February 16, 2009

በኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰተው የክርስትና-እስልምና ግጭት መንስዔው “ወሀቢያና እርሱ የፈለፈላቸው ጫጩቶች” ናቸው ተባለ

በኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰተው የክርስትና-እስልምና ግጭት መንስዔው “ወሀቢያና እርሱ የፈለፈላቸው ጫጩቶች” ያሏቸው አክራሪዎች መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት መ/ፕሬዚደንት አረጋገጡ። በአክራሪዎች ዘንድ “የወያኔ ደጋፊ፣ አፍቃሪ ክርስቲያን” በመባል ብዙ ነቀፋና ዘለፋ የሚሰነዘርባቸው ሼህ ኤልያስ ሬድዋን ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳረጋገጡት “በአረብ ሳት ቴሌቪዥን … የሚተላለፈውን ፕሮግራም በመተርጎምና በማባዛት የትርጉም ሥራ የሚሰሩ ነጋዴዎችና ወረቀት የሚያባዙ የህትመት” ባለሙያዎችን ጨምሮ አክራሪ ፀረ ክርስቲያን መልእክት ያላቸው ነገሮችን የሚያሰራጩ መኖራቸውን ም/ፕሬዚደንቱ ገልጸዋል።
“ዲሞክራሲ ሽፋን እየተደረገ ሀገር ሲጠፋ ዝም ብለን አንቆምም” ያሉት ም/ፕሬዚደንቱ “ሕዝባችንም ሊከላከላቸው ይገባል” ብለዋል። በም/ቤታቸው በኩል ስላለው እንቅስቃሴም ሲናገሩ “ለምክር ቤቱ እናሳውቃለን፤ እንመክራለን። ከዛም አልፎ ከመንግሥት ጋር እንመካከራለን። ለምን? ሀገሪቱ የመንግሥት ሀገር ናት፣ አባት አላት። መንግሥት የሚባል። የመጣውም ነገር የሀገር ጥፋት መሆኑን እናሳውቃለን። በጋራም እንሠራለን። ለሰላምም አብረን እንቆማለን” ብለዋል። በኢሕአዴግ አስተዳደር ሙስሊሙ ሕብረተሰብ ተጠቃሚ መሆኑን የተናገሩት ሼህ ኤልያስ “እየመጣ ያለው ነገር የእምነት ነጻነቱን የሚጋፋና ሕገ መንግሥቱን የሚሸራርፍ” መሆኑን ተናግረዋል።
አክራሪነት በኢትዮጵያ ውስጥ የለም በሚል ጭፍን ክርክር የሚያደርጉ ሰዎችን መልስ በሚያሳጣ መልኩ አክራሪነት እየተስፋፋ መምጣቱን ያብራሩት ሼህ ኤልያስ አክራሪነቱ ከፖለቲካ ጋር እየተቀየጠ መንጸባረቁንም አልደበቁም። ጉዳዩን ከምርጫ 97 እና ድህረ 97 ምርጫ ጋር በማገናኘት ከተናገሩ በሁዋላ ምንጩ ከውጪ መሆኑን፣ ምንነቱ ያልታወቀ ገንዘብ በሀገሪቱ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ፣ በኤን.ጂ.ኦ ስም የተለያዩ አክራሪነት ተግባራት እንደሚሠሩ፣ መንግሥት በቅርቡ ባጸደቀው የመያዶች(መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች) ደንብ መሠረት እንደዚህ ዓይነት ድርጅቶች እንደሚገሩ ሼህ ኤልያስ አብራርተዋል።
አክራሪዎች በተለይም ከደርግ ዘመን ጀምሮ ብቅ ብቅ ማለታቸውን የገለጹት ሹህ ኤልያስ ለጊዜው የአክራሪነት መንፈስ ያላቸው ሰዎች በም/ቤታቸው እንደሌሉ ለዚህም ምክንያቱ “የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ መተዳደሪያ ደንብ በግልጽ’” እንዳስቀመጠው፣ “ማንም የጽንፈኝነት፣ አክራሪነት፤ የችግር ፈጣሪነት አመላከት የሚያራምድ (አባል የሆነ አካል) በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ም/ቤት ማንኛውም እርከን ላይ መቀመጥ” እንደማይችል ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ካሉ ሌሎች እምነቶች ጋር ስላላቸው ግንኙነት ሲመልሱም ከኦርቶዶክስና ከመካነ የሱስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር አብረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል። “ህዝባችንን አደጋ ከመድረሱ በፊት እየመከርን ነው። የምስራቅ አፍሪካ እምነቶች ማህበር ለማቋቋም ጥረት ላይ ነው ያለነው። ቅዱስ አባታችን ሰብሳቢ እንዲሆኑ እያመናቸው (እየለመናቸው?) ነው ያለነው።፡ይሄ ማህበር ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቋቋም እያደረግን ነው። ከራሳችን አልፈን የሰው ሀገር እየመከርን ነው። አፍሪካዊ አጀንዳ ይኑረን እያልን ነው ያለነው” ሲሉ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)