February 21, 2009

ጽድቅን ሁሉ "ቀሲስ" አስተርአየም መፈጸም ይገባዋል!

Dear Dejeselamaweyan,
Here is an article contributed to Deje Selam in relation to another article posted some time ago, not here, but for example on ETHIOMEDIA.COM. It was entitled "ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል" by a certain ቀሲስ አስተርአየ. So,........ Enjoy both these articles and judge yourselves!!!!
Cher Were Yaseman,amen
DS
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ጽድቅን ሁሉ "ቀሲስ" አስተርአየም መፈጸም ይገባዋል!

በቅድሚያ: "ቀሲስ አስተርአየ" በሚል ስም የተጠቀመ ግለሰብ: የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የሆነ ካህን በመምሰል : ጥምቀትን አስመልክቶ የጻፈውን መጣጥፍ አነበብኩት:: እውነቱን ለመናገር: ጽሑፉን ተመልክቼ: ጸሐፊው እውነተኛ ኢትዮጵያዊ የተዋሕዶ እምነት ተከታይ አለመሆኑን ለማወቅ: ብዙ ገጽ ማንበብ እንዳላስፈለገኝ ስገልጽ "ቀሲስ" አስተርአየ ሞራሉ እንደማይነካ በማመን ነው::
የ8ኛ ክፍል የአማርኛ ክፍለ ጊዜ እንኳ የሚያስተምረንን የመጣጥፍ አጻጻፍ መመርያ ተከትሎ: ለማን ከማን እና ምንን አስመልክቶ እንደተጻፈ በግልጽ ማስፈር ያልቻለው "ቀሲስ" አስተርአየ: ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናንንና አባቶችን "የተለሰኑ የኖራ መቃብሮች" እያለ ሲወርድባቸው ትንሽ አለማፈሩ አስገርሞኛል:: በቃ: ይሄ በጥቅም የታሰሩ አንዳንድ የቤተክህነት ሹማምንት የሚሠሩት ሥራን እየታከኩ: መላውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን እምነትና ሥርዓት መስደብ: የተሀድሶ ፕሮቴስታንቶች ባሕል ሆኖ ቀረ አይደል?
ቀጥታ ወደነጥቦቼ ልግባ! እኔም እንደ"ቀሲስ" አስተርአየ መንዘባዘብ ስለማልፈልግ!
ለመሆኑ የ “ቀሲስ” አስተርአየ ጽሑፍ ዓላማ ምንድነው?
መንጋውን ለመጠበቅ የተቀበሉትን አደራ: በተለያየ ፖለቲካዊ ምክንያት ሳይወጡ የቀሩትን የቤተክህነት ቁልፍ ሹማምንት ለመውቀስ ነው? አዎ አጀማመሩ እንደዚያ ይመስላል! ግን ዋና ዓላማው ያ አይደለም::
መጀመሪያ እንዲህ በማለት አደራቸውን ያልተወጡ የሃይማንቶ አባቶችን እየወቀሰ ለማስመሰል ሞከረ-
"የበአሉ ዋና አላማና መልዕክት ከእኛ ከካህናቱና ከዘመኑ መንፈሳውያን መሪዎች ጋር እጅግ የተጋጨና ፍርቅ ሆነብኝ"
በማለት ጽሑፉ "ይህን ምዕመን በቅንነት በጽድቅ እናገልግለው" የሚል ስሜት ያለው መግቢያ ቢጤ ጣል አደረገልን:: "አባቶቻችንና እናቶቻችን"፣"ጽድቅና ኩነኔ"፣ "አባቶቻችን ሊቃውንት በግዕዝ ቋንቋቸው" ወ ዘ ተ... የሚሉ ቃላትን በመጠቀም የተዋሕዶ እምነት ተከታይ ለመምሰልም በእጅጉ ተፍጨረጨረ:: "የጥምቀቱ በአል አከባበር ለምን እኛ ከሌሎች ኦርቶዶክሶች ተለየን?" የሚል ጥያቄ ከሰዎች እንደቀረበለትና፡ ይህ እንዲጽፍ እንዳነሳሳው ነገረን- "ቀሲስ" አስተርአየ!
በሚገርም ሁኔታ፡ ትንሽ ወረድ ብሎ: የሃይማኖት አባቶችን መንፈሳዊ አደራ በአግባቡ አለመወጣት አጀንዳ ተወት አድርጎ: በተዋሕዶ እምነት ሥርዓት ላይ፡ በተምታቱ ቃላት: እንደልቡ ይጨፍርበትና ይዘልፈው ገባ::
"ዮሐንስ በራእዩ.." አለ "ቀሲስ" አስተርአየ.."ዮሐንስ በራእዩ ሰማይ ተከፍቶ ሲመለከት በሰማይ ባለው ቤተመቅደስ ያለው ሰማያዊ የቃል ኪዳን ታቦት አይቷል (ራእ 11:19) እኛም ይህን ምሳሌ ከባሕላችን ጋራ በማዛመድ በጥምቀቱ ጽድቅ ሁሉ ሲፈጸም የቤተመቅደሶቻችንን በሮች በመክፈት በየቤተ መቅደሶቻችን ያሉትን የቃል ኪዳን ጽላቶች እንገልጻቸዋለን" አለ:: (ሰረዝ የእኔ)
እኔ የምለው... የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን ጥምቀቱን ከባሕሉ ጋር ነው እንዴ ያዛመደው? ወይስ የሰማዩን ሥርዓት ነው ባሕሉ ያደረገው? እነዚህ ሁለቱን ለይተሃል አስተርአየ? ዮሐንስ በሰማይ ታቦት እንዳየ ራእይን ከጠቀሰ በኋላ: "ቀሲስ" አስተርአየ እንዴት ታቦትን ማውጣት "ከኢትዮጵያ ባሕል ጋር በማዛመድ" ሊለው ቻለ? ኢትዮጵያ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊውና ከሰማያዊው የታቦት ማውጣት ምሥጢር የተለየ "የታቦት ባሕል" አላት እንዴ? ታቦት ማውጣት እኮ- ለኢትዮጵያ የአምልኮ ሥርዓቷ እንጂ ባሕሏ አይደለም "ቀሲስ" አስተርአየ?! እንዴት ይህንን ሳታውቅ ቀሰስህ?
እኛ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች "ታቦት ባሕል እንጂ ሃይማኖት አይደለም" የሚለውን የነ ፓስተር አስተርአየን ስብከት እስኪበቃን እስኪያቅለሸልሸን ሰምተናል:: አሁን ቀሲስ እያላችሁ ስለማታውቁት አትቀባጥሩ ባካችሁ እናንተ ፕሮቴስታንቶች?!!


የአርአየ ፀብ ከሥርዓቱ ነው ወይስ ሥርዓቱን ካበላሹ ሰዎች ጋር?
የመንፈሳውያን አባቶችን አደራ አለመወጣት የበለጠ "በነብያት ትንቢት ባትሪነት" ሲያስረዳን "ቀሲስ" አስተርአየ እንዲህ እያለ ተንዘባዘበ:-
"አሁን ያለነው: በተለይም ሙተናል: መንኩሰናል: ቀስሰናል: ተጰጵሰናል ከምንለው ሁሉ የሚፈልቁት ግብራችን የምናሳየው ሁሉ ጌታችን ክርስቶስ የፈሪሳውያንን ባሕርይ ለመግለጽ በማትዎስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ላይ የደረደአቸው በግብዝነት ላይ የተመሠረቱ ጠባዮች ናቸው...." በማለት የሚከተሉትን ዘረዘረልን:-
(ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ካህናት፡ “በልክ የተሰፋ” ወቀሳ፡ ከማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ላይ እንደልቡ ሊያገኝ ባለመቻሉ: ለሁሉ ካህናት፣ ቀሳውስት፣ መነኮሳት፣ እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች የሚሆን የወቀሳ ጥብቆ ለመስፋት፡ ብዙ ነገሮችን ለመጨመር ተገደደ- ቀሲስ አስተርአየ)
• “ለሰው ለመታየት ጥቁር ቀሚስ ማንዘርፈፍ” (ይህ የቤተክርስቲያን ቀኖናዋ ነው:: "ቀሲስ" አስተርአየ፤ አንተን ምን አገባህ? ቀሚሱን መልበሱ ምን አጠፋ? የተደነገገ ሥርዓትን ነው እየነቀፍክ ያለኸው? ወይስ ቀሚሱን ሳይገባቸው የሚያጠልቁ ሰዎችን ምግባራቸውን እንዲመረምሩ እየመከርካቸው ነው?)

• “ኩፌት (ቆብ) መድፋት”- አሁንም ኩፌት መድፋት ሃይማኖታዊ ትርጉም ያለው ክቡር ነገር ነው:: አስተርአየ: መነኮሳት ኩፌት መድፋታቸው ነው ያበሳጨህ ወይስ አንዳንድ ኩፌት የደፉ ሰዎች፡ ምንም እንኳ ኩፌት ቢደፉም፡ እውነተኛ የመነኩሴ ግብር አለመያዛቸው እውነት አሳዝኖህ ነው?

• “ባለዘርፍ ቀጸላ መከናነብ.”. አሁንም ጥያቄዬ ተመሳሳይ ነው:: ጸብህ ከምንኩስናና ከቅስና ሥርዓት ነው ወይስ እውነት የካህናት ሥነ-ምግባር ማማር አስጨንቆህ ነው?

• “በሄዱበት ቦታ ሁሉ በከበሬታ ወንበር መቀመጥ”- ምዕመኑ ካከበራቸው: አስተርአየ: አንተን ምን አገባህ? የከበሬታ ወንበር ለሃይማኖት አባቶች በሙሉ ይገባል:: አሁንም ካህናት መከበራቸው ነው ያናደደህ ወይስ መከበር የማይገባቸው አንዳንድ ካህናት ናቸው ያበሳጩህ? ጸብህ ከሥርዓቱ ነው ወይስ ሥርዓቱን ከሚያጎድፉ አንዳንድ ሰዎች?

• “በጉባኤው ሙያ ሳይበስል በድፍረት ራስን መምሕር ብሎ መሰየም” - ይሄ ለማነው? መጀመርያ "ቀሲስ" አስተርአየን እጠቁማለሁ:: ሳይቀስስ ራሱን "ቀሲስ" ብሎ ያወጀ ሁሉ እንደስምዖን መሠሪ የሚጠብቀው መቅሰፍት ብቻ ነው!

• “ለአረጋውያን አባቶች ይሰጥ የነበረውን ቁምስና መንጠቅ”- መንጠቅ እንዴት? በኃይል? ተቃውሞህ ለወጣት ቁምስና መሰጠት የለበትም ነው? ወይስ ቆሞሶች በኃይል ቁምስና ሊሰጣቸው አይገባም ነው? ሁለተኛው ከሆነ ልክ ነው:: አንደኛው ከሆነ ግን ተቃውሞህ: ቤተክርስቲያን ማንንም ትሹም ማን: በሃይማኖቱና በምግባሩ ህጸጽ ካገኘህበት ስለርሱ ችግር አውራ እንጂ ስለቁምስና አሰጣጥ ሥርዓት እርማት ሰጪ አድርገህ ራስህን በድፍረት አትሰይም:: በቆሞስነቱ አግባብ ያልሠራ ሁሉ በሥራው ይወቀስበታል: ሊወቀስም ይገባዋል:: ከዚህ ውጪ: ቤተክርስቲያን ለምን ወጣት ቆሞስ ሾመች ብሎ መከራከር- ትኩስ ኃይልን ከሚፈራ ያረጀ የተሃድሶ ርዝራዥ ብቻ የሚጠበቅ ከንቱ ፉከራ ነው!!

• ..በጣም የገረመኝ ግን... "ምን ማለት እንደሆነ ራሳቸው የማያውቁትን የተወላከፈ ግዕዝ ማነብነብ…" የሚለው ትችት ነው:: "ሊቃውንት አባቶቻችን በግዕዝ ጽፈው እንዳስቀመጡልን" እያለ ከላይ ኦርቶዶክሳዊ ለዛ ለጽሑፉ ለመስጠት የሞከረው ፓስተር አስተርአየ: ትንሽ ቆይቶ "ካህናት ምን ማለት እንደሆነ የማያውቁትን የተወለካከፈ ግዕዝ ማነብነብ" በማለት የጭቃ ምርጊቱን መረገ:: ምን ማለት እንደሚችሉና እንደማይችሉ ራሳቸው ካህናቱ ያውቃሉ:: ምናልባትም "ኩሉ ዕብን ለአዕባን" ብለው ይቀኙብህም ይሆናል:: አንድ ነገር ግን አስረግጬ ልንገርህ! ያም- እነሱ "ትርጉሙ ሳይገባቸው የሚወለካከፉበት" ግዕዝ: ይኸው ከባሕር ማዶ ሳይቀር አጋንንት የተጠናወተውን ጸረ-ተዋሕዶ ኃይል እየመታ በየሚድያው እያስለፈለፈ መሆኑን ነው! ግዕዝን ከኢትዮጵያውያን ካህናት አንደበት በሰሙ ጊዜ ሁሉ: የማያውቁት ኃይል እያንቀጠቀጠ ደማቸውን የሚያፈላቸው አስተርአየና ጓደኞቹ: ግዕዝ ለማያውቁ ካህናት "በግዕዝ እንዳይወለካከፉ" የቋንቋ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ያሰቡ ይመስል ይኸው ራሳቸው በግዕዝ እየተወለካከፉ ይጽፋሉ: ይናገራሉ:: አስተርአየ- አንዲት ቲፕ ልስጥህና- "ሥላሴ" እንጂ "ስላሴ" ተብሎ አይጻፍም:: "ተዋሐደ" እንጂ "ተወሐደ" ተብሎ አይጻፍም:: ይህንን መሰል ቁልፍ ሃይማኖታዊ የግዕዝ ቃላትን አወለካክፎ መጻፍ ስታቆም: ሌሎችን ለማረም ትነሳለህ::

• “መዝረፍ”- ማናችንንም ይመለከታል::
• “መስከር”- ይህም ማናችንንም ይመለከታል:: ቄሶች ሰከሩ: ሰረቁ: ወ ዘ ተ... የሚል ማጥላያ ግን ከሕጻንነቴ ጀምሮ ስሰማው የኖርኩት የፕሮቴስታንቶች ዲስኩር ሆኖ እስካሁን መኖሩ ይገርመኛል:: መቼ ነው ይሄ ክስ የሚያበቃው?? በምንፍቅና የሰከረ: ጾምን የማያውቅ: ስግደትን የማያውቅ: "ዲሪሪሪማማማማራርራራ!" እያለ ከመጮህ በቀር ቀድሶ ማቁረብ: አናዝዞ መፍታት: አጥምቆ የእግዚአብሔር ልጅ ማድረግ የሚችል ካህን የሌላቸው ፕሮቴስታንት"ቀሲሶች"፡ "ቄሶች ሰከሩ" ብለው ተራ የሆነ ውንጀላ በድረ-ገጽ ላይ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መለጠፋቸው ድንጋይ መሆናቸውን ያሳያል::

• "ብጹዕ ወቅዱስ መባል"- አቡነ ጳውሎስን ነው? ለምን በቀጥታ አቡነ ጳውሎስን የተመለከተ ጽሑፍ አትጽፍም ነበር? ለምን ካህናትን በጅምላ ስትጨፈጭፍና ዙርያውን ስትሽከረከር ቆየህ እስካሁን? ስለ አቡነ ጳውሎስ ክፋት ወይ ደግነት፡ አንተ ከኦርቶዶከሳዊው የበለጠ አውቀህ ልትነግረው ነው ወይ? አይደለም! የተለመደውን ጸረ-ተዋሕዶ ዲሰኩራችሁን ለመደሰኮር እንደ መንደርደርያ እየተጠቀምከው ነው እንጂ፡፡

• "የጥምቀትን በዐል ለማክበር አብሮ መሰለፍ"- ወይ ጉ......ድ! ይህም ወንጀል ሆነ? በጥምቀት በዐል መሳተፍ ያለባቸው ንጹሐን ካህናት ብቻ ቢሆኑ: እኔ በዐሥር ጣቴ እፈርማለሁ- "ቀሲስ" አስተርአየ እንደማይመጣ!!

ባሕል እና ጥምቀት
ጥምቀት ባሕላችን ሆኗል:: ተዋሕዶናል:: እሰየሁ! ይሄ የሚያስደስት ነው:: በጥምቀት በዓል አከባበር ፍጹም ዓለማዊ የሆነ ዘፈን የሚጨፍሩና የሚዳሩ ብዙዎች አሉ:: ይሄ የሚያሳዝን ነው:: ስህተት እንደሆነ እያወቁ: ስህተት ውስጥ ከገቡ: ቤተክርስቲያን ምንም ልታደርጋቸው አትችልም:: "ሂዱ ከዚህ" ብላ አታባርርም:: ቢያንስ በሩቁ ታቦቱን ተሳልመው: በልባቸው ጸሎታቸው አድርሰው: አርሞኒካቸውን ይዘው: ልብሳቸውን አስተካክለው: ወደቤታቸው ይገባሉ:: ማን ያውቃል? የዛሬ ዓመት የተሻለ ሰው ሆነው ይመጣሉ::
ፕሮቴስታንቶች: ይህችን የሥነምግባር ጉድለት ይዘው: ለብዙ ዘመናት "ጥምቀት መንፈሳዊ ሳይሆን ዓለማዊ በዓል ነው፤ ስለሆነም መቅረት አለበት" እያሉ ሲወተውቱ ኖረዋል:: የዘንድሮው ጥምቀት ግን አስደነገጣቸው:: በኢ-አማንያንና በመናፍቃን ድርጊት ልቡ ያዘነ ሕዝበ ክርስቲያን፡ አንዲትም ጭፈራና መዳራት ውስጥ ሳይገባ፡ በእንባና በዝማሬ: ሃርሞኒካውን ቤቱ ጥሎ፡ ጌታን ሲያመሰግንና ሲማጸን ዋለ:: እንዲሁም ታይቶ የማይታወቅ አንዳንድ ክስተት ተከሰተ:: ለምሳሌ የቃሊቲዋ ቁስቋም ታቦት፡ ባለችበት የጥምቀት ባሕር መቀመጥ እንደምትፈልግ ለካህናቱ አስደናቂ ምልክቶችን አሳይታ፡ በጥምቀተ ባሕሩ ከተመች:: የክርስቲያኖች እንባ፡ ጽርሐ አርያም ደርሶ ያንኳኳ ይመስላል!
ታድያ ይህ፡ መንፈሳውያን ነን ለሚሉ ሁሉ፡ መልካም ዜና ሊሆን ይገባው ነበር:: ፕሮቴስታንቶች በእውነት ለጥምቀት ተቆርቋሪ ቢሆኑ ኖሮ፡ በዘንድሮው ጥምቀት ደስታቸውን መግለጥ ነበረባቸው:: ቢሆንም እነ "ቀሲስ" አስተርአየ ያሉትን ተመልከቱ:-
"በየአመቱ ስናከብረው: ካለፈው (ካምናው) በአላችን እለት ጀምሮ እስከዘንድሮው እለት ከተፈጸሙት ሁሉ የ"ጽድቅ" ተቃራኒዎች ለመሸሽና ለመራቅ ጽድቅን (እውነትን) ለመመስከር ስንታገል ይህ አመት አለፈ ብለን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደኛ በሚጎርፉት ሰዎች ፊት ቆመን ለመምስከር ነበር:: ዘንድሮ ደግሞ ከዚህች ዕለት እስከ ከርሞ እለተ-ጥምቀት ድረስ እግዚአብሔር ቢአቆየን "ጽድቅን ሁሉ ለመፈጸም" መዘጋጀታችንን ለአለሙ ሁሉ በአደባባይ መግለጽ ነበረብን: አልተቻለም"
እኔ የምለው አስተርአየ: ጽድቃችን ለአለም ተገለጠ የሚባለው እንደአንተና እንደጓደኞችህ ተሃድሶዎች ፒያኖ ይዘን: ጃዝና ጊታር አንጠልጥለን: ሱፍና ከረባት ለብሰን: ወደላይ እንጣጥ እንጣጥ እያልን... "ጌታ ጌታ!" ስንል ይሆን? ምን እንድንጠብስልህ ፈልገህ ነበር በዘንድሮው ጥምቀት? ጽድቅን የፈጸሙ እነማን ይሁኑ: ያልፈጸሙ እነማን ይሁኑ አንተ በምንህ አወቅህ? የእያንዳንዱ ሰው ጽድቅ መለኪያ "ጽድቆሜትር" ዓይንህ ላይ ገጥመሃል? ጌታ ጸሎታችንን፡ እንባችንን ይቀበል፡ አይቀበል፡ መጥተህ የምትነግረን፡ አንተ በእኛ ላይ የተሾምህ፡ የተቀባህ ነቢይ ነህ? ምንድነህ?
ደስ አይበልህና፡ በዘንድሮው ጥምቀት ልባዊ አከባበር ልባቸው የተነካ ጥቂት ጎብኚዎች፡ በኢትዮጵያ ኦርስቶሶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነትና ሥርዓት መሠረት ጥምቀታቸውን ፈጽመው፡ ሃብተ-ወልድ: ስመ ክርስትናን ተቀብለዋል:: ለሚቀጥለው ዓመት፡ አንተና ዘመዶችህ "በመደሰት በመሳቅ ማክበር ነው እንጂ: የምን ማልቀስና መለማመጥ ነው" የሚል ለወጥ ያለ ማደናገሪያ ስብከት ይዛችሁ እንደምትመጡ እንጠብቃለን:: ይህ ሕዝብ፡ ታቦቱን ከብቦ ሲስቅም ሆነ ሲያለቅስ: ሲደሰትም ሆነ ሲያዝን: አንተና መሰሎችህ ሁሌ ተቃራኒውን እየነገራችሁ ግራ ልታጋቡት ትሞክራላችሁ:: የጽድቅ ጠላት የሆነ መንፈስ በእናንተ ላይ ሰልጥኗል!
የጥምቀት በአል ፈጽሞ ሊቀር የሚገባው መሆኑን ለማሳመን ፈለግህና ደግሞ እንዲህ አልህ፡-
"የጥምቀት በአል ስናከብር ሊፈጸሙ ከሚገባቸው ጽድቆች ጋራ ተያይዘው የሚፈጸሙ ባሕላውያን ትርፍራፊዎች አሉ:: እነሱም- ሆታዎች: ሽብሸባዎች: ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እያልን የምንለብሳቸው የልብሶቻችን አይነቶች ናቸው::"
"ከቤት አሠራራችንና ልብሳችን ጀምሮ: እስከምንጎርሳቸው ምግቦቻችን ከእኛነታችን ጋር የተዋሐዱት እንደዛሬው ሕይወታችን ከጽድቅ ተለይተው እንደገፈት ካላጠለሉ በቀር ከታሪካችንና ከባሕላችን ጭምር ነው"
እንደፍየል አንጀት የተጥመዘመዙትን እኒህን ዐረፍተ ነገሮችህን ስረዳቸው- “ያሬዳዊ ሽብሸባም ሆነ የአባቶች የእናቶች ሆታና እልልታ: እንዲሁም በአሉን አስመልክቶ የሚደረገው ግብዣና ድግስ ሁሉ ፈጽሞ ከእኛ ተለይቶ "ሊጠልል" ይገባዋል” የሚል ስሜት ይሰጡኛል::
እሺ: ሆታውን እልልታውን: የካህናቱን ሽብሸባ አቆምን:: ድግሱም ቀረ:: ጥምቀት እንዴት ይከበር? በዝምታ? ታቦቱ አይውጣ? ካህናት አይዘምሩ? እናቶች እልል አይበሉ? አባቶች ሆ አይበሉ? ምን እናድርግ? "ራፓፓፓ...ካካክካ..ሪሪሪርማማማስስስስ!" እያልን ቤታችን ወንበር ሥር በመንፈራፈር "ሃሌሉያ ጌታ ሆይ! ሃሌሉያ!" እያልን ዐረፋ እየደፈቅን: እየተንዘፈዘፍን ቀኑን እናስበው? እንደዚያ ነው የፈለግኸው?
ከተለያዩ ሃገራት መጥተው የእኛን ጥምቀት የሚካፈሉ የሌላ ሃገር "ክርስቲያኖችንም" እንዲህ ስትል ተቆርቁረህላቸዋል:-
"ሌሎች ክርስቲያኖች ካሜራቸውን ተሸክመው በየአመቱ ወደኛ የሚጎርፉት እራሳቸው በአገራቸው ለማክበር ሜዳ: ካህናት ስለሌሏቸው አይደለም:: እጅግ ሰፊ የሰማይ ስባሪ የመሰለ ሜዳ አላቸው:: እጅግ የረቀቁ ሊቃውንት ካህናትም አሏቸው"
እዚህ ጋር ወራጅ አለ::
1. ቱሪስቶች ወደእኛ የሚመጡት፡ ሜዳ ስለሌላቸው እንዳልሆነ፡ ማንም ኦርቶዶክሳዊ ያውቃል:
2. የረቀቁ ሊቃውንት ካህናት አሏቸው ያልከው ደግሞ፡ ከተዋሕዶ ውጪ የረቀቁ ሊቃውንት የሚረቅቁት፡ በሃይማኖት መሰል ፍልስፍና እንጂ፡ በእውነተኛ ሃይማኖት እንዳልሆነ ላሰምርልህ ግድ ይለኛል:: አንዲት ሃይማኖት- እሷም ተዋሕዶ! ከዚያ ውጪ የተራቀቀ ሁሉ ከመንግሥተ ሰማያት የራቀ ነው:: ሥልጣነ ክህነትም በእጁ የለችም:: ይህ ሮማውያንንና በፕሮቴስታንቲዝም ሥር ያሉ ልዩ ልዩ ክፍልፋዮችን: እንዲሁም በስም ኦርቶዶክስ የሚባሉ የሁለት ባህርይ አማኝ ግሪኮችንና ራሽያኖችን ይጨምራል::
ለእኛ በተዋሕዶ የጸኑ ጥቂቶች ኤርትራውያን: ግብጻውያን: ሶርያውያን: ሕንዳውያንና: አርመንያውያን ተዋሕዶ አምሳያዎች አሉን:: በተረፈ ሌሎቹ የሚራቀቁት በአሬዎስ: በሰባስልዮስ: በንስጥሮስና በሉተር ፍልስፍና ስለሆነ፡ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን አታውቃቸውም::
ይህን ሳትማር ነው "የቀሰስከው" አስተርአየ?
ስለቱሪስቶቹ ቀጠልክና ደግሞ እንዲህ አልከን...
"እነሱ እንደእኛ የማያከብሩት ክርስትና በየሃገራቸው ሲገባ የተቀበሉት የመጀመርያ ክርስቲያን አባቶቻቸው cultural theolojy ስላላደረጉላቸው ብቻ ነው::
ቸብ ቸብ ቸብ! እሰይ የእኔ አዋቂ "ቀሲስ" አስተርአየ!! እንዴት አድርገህ አስተራይከው ባክህ?!
በመጀመርያ ደረጃ ከኢትዮጵያ በቀር፡ ሌሎች ሃገራት ይህን የማያውቁት፡ በባሕል ሳይሆን በሃይማኖት ልዩነት ነው! ኢትዮጵያ ከክርስትና በፊት በሕገ-ኦሪት ስለነበረች: ታቦትን በንግሥት ማክዳ ልጅ በሚኒሊክ አማካኝነት ተቀብላለች:: በኦሪቱ ይከበር የነበረውንም፡ እስራኤላውያን በደጅ ዳስ ጥለው ታቦቱን ይዘው የተንከራተቱበትን ጊዜ እያስታወሱ የሚያከብሩትን የዳስ በአል፡ ልክ እንደእሥራኤላውያን ታከብረው ነበር:: በሐዲስ ኪዳን፡ የዳስ በአል የበለጠ አምሮና ሸብርቆ: በክርስቶስ ጥምቀት አማካኝነት አማናዊና ፍጹም ሆነ:: ስለሆነም: የዳስ በአል ድርብ ድርብርብ ትርጉሞችን ይዞ በዐቢይነት የጌታ ጥምቀት መታሰቢያ ሆነ::
ይሄ ነው የጥምቀት በዐል ነገር በአጭሩ! ኢትዮጵያ በኦሪቱ ስለነበረች፡ በአሉን ቀድሞውኑ ታውቀው ነበረ- በሃይማኖታዊነቱ:: ስለሆነም የሃይማኖት እንጂ፡ በባሕል በአል አይደለምና፡ ይህንን ድጋሜ አጥርተህ እንድትማር፡ ወደቄስ ትምህርት ቤት እንድትመለስ ምክሬን እለግስሃለሁ!!
በመጨረሻም: በጣም ወጥ የረገጥክበትንና ተዋሕዶን የሰደብክበትን አንዲቷን ነጥብህን ላስታውስህ::
እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር- ላይህ ላይ ያለው የዘንዶ መንፈስ:-
"የጥምቀት በአል .... የግላችን ኢትዮጵያዊ በአል ነው:: የግላችን ነው ስል ከአብነቱ አተረጓጎማችን ክልል ወጥቶ: ከእኅት አብያተ ክርስቲኢያናት ኅብረት አፈንግጦ: ከካቶሊኮች ተቀላውጦ በእኛ ዘመን እንደታወጀው እንደነገረ ማርያሙ ማለቴ አይደለም::
በዚህ ፍጹም ሰይጣናዊ በሆነ ስድብህ ውስጥ ሁለት አጋንንታዊ ሃሳቦች ጠቅሰሃል:-
1. “ነገረ ማርያም ከአብነት ትምህርት አተረጎአጎማችን ጋር አይሄድም”- እንዴት አይሄድም? ነገረ ማርያም መግቢያው እንዲህ ይላል:-
"ከነገረ ነብያት ቀጥሎ: ከምሥጢረ ሥጋዌ አስቀድሞ: ነገረ ማርያምን ይማሩ ዘንድ ይገባል:: ስለምን ነው ቢሉ: ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከማንም ከማን ሰው አልሆነም: ሥጋ አልለበሰም: ከእመቤታችን ከእግዝእትነ ማርያም ነውና"
እንዲሁም: ከነገረ ማርያም (የድንግል ማርያምን ታሪክ) ከሚገልጸው መጽሐፍ ላይ: አንተ መግቢያህ ላይ በሽንገላ ስታሞካሻቸው የነበሩ የግዕዝ መጻሕፍትና የግዕዝ ሊቃውንት: በየአንድምታ ወንጌሉና: በውዳሴ-ማርያም: ቅዳሴ-ማርያም ትርጓሜ ሁሉ አስገብተዋቸው: ሲጸልዩባቸውና ሲያስተምሩባቸው ለዘመናት ኖረዋል::
እነዚህ ሊቃውንት: የእመቤታን ታሪክ ጠፍቷቸው: ከካቶሊክ ቀላወጡት ልትል የደፈርከው: የፈረንጅ ካልቀላወጡ ትክክል የማይመስላቸው የ"ቀሲስ" አስተርአየ ቢጤ መሰሉህ ወይ?
2. ቀጠልክና "ከእኅት አብያተ ክርስቲያናት ያፈነገጠ" አልከው:: በእመቤታችን ጥንተ-ነገር: በታሪኳ ከየትኞቹ እኅት አብያተ ክርስቲያናት ጋር እንለያያለን? ልዩነቱን አውጣ ብትባል ይህ ነው የሚባል የረባ ነገር ይዘህ እንደማትመጣ አውቃለሁ:: ምክንያቱም: በአብነት ትምህርት ቤት ገብተህ መማር ቀርቶ በአጠገቡም ስላላለፍክ!

ማጠቃለያዬ:
“መንፈሳውያን መሪዎች ሥነምግባራቸው ያማረ መሆን አለበት” በሚል ለዘመኑ ፖለቲካ በሚመች: እውነተኛ ተቆርቋሪ የሚያስመስል አጀንዳ ተነስተህ: ጥምቀት በአልን "ባሕል" እንጂ "ሃይማኖታዊ ትውፊት የሌለው" ብለህ ለመሳደብ በመብቃትህ ሃይማኖትህ ምን እንደሆነ ለመረዳት አብቅቶኛል:: ሌሎች ኦርቶዶክሳውያንም ሲያነቡ በትክክል ፕሮቴስታንት-ተሃድሶ እንደሆንክ እንደሚረዱ እርግጠኛ ነኝ::
“ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል” ስትል ካንተ ብትጀምረው ጥሩ ነው:: መዋሸት: መዘላበድ: እዚህ እዚያ መርገጥና ግልጽነት የሌለው መልእክት በመጻፍ: ተዋሕዶንና ሥርዓቶቿን ለማጥላላት የምታደርገውን ዘመቻ ብታቆም ጥሩ ጅምር ይሆንሃል::

የተዋሕዶ ምዕመን

2 comments:

Anonymous said...

እጹብ ድንቅ የሆነ መልስ ነው!! ሠራዊተ ዲያቢሎስ የተለያየ ጭምብል እየለበሰ በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ላይ የጀመረውን ዘመቻ እንዲህ በብቃት እና በቁርጠኝነት መዋጋት የዘመናችን የተዋሕዶ ልጆች ግዳጅ ነው።
"ቀሲስ" ተብዬው የሐሰት እንክርዳዱን ለመዝራት የተጠቀመበት ዌብ ሳይት ላይ መልሱ እንዲወጣ ቢላክ ... ተልኮ ካላወጡት ደግሞ ጸረ ቤተክርስቲያን አቋማቸውን በገሃድ ማጋለጥ አስፈላጊ ነው።
ለጽሑፉ አዘጋጅ ያላኝን ታላቅ አድናኦት እና አክብሮት እየገለጽኩኝ
ለሌሎቻችን ዝምታው ያብቃ እላለሁ!!
ወስብሐት ሌግዚአብሔር

Anonymous said...

ይገርማል ቄስ ሳትሆን "ቀሲስ" አስተርአየ ነኝ ያልከዉ ሁነህም ከሆነ ሳትማርና ሳታዉቅ ሳይገባህና ሳይገባህ (ጠብቆ ይነበብ) ስለሆነ ለጥፋት ሆነብህ ደግሞስ የለየልህ መናፍቅ ተሃድሶ ፕሮቴስታንት (የሚስማማህን መርጠህ ዉሰድ) እንደሆንክ ቃላቶችህና የብዕር አጣጣልህ ይገልጡሀል፡፡
አንተ እንኩንስ ቄስ ልትሆን በቄስ ት/ቤት በር ላይ አላለፍክም የተዋህዶ ምዕመን በዚህ በ Deje Selam ሳይት ላይ የመለሰልህ ላንተና ለመሰሎችህ በሙሉ ይጠቅማችኁልና ደጋግመህ አንብበዉ ከዚያ በኁላ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምንም ልትናገር እንደማትችል ባዶ የባዶ ባዶ እንደሆንክ እዉነትን የማታዉቃትና ምናልባትም እስከ አሁን በኖርክባቸዉ ዘመናትም ስለ እዉነት ተናገረህ የማታዉቅ መሆንክን በደንብ ትረዳለህ እናም እንዲህ አይነት ማጭበርበር ቢቀርባችሁ ይሻላችኁል
የተዋህዶ ምዕመን አንጀቴን ነዉ ያራስከዉ እግዚአብሔር እድሜንና ጤናን ይስጥህ፡፡
ከአንባቢ

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)