍታት ሥልጣን ያለው፤ ሌሎችንም የቤተክርስቲያን ምስጢራት ለማክበር ለመፈጸም ችሎታ ያለው /የተመረጠ/፤ ክርስቶስ የመሠረተውና የሠራው ሥርዓት ነው፡፡ ከእርሱም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያላማቋረጥ የሚሰጥ ጸጋ ነው፡፡ ይህንንም ሥልጣን ክርስቶስ ለሐዋርያት በንፍሐት በአንብሮተእድ ስጥቷ ቸዋል፡፡ ዮሐንስ 20 ፣ 21 እና 23፣ ሉቃስ 24.50፣ ከዚያም ሐዋርያት ከጌታ የተቀበሉትን ለተከታዮቻቸው በመስጠት ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ከሐዋርያት የተቀበለችውን ሥርዓት ይዛ ዛሬ ድረስ ክርስቶስ ለመረጣቸው /ለለያቸው/ ስልጣነ ክህነትን ስትሰጥ ቆይታለች፡፡ ወደፊትም እስከምጽአት ይቀጥላል፡፡

ሊቃነ ጳጳሳት ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ ክርስቶስ የሾማቸው የሐዋርያት ተከታዮች ናቸው፡፡ /የሐዋርያት ሥራ 20:28/ አንድ ጳጳስ ሲሾም ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ይገኛሉ፡፡ ይህም ሹመት ያለ ኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤ አይደረግም፡፡ የሚሾመውም ሰው ነውር የሌለበት የተማረ በልቡናው ከሐኬት የነቃ፣ እንግዳ መቀበልን የሚወድ፣ አብዝቶ የማይጠጣ ወዘተ መሆኑ የተመሠከረለት ሲሆን ነው፡፡
ስለዚህም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተመርጦ በአንብሮተ ዕድና በቅብዐተ መንፈስ ቅዱሰ የሚሾመው አባት «ብፁዕ» የሚል ቅጽል ይሰጠዋል፡፡ ከጳጳሳት በታች ያለ ማንኛውም ሠልጣነ ክህነት ያለው ሰው ይህ ቅጽል አይሰጠውም፡፡ በመሆኑም ይህ ሰው «ብፁዕ...» እባላላሁ ሲል ጳጳስ ነበርኩ እያለ ነው፡፡

የዚህ ሐሰተኛ ግለሰብ ድርጊት ግን ዐይን ያወጣ ውሸት መሆኑን ሁሉም ሊያውቀው ሊረዳው ይገባል፡፡ ግለሰቡ ብፁዕ የሚለው ቅጽል ለማን እንኳን እንደሚሰጥ ያልተረዳ ዋሾ /ብልጣ ብልጥ እበላ ባይ/ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ይህ ግለሰብ እንኳን ካህን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመን ሆኖ እንደማያውቅ ከአነጋገሩ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በቤተክርስቲያናችን አንድ ሰው ራሱን ብፁዕ ብሎ አይጠራም፤ ከላይ በመግቢያችን ለማሳየት እንደሞከርነው በቤተክርስቲያናችን በጸሎትና በቅብዐ መንፈስ ቅዱስ ብፁዕ ይባላል እንጂ፤ በየቦታው በየአጋጣሚው ራሱን ብፁዕ ብሎ አይገልጽም፡፡ የቤተክርሰቲያንችንም ሥርዓት፤ የአባቶቻችን ትምህርት ይህን አያስተምረንም፡፡ ግለሰቡ ግን የዕለት ምግብና ጊዜያዊ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ የአንዲትን ሉዐላዊት ቤተክርስቲያን ስምና መልካም ዝና ማጉደፍ፤ እንዲሁም ክብር በሚነካ ሁኔታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ሥርዓት ማፍለስ፣ የአባቶችን ስም ማጥፋት በሕግ ከመጠየቅ እንደማያድነው ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

የዚህን ህሊና ቢስ ተረታ ተግባር እና ውሸት በቪሲዲ፣ በኢንተርኔትና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ማስራጨት ወንጌልን አስተምራለሁ፤ ሞራልና ሥነ ምግባር አለኝ ከሚል የእምነት ድርጅት የማይጠበቅ መሆኑንም ለመናገር እንፈልጋለን፣ ድርጊቱ የአንድን ልዑላዊት ቤተክርሰቲያን ክብርና ልዕልና የሚጎዳና የሚያጎድፍ እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነውና፡፡

ድርጊቱም በሃይማኖት መካከል ግጭትን የሚያነሣሣ አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡ ይሄን አሳፋሪና አስነዋሪ ተግባር ማሰራጨት ከአንድ የሃይማኖት ድርጅት ይጠበቃልን) ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት እየደጋገሙ አባዝቶ መሸጥ እና በኢንተርኔት ማሰራጨት ምን ዓይነት ሥነ ምግባር ነው) የሃይማኖት ድርጅቱ በእውነት በሕግ እንደሚጠየቅ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡ ድርጊቱንም ሊመረምር፣ ስርጭቱንም ሊያስቆምና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በግልፅ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ በመሆኑም የቅሰጣና የማጥላላት ተግባር በሕግ የሚያስቀጣ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

የደርጊቱ ፈጻሚንም ሆነ በሃይማኖት ተቋም ስም ቪሲዲውን የሚያባዛ ካለ ለሕግ በማቅረብ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድበት መደረግ አለበት፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም ድርጊቱን ተከታትለው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱበት እንጠቁማለን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን በዚህ ድርጊት መሸበር እንዳሌለባቸው ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን መሪዋ ከሆነው ክርስቶስ ትዕግስት፣ ጽናትና ፍቅርን ለተከታዩቿ ስታስተምር ኖራለች፡፡ ወደፊትም ትኖራለች ተከታዮቿም ትምህርቷን ይዘው በቤተክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ፈተና በትዕግስት ሲያልፉት፣ በእምነት ከማይመስሏቸውም ጋር በፍቅር ሲኖሩ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡

ምእመናንም በጉዳዩ ሳይደናገጡ ተመሳሳይ ድርጊቶችን እግዚአብሔር እንዲገሰጽ በጸሎታቸው እንዲተጉ፤ በእምነት ያልጠነከሩትም ድርጊቱ እንደተለመደው በቤተክርስቲያን ላይ የተቃጣ የቅሰጣ ተግባር መሆኑን ተረድተው በእምነታቸው ሊጠነክሩ ይገባል እንላለን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ያሬድ የሚባሉ የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ አባት ያሏት እንጂ፤ ወደ ሌላ የእምነት ድርጅት የገባ ሊቀ ጳጳስ የላትም፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

May 3, 2009

ሐይማኖትን የፖለቲካ መሳሪያ የማድረግ አዝማሚያ አገሪቷን የመበታተን ዓላማ እንዳለው ተገለጸ

Saturday, 02 May 2009
ጅጅጋ፤ ሚያዚያ 24/2001/ዋኢማ/ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ መታየት የጀመረው ሐይማኖትን የፖለቲካ መሳሪያ የማድረግ አዝማሚያ አገሪቷን የመበታተን ዓላማ ያለው በመሆኑ ድርጊቱ ሊታገስ እንደማይገባ የሶማሌ ክልል የመንግስት ሠራተኞችና ምሁራን ገለጹ። ሠራተኞችና ምሁራኑ በጉዳዩ ላይ ዛሬ ከክልሉ አመራር አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል።
በጅጅጋ ሁለገብ አዳራሽ የአንድ ቀን ውይይት ያደረጉት የክልሉ የመንግስት ሠራተኞችና ምሁራን እንደገለጹት፤ የአገሪቷን ህገ መንግስትና ሐይማኖታዊ መርሆችን በሚፃረር መልኩ ሐይማኖትን እንደ ሽፋን በመጠቀም የፖለቲካ ዓላማን ለማሳካት የሚደረገው ሙከራ ጥፋትን ከማስከተል ውጭ ማንንም የሚጠቅም አይደለም።
ስለሐይማኖት ምንም ደንታ የሌላቸው ግለሰቦች ወደ እምነት ተቋማት ጎራ እያሉ ምዕመናንን የሚያሳስትና ለግጭት የሚያነሳሳ ፖለቲካ እንደሚሰብኩ ያመለከቱት ሠራተኞችና ምሁራኑ ይህ የጥፋት ድርጊታቸው በዝምታ መታለፍ የለበትም ብለዋል።

ቀደም ሲል ሰዎችን በሐይማኖት ስም ቀስቅሰው ህብረተሰቡን ከጎናቸው ለማሰለፍ ሲፍጨረጨሩ የነበሩት ራሱን የኦጋዴን ነፃነት ግንባር ብሎ የሚጠራውና እነ አልሂታድ አል እስላሚያ የመሳሰሉ አሸባሪ ቡድኖች ብቻ እንደነበሩ የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን በፌዴራል ደረጃ ህገ መንግስቱ በማይፈቅድላቸው መንገድ ስልጣንን ለመቆናጠጥ ሞክረው ያልተሳካላቸው ኃይሎች ጭምር ህብረተሰቡን በሐይማኖት ሰበብ አጋጭተው ህልማቸውን እውን ለማድረግ ጥረት መጀመራቸው እጅግ አደገኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
የመንግስት ሠራተኞችና ምሁራኑን ያወያዩት የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ አረብ በበኩላቸው፤ ለነፃና ሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር ብቃት የሌላቸው ፖለቲከኞችና ፀረ ሰላም ኃይሎች በሐይማኖት ሽፋን ፍላጎታቸውን ለማሳካት የጀመሩትን ዘመቻ ጠንቅቆ በመረዳት መከላከልና ሴራቸውን ማክሸፍ ይገባል ብለዋል።
የመንግስት ሠራተኞችም መንግስታዊ አገልግሎቶችን ከሐይማኖታዊ ወገንተኝነት ነፃ በማድረግና ሁሉንም በእኩል በማገልገል ህገ መንግስታዊ ግዴታቸውን የመወጣት ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የክልሉ የመንግስት ሠራተኞችና ምሁራኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስና ተጽዕኖውን መቀነስ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ውይይት ማድረጋቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)