January 25, 2009

የመንግሥት መግለጫ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አሳዝኗል


የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ጥር 13 ቀን 2001 ዓ.ም “አንዱ በሌላው የእምነት ሥፍራዎች ወደ መስጊድና ወደ ቤተ ክርስቲያን በመግባት ተገቢ ያልሆኑ ተግባራትን መፈፀም” በሚል የሰጠውን መግለጫ በመጥቀስ፤ ኦርቶዶክስና እስልምና በሚል ዜይቤ በማጫፈር በመገናኛ ብዙሀን ያሳለፈው መግለጫ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሆኑትን ሁሉ ማሣዘኑን ቤተክርስቲያኗ ከትናንት በስትያ ጥር 15 ቀን 2001 ዓ.ም ገለፀች፡፡
ጥር 15 ቀን 2001 ዓ.ም ከሠዓት በኋላ በፓትሪያርክ ጽሕፈት ቤት ሲኖዶስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፤ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ፣ የፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር፣ የመንግሥት ኮሚውኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና፣ ከአዲስ አበባ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የመጡ ሊቀ ጳጳሳትና የሲኖዶስ አባላት በተገኙበት በተሰጠ መግለጫ ላይ ነበር ቤተክርስቲያኗ ማዘኗን የገለፀችው፡፡

ቤተክርስቲያኗ እንዳስታወቀችው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጽ/ቤት ጥር 13 ቀን 2001 ዓ.ም የሰጠው መግለጫ በጥፋት መድረክ ያልተገኘችውን ቤተ ክርስቲያን ሕይወትና ተከታዮቿን የሚጐዳ ስለሆነ ማስተባበያ እንዲሰጥበት ጠይቃ፣ የሕገወጦች እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና እየከፋ መጥቶ የባሰ አደጋ ከማስከተሉ በፊት አስቸኳይ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስባለች፡፡

ቤተክርስቲያኗ ባስተላለፈችው መግለጫ ላይ፣ ከሕገመንግስት ድንጋጌና ከሃይማኖታዊ ስነ ምግባር ውጭ በመንቀሳቀስ አንዳንድ ፀረ-ቤተክርስቲያን (አክራሪዎች) ከአዲስ አበባ ከተማ ጀምሮ በየክልሉ ባሉ ዞኖች እየፈፀሙት ያለው ተንኮልና ደባ እየሰፋ፣ እያደገና እየተጠናከረ ከመምጣቱ በፊት ከችግሩ አስከፊነት አንፃር በዳኝነት ታይቶ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድ የሚያስችል አመራር ይሰጥ ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፈውን ውሳኔና ማስረጃ በማያያዝ ጥቅምት 15 ቀን 2001 ዓ.ም ለሚመለከተው አካል አቤት ማለቷን አስታውሳለች፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በረጅም ታሪኩ በሃይማኖት፣ በጐሣ፣ በዘር ሣይከፋፈል ችግሩን በውይይት እየፈታ፣ ትዕግስትንና መቻቻልን ማዕከል አድርጐ በፍቅር አንድነት ተሳስቦ የኖረውን ያህል፣ ዛሬ ዛሬ አንዳንድ ሕገወጦች በመፍጠር ላይ ባሉት አፍራሽ ተልዕኮ ክርስቲያኑንና ሙስሊሙን ህብረተሰብ የሚያቃቅር፣ ሰላምን የሚያደፈርስ ህገ ወጥ ድርጊት ሲፈፀም እንደሚታይ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

በሃይማኖት ሽፋን እየተደረገ ያለው ሕገወጥ እንቅስቃሴ እያደገ ሲሄድ ቤተክርስቲያኒቷን ብቻ ሣይሆን የአገሪቱንም ህልውና እስከመፈታተን ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል ስጋት እንዳለ መግለጫው አመልክቷል፡፡

የአንድ አገር መሠረታዊ ፍላጐት ግቡን ሊመታ የሚችለው ሃይማኖታዊም ሆነ ሞራላዊ ስሜቱ የማይወቅሰውን የሚሠራ፣ በመልካም ስነ ምግባር የታነፀ፣ የሥራን ክቡርነት የተረዳና እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ መሆኑን ባስተዋለ ትውልድ ተደግፎ ሲገኝ ጭምር መሆኑን ለመረዳት በመቻሉ ነው፡፡

የእምነቱ ተከታዮች የሆኑትን ምዕመናን መንፈሣዊ ሕይወት በሰላማዊ መንገድ ለመምራት ቤተክርስቲያኗ በምታደርገው ጥረት ያልተጠበቀ ፈተና እየገጠማት ቢታይም፣ ፈተናውን ለማለፍ የምትችለው በትዕግስትና በመቻቻል፣ በመከባበርና በመደማመጥ በመሆኑ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ በመግባባትና በአንድነት ተባብሮ ሲሰራ ቢቆይም፣ አንዳንድ አክራሪ ነን የሚሉ ህገወጦች በሚፈጥሩት ሁከትና ሽብር የሕዝበ ክርስቲያኑ የሞራል ስሜት ተነክቶ ለከፋ ችግር በሚዳርግ ሁኔታ ላይ መሆኑን መግለጫው ያመለክታል፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ በመግለጫዋ ከመስከረም 30 ቀን 2001 ዓ.ም እስከ ጥር 12 ቀን 2001 ዓ.ም በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በአጠቃላይ ከ24 የሚበልጡ ዕምነት ተፃራሪ ድርጊቶች እንደደረሱባትና ይህንንም ከጅምሩ ለመግታት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጀምሮ በየስልጣን ተዋረዱ ላሉት የመንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አቤቱታዋን ስታሰማ መቆየቷን ገልፃለች፡፡

በሲኖዶስ አባላት ፀድቆ የተነበበው መግለጫ እንዳበቃ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም “በአገራችን ትልቁ እሴት ብለን የምንወስደው ተቻችለን መኖራችንን ነው፡፡ በውይይታችንም ወቅት ራሳችንን ማየት ይኖርብናል” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ከሌሎችም የእምነት ተከታዮች ጋር ጥር 14 ቀን 2001 ዓ.ም መወያየታቸውን ሚኒስትሩ ገልፀው፤ በሁሉም ዘንድ አንድ ዓይነት መርህ እንደሚከተሉ፣ ነገር ግን ማንም እከሌ እከሌ ከማለቱ በፊት ውስጡን በደንብ ቢያይ የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

“በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በመሪዎች ዘንድ የሚተላለፍ ነገር ካለ ብናየው ጥሩ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፣ እንደመሪ ምን ማድረግ አለብን? ወይም ነበረብን? በማለት “ሌላውን ከመምከራችንና ከመውቀሳችን በፊት ራሳችንን አጥርተን ብናይ የተሻለና ጥሩ ነው” ብለው ቤተክርስቲያኗ ውስጧን እንድትመረምር መክረዋል፡፡

የተፈጠረውን ማንኛውንም ችግር በውይይት መፍታት የሚቻል መሆኑን የገለፁት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ ሲሆኑ፣ መንግስት ምን አጉድሏል? ምን ማድረግስ አለበት? በማለት ጠይቀው፤ መንግስት የሠጠውን መግለጫ በተመለከተ፣ መንግስት የእምነቶችን እኩልነት የማረጋገጥና ህገ መንግስቱን የማስጠበቅ ግዴታ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

መንግስት ሕዝብ ሲሞት፣ የሕዝብ ንብረት ሲቃጠል ህገወጦችን ዝም ብሎ እንደማይመለከት የገለፁት ከንቲባው፣ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ጥር 14 ቀን 2001 ዓ.ም. መወያየታቸውን ተናግረው “እኔ ንፁህ ነኝ እከሌ እንደዚህ ነው” በማለት ነገሮችን ሸፋፍኖ ማለፍ ሣይሆን፣ ነጩን ነጭ፣ ጥቁሩን ጥቁር ማለት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

“ሁላችንም የአገራችን ሁኔታ ያሳስበናል፡፡ ሁሉም ነገር የሚያምረው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በመግለጫው ላይ የተባሉትንና ሌሎችንም መንግስት በደንብ ጠንቅቆ ያውቃቸዋል” ያሉት ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው፡፡ በውይይትና በምክክር ሰላም መምጣት እንዳለበት ከተናገሩ በኋላ ቅድስት ቤተክርስቲያንም ብትሆን በምታውቀውም ይሁን በማታውቀው፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ውስጧን አጥርታ መጓዝ እንዳለባት አሳስበዋል፡፡

በማንኛውም ጉዳይ ላይ መንግስት ዝርዝር መረጃ እንዳለው የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ መንግሥት ሁሉም ነገር በምክክርና በውይይት መፍትሄ ቢገኝለት የተሻለ መሆኑን እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡

በቤተክርስቲያኗ የእምነት መሪዎችና በመንግስት ተወካዮች መካከል ሠፋ ያለ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ሕገወጦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የማድረግ ሥራ የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮችና መሪዎች መሆን እንዳለበት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ከእንግዲህ በሀይማኖት ስም ህገወጥ ሥራ የሚሠሩና ህገ መንግስቱን የሚቃረን ሥራ የሚሠሩትን በማጋለጥ፣ ከመንግስት ጐን በመሠለፍ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም የሃይማኖት መሪዎቹ አረጋግጠዋል፡፡
Last Updated ( Sunday, 25 January 2009 )

2 comments:

Anonymous said...

The story can be summerized as one of the following:

1. an extremely late reaction or

2. still marching as an agent for the divide and rule politics of that regime.

Anonymous said...

for all crimes abune paulos is responsible

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)