March 17, 2009

በሃይማኖት ሽፋን አፍራሽ አጀንዳዎችን ይዘው ወደ አደባባይ የሚወጡ ፀረ ሠላም ሃይሎችን ማጋለጥ እንደሚገባ ተነገረ

ድሬዳዋ፤ መጋቢት 5/2001/ዋኢማ/
በሃይማኖት ሽፋን አፍራሽ አጀንዳዎችን ይዘው ወደ አደባባይ የሚወጡ ፀረ ሠላም ሃይሎችን በማጋለጥ ለዘመናት የቆየውን ተከባብሮ የመኖር ባህል ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚሰሩ በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙ የእምነት አባቶች ገለፁ።
የአስተዳደሩ ፀጥታና ፍትህ ጉዳዮች ቢሮና የማስታወቂያና ህዝብ ግንኙነት ቢሮ በጋራ ያዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኦሮቶዶክስ፣ የካቶሊክ፣ የእስልምና፣ የወንጌላውያን ህብረት መሪዎች እንደገለፁት፤ እምነቶችን ሽፋን በማድረግ በሲዲዎችና በህትመት ስራዎች ተገቢነት የሌላቸውን መልእክቶች የሚያሰራጩ ግለሰቦችን በማጋለጥ ለዘመናት የቆየውን የመቻቻል ባህል እንዳይደናቀፍ ይሰራሉ።

ሁሉም ዜጐች እምነታቸውን አጠናክረው በመያዝ ለአገሪቱ የልማት እድገት ሊሰሩ ይገባል ያሉት የየእምነት መሪዎች፤ ያሉትን መግባባቶች መቻቻልንና አንድነትን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ድርጊቶችን በመከላከል ማክሸፍ የየእምነቱ ተከታዮች ሃላፊነት እንደሆነም ገልፀዋል።

ከቀድሞ አባቶቻችን የወረስናቸውን መልካም እሴቶች ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በእምነት ተቋማቱ የግብረገብ ትምህርቶችን ማስተማር ሃላፊነታቸውን እንደሚወስዱ የየእምነቱ መሪዎች ጠቅሰው፤ መንግስትም በእምነቶች መካከል አፍራሽ ድርጊት በመፈፀም ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ ህገ መንግስታዊ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በአስተዳደሩ የሚታየውን የእምነቶች መቻቻልና መግባባት ተጠናክሮ ለማስቀጠልና በየእምነቱ መካከል ግጭት ለማስነሳት የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለመቆጣጠር የሚያስችል 12 አባላት ያሉት የሰላም ኮሚቴ ከሁሉም እምነቶች ተውጣጥተው ተቋቁመዋል።

የአስተዳደሩ ፀጥታና ፍትህ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ኢብራሂም ዮሱፍ በበኩላቸው፤ ህገ መንግስቱ የእምነት እኩልነት ማረጋገጡን ጠቅሰው፤ በሲዲ አማካኝነት የሚታዩ ስህተቶች የክርስትናና የሙስሊሙን አማኞች የማይወክል መሆኑን መንግስት ይገነዘባል ብለዋል።

ነገር ግን ድርጊቱን በሃይማኖቱ ስም የሚፈጽሙ ስግብግብ ግለሰቦች ለማጋለጥና ለይቶ ለማውጣት በጋራ ማቆም ይገባል ማለታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)