January 20, 2009

በዓድዋ የዘመነ አክሱም ከተማ ተገኘ

(በሔኖክ ያሬድ)
“ዋ! ... ዓድዋ
ዓድዋ የትላንትናዋ
ይኸው ባንቺ ሕልውና
በትዝታሽ ብፅዕና
በመስዋዕት ክንድሽ ዝና
በነፃነት ቅርስሽ ዜና
አበው ተነሱ እንደገና”

(Addis Reporter):
በኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክም ሆነ በጥቁር ሕዝብ ዘንድ ዓይነተኛ ስፍራ ያላት ዓድዋ በነዚያ አርበኛ በኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎ ትዘከራለች፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካም ትነሣለች፡፡ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከቦታዋ የተገኘው ነፍስ ኄር ባለቅኔው ጸጋዬ ገብረ መድኅን ስንኝ አስሮላታል፡፡ አበው በጀግንነታቸው እንደሚነሡባት ሁሉ የቅርስ ማዕከልነቷም ዜና ሆኖ እንዲናኝ አስችሏታል፡፡

አሁን ደግሞ ሦስተኛው ሺሕ ዓመት (ሚሌኒየም) በባተበት ዓመት በዘመነ አክሱም (ከ3ኛ-5ኛው ምእት ዓመት) የነበረ ጥንታዊ ከተማ በአካባቢው ለመገኘት ችሏል፡፡

ከዓድዋ በስተሰሜን ስብአት በሚባል ቦታ የተገኘው ከተማ በ10 ሔክታር ዙርያ የሰፈረ ሲሆን፣ በኅብረሰቡ ጥቆማ መሠረት በኅዳር ወር 2001 ዓ.ም በአካባቢው ጥናት ያካሄደው ቡድን ስፍራው የዘመነ አክሱም ቅርስ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመካነ ልማት ጥናት ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ሥር የተደራጀውና ከልዩ ልዩ ተቋማት የተውጣጣው ቡድን ጥናቱን አካሂዷል፡፡

የቡድኑ አባልና በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ምዝገባና ቁጥጥር መምሪያ ኃላፊ አቶ ተክሌ ሐጎስ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ስብአት በተባለው ተራራ ግርጌ በተገኘው የከተማ ፍራሽ የተለያዩ ቅርጽ ያላቸው ሐውልቶች፣ የጥንት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መስቀሎች፣ የነሐስ ሳንቲሞች ተገኝተዋል፡፡

በአካባቢው ባለው ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ሕንፃ ሥር በጥንታውያኑ አክሱማውያን የተሠራ ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡

ይኸን የሚያሳይ ሰባት ደረጃዎች ያሉት ደረጃ ከግኝቱ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የአሁኑ ገዳም የተሠራው በጥንቱ ሕንፃ አናት ላይ ነው፡፡ መሠረቱ ይታያል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑን ሲሠሩ አፍርሰውታል፡፡ ነባሩ ሕንፃ ዘጠኝ ሜትር ወደ ጎን ሰባት ሜትር ወደ ላይ ከፍታ እንደነበረው አቶ ተክሌ አመልክተዋል፡፡

የአክሱም አብያተ መንግሥትም ሆነ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰሩት መሠረቱ ከፍ ባለ ሕንፃ ላይ በመሆኑ አዲሱ ግኝት የዚያ ዘመን ቅሬት ነው የሚባለው በዚህ ምክንያት መሆኑን አቶ ተክሌ ጠቁመዋል፡፡ በኃላፊው አገላለጽ የአክሱም ዘመን ቅርስ ነው የሚያሰኘው ሌላው ምክንያት ከፈረሰው ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን የዚያ ዘመን መስቀል በግድግዳው ላይ የነበረው በድንጋይ ተቀርጾ የተሠራው የአክሱም ዘመን መስቀል ቤተ ክርስቲያኑን አፍርሰው ሲሰሩት ነባሩን መስቀል አካትተውታል፡፡ የተገኙት ዘጠኝ ሐውልቶችም በአክሱም ካሉት ጋር ይመሳሰላሉ፡፡

ሌላው የአክሱም ዘመን ከስድስት የነሐስ ሳንቲሞች መካከል ሁለቱ የንጉሥ አርማሐ ናቸው፡፡ ንጉሥ አርማሐ በዙፋኑ ላይ ቁጭ ብሎ ትልቅ መስቀል ይዞ ይታያል፡፡ “ነገሠ አረመሐ” የሚል ጽሑፍና መስቀልም አለው፡፡

በሳንቲሞቹ የሚታወቀውን ንጉሥ አርማሐ በአንድ እጁ የጨበጠው ረዥሙ ምስል ብቻ ሳይሆን ራሱ መስቀሉም መገኘቱን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

የንጉሥ አርማሐ ስምና ምስል የተቀረጸባቸው የነሐስ ሳንቲሞች የክርስትናውን ዘመን የሚያሳዩ ናቸው፡፡

በስብዓት ባሁን ጊዜ ባለው የደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ዐውደ ምሕረት ሐውልቶች ተሰባጥረው ይታያሉ፡፡ የአካባቢው ኅብረተሰብ ለልማት፣ ውሃ ማቆሪያ ለማዘጋጀት ቁፋሮ ሲያደርግ ነው ልዩ ልዩ ቅርሶችን ለማግኘት የቻለው፡፡

በአቶ ተክሌ አነጋገር፣ ግኝቱ በአርኪዮሎጂ በቁፋሮ የተገኘ ሳይሆን የአካባቢው ሕዝብ በሰጠው ጥቆማ የዓድዋ ቱሪዝም ዴስክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ጋር በመሆን ምርመራውን አካሂዷል፡፡ መካነ ቅርሱን ከሌላው የሚለየው ዙርያው በሙሉ በጋራ የተከበበ መሆኑ ነው፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማ በአካባቢው ያለውን የኢኮ ቱሪዝም ሀብት ለሕዝቡ ማስታወቅ፣ ዳታ ቤዝ እንዲኖረው ማድረግና ለቱሪዝም ሀብት ማልማት ነው፡፡

ቱሪስቶች በታሪካዊው የጉዞ መስመር ደርሰው የሚመጡት በአክሱምና አካባቢው ሲሆን ከየሀ በስተቀር በዓድዋና አካባቢው ያለው የታሪክና የተፈጥሮ መስህብ እንዲታወቅ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያስረዱት አቶ ተክሌ፣ “ያለንን ሀብት እንወቀው፣ ካወቅነው ሕዝቡን ለማስተማር፣ ከባህላዊውም ሆነ ተፈጥሯዊው ቅርሱ ዘላቂ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችለዋል” ብለዋል፡፡

በስብአት ተራራ የተገኙት ቀያይ የሸክላ ሥራዎች በአክሱማውያን የእደ ጥበብ ልዕልና ዘመን ይሠሩ የነበሩት ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ቅርጽ ያላቸውና ያሸበረቁ ናቸው፡፡ በሸክላዎቹ ላይ ቅርጽ የማውጣት ጥበብ የጀመሩት በሁለተኛው ምእት ዓመት አካበቢ ነው፡፡

የሸክላ ውጤቶችን በተመለከተ ሁለት አመለካከት መኖሩ፣ አንደኛው አልፎራ ተብለው የሚጠሩት ከሜዲትራኒያን ባሕር አካባቢ እንደመጡ የሚታመን ቢሆንም አንዳንድ አጥኚዎች ኬሚካላዊ ትንተና በማድረግ እዚሁ የተሠሩ ናቸው የሚሉ መኖራቸውን አቶ ተክሌ ጠቁመዋል፡፡ በስብአት ሌላው የተገኘው ጡብ ነው፡፡ ቀያይ ጡቦች በአክሱም ሥልጣኔ 7ኛው ምእት አካባቢ የነበሩ ናቸው፡፡

የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች መስቀሎች፣ የድንጋይ ማሕተም፣ ጨሌዎች መገኘታቸው ያወሱት አቶ ተክሌ፣ በሳንቲሞች ላይ የንጉሡ ስም በተናባቢ ፊደሎች “ነገሠ አረመሀ” ተብሎ የተጻፈበትም መገኘቱ የግእዝ ፊደላት አነሳስና ሂደት የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ የኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት በማስፋፋት በዓድዋና በአካባቢው ያሉትን ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ማጥናት፣ አጥንቶ መረጃዎችን ማደራጀት ለአገሪቱ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ያመለከቱት ኃላፊው፣ ሰዎች ያላቸውን ሀብት አውቀው እንዲጠብቁትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የፕሮጀክቱ ግብ ነው፡፡

በአገሪቱ ያሉት እንዲሁም በየጊዜው የሚገኙትን ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን ለኅብረተሰቡ በማስተዋወቅ ረገድ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በልዩ ልዩ የሕትመት ውጤቶች በብሩሸርስ፣ በመጽሔትና በመጻሕፍት መልክ በማውጣት ላይ ይገኛል፡፡

የቅርሶችን መዘርዘር ከመግለጫ ጋር የያዘ ዓመታዊ ካታሎግ አራት ቅጾች የታተመ ሲሆን አምስተኛው ቅጽ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ቅርሶች ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብና በጥናት ይፋ ለማድረግ በመሰረተ ልማት ግንባታ የተነሣ ባለማወቅ የሚደርሰውን ጥፋት ለመከላከል የዘርፉ ባለሙያዎች “የኢትዮጵያ አርኪዮሊጂስት አሶሴሽን” የተሰኘ ማኅበር ማቋቋማቸውንም ገልጸዋል፡፡ ስብአትን የመሳሰሉ አዳዲስ ግኝቶችና በቅርሶች ያለው ወቅታዊ ሁኔታ የሚያመላክት የውይይት መድረክም ማዘጋጀት የማኅበሩ ዓላማ እንደሚሆን አቶ ተክሌ አመልክተዋል፡፡

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)