April 1, 2009

በሃይማኖት ጉዳይ - ተቃዋሚዎች ላይ ጣት ተቀሥሯል

በጌታቸው ንጋቱ
በኢትዮጵያ ባልተለመደ መልኩ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እዚህም እዚያም የሃይማኖት ግጭቶች ደረሱ ሲባል ምንድነው ነገሩ የሚል ጥያቄ በሁሉም ሕሊና ውስጥ ይነሳል፡፡ ኢሕአዴግ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መበራከታቸውን ሲገልፅ ሃይማኖትን መደበቂያ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች እንዳሉም ይገልፃል፡፡ ተቃዋሚዎች ሃይማኖትን ለፖለቲካ መጠቀሚያ እንደማያደርጉ ሲገልፁ የኢሕአዴግንም አገላለፅ "ጅምላ" ፍረጃ በማለት ይቃወማሉ፡፡
ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ይንቀሳቀሳሉ ያላቸውን የፖለቲካ ኃይሎችንም ኢሕአዴግ "የከሠሩ ፖለቲካኞች" ሲል ይገለፃቸዋል፡፡ ፓርቲው ልሣኑ በሆነው አዲስ ራዕይ መፅሄት ላይ እንደገለፀው "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች አክራሪና የከሠሩ ፖለቲከኞች ሃይማኖትን በሽፋንነት በመጠቀም ግጭት ለመቀስቀስ ሲሞክሩ ማየትና መስማት የተለመደ ነው፡፡ ሃይማኖትን በሽፋንነት ለመጠቀም የቆረጡት እነዚህ ወገኖች በአገራችን ለሃይማኖት እኩልነትና ነፃነት የተፈጠረውን አመቺ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ በመጠቀም የመንግሥትን ቻይነት እንደድክመት በመቁጠር በአደባባይ ሕግን ተላልፈው እስከመንቀሳቀስ ደርሰዋል" ሲል ያስረዳል፡፡

"ሃይማኖትን በሽፋንነት ለመጠቀም ሲደረግ የቆየው ሙከራ ከተጀመረ የሠነባበተ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የክርስትናንም ሆነ የእስልምና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚካሄደው ቅስቀሳና ማነሳሳት ገደቡን አልፎ ሲገለፅ ሠንብቷል" የሚለው ፓርቲው ጠብ ያለሽ በዳቦ ዓይነት አካሄድ በክርስትናም፤ በእስልምና ሃይማኖትም ውስጥ ሰርገው በገቡ ተቃዋሚዎች እየተፈፀመ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ተቃዋሚዎች በአንድ ቃል ይህንን የኢሕአዴግ ፍረጃ እንደማይቀበሉት ይገልፃሉ፡፡ ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ ተስፋ የቆረጡ ተቃዋሚዎች ፖለቲከኞች ሃይማኖትን በመጠቀም አጀንዳቸውን እያራመዱ እንደሆነ ይገልፃል፡፡

በሃይማኖት ሽፋን ግጭት ለመቀስቀስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በብቃት ለመመከት የሚቻለው መንስዔውን በትክክል መገንዘብ ሲቻል መሆኑን የሚገልፀው ፅሁፍ ለግጭት መንሥዔ ሊሆኑ አይችሉም ብሎ የሚያምንባቸውን ጉዳዮች በመጀመሪያ ይለያል፡፡ የመጀመሪያው አመለካከትም "ሃይማኖት መቼም ቢሆን የግጭት መንስዔ ሊሆን አይችልም" የሚል ነው፡፡ ይህም መነሻውን ያደገው ሃይማኖት ፍቅርና ሠላምን፤ ትዕግሥትና መቻቻልን እንጂ ጥላቻና ግጭትን የሚሰብክ ይዘት የለውም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው መነሻ "ሕገ መንግሥታዊ ስርዓታችን ለሃይማኖት ግጭት ቦታ የለውም" የሚል ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሃይማኖት የግል እንደሆነና በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሃይማኖቶች እኩል እንደሚታዩ ቢደነገግም "የከሰሩ ፖለቲካኞች ይህንን የሃይማኖት እኩልነት የረባ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ምክንያት በሌለበት ወቅት የሚካሄዱ ግጭቶች የመቀስቀስ ሙከራዎች መንስዔያቸው አሁንም ፍላጐታቸውን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ማራመድ የተሳናቸው ወገኖች እንደሆኑ አመላካች ነው" ይላል፡፡

በእርግጥ ኢሕአዴግ እንደሚለውና እንደሚያምነው ተቃዋሚዎች በሃይማኖት ግጭት እናተርፋለን ብለው ያስባሉ? ወይስ ኢሕአዴግ ትክክለኛ ባልሆነ መልኩ እየፈረጃቸው ነው? በትክክል በእንደዚህ ዓይነት የወንጀል ተግባር የተሰማሩ ተቃዋሚዎች ካሉስ የትኞቹ ናቸው? ካለስ ተለይተው ለምን ለፍርድ አይቀርቡም? የሚሉና ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡

ተቃዋሚዎቹ በዚህ ዙሪያ በሚሰጡት ምላሽ ኢሕአዴግ ሕዝቡን ለማሸማቀቅና ከተቃዋሚዎች ጋር የሚሰለፍ ኃይል እንዲጠፋ ሆን ብሎ የሚነዛው ፕሮፖጋንዳ ነው በማለት ይቃወማሉ፡፡ የፈንጂ አደጋ፣ የሃይማኖት ግጭት፣ የኤርትራ ጉዳይ በተነሱና በደረሱ ቁጥር ተቃዋሚዎች እጃቸው እንዳለበት ኢሕአዴግ መግለፁ የተቃዋሚውን ኃይል ከሕዝቡ ለመለየትና የራሱን አቅም ለማደራጀት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ኢሕአዴግ የፖለቲካ መድረኩን እያጠበበ መምጣቱን ከሚታይበት መንገድ አንዱ የሆነው እንደዚህ ዓይነቱ ፍርጃ ነው ይላሉ፡፡ ተቃዋሚዎቹ በአገሪቱ ሠላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለማድረግ እንጂ ለብጥብጥ እንዳልተደራጁም ይናገራሉ፡፡

"የአገር ውስጥ የከሠሩ ፖለቲከኞች ሃይማኖትን እንደ ምሽግ መጠቀም መርጠዋል" የሚለው የኢሕአዴግ ልሳን የሆነው አዲስ ራዕይ "በአገሪቱ የሃይማኖት እኩልነትን በሕግና በተግባር ለማረጋገጥ በተካሄደ ትግል የተሳካ ውጤት ለማምጣት ብንችልም የከሠሩ ፖለቲከኞች በሃይማኖት ዙሪያ ሁከትና ብጥብጥን ለመቀስቀስ የማይሞክሩት ነገር የለም" ሲል ይወነጅላል፡፡

እነዚህ ሃይሎችም በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ሠርገው በመግባት ሃይማኖቱን በፖለቲካ ለመበረዝ የተለያዩ ጥረቶች እንደሚያደርጉ የሚገልፀው ኢሕአዴግ "የከሠሩ ፖለቲከኞች የወቅቱ ስልት በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሠርገው በመግባት ሃይማኖትን የፖለቲካ አላማቸው ማራመጃ ማድረግ ሆኗል" ይላል፡፡

የከሠሩ ፖለቲከኞች ተብለው የተፈረጁትም በምርጫ 97 ተወዳድረው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫን አሸንፈውና በፓርላማና በክልል መቀመጫ አግኝተው፤ ሙሉ በሙሉ ስልጣን ካልያዝን ብለው ወደ አመፅ ያመሩት ኃይሎች፤ የአመፅ መንገዳቸው ስለተዳፈነ የመረጡት አዲስ የትግል ስልት መሆኑን ኢሕአዴግ ይገልፃል፡፡ ተበታትኖና ተከፋፍሎ ያለቀው የምርጫ 97 ዋነኛ ተቃዋሚ ቅንጅት አባላት የነበሩ ሰዎች አሁን እዚህም እዚያም ለሚታዩ የተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮች ግጭት አንቀሳቃሾች እንደሆኑም ይገልፃል፡፡

"ሃይማኖትን በሽፋንነት ለመጠቀም የሚሹት እነዚህ ኃይሎች በኦርቶዶክስም ሆነ በእስልምና ሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ቀላል በማይባል ደረጃ ሰርገው ለመግባት ችለዋል፡፡ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎችም ከመንፈሳዊ ግዴታቸው ባፈነገጠ አኳኋን አለማዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ እስከመግባት ሲደርሱ መመልከት የተለመደ ሆኗል" የሚለው ልሳኑ "የከሠሩ ፖለቲከኞች" የሚላቸው ወገኖች "በሃይማኖት ተቋማት ዙሪያ ሠርጐ በመግባት ብቻ ሳይወሰኑ የመንግሥት ተቋማትንም በሃይማኖት አስተሳሰብና ወገናዊ ተግባር በመበከል የሚፈልጉትን የገበያ ግርግር ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ" መምጣታቸው የተለመደ ተግባር መሆኑን ያትታል፡፡

"የከሠሩ ፖለቲከኞች" ሰርገው ለገቡበት ወይም ደግሞ ለብጥብጥ መፍጠሪያ በሽፋንነት ለሚጠቀሙበት ሃይማኖት አክብሮት እንደሌላቸው የሚገልፀው ኢሕአዴግ "በዚህ ረገድ ከሚታዩት እውነታዎች ቀዳሚው የአገራችን የጥፋት ፖለቲከኞች ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል በከፍተኛ ደረጃ መጋለጣቸውና መሸነፋቸው ነው፡፡ ስልጣንን ከተቻለ በምርጫ ካልተቻለ ደግሞ በሃይል ለመያዝ አልመው የተነሱት ኃይሎች በሁለቱም መንገድ እንደተሸነፉ በግልፅ ይታወቃል፡፡ በምርጫ የተወሰነ ወንበር ለመጨመርና አዲስ አበባንም ለማሸነፍ ችለው የነበሩት ተቃዋሚዎች ሁሉንም ስልጣን ካልጠቀለልን ብለው ወደ አመፅ ካመሩ በኋላ አመፁ በቁጥጥር ሥር ውሎ በሕጋዊ ትግልም ተረትተው ክፉኛ ተጋልጠዋል" ይላል፡፡

ኢሕአዴግ በዚህ መልኩ ያስቀመጠው ቅንጅትን ሲሆን በዚህ ሥም ደግሞ በሕጋዊ መልኩ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ አለ፡፡ በአቶ አየለ ጫሚሶ የሚመራው ቅንጅት በፊት አባል የነበሩትንና ሌሎችንም አሰባስቦ በአዲስ መልክ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይገልፃል፡፡ የቀድሞው የቅንጅት ሊቀመንበር አቶ ኃይሉ ሻውል መኢአድ (የመላው ኢትዮጵያዊያን አንድነት ድርጅት) ፕሬዚዳንት ሆነው እየሠሩ ነው፡፡ ዕጩ ከንቲባ ሆነው የነበሩት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከባህር ማዶ መታገልን መርጠዋል፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን የሚመሩት አንድነት ፓርቲ በአዲስ መልኩ ቢደራጅም ሊቀመንበሯ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው ወሕኒ ቤት ይገኛሉ፡፡ አቶ ልደቱ ኢዴፓን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ይገኛሉ፡፡

ኢሕአዴግ ከሃይማኖት ግጭቶች ጀርባ አሉ የሚላቸው የትኞቹን ኃይሎች እንደሆነ በግልፅ ባያስቀምጥም ከምርጫ 97 በኋላ "የከሠሩ ፖለቲከኞች" ያመጡት እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ ሆነ ብሎ እንዲሸማቀቁ ለማድረግና የተዳከመ የተቃዋሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማድረግ እንጂ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የፖለቲካ ትርፍ የማግኘት ሃሳብን ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበሉትና እንደማይደግፉ ያስረዳሉ፡፡ ተቃዋሚዎች በዚህ መልኩ ከተፈረጁ አባላት ለማሰባሰብ ይቸገራሉ፤ የሕዝብ ድጋፍ ያጣሉ በሚል ስሌት ሆን ብሎ ኢሕአዴግ እያጠቃቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ኢሕአዴግ ከተቃዋሚዎች በመቀጠል በተለያዩ ቦታዎች ለሚታዩ የሃይማኖት ግጭቶች ምክንያት የሆኑና ያባባሱ ያላቸውን ኃይሎች ዘርዝሯል፡፡ የየራሳቸው አጀንዳ ያላቸው የውጭ ኃይሎችም እጃቸው እንዳለበት፣ የሚገልፀው ልሳኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ዘመናዊ የመስቀል ጦርነት ኢትዮጵያ አንድ አካል እንድትሆን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንደሚደረጉ ያመለክታል፡፡ በሃይማኖት ሽፋን ለሚፈጠር ግርግር አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩ ተጨማሪ ጉዳዮች ተብለው ከቀረቡትም በላይ ሁሉ ግን "የከሠሩ ፖለቲከኞች" የተባሉት ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

"በሃይማኖት ሽፋን ግጭትን ለመቀስቀስ የሚደረገው ሙከራ በዋነኛነት በአገር ውስጥ ካሉ የከሠሩ ፖለቲከኞች ከዚሁ ጋር በተያያዘ አኳኋን ደግሞ ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ አክራሪዎች ሽኩቻ መናሃሪያ ለማድረግ በሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች የተጠነሰሰና የሚራመድ ቢሆንም ለዚህ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ውስጣዊ ድክመት የለንም ማለት አይቻልም" የሚለው ልሳኑ የሃይማኖት ተቋማትም ያለባቸውን ድክመት ያስቀምጣል፡፡

እንደ ኢሕአዴግ እምነት በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄድ የፖለቲካ ግጭት ስልት ለማምከን መውሰድ ያለባቸው እርምጃዎች አሉ፡፡ "ታግሎ ማሸነፍ የሚቻለው በአንድ በኩል መላውን የድርጅታችንን አቅም በፖለቲካዊ ትግሉ ላይ በማረባረብና ተፈላጊውን ውጤት በማምጣት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላም ወዳጅ የአገራችን ሕዝብ በጉዳዩ ላይ ግልፅነት እንዲኖረው በማድረግ የመፍትሔው አካል ሆኖ እንዲታገል በማድረግ ነው" ይላል፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ የከሠሩ ፖለቲከኞች የሚላቸውንና የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው የውጭ ወገኖች ለሚያካሂዱት አፍራሽ እንቅስቃሴ ለም አፈር ሆነው የሚያገለግሉ የፓርቲውን ችግሮች አንድ በአንድ ነቅሶ ማወጣት እንደሚያስፈልግ ይገልፃል፡፡ በዚህም የመንግሥት ኃላፊዎችንና የከተማ ከንቲባዎችን ጭምር ገለልተኛ ባለመሆን ተችቷቸዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩበት ጥፋቱን በተቃዋሚዎች ላይ በማስቀመጥ መፈረጁን የማቃወሙ ፖለቲከኞች አሁንም በሃይማኖት ሽፋን ይንቀሳቀሳሉ መባላቸውን አይቀበሉትም፡፡ የሃይማኖት ግጭት የሃገሪቱ ታሪክ እንዳልሆነና ይህንንም አጥብቀው እንደሚታገሉት ያስረዳሉ፡፡

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)