February 18, 2009

በኢትዮጵያ ያለውን ሃይማኖታዊ ሁኔታ የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ሊደረግ ነው

በኢትዮጵያ አለ የተባለውን የእስልምና ጭቆና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በዲሲ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ሐጂ ነጂብ መሐመድ የተባሉ “የፈርስት ሒጅራ ፋውንዴሽን” ፕሬዚዳንት ፌብሩዋሪ 15/2009 ከስዊዲን ስቶኮልም ለሚተላለፈው “ሬዲዮ ነጋሺ” አስታወቁ።
ይህ በዓይነቱ ልዩ ነው ተብሎ የተገለጸውን ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጊያ ምክንያቱ በኢትዮጵያ በ2007 የተደገውንና ውጤቱ ከጥቂት ወራት በፊት የተገለጸውን የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መቃወም እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የሃይማኖት ግጭት ለዓለም ለማሳወቅ መሆኑን በመግቢያነት ያስቀመጠው የዕለቱ ቃለ ምልልስ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሚያደርጉት የመጀመሪያው ሰልፍ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
“በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ ለብዙ ዘመናት የተለያዩ ጥቃቶች” ሲደርሱ እንደነበር በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ “በአክራሪ ክርስቲያኖች” እምነታቸው እየተንቋሸሸ መሆኑን የገለጹት ሐጂ ነጂብ ይህንን ጉዳይ ለመቃወም ሕዝቡ በመነሣሣቱ ማርች 20/2009 በኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰልፍ ለማድረግ መወሰናቸውንንና እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን አስረድተዋል። የዲሲውን ሰላማዊ ሰልፍ ያዘጋጀው ፈርስት ሒጅራ ፋውንዴሽን ቢሆንም ጉዳዩን ዓለማቀፋዊ ገጽታ ለማላበስ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ሊቀሰቅስ በሚችለው “በድር ኢንተርናሽናል” በተባለው ድርጅታቸው አማካይነት ደግሞ በሌሎችም ቦታዎች ለመሰለፍ ሐሳብ እንዳለ ገልጸዋል።
ሰልፉን በኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ማድረግ ለምን እንዳስፈለገ፤ ምናልባትም መመንግሥትን ለመቃወም ወይንም ቤተ ክህነትን ለመቃወም ይሁን አይሁን እንዲገልጹ የተጠየቁት ሐጂ ነጂብ “ችግሩ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ የችግሩም ባለቤት የኢትዮጵያ መንግሥት ነው” ካሉ በሁዋላ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስሊሙን የሚቃወሙ ፀረ ሙስሊም ሃይሎች ተነሥተዋል፤ ይህንን በመቃወምና ለሰላም ጥሪ ነው … መንግሥት አክራሪ ክርስቲያኖች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ነው” ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ በወጣው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት “ወደውም ሆነ ተገደው የሙስሊሙን ቁጥር በግማሽ ያሣነሱ” ክፍሎችን ለመቃወምም እንደሆነ አስረድተዋል። መንግሥት ሙስሊሙን ቁጥር በግማሽ ያሣነሠው “በቤተ ክህነት ኮንስፒረሲ (አሻጥር)” እንደሆነም አብራርተዋል።
ሰልፉን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ኮሚቴዎች እንደተዋቀሩ ያስታወቁት ሐጂ ነጂብ ከነዚህም ውስጥ ቅስቀሳና መፈክሮችን የሚያዘጋጅ የሞቢላይዜሽን ኮሚቴ ፣ በጎሳና በተለያዩ ነገሮች ባሏቸው የተከፋፈለውን ሙስሊም የሚያነቃቃ የሥነ ጽሑፍ ኮሚቴ እንደሚገኙበት ተናግረዋል። ከዚህ በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው በተባለው ሰልፍ የሚጠበቁት ውጤቶች ምን እንደሆኑ ሲመልሱም “መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ ለማሳሰብ”፤ ሀገር ቤት ላሉ ሙስሊሞችም “አይዟችሁ አለንላችሁ፣ ድምጻችሁ ነን ለማለት” መሆኑን በዝርዝር ለማቅረብ ደግሞ፦
1. አክራሪነትን በሙሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመቃወም፣
2. “ክርስቲያን አክራሪዎች” በሙስሊሙ ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመቃወም፣
3. የሕዝብ ቆጠራውን ውጤት ለመቃወም፣
4. መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ላይ የቀረጸውን የእምነትና የሃይመኖት ነጻነት በእኩልነት እንዲያከብር ለመጠየቅ፣
5. በአክሱም መስጊድ እንዲሠራ ለመጠየቅ፣
6. የተለያዩ ሃይማኖቶች በመከባበር ለአንድነትና ለመተባበር ቁጭ ብለው እንዲነጋገሩና አብረው እንዲሠሩ መጠየቅ፣
7. መንግሥት የሃይማኖት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት (በጽ/ቤት ደረጃም ቢሆን) እንዲያቋቁም መጠየቅ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሐጂ ነጂብ እግረ መንገዳቸውን ስለ ጅማ አካባቢ የ1999 ዓ.ም የክርስቲያኖች ጭፍጨፋ ሲናገሩ “በክርስቲያኖች ቁስቆሳ” እንደደረሰ ገልጸው በተለይም የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ የተከሰቱትን የሐረር አካባቢ፣ የአርሲ፣ የባሌ፣ የጅማ የክርስቲያኖች ጭፍጨፋ ወደ ሙስሊሞች ጭፍጨፋ በመቀየር የተጎዱት ሙስሊሞች መሆናቸውን ለማሳመን ሲሞክሩ ተደምጠዋል።
ከ200 በላይ ፀረ ክርስትና መጻሕፍት የተጻፈው በሙስሊሙ በኩል መሆኑን ያልጠቀሱት ሐጂ ነጂብ በቅርቡ ለሕትመት የቀረቡ ከአራት የማይበልጡ የክርስቲያን መጻሕፍት በመጥቀስ እስልምና ተንቋሸሸ፣ “ይህንን ጉዳይ በአረብኛ ተርጉመን ብናሰራጭ” ኢትዮጵያ “በኢኮኖሚም በሌላም በኩል ጉዷ ይፈላል” ለማለት ሞክረዋል።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)