March 20, 2009

መንግስት ሁከት ለመፍጠር የሚንቀሰቀሱ ግለሰቦችን ለመከላከል ከዕምነት ተቋማት ጋር ይሰራል


አዲስ አበባ መጋቢት 10/2001/ዋኢማ/ መንግስት የኃይማኖት ተቋማትን ተገን አደርገው ሁከትን በመፍጠር የህብረተሰቡን ደህንነትና ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ለመከላከል ከተለያዩ የዕምነት ተቋማት ጋር እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ ገለጹ። አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በኃይማኖት መቻቻል ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄዷል።

የከተማው ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ ዛሬ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር በጽህፈት ቤታቸው ባደረጉት ውይይት እንደገለፁት፤ የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው በዕምነት ተቋማት መካከል ግጭቶችን ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ምንጮችን መንግስትና የተለያዩ የእምነት ተቋማት የማድረቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
መንግስት የአገሪቱን ሰላም፣ ደህንነትና ህግ ማስከበር ዋነኛ ተግባሩ መሆኑን ያመለከቱት ከንቲባው፤ በኃይማኖት ሽፋን አፍራሽ ተልዕኮ አንግበው ውዥንብር የሚነዙ ኃይሎችን በመከላከል ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኃይማኖት ነጻነትና ዕኩልነት የተረጋጋጠበት ጊዜ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ኩማ፤ ህብረተሰቡም በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን በመከላከልና ለህግ አሳልፎ በመስጠት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጎች በመከባበርና በመግባባት የሚኖሩባት አገር መሆኗን አቶ ኩማ አመልክተው፤ ከዚህ አኳያ በአገሪቱ በመከባበር ላይ የተመሰረተው ባህል ይበልጥ ሊጎለብት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የከንቲባው የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው፤ የተለየ አጀንዳ ይዘው በህብረተሰቡ መካከል ግጭት በመፍጠር ሰላምና ጸጥታን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን መለየት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የዕምነት ተቋማት ከዚህ አኳያ የጎላ ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወ ቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በበኩላቸው፤ የአገሪቱ ህገ መንግስት ከምንጊዜውም በላይ የዜጎችን የኃይማኖት ነጻነት የሚጠብቅና የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ የዕምነት ተከታዮች በፍቅር፣ በሰላምና በመቻቻል እንደሚኖርባትና የዳበረና የካበተ ልምድ እንዳላት አመልክተው፤ ይህንኑ ባህላዊ ዕሴት ለማፋለስ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በአገሪቱ ከሰፈነው የዜጎች የዕምነት ነጻነት መረጋገጥ ጋር ተያይዞ የመቻቻልና የመከባበር ባህል መዳበር እንዳለበት ገልፀው፤ ለተግባራዊነቱ ቤተ ክርስቲያኒቷ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነች መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)