February 22, 2009

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በፓልቶክ ስለተጀመረው ጸረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ የግል እማኝነታቸውን ሰጡ

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በፓልቶክ ስለተጀመረው ጸረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ የግል እማኝነታቸውን ሰጡ


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን በመከሰት ላይ ያለውን የሙስሊም-ክርስቲያን መሳሳብን አስመልክቶ ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የታሪክ፣ የሃይማኖትና የሴማውያን ቋንቋዎች ሊቅ እንዲሁም የዘመናዊው የሀገራችን ፖለቲካ የቅርብ ተከታታይ የሆኑት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የግል እማኝነታቸውን ሰጡ። “የሙስሊሞችና የክርስቲያኖች ግጭት፡ ፓልቶክ ደርሶ መልስ” በሚል ርዕስ በድረ ገጽ ባስነበቡት መጣጥፋቸው ሁለት የተለያዩ ግብዣዎች እንደደረሷቸውና በሁለቱም ላይ በመገኘት ንግግር እንዳደረጉ ገልጸዋል። “የመጀመሪያው በግል ሕይወቴ ከደረሰውና ካጋጠመኝ አንዳፍታ ላውጋችሁ በሚል ርእስ … ስለአሳተምኩት መጽሐፍ ሲሆን፤ ሁለተኛው ሰሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ በሙስሊሞቹና በክርስቲያኖቹ ኅብረተሰብ መካከል ስለተነሣው አለመግባባት አስተያየቴን ለማሰማትና ለሌሎችም ከዚያው ጉዳይ ጋር ተያይዘው ለሚነሡ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ነበር” ብለዋል። አስተያየት እንዲሰጡ በተጋበዙበት በዚሁ ዝግጅት ላይ “የአንዱ ሃይማኖት ተከታይ በመሆኔ የማዳላት መልስ የምሰጥ የመሰላቸው መኖሩን በማየቴ ቅር” ተሰኝቻለሁ ያሉት ፕሮፌሰር ጌታቸው “በውይይቱም ጊዜ ሆነ ወይም በዚህ ጽሑፍ ሚዛናዊ ለመሆን እንጂ፤ የየትኛው ሃይማኖት ተከታይ መሆኔን የሚያሳዩ ምልክቶችን ለመደበቅ አልተጨነቅሁም። ደግሞስ ከማን ነው የምደብቀው?” ብለዋል።

ወደ ርዕሰ ጉዳያቸው ጠልቀው በመግባት “በሕዝብ ደረጃ ሲታይ ከወያኔዎች አገዛዝ በፊት በሙስሊሞችና በክርስቲያኖች መካከል ሊተች የሚገባው ነፍስ ያለበት ግጪት ትዝ አይለኝም” ብለው በእማኝነት ደግሞ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን እስላማዊ ድርጅቶችን የኒያቅፈውን በድር ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ማህበር ለጠ/ሚኒስትር መለስ የጻፈውን ደብዳቤ ጠቅሰዋል። በምንግሥት ደረጃ በተለያየ መልኩ ጥንትም አሁንም ችግር እንዳለ ጠቁመው በፓልቶኩ ላይ ይቀርበው የነበረው አቀራረብ ግን እውነታን ሙሉ በሙሉ የማይመለከት እንደነበር ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ “ክርስቲያኖች ያቋቋሙት መንግሥት ‘የክርስቲያኖች መንግሥት’ ቢሆንና ቢባል ስሕተቱ ከምኑ ላይ ነው? እስቲ እስራኤላውያንንና የዓረብ ሀገር ባለሥልጣኖችን ስለራሳቸው መንግሥታት እንጠይቃቸውና ምን እንደሚሉ እንስማቸው?” ሲሉ ጥያቄያዊ አስተያየታቸውን አስፍረዋል።
“የክርስቲያን ደሴት” ስለሚለው የሙስሊሞች ምሬት በጠቀሱበት ሥፍራ “ሀገራችን ኢትዮጵያ ክርስቲያኖቹ ጥርቃሞ ጎሳዎችን ሰባስበው የፈጠሯት ሀገር ናት፤ መንግሥቱም፤ ክርስቲያኖቹ ስላቋቋሙት የነሱ መንግሥት ነበረ። ታሪኩ በአንስታይ ጾታ “መንግሥት መሲሐዊት” ይላታል። ክርስቲያኖች ያቋቋሙት መንግሥት ‘የክርስቲያኖች መንግሥት’ ቢሆንና ቢባል ስሕተቱ ከምኑ ላይ ነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ። “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት” ማለትም በሀገሪቱ ውስጥ ሌላ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች አይኖሩባትም ማለት ሳይሆን፤ በእነሱ ማህል የክርስቲያን መንግሥት (“መንግሥት መሲሐዊት”) ያለባት ሀገር ናት ማለት ነው። በአንድ በኩል “መንግሥቱ የክርስቲያኖች እንጂ ሙስሊሞች ድርሻ የለንም” ብሎ፤ ያንንን አዳምጠን ሳንጨርስ ወዲያው “የክርስቲያን ደሴት አትበሏት” ብሎ መቆጣት የአስተሳሰብ ቅራኔ ነው። … የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች(ም) እንደሌሎቹ አገር ሕዝቦች መንግሥት በማቋቋማቸው ኢትዮጵያን ጥንታዊትና ባለባህል አሰኝተዋታል፤ በበኩላችን ጥንጣውያንና የባህል ጌቶች ስላደረጉን እንኮራባቸዋለን” ሲሉ አስረድተዋል።
ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ክርስትናን ከሚከሱበት ጉዳይ አንዱ “እምነታችንን ከዐረቦች ጋር ታገናኙታላችሁ፣ ዐረቦች እንጂ ኢኦትዮጵያውያን አንመስላችሁም” ወዘተ ወዘተ የሚለው ክስ ነው። ስለዚሁ ጉዳይ የጠቃቀሱት ፕሮፌሰር ጌታቸው “እስልምና መጤ ሃይማኖት ነው የሚሉ ካሉ ፤ ክርስትና ቤት ሠርቶ፣ ኮርቶ፣ በመቶ በሚቀፖጠሩ ዓመታት በተቀመጠበት አገር መጥቶ (እስልምና) ስለገባበት ነው። የቅድሚያ ጉዳይ ነው እንጂ፣ ሃይማኖቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ ዓለምን የወረሩት ከአንድ ቦታ እየመጡ ነው። እስልምና መጤ የሚያሰኘው ሌላም ምክንያት አለው- እንደ ኮሎኒያሊስቶች የባህል ወራሪነት ጠባይ ይታይበታል። የሱዳንን ጥቁር ሕዝብ “ዓረቦች ነን” እንዲሉ እንዳሳሰባቸው እናስታውስ። ክርስትናን ግን አባቶቻችን ኢትዮጵያ ያስገቡት ሃይመኖቱን ከባህሉ አልላቀው እንጂ ከነባህሉ አይደለም። ማለት፣ አባቶቻችን እምነቱን የተቀበሉት በራሳቸው ፊደልና ቋንቋ ነው። በዚያ ላይ በራሳቸው ሥነ ጽሑፍ ኢትዮጵያዊነት መልክ እየሰጡት በ’የእኛ’ነት አዳብረውታል።” ሲሉ በሰፊው አብራርተዋል።
“የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ታላላቆቹን የጥንቶቹን የሃይማኖት አባቶች ለማስታወስ ያህል አንዳንድ ጊዜ ለልጆቻቸው “ጴጥሮስ፣ ጳውሎስ” ወዘተ የሚል ስም ይሰጡ እንደሆን እንጂ የክርስቲያኑ ሁሉ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ የወጣ አይደለም። … በዚሁ አንጻር ሙስሊሞቹ እስልምናን እንዴት እንደተቀበሉት ስናይ ሃይማኖቱን መጤ የሚያሰኝ ባህል ሲያመጣብን እንገኘዋለን። ኢትዮጵያ ሀገራችን የቋንቋ ሀብታም ሆና ሳለ፣ (እስልምና) የሚጠናው በዐረቢኛ ነው። የተከታዮቹ (ሙስሊሞች) ስም ዓረቢኛ እንጂ ኢትዮጵኛ አይደለም። … ሃይማኖቱን አልብሶ የመጣው ባህል አለያየን …የመካከለኛው ምሥራቅ ክርስቲያኖች ሃይማኖታቸውን ሳይቀር የሚማሩት በብሔራዊው ቋንቋ (በዓረቢኛ) እንጂ በራሳቸው በቅብጡ በሱርስት አይደለም። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ግንበባህል ረገድ “የዓረብ ጠረን” አለባቸው። ለዓረብ ሊግ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ የከፈቱ ሰዎች በሀገሪቱ ውስጥ ኣረቦች አሉ ብለው ሳይሆን፣ እንደ ሱዳኖች ዓረቦች ሊሆኒዩ የሚችሉ ሙስሊሞች አሉ ብለው በመገመት ነው።” ብለዋል።
የውይይት አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነገር እንዳልሆን የተናገሩት ምሁሩ “ወደ ኋላ የሚታየው ያለፈው ስሕተት እንዳይደገም ለማድረግ እንጂ፣ ለበቀል” መሆን እንደሌለበት ሲመክሩ “ለበቀል ከሆነ ሁሉም ቢላዋውን ይስልና መተላለቁ ይቀጥላል። … ከአለፈው ለመላቀቅ የምንችለው ለመርታት እየተከራከርን ሴኢሆን የሆነውን ተቀብለን ታሪክ ያመጣብንን ስሕተት ለማረምና ለመቀበል ስንዘጋጅ ነው” ብለዋል።
የቤተ ክርስቲያን አምላክ ይጠብቅዎ፣ ረዥም ዕድሜ ያድልዎ!!!!!!!!!!!!
ሰው አያሳጣን።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)