April 1, 2009

የኢትዮጵያ ቅርሶች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል


በሔኖክ ያሬድ

የአገር ሥልጣኔ፣ የአገር ታሪክ፣ የአገር ሥነ ጥበብ አመልካች የሆኑት የኢትዮጵያ ቅርሶች በመጥፋትና በመሰረቅ እየጠፉ መሆናቸው ተጠቆመ፡፡
ከዘመነ አክሱም ጀምሮ ተሰባስበው የነበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ቅርሶች በአውሮፓና በአሜሪካ የቅርስ ገበያዎች ላይ እየተሸጡ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
በብሔራዊ ሙዚየም መጋቢት 5 ቀን 2001 ዓ.ም. በተዘጋጀውና “ቅርሶች እንዴት ይጠበቁ?” በሚል ርእስ በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ፣ አርኪዮሎጂስቱ አቶ ተክሌ ሐጎስ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ቅርሶች በአሁን ጊዜ በጣም አሳሳቢ ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡
“ቅርሶች የታሪክ መረጃዎች ናቸው፡፡ ቅርሶች ከሌሉ የአገራችን ታሪክ ተረት ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ መረጃው ያለው በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ መረጃው እየተሸረሸረ እየተናደ እየጠፋና እየወደመ ነው፡፡” ያሉት አቶ ተክሌ፣ የችግሩን ምንጭ አመልክተዋል፡፡

የሕገ ወጥ የቅርስ ዝውውር በአገራችን በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በዓለም አቀፍም፣ በገጠርም በከተማም በስፋት እየተካሄደ ነው፡፡ በአሜሪካ ኢቤይ በሚባል ድረ ገጽ የቅርሶቹ የጨረታ ሽያጭ ይፈጸማል፡፡ ድረ ገፁ ለ48 አገሮች ሽያጭ የሚያካሂደው በኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ ሲሆን፣ በከፍተኛ ደረጃ የሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅርሶች የሆኑት የብራና መጻሕፍት ናቸው፡፡

መጻሕፍቱ ታሪኩንም፣ ንባቡንም፣ ጥበበ ዕዱንም፣ ፊደሉንም የያዙ መሆናቸውና ከብረታ ብረትና ከእንጨት የተሰሩ መስቀሎችም እየተቸበቸቡ ናቸው፡፡

በአቶ ተክሌ አነጋገር፣ “ሁላችንም ልናስብ ልንቆረቆር ይገባናል፡፡ በባለቤትነት የቤተክርስቲያን ይሁን እንጂ ቅርስ የሕዝብ ነው፡፡ ሌላው ቅርሶችን አደጋ ላይ የከተታቸው ሕገወጥ ቁፋሮ ነው፡፡ በመሬት ውስጥ ብዙ የአርኪዮሎጂ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ በመቃብርና በቤተ እምነት ቦታዎች የተቀበሩ ንዋየ ቅድሳት ለማውጣት እየተባለ የቁፋሮ ጥበብ በሌላቸው ሰዎች ቁፋሮ እየተካሄደ በመሆኑ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡”

ቅርስን፣ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠገን፣ ጥንት የተሰሩትንም ለማደስ በሚደረግ አዝማሚያ፣ መልካቸውና ጥንታዊ ታሪካዊ ይዘታቸውንና የሥነ ጥበብ ውበታቸው ያጡና ዘመናዊ ቤት ይሆናል ያሉት አርኪዮሎጂስቱ በምሳሌነት ያቀረቡት በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተፈጸመውን ጥገና ነው፡፡

“ቤተ መርቆሪዎስ ላይ ከአለት በተፈለፈለ ቤተ ክርስቲያን ላይ እንጠግናለን ብለው ዘመናዊ የሆነ ብሎኬት ተክለዋል፡፡ በዚያ ጥበብ ላይ ባዕድ የሆነ የዘመኑ ቁስ ሲደረግበት አስቀያሚና ከባድ አዝማሚያ ስለሆነ ልናስወግደው ይገባል፡፡”

አሮጌ ሕንፃን አፍርሶ በአዲስ መሥራት እየታየ ያለ አደገኛ አዝማሚያ መሆኑን ያወሱት ባለሙያው በተለይ በዘመነ አክሱም ሆነ በኋላ የተሰሩትን ጥንታውያን ሕንፃዎች አፍርሶ በአዲስ ለመተካት የሚንቀሳቀሱበት መንገድ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

“በ4ኛው መቶ ዘመን የተሰራችውና በትግራይ የምትገኘውን አንዛ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አፍርሰን ሌላ ሕንፃ እንሰራለን ይባላል፡፡ ያ የጥንቱ የአርኪዮሎጂ መረጃ፣ የቤተ ክርስቲን ታሪኳ በሙሉ ፈጽሞ ይጠፋል፡፡ አደገኛ አካሄድ ስለሆነ ሊገታ ይገባዋል” ብለዋል፡፡

ያሉት ቅርሶች አጠባበቅና አያያዝ ሌላው አሳሳቢና አሳዛኝ መሆኑም በተጠቀሰበት የውይይት መድረክ የብራና መጻሕፍቱ አቀማመጥ፣ የዕቃ ቤቱ ገጽታ፣ መስቀሉ፣ ብራናው፣ ሥዕሉ፣ ከብረት፣ ከእንጨት የተሰራው አንድ ላይ መነባበሩ ለጥፋት እየዳረገው መሆኑ ተመልክቷል፡፡ “አንዱ ለአንዱ ጠር ነው፡፡ በሥነ ሥርዓት እንኳን አልተቀመጡም፡፡ ቅርሶቹ ሲቀመጡ አየርም አያገኙም፡፡ ለምስጥ፣ ለተባይ፣ የተጋለጡ ናቸው” ያሉት ባለሙያው የ14ኛውን 15ኛ መቶ ዘመን ብራናዎች የሚገኙበት የጣና ሐይቅ ደሴቶች ገዳማትና በአዲስ አበባም በሚያሳስብ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ አመልክተዋል፡፡

የብራና መጻሕፍት አጠቃቀም ላይም ተመሳሳይ ችግር ይታያል፡፡ በአብዛኛው አያያዙ ሥርዓት የለውም፡፡ በትግራይ በሚገኘው የአባ ገሪማ ገዳም ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ ረ1,500 ዓመትሪ የብራና መጽሐፍ ቢኖርም ባለሥልጣኖችና ፈረንጆች ሲመጡ እያወጡ በማሳየትና በእጅ ሲያገላብጡት ለአደጋ እየተጋለጠ በመሆኑ በሥርዓት ሊያዝ እንደሚገባና ሥዕሎቹንም በፍላሽ ፎቶ ግራፍ በማንሳት በመደብዘዝ ላይ በመሆናቸው የሚመለከተው ክፍል ትኩረት እንዲሰጥበት ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

በላሊበላም በመኪና መድኃኔ ዓለም ዐምዶች ላይ ያሉት ሥዕሎች ላይ ሰዎች እየተደገፉ፣ ሻማ፣ ጧፍ እያነደዱ እየጠፉ በመሆናቸው በሁሉም አካባቢ ተገቢው ትኩት ካልተሰጠው የቅርሶቹ ሕልውና አሳሳቢ እንደሚሆን ተመልክቷል፡፡

“በአገሪቱ ላሉት ችግሮች መንስኤው አንደኛው በአንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ያለው ቅርስ በቅጡ አይታወቅም፡፡ እንዲታወቅም አይፈለግም፡፡ ያለው አካሄድ ይህ ነው፡፡ ካላወቅነው አንቆጣጠረውም፡፡ ስለማይታወቅ በየጊዜው ወደ አሜሪካ እየሄደ እየተቸበቸበ ነው፡፡ ስለዚህ በየቦታው ያለው ቅርስ ተቆጥሮ ከተመዘገበ የጎደለው ይታወቃል ያሉት አቶ ተክሌ፣ የቤተ ክርስቲያን ቅርስ ጠባቂዎች በቅርስ ላይ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛና ተቆርቋሪነትም ስማይታይ የማስገንዘቢያ መድረክ በተከታታይ ማዘጋጀት አስፈላጊነቱን ጠቁመዋል፡፡

በመንግሥት በኩልም ለቅርሶች ትኩረት ተሰጥቶ ልዩ ልዩ አዋጆችና ድንጋጌዎች፣ ስምምነቶችም ቢወጡም ችግሮች እየታዩ በመሆኑ ጊዜ ሊሰጠውም ስለማይገባ ቅርሶች በየቤተክህነቱ በተከታታይ ምዝገባ በማካሄድ ያለውን ቁጥር ማወቅና ቄሰ ገበዙም ሆነ የሰበካው ጉባኤ መረጃውን አጠናቅሮ መያዝ እንደሚገባቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

ቅርስ ከተመዘገበ በፖሊሲም በፍርድ ቤትም ከታወቀ ውጭ አገር ቢሄድም በማስረጃ ማስመጣት ይቻላል፡፡ የላሊበላው ፣አፍሮ አይገባ፣ መስቀል በመመዝገቡ ተዘርፎ ከተወሰደበት አገር ማስመለስ መቻሉን በመድረኩ አጽንኦት ተሰጥቶበታል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ባቀረቡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ቅርሶች በዓይነትና በብዛት የትየለሌ መሆናቸው፣ የአብያተ ክርስቲያን ሕንፃዎች፣ መካናተ መቃብር፣ ጥንታውያን ሥዕሎች የብራና መጻሕፍት፣ ያሬዳዊ ዜማና መንፈሳዊ በዓላት የመሳሰሉት ተጠቃሽ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

ቅርሶች የማንነት መገለጫዎችና የታሪክ የመረጃ ምንጮች ከመሆናቸው ባሻገር ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ ከታሪክ መረጃነት ሌላ አገራዊ ስሜትን ለመገንባት አንድ አገርና ሕዝብ ከሌላው የሚለይበትን ነገር የሚያሳዩ የማንነት መገለጫዎች በመሆናቸው በክብር ተጠብቀውና ተይዘው ወደትውልድ ለማስተላለፍ አፋጣኝ የመፍትሔ ሃሳብ ተብሎም የተጠቆሙት በሚመለከታቸው ተቋማት አማካይነት ግንዛቤን መፍጠር፣ ምዝገባና ቆጠራ ማካሄድ፣ ጠንካራ ሕጎችን በማውጣት ተግባራዊ ማድረግ፣ ተገቢ ካልሆነ የዕድሳት ሥራ መቆጠብ ናቸው፡፡

በውይይቱ መድረክ እንደተመለከተው ሕገ ወጥ ዝውውር የሚከናወንባቸው አንዳንድ የገጸ በረከት መሸጫ መደብሮች፣ በአንዳንድ ከተሞች ድብቅ ቤቶች ውስጥ የቅርስ ሽያጭ የሚፈፀምባቸውን ቦታዎች እንዲገቱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አንዲት ባለሙያ በሐረር ከተማ ውስጥ በድብቅ ቅርሶች የሚሸጡበትና ቱሪስቶች እየተመሩ የሚሄዱበት ቦታ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተወካይ ሕገወጥ ዝውውርን ለመግታት ተቋሙ ባደረገው ጥብቅ ቁጥጥር፣ በአየርና በየብስ መውጪያ ኬላዎች ላይ ሊሾልኩ የነበሩ 1925 ቅርሶች በመያዝ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ማስረከቡን ተናግረዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በአሜሪካ ኮሌጅ ቪል በሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ በአደጋ ላይ ስላሉት የኢትዮጵያ ቅርሶች ንግግር እንደሚካሄድ የሒል ሙዚየም ኤንድ ማኑስክራፕት ላይብረሪ (ኤች.ኤም.ኤም.ኤል) አስታውቋል፡፡

የፊታችን ማክሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2001 ዓ.ም. በሚኖሶታ በሚካሄደው መሰናዶ ንግግሩን የሚያደርጉት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ሲሆኑ፣ ርእሳቸውም “ኢትዮጵያ ኢንዳንጀርድ ጋርደን ኦፍ ክርስቲያኒቲስ ኢርሊየስት ትራዲሽንስ” መሆኑ ከዩኒቨርሲቲው ድረ ገጽ ዘገባ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ክርስትናን በይፋ ሃይማኖትነት በ4ኛው ምእት ዓመት በመቀበል ሁለተኛዋ አገር መሆኗንና ቅድመ ክርስትና የእምነተ አይሁድ ሥርዓት መኖሩን ያስታወሰው ዩኒቨርሲቲው፣ ያካበታቸውን ጥንታዊ የአይሁድና ክርስትና ሥርዓቶች፣ ልምዶችና ትውፊቶች በየትም አገር እንደማይገኙና ከነዚህም መካከል በእጅ የተጻፉ ቀዳሚ ሃይማኖታዊ የብራና መጻሕፍት እንዳሉበት አመልክቷል፡፡ ጥንታውያን የዕብራውያንና የክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት በሌሎቹ ጠፍተው በብቸኝነት ተጠብቀው የሚገኙት በኢትዮጵያ ትውፊት ውስጥ እንደሆነ ያመለከተው ዘገባ፣ በአሁን ጊዜ ቁጥራቸው የማይታወቁ የኢትዮጵያ ብራናዎች እየተሰረቁ ወይም እየጠፉ መሆናቸው ለዚህም ድህነትና አካባቢያዊ አለመረጋጋት ምክንያቱ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ የሒል ሙዚየምና ብራናዎች ቤተ መጻሕፍት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ከኢትዮጵያውያን ምሁራንና ከቤተክህነት ሹማምንት ጋር በመተባበር የብራና መጻሕፍትን ጠብቆ ለማቆየት በማይክሮ ፊልም ባስነሳበት ጊዜ ከተሳተፉትና ካስተባበሩት ታዋቂ ምሁራን መካከል ፕሮፌሰር ጌታቸው አንዱ ነበሩ፡፡

የኢትዮጵያ ብራና መጻሕፍት ልዩ ልዩ ይዘት ወደተለያዩ ቋንቋዎች በመተርጎምና እሴታቸውን በማስተዋወቅ የሚታወቁት ፕሮፌሰሩ በሚያደርጉት ንግግር ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ውስጥ ያላትን ልዩ ስፍራ የሚያጋሩበት እንደሆነ ተቋሙ አመልክቷል፡፡

Last Updated ( Sunday, 29 March 2009 )

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)