April 2, 2009

ላሉት የሕልውና ጥንካሬን፤ ለጠፉት ትንሣኤን የሚሰጥ ተስፋ

ላሉት የሕልውና ጥንካሬን፤ ለጠፉት ትንሣኤን የሚሰጥ ተስፋ
የደብረ አሜን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ የሚገኘው ትንሽ አዳራሽ በምእመናን ተጨናንቋል፡፡ እሁድ ኅዳር 21 ቀን 2001 ዓ.ም፡፡ የመለከት መጽሔት ኅትመት የጀመረበት 17ኛ ዓመት ለማክበር ነው፤ የምእመናኑ የመሰብሰብ ምክንያት፡፡ እናም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተወካይ ላዕከ ወንጌል በዕደ ማርያም ለክብረ በዓሉ የተዘጋጀውን ሻማ ከለኮሱ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት የተጀመረው ይህ በዓል በጸሎት፣ በውይይት፣ በምስጋናና በዝማሬ ደምቆ ነበር፡፡ መለከት መጽሔት በነዚህ ዓመታት የእግዚአብሔርን ቃል ለምእመናን ለማድረስ ባደረገው ጥረት ብዙዎች በእምነታቸው እንዲጸኑ፣ ስለ ሃይማ ኖታቸው ጠንቅቀው እንዲረዱ፣ በተኩላዎች እንዳይነጠቁ፣ ለሥጋዊ እና መንፈሳዊ ሕይወታቸው ስንቅ የሚሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃልን እንዲያውቁ አስችሏል፡፡
በዚህ ክብረ በዓል ላይ በተሳታፊዎች ሲሰጥ በነበረው አስተያየት መጽሔቱ መጠንከር፣ የአንባቢያን ቁጥሯን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ያሉባትንም መጠነኛ ድክመቶች አርሞ የሃይማኖታዊ አስተምህሮ ተልዕኮዋን መወጣት እንዳለባት ነው፡፡ በእለቱ የቀረቡ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎችም ይህንኑ መልዕክት አጠናክረው የሚናገሩ ነበሩ፡፡
በተለይ በወ/ሪት መሠረት ከበደ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ የመጽሔቱን አጠቃላይ ድክመትና ጥንካሬ የዳሰሰ ሲሆን ወደፊት መከተል የሚ ኖርበትን አቅጣጫም ጠቁሟል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በመጽሔቱ ላይ የቀረበውን ጥናት መቃኘት አይደለም፡፡ በዚህ እለት «የመንፈሳዊ መጽሔቶችና ጋዜጦች የንባብና ሥርጭት ችግር» በሚል ርዕስ በአቶ ነፃነት ተስፋዬ የቀረበውን ጥናት በስሱ ለመዳሰስና በቅርቡ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በዚሁ ጉዳይ ላይ የተወያዩበትንና የአቋም መግለጫ ለማመላከት እንጂ፡፡
እንደሚታወቀው የመንፈሳዊ ጋዜጦች ኅትመት 8 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በ1939 ዓ.ም መንፈሳዊ የኅትመት ውጤቶች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር መታተም ከጀመሩ ወዲህ ዜና ቤተ ክርስቲያን፣ ድምፀ ተዋሕዶ እና ሌሎችም ጥቂት መንፈሳዊ ጋዜጦችና መጽሔቶች ለኅትመት በቅተው እንደነበር ይታወቃል፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር ከታተሙት በተጨማሪ መለከት እና ሐመር መጽሔት፣ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣና ሌሎችም መንፈሳዊ የኅትመት ውጤቶች ዛሬ ድረስ ምዕመናንን ሲያስተምሩና ሲያነቁ መቆየታቸው እሙን ነው፡፡
ጥናት አቅራቢው በጽሑፋቸው እንዳሰፈሩት እነዚህ የኅትመት ውጤቶች ቃለ እግዚአብሔርን በማስፋፋት ረገድ እየተጫወቱት ያለውሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
የመንፈሳዊ ጋዜጦች ኅትመት 8 ዓመት ታሪክ ቢኖረውም፤ ከአጀማ መሩ አንፃር ሲታይ ሂደቱ እጅግ አዝጋሚ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ከክርስቲያኑ ሕዝብ ቁጥርና ፍላጎት ጋር ሲታይ የኅትመት ብዛቱ፣ ዓይነቱም ሆነ ሥርጭቱ የሰማይና የምድር ያህል ነው ቢባል አልተጋነነም፡፡ ዛሬ ከሰባ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ከሚገመተው የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር በአብዛኛው ክርስቲያን ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ቁጥርም እጅግ ከፍተኛ እንደሆነም ይታመናል፡፡
አቶ ነፃነት የኅትመት ውጤቶችን በንፅፅር ሲያስቀምጡም በአሁኑ ወቅት የመንግሥትን ሳይጨምር ከ 22 በላይ ጋዜጦች በኅትመት ላይ ይገኛሉ፡፡ በውል የሚታወቁት መንፈሳዊ ጋዜጣዎችና መጽሔቶች ግን ከ6 አልበለጡም፡፡ እነዚም መንፈሳዊያን ጋዜጦችና መጽሔትም በወር በአማካኝ ከሃምሳ እስከ ሰባ ሺህ ቅጂዎች ብቻ ሲታተሙ ዓለማዊ ጋዜጦች ግን ዘጠኝ መቶ ሰባ ሁለት ሺህ ቅጂዎች ታትመው ለሥርጭት ይበቃሉ፡፡
እንደ ጥናቱ ዝርዝር ሠላሳ ስድስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ለሚሆኑ ምእመናን የሚደርሰው ከ70ሺ ያልበለጠ ኮፒ ነው፡፡ ይህ ኮፒ ለምእመናን ቃለ እግዚአብሔርን ማድረስ አስችሏል ብሎ ለመናገር የሚደፍር አይኖርም፡፡
ዛሬ ዛሬ የንባብ ባህል ቢያድግም በአሠረጫጨት ችግር ምክንያት የምእመናንን ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም፡፡ መንፈሳዊ ምግብን የመቋደስ እድል በጥቂት ዋና ዋና ከተሞች ብቻ መወሰኑም ይኸው የአሰረጫጨት ችግር መሆኑ በዚሁ ወቅት ተነግሯል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር መዋቅር ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ወጥ የሆነ የሥርጭት መስመር አለመኖር፣ የመጽሔትና ጋዜጣቹ ዝግጅት ሳቢ አለመሆን፣ ምእመናን ለዓለማዊ የኅትመት ውጤቶች ትኩረት መስጠት፣ የኅትመት ዋጋ ንረት እና የመሳሰሉት ምክ ንያቶች የመንፈሳዊ ኅትመቶች ወደ ምእመናን ዘንድ እንዳይደርስ እንቅፋት ሆነዋል፡፡
ለተጠቀሱት ችግሮች በጥናታዊ ጽሑፉ እንደ መፍትሔ የተቀመጡ ነጥቦችም አሉ፡፡ የጋዜጦቹንና የመጽሔቶችን አቀራረብ ይዘት እንደ ዘመኑ ሁኔታ ማስተካከል፣ ማሻሻል፣ በምእመናን ዘንድ የንባብ ባህልን ለማሳደግ መጣር ይገባል፡፡ በዚህም የሰርክ ጉባኤ፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የርዕሰ አድባራት፣ የጽዋና የጉዞ ማኅበራት እንዲሁም ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት አስተዋጽዖአቸው ከፍተኛ እንደሆነ በማሰብ እነርሱን መጠቀምም ተገቢ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በራሷ መዋቅር መጽሔቶችና ጋዜጦች የሚሰራጩበትን መንገድ መፍጠር፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ የንዋያተ ቅድሳት መሸጫ ሱቆችን አጠናክሮ መጠቀም፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በሥርጭቱ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማመቻቸትና የኅትመት ውጠ@ቶችን ለሚያድሉ ማስታወቂያ ማውጣት ችግሮቹን ለመቅረፍ እንደ መፍትሔ በጥናታዊ ጽሑፉ ተመልክቷል፡፡
ይህን ጥናታዊ ጽሑፍ መሠረት በማድረግ በእለቱ የተደረገው ውይይት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ጋር ለመ ድረስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቃለ እግዚአብሔርን የያዙ የኅትመት ውጤቶችን በዓይነትና በስፋት ማብዛት እንዳለባት ነው የተጠቆመው፡፡
ዛሬ በገበያ ላይ አሉ የተባሉት የኅትመት ውጤቶች ከሌሎች የሃይማኖት ድርጅቶች ኅትመቶች ጋር ሲነፃፀር ኢምንት መሆኑም ይታወቃል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ምእመናንን ወደ ሌላ ሃይማኖት የሚሳቡበትን ሁኔታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያባባሰው መምጣቱን በወቅቱ አንዳንድ ተሳታፊዎች ከሰጡት አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡
ይህ የመንፈሳዊ የኅትመት ውጤት የንባብና ሥርጭት ችግር መፍትሔ ያገኝ ዘንድ በተለያዩ መድረኮች መነሳቱ አልቀረም፡፡ በቅርቡ በኢትዮ ጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ¬ትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በተካሄደው የሁለት ቀን ሀገር አቀፍ የሰበካ ጉባኤ ሴሚናር ላይ የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጆ መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍም ይህንኑ የሚያስገነዝብ ነው፡፡
«ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶችን ያቀፈች፣ በየደብሩ አያሌ የአብነት መምህራን ያላት፣ ከመንፈሳዊ ኮሌጆች በድግሪና በዲፕሎም የተመረቁ፣ በተለያዩ ልሳናት የሚናገሩ የሥነ ጽሑፍ ችሎታ ያላቸውና የየራሳቸውን መጽሐፍ በመጻፍ ችሎታቸውን ያስመሰከሩ በርካታ ዘመናውያን ልጆች ያሏት ቤተ ክርስቲያን የሰው ኃይልና የገንዘብ አቅም እጥረት ሳይኖርባት በአስተዳደር ድክመት፣ የመደራጀትና የማደራጀት ክህሎት በማጣት ብቻ እንዴት በጋዜጣና መጽሔት ድርቅ ትመታ)» ሲሉ በጥናታዊ ጽሑፋቸው አምረው የገለጹት መጋቤ ምስጢር፤ የሴሚናሩ ተሳታፊዎች በጉዳዩ አንድ መፍትሔ ይፈልጉ ዘንድ የተማጽንኦ ቃላትም ሰንዝረዋል፡፡
የዚህ ሴሚናር ማጠቃለያ ላይ የተነበበው የአቋም መግለጫ ላይ ይህን ኅትመትን በማስመልከት የሰፈረው ነጥብ ተሳታፊዎቹ ጉዳዩን በጥልቀት የተገነዘቡት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአቋም መግለጫው ቁጥር አራት የሰፈረው ቃል እንዲህ ይላል፡፡
«በመንበረ ¬ትርያርኩ የሚታተመው ጋዜጣና መጽሔት ውስን መሆኑ ተነግሯል፡፡ እነዚህ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሥርጭታቸውም ችግር እንዳለበት ታውቋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ተልዕኮ ይሳካ ዘንድ ጋዜጦችና መጽሔቶች ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን ጋዜጦችና መጽሔቶች በሰው ኃይል በሊቃውንትም ተጠናክረው በብዛትና በጥራት እንዲታተሙ እስከ ቅርብ ዓመታትም እየታተሙ ለአንባቢዎች ይሰራጩ የነበሩ በአሁኑ ጊዜ የተቋረጡ መጽሔቶችና ጋዜጦች ኅትመታቸው እንዲቀጥል፣ አቅም ያላቸው የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤት አብያተ ክርስቲያናት የሊቃውንት ተሳትፎ ያልተለያቸው ትምህርታዊ ጽሑፎችን እያሳተሙ እንዲያሰራጩ ጉባኤው አበክሮ ይጠይቃል፡፡» ይህ አቋም ላሉት የሃይማኖት መጽሔቶች ህልውና መጠንከር፤ ለጠፉትም ትንሳኤን የሚያስገኝ ተስፋን ይሰጣል፡፡ በዚህ ረገድ የምእመናኑ ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡ በሃይማኖቱ እንዲጸና፣ እንዲጠነክር፣ እንዲበረታ፣ በእግዚአብሔር ቃል እየተጽናና፣ ነሕይወቱን እንዲያለመልም ብቃት፣ ጥራትና ብዛት ያላቸው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኅትመት ውጤቶች ያስፈልጉታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ እያንዳንዱ ደብር እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ከቡር፡፡
Source: Mahibere Kidusan WebsiteNo comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)