February 22, 2009

"ብቸኛው አፍሪካዊ ፊደል" (The Sole African Alphabet) የተሰኘው በዶክተር ፍቅሬ ዮሴፍ የተዘጋጀው መጽሐፍ


በቅርቡ ገበያ ላይ ከወጡት ልዩ ልዩ መጻሕፍት መካከል ለየት ያለ ይዘት ያነሳውና አነጋጋሪ የሆነው "ብቸኛው አፍሪካዊ ፊደል" (The Sole African Alphabet) የተሰኘው በዶክተር ፍቅሬ ዮሴፍ የተዘጋጀው መጽሐፍ ነው፡፡

መጽሐፉ ተሻሽሎ የቀረበ አዲስ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ፊደል ገበታና የንባብ መለማመጃ የሚል ንኡስ ርእስም ተካትቶበታል፡፡

የመጽሐፉ አዘጋጅ አሻሽለው ያቀረቡት የፊደል ገበታ ጠቀሜታ ለማሳየት ካሁን በፊት የነበረውና በአገልግሎት ላይ ያለው ፊደል የነበረበትን ችግርና ጉድለት በመዳሰስ መፍትሔ ያሉትን አዲስ የፊደል ገበታ አቅርበዋል፡፡ "የኢትዮጵያ ሥርዓተ ፊደል ገበታ" በሚል ርእስ 29 ሆሄያትን መደብ በማድረግና የሞክሼ ድምፆችን ምልክቶች በማስወገድ፣ ከሀ ግእዝ እስከ ሆ ሳብዕ (ሰባቱ ሆሄያት) የተዋረድ ቅጥያ አንድ ወጥ በማድረግ የማጥበቂያና የማላሊያ ምልክቶች የያዘ ሰሌዳ አዘጋጅተዋል፡፡
አነጋጋሪ የሆነውና የዚህን ፊደል ገበታን ከንባብ መለማመጃ ጋር የያዘው መጽሐፍ ለምረቃ በቀረበበት ኢምፔሪያል ሆቴል መድረክ፣ ምሁራን አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡ በመጽሐፉ መነሻ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ፊደል አቅጣጫና ግብ ምን መሆን እንዳለበት ሀሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ዶክተር ሙሉጌታ ሥዩም ያቀረቡት ተጠቃሽ ነው፡፡

በዶ/ር ሙሉጌታ አገላለጽ፣ ከተለያዩ መረጃዎች እንደሚገኘው የግእዝ ፊደል የተፈጠረበት፣ ያደገበትና እዚህ ደረጃ የደረሰበት ሰፊ ታሪክ አለው፡፡ የተሻሻለበት፣ ከሳባ ፊደልና ከጥንታውያን ቋንቋዎች ጠቃሚ ነገር በመውሰድ ከቀኝ ወደ ግራ የነበረውን አፃፃፍ ከግራ ወደ ቀኝ አፃፃፍ አቅጣጫ በመለወጥ የራሱን መንገድ የያዘ ነው፡፡ የግእዝ ፊደል ገበታ ጥንታዊና ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ባገሪቱ ላሉት ብሔረሰቦች ሀብት መሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

እኛ ትኩረት ነፈግነው እንጂ ባደጉት አገሮች ግእዝ በታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች በጥንታዊ የኢትዮጵያ ቋንቋነቱ ትኩረት ተሰጥቶት እየተጠና በኮርስም መልክ እየተሰጠ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ግእዝን ጠብቃ፣ ለትውልዱ እያስተማረች፣ ለእምነት አገልግሎቷም ደግሞ ዕለት ተዕለት በሥነ ጽሑፍዋ፣ በዜማዋ በጸሎቷ እየተጠቀመች፣ ቋንቋ ተናጋሪ ብሔር ሳይኖረው እስካሁን ይፋ አድርጋ ማቆየቷ ባለውለታ መሆኗን የገለጹት ዶ/ር ሙሉጌታ፣ ላቲኑ ለአውሮጳውያኑ ቋንቋ ሁሉ የጽሑፍ መሠረት እናት እንደሆነ ሁሉ ግእዙም ለኢትዮጵያ መሆኑን ማስገንዘቢያ ሰጥተዋል፡፡ ሁሉም ፊደል ለየቋንቋው ይሰራል ማለት ባይሆንም ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸው የሚመስሉ ፊደላት በግእዙ ትርጉም ስላላቸው ሊጠበቁ እንደሚገባ በየቋንቋቸው ባሕርይ በመነሳትም ሌሎች ቋንቋዎች ለድምፃቸው ፊደሉን መሠረት በማድረግ ወካይ ምልክት መፍጠር እንደሚችሉ በዳሰሳው ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ 80 የሚደርሱ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩባት ነች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 24 የሚደርሱት የጽሑፍ ዘዴ የተሰራላቸው ሲሆን አብዛኞቹ ግን ለዚህ ዕድል አልታደሉም፡፡

በነዚህ ጅምር ሥራዎች ላይ እንደሚታየው በፊደል ቀረፃው ሥራ በእያንዳንዱ ቋንቋ ውስጥ ያሉትን ድምፆች በተገቢው መንገድ የመቅረጹና የኢትዮጵያ ፊደል ወይስ የላቲኑ ፊደል ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ይበጃል በሚለው አመራረጥ በኩል ብዙ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡

ደራሲው ዶ/ር ፍቅሬ በመጽሐፋቸው ገጽ 43 እንደገለጹት፣ ጥንት የላቲን ፊደል የነበረው ፈረንጆቹ በሚስማማቸው መንገድ አስተካክለው የፈረንሳይኛ፣ የጣሊያንኛ፣ የእንግሊዝኛ ወዘተ. በማለት የላቲኑን ሥረ መሠረት በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፡፡

በተሳሳተ እምነትና መረጃ ፊደላችን በተሰጠው ስያሜ ምክንያት ብቻ የባለቤትነትና የብሔራዊነት ይዘቱ ባለመጠናከሩ እንጂ የዛሬዋ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችም የግእዝን ፊደል በሚስማማቸው መሠረት አስተካክለውና አሟልተው የአማርኛ፣ የትግርኛ፣ የኦሮምኛ፣ የአፋርኛ፣ የወላይትኛ ወዘተ. የፊደል ገበታ አዘጋጅተው በመጠቀም ቋንቋቸውን ለመጻፍ በቻሉ ነበር፡፡

ምእራባውያኑ የሚጠቀሙት ፊደል መሠረቱ የላቲን እንጂ የፈረንሳይ፣ የስፔን ወይም የሌላ አይደለም ያሉት ዶ/ር ሙሉጌታ፣ እኛም ጥንታዊ ኢትዮጵያዊ ፊደል ስላለን እርሱን መጠቀም እንደሚበጀንን እና "የራስን ጥሎ የሰውን አንጠልጥሎ እንዳይሆን" በማለት አጽንዖት ሰጥተውበታል፡፡

በመጽሐፉ ላይ ያላቸውን አስተያየት አክለው የገለጹት ዶ/ር ሙሉጌታ ርእሱ ላይ ያለውን ችግር ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከቅኝ ግዢ ነፃ በመሆኗ የራሷ የሆነ በብሔራዊ ደረጃ የምትጠቀምበት ቋንቋና ፊደል ያላት መሆኗ ትክክል ነው፡፡ ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገሮች በብሔራዊ ቋንቋነት የሚጠቀሙት የባዕድ ሀገር ቋንቋና ፊደል በመሆኑ የእኛ ብቸኛ አፍሪካዊ ፊደል ልንለው እንችል ይሆናል፡፡ ይሁንና በብሔራዊ ደረጃ ባይጠቀሙበትም ከዚያ ዝቅ ብሎ በመማሪያነት የሚጠቀሙበት አፍሪካዊ ፊደል ያላቸው አገሮች እንደ ኒጀር፣ ግብፅ መኖራቸው መዘንጋት እንደሌለበትና በአፍሪካ ሌላ ፊደል ያለው ከኢትዮጵያ በቀር የለም ከማለት እንድንጠነቀቅ አሳስበዋል፡፡

የሀ፣ ሠ፣ ፀ የድምፅ ሞክሼዎች ያላቸው ምልክቶች በግእዝ ውስጥ አስፈላጊ ናቸው፡፡ የአንዱ ፊደል ቦታ መልቀቅ የትርጉም ለውጥ ስለሚያመጣም መጠበቅ እንዳለበት ፊደላቱ ይቀነሱ ሲባል የግእዙን ፊደል መሠረት አድርጎ የሌሎችን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሲቀረጽ እዚያ ላይ የማያስፈልጉት ሊቀነሱ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

እንደ ቋንቋው ባሕርይ እንጂ ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸው ፊደሎች ተግባር የላቸውም የተደረደሩ ናቸው የሚል ግንዛቤ መፈጠር እንደሌለበትና መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ሙለጌታ አመልክተዋል፡፡

የማጥበቅና የማላላትን ለማመልከት በፊደል ገበታ ውስጥ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የዶ/ር ፍቅሬ ጥረት ቢደነቅም፣ ምልክቶችን ስንፈጥር በኢንተርናሽናል ፎኔቲክ አልፋቤት ከተለመዱ የድምፅ አወካከሎች ጋር ሊገናዘብ ወይም ደግሞ ኢትዮጵያዊ ፊደል ካልን ኢትዮጵያዊ ለማድረግ የማጥበቅ፣ የማላላት፣ የማርዘም፣ የመሳብ፣ የመጎተት የሚለውን በዚህ በኩል የታወቀው ደራሲ ቅዱስ ያሬድ ስለሆነ ከዚያ ጋር ሊስማሙ የሚችሉትን ብንወስድ የበለጠ ኢትዮጵያዊ ያደርገዋል የሚል አስተያየታቸውን ዳሳሹ አመልክተዋል፡፡ በዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ አንድ ሥርዓተ ፊደል እንዲኖር መቀመጡም አስቸጋሪ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በዶ/ር ሙሉጌታ አገላለጽ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚነገሩ ቋንቋዎች ሁሉ አንድ ወጥ ፊደል ማዘጋጀት ከፊደል ሙያ አኳያ አመቼ አለመሆኑ፣ በአራቱ የቋንቋ ቤተሰቦች (ሴማዊ፣ ኩሻዊ፣ ኦሟዊ፣ አባይ ሰሃራዊ) የተለያዩ ድምፆች ባሉበት ሁኔታ አንድ የፊደል ገበታ ውስጥ ለማስገባት ይከብዳል፡፡

መሠረቱ የግእዝ ፊደል የሆነ የየራሳቸው ቋንቋ የፊደል ገበታ እንዲኖራቸው፣ የግእዙ ፊደል የሚወክለውን ይዘው ለማይወክለው ደግሞ እያቃኑ ቅጥሎችን እየጨመሩ መፍጠር እንደሚቻልም ተመልክቷል፡፡

በነባሩና በነዋሪው ገበታ ፊደሉ ብቻ ሳይሆን አኀዝም የተካተተበት ሲሆን፣ በአዲሱ የገበታ ንድፍ አኀዝ አለመካተቱ ከመተቸት አላዳነውም፡፡ ኢትዮጵያ ፊደል ብቻ ሳይሆን የራሷ ቁጥር ያላት በመሆኑ ፊደሉ ሲተዋወቅ ቁጥሩንም ማስተዋወቅ ሊዘነጋ እንደማይገባ የጠቆሙት ዶ/ር ሙሉጌታ፣ ስጋት ብለው የጠቀሱት ነጥብ አለ፡፡ አዲስ ነገር ሲፈለሰፍ አብሮ ሊታይ የሚገባው፣ የፊደሉ የቁጥር ብዛት ሲቀነስ፣ ተማሪው በቀላሉ መንገድ እንዲማር ሲደረግ፣ የሚቀጥለው ትውልድ፣ ባጭሩ እንዲማር ሲደረግ፣ እስካሁን ድረስ በነባሩ ፊደል የተጻፉት ሰነዶች ምን ያደርጋቸዋል? የራሱን ማንነት አንብቦ እንዳይረዳ ደግሞ ማይም ስለሚያደርገው ማሰብና መፍትሔ መስጠትም ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ ፊደል ጉዳይ ከታሪክ፣ ከፖለቲካና ከማንነት ጥያቄ ጋር አያይዘው የጉዳዩ ባለቤቶች፣ የቋንቋው ተናጋሪዎች፣ የቋንቋው ጥናት ባለሙያዎችና መንግሥት በሚገባ ሊያጤኑት ይገባል፡፡

በዛሬው ዘመን ወደ መፍትሔ ካልተመጣ "ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል ያላት ሀገር ናት" የሚለው አባባል ታሪክ ሆኖ መቅረቱ የማይቀር ነው፡፡ ሁሉም ብሔር/ብሔረሰብ የራሱን ትቶ ወደ ላቲን ፊደል ከኮበለለ የኢትዮጵያ ፊደል ወደ ሞት እያዘገመ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ አደጋ ላይ ነው ያለው ማለት ነው፡፡

እንደ ምሁራኑ አስተያየት፣ የኢትዮጵያን ፊደል መጠቀም ከላቲኑ ፊደል ይልቅ በቋንቋ ቤተሰብም እንኳ ቢሆን አፍሮ እስያዊ በመሆኑ ከኢንዶ አውሮፓውም ሆነ ከሌሎች ምድቦች ግእዙ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ቤተሰቦች (ለኩሽቲክ፣ ኦሞቲክ . . . " የበለጠ ይቀርባል፡፡

አጥኚው ዶ/ር ፍቅሬ ባዘጋጁት የፊደል ገበታ ብቻ፣ የኢትዮጵያያውን ቋንቋዎችን ድምፅ መወከል አስቸጋሪ ስለሚሆን የግእዙን ፊደል መሠረት አድርጎ ለእያንዳንዱ ቋንቋ የፊደል ገበታ መቅረጽ ይጠይቀል፡፡ እንደ ዶ/ር ሙለጌታ ግምት ምናልባትም የእሳቸው ገበታ ለኦሮምኛ ቋንቋ ሊያገለግል ይችላል፡፡

ሁሉም ቋንቋዎች አንድ ዓይነት ፊደል መጠቀማቸው ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከታሪክና ከማንነት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ፣ የራስን ፊደል መጠቀም እየተቻለ አማራጭ እንደሌለው ትቶ ወደ ሌላ መሄዱ የኢትዮጵያን ፊደል አገልግሎት የሚያኮስስ ይሆናል፡፡

በመጽሐፉ ላይ ዳሰሳ ያደረጉት ደግሞ ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ማዘንጊያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳንና የፊደል መምህር ናቸው፡፡

በአገሪቱ ፊደልን የማሻሻል እንቅስቃሴ 100 ዓመት አካባቢ ማስቆጠሩ የአሁኑም ጥረት የዚያ ተቀጽላ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሽመልስ፣ ዶክተር ፍቅሬ ያዘጋጁት ገበታ መነሻው ከ1940 ዓ.ም. የትምህርት ወዳጆች ቡድን "ፊደልን ማሻሻል" በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ ፊደሉን የማሻሻያ አምስት ዓይነት አማራጮች ማቅረባቸውን አመልክተዋል፡፡

በአማራጮቹ መካከል ዶ/ር ፍቅሬ መሠረት ያደረጉት የሚመስለው አቶ አበበ ረታ ካቀረቧቸው ሁለት አማራጮች አንዱን ባብዛኛው ይመስላል፡፡

ከታዳሚዎች ከቀረቡት ቀዳሚ አስተያየቶች መካከል አንዱ ባቀረበው አስተያየት፣ የፊደል ማሻሻል እንቅስቃሴ ውስጥ ፊደላችን የላቲን ከሚሉት ከነ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስ በተፃራሪ አለቃ ለማ ኃይሉ የዐረብኛውን ፊደል እንጠቀም ማለታቸውን በመጽሐፉ የተገለጸው ስህተት መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ እንደሰፈረው፣ ". . . ሁለተኛው ደግሞ፣ የብላታ መርስዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስ ወገን የሚከተለው፣ ቃላቱ በአማርኛ ሆኖ፣ ፊደላቱ ግን የላቲኑ እንዲሆን ነው፡፡ እንዲሁም ሌሎች ደግሞ እንደ አለቃ ለማ ኃይሉ አስተያየት፣ ቃላቱ በአማርኛ ሆኖ፣ ፊደሉ ግን የዐረብኛ እንዲሆን የሰነዘሩት ሐሳብ ነው፡፡"

ደራሲው የመንግሥቱ ለማ ግለ ታሪክን ማስረጃ አድርገው ነው ያቀረቡት፡፡ አለቃ ለማ የዐረብኛ ፊደል ፈላጊ እንደሆኑ አድርጎ አሳይቶኛል ብለው ነው ያስቀመጡት፡፡ የተጠቀሰው የልጃቸው መጽሐፍ በምልዐት ባለመታየቱ አለቃ ለማ ያላራመዱትን ሐሳብ እንደያዙ ማድረጉ ዝበት እንዲፈጠር አድርጎታል፡፡

ፊደላችን የዐረብኛው ይሁን የሚለው አጋጣሚ የመጣው፣ ፊደሉን ስለማሻሻል ከመንግሥት ወገን የቤተ ክህነት መንፈሳዊ ጉባዔ እንዲመክርበት በተላከ ጊዜ ነበር፡፡

ሊቃውንቱ በሚመክሩበት ጉባዔ የተገኙት አለቃ ለማ "የላቲን ይሁን" አራማጆችን ሐሳብ ለማፍረስና ጉባኤውን ለመበተን የተጠቀሙበት ስልት እንደነበረ በግለ ታሪኩ ተመልክቷል፡፡

"ጠና ጠና ያልነው አልተናገርንም፡፡ ለማ አልተናገረም ዝም ብሎ እጃቸውን ያያል፡፡ . . . ክርክሩ ቀጠለ፡፡ መጯጯህ ሆነ፤ ፣ከዚህ በፊት ያልተናገሩ ከሽማግሌዎቹ ይናገሩ፤ እነሱም ይስሙ፣ አሉ፡፡ ለማ ተነሳ፡፡ ፣እንግዲህ ይህ ታሪካችን፣ መጻሕፍት ቅዱሳታችን፣ . . . የተጻፈበት ያባቶቻችን ፊደል አሮጌ ነው፤ ጊዜው አልፏል፣ አይረባንም፣ እሱን አንፈልገውም አይደለም? . . . በሱ ቦታ ሌላ ፊደል ይተካልን ካላችሁ ለማ የሚጣላችሁ አይደለም፣ እኔ ከክርክራችሁ አልገባም . . . ለኔ አታስቡ፣ ብቻ ለሕዝቡስ አታስቡም? . . . እስላሙ ቁርዓኑ ለተጻፈበት ለዓረቡ ቋንቋ ለዓረቡ ፊደል ቀናዒ ነው፡፡ ቋንቋውም ፊደሉም ነፍሱ ነው፤ ይወደዋል ሲበዛ፡፡ ዛዲያ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስላሙም ክርስቲያኑም ካልለመደው ባይሆን፣ ገሚሱ የወደደው አይሻልም? ሁለቱም ቢያዝኑ ምን ይረባል? ባይሆን አንዳቸው ይደሰቱ፡፡ ፊደላችን ዓረቢኛ ይሁን" ብዬ ተቀመጥኩ፡፡ ጉባዔው ብጥብጥ ብሎ ተበጠበጠ፡፡ በዚያው ተበታተነ" እዚያው በዶ/ር ፍቅሬ በተጠቀሰው መጽሐፍ ውስጥ፣ አለቃ ለማ የዓረብኛውን ፊደል ደጋፊ አለመሆናቸውን ለምንስ ዓላማ እንደተጠቀሙበት ተመልክቷል፡፡

"ሞኜ" ለማ ከግእዙ ፊደላችን፣ ዓረቢውን ይመርጣል ብለህ ነው? የለም ለማ ለብልሃቱ ነው ዓረቡ ይሁን ያለ፡፡ ለማሸበሪያ ጉባዔውን ለማፍረስ ነው፡፡ እውነትም እንደተመኘሁት እንዳሰብኩት ሆነልኝ፡፡ ቀናኝ፡፡ "የእስላም ፊደል" የስላም ፊደል? . . . እያለ ያ ባለቆብ፣ ባለካባና ባለጥምጥም ሁሉ ተደናግጦ ተበታተነ፡፡ ከዚያ ቀን ወዲያ በመንፈሳዊ ጉባዔ የፊደል መለወጥ ነገር አልተነሳም፡፡"
Last Updated ( Sunday, 22 February 2009 )

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)