December 4, 2008

ሰማኸኝ: Listening as a Favor

Have you ever thought of listening to people as doing them a favor? Here is an interesting article you will enjoy and learn. It was written by Daniel Kibret and printed on Addis Neger Newspaper. I thank a Deje-Selamawi for sharing the article.
Cher Were Yaseman.
ዳንኤል ክብረት
ከሎስ አንጀለስ ወደ ቺካጎ ኦሐሬ አውሮፕላን ማረፊያ በመጓዝ ላይ ነበርኩ፡፡ አንዲት ሴትዮ አጠገቤ መጥታ ተቀመጠች፡፡ ነጭ ናት፡፡ አውሮፕላኑ ሲነሣ ሴትዮዋ ለብሼው የነበረውን የላሊበላ መስቀል ያለበት ነጭ ከናቴራ ተመለከተችና ‹‹ካህን ነህ ወይ›› ስትል ጠየቀችኝ፡፡ ምን እንደሆንኩ ነገርኳት፡፡ በዚያውም አስታክካ አንዳንድ ነገሮችን ማንሣት ጀመረች፡፡ እኔም የማውቀውን እየነገርኳት ተግባባን፡፡ በኋላም የቤትዋን ጉዳይ አንሥታ በእርስዋ እና በባለቤትዋ መካከል ስላለው ችግር ታወራኝ ጀመር፡፡ እኔም ታሪኩ ልቤን ነክቶኝ በእነርሱ ልማድ ‹‹አይ ኖው›› እያልኩ በጥሞና ሰማሁዋት፡፡

ምናልባት ከሦስት ሰዓት በረራ በኋላ ኦሐሬ አውሮፕላን ማረፊያ ስንደርስ ሴትዮዋ እጅግ አድርጋ አመሰገነችኝ፡፡ እኔም ገርሞኝ ‹‹ምን አደረግኩልሽ›› ስል ጠየቅኳት፡፡ ‹‹ሰማኸኝ፤ለረዥም ሰዓት በጥሞና ሰማኸኝ፤ በሕይወቴ እንደዚህ አድርጎ የሰማኝ የለም›› አለችኝ፡፡ እያመሰገነችኘ ተለያየን፡፡ እስካሁን ከአእምሮየ አትጠፋም፡፡
መሰማት ለካ የሰው ልጅ ከሚፈልጋቸው ነገሮች አንዱ ነው አልኩ ለራሴ፡፡ ብዙ ጊዜ ስለመናገር መብት እንጂ ስለ መሰማት ሲነገር ሰምቼ አላውቅም ነበር፡፡ ሰው ቢናገር የሚሰማው ከሌለው ምን ዋጋ አለው፡፡ በየቤተ እምነቱ አማንያን ለጸሎት ተግተው ልባቸውን ሲያፈስሱ የሚገኙት አምላካ ይሰማናል ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ አንድ አማኝ አምላኬ አይሰማኝም ብሎ ካመነ እምነቱ ይቀዘቅዛል፡፡
የሚናገሩ መሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ የሚያዳምጡ ግን ጥቂት፡፡ እንደ ቀድሞው የኩባ መሪ እንደ ፊደል ካስትሮ ለአራት ሰዓታት ባለማቋረጥ ለሕዝባቸው ንግግር የሚያደርጉ ነገር ግን አራት ደቂቃ እንኳን ሕዝባቸውን ለመስማት የማይፈልጉ መሪዎችን ዓለማችን አስተናግዳለች፡፡ ሕዝብ መሪዎቹ እንደማይሰሙት ማሰብ ከጀመረ ብሶቱን በማንጎራጎር መወጣት ይጀምራል፡፡
በቀድሞው ጊዜ አንዳንድ ነገሥታት እና መኳንንት ‹‹እረኛ ምን ይላል›› እያሉ ይጠይቁ ነበር ይባላል፡፡ በየወፍጮ፣ በየወንዙ፣ በየልቅሶው፣ በየሠርጉ፣ ይነገር የነበረው ሥነ ቃል ለዚያ ሥነ ሥርዓት ማድመቂያነት ብቻ ሳይሆን ‹‹ዛሬ ምን ተባለ›› ብለው የሚያዳምጡ መኳንንት እንዲሰሙት ጭምር የሚሠነዘር ነበር፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ እና ምንትዋብ የተዋወቁት
ሺ ፈረስ ከኋላው ሺ ፈረስ ከፊቱ
ይህን ሳታይ ሞተች ኮሶ ሻጭ እናቱ
ይህንን ሲሰማ ያጎራል ላመሉ
ማናትም ቢሏችሁ ምንትዋብ ናት በሉ
ብላ በልቅሶ ላይ የገጠመችው ግጥም ከቴዎድሮስ ጆሮ በመድረሱ ነው፡፡
ጆሮየ መስማት አይችሉም በለው ያሳብቡ የነበሩ አሮጊት አንድ ቀን ስለ እርሳቸው ክፉ ሲነገር ሰሙና ተቀየሙ፡፡ ሰዎቹም ገርሟቸው ‹‹ይሰማሉ እንዴ›› ብለው ጠየቋቸው፡፡ አሮጊቷም ‹‹ክፉ ክፉውንማ እሰማለሁ›› አሉ አሉ፡፡ ታድያ እኛም ምላሽ ለመስጠት ብቻ ብቅ የምንልበት ጠባያችን አንዳንዴ እንደ አሮጊቷ ክፉ ክፉውን ብቻ የምንሰማ ይመስልብናል፡፡
በየመሥሪያ ቤቱ የሚገኙ ባለሞያዎች ጥናት ለማጥናት ልቡናቸው የሚነሣሣው፣ የበታች ሠራተኞች ሙስናን በመታገል ግንባር ቀደም የሚሆኑት፣ የተበላሸ አሠራርን የሚቃወሙት፣ አዳዲስ ሃሳብ የሚያፈልቁት፣ መሰማታቸውን ካረጋገጡ ብቻ ነው፡፡ ሌባ አይታ ሌሊቱን በሙሉ ብትጮህ ብትጮህ ባለቤቷ አልነሣ ብሎ ያናደዳት ውሻ ‹‹ጩኸን ጩኸን እንዳልጮህን ሆንን›› አለች አሉ፡፡ የተናገሩት ነገር፣ ያቀረቡት ሃሳብ፣ ያጠኑት ጥናት፣ ያቀረቡት ጥቆማ፣ የሰጡት አስተያየት የውኃ ሽታ ሆኖ የቀረባቸው ሠራተኞች ጆሮ ገብ አለመሆናቸውን ሲያወቁ አይተው እንዳላዩ ሰምተውም እንዳልሰሙ ማለፍ ይጀምራሉ፡፡ ‹‹የድኻ ምክር ጥሩ ነው የሚሰማው የለም ፣የሐምሌ ውኃ ንጹሕ ነው የሚጠጣው የለም›› የሚለውን ተረትም እድሜ እንቀጥልለታለን፡፡
መስማት ግዴታቸው ብቻ ሳይሆን የመፍትሔው አንዱ ቁልፍ መሆኑን ያልተረዱ ባለሥልጣናት እና ባለሞያዎች ለመስማት ተቀምጠው እንኳን የተነገረውን ከማስተዋል ይልቅ የሚሰጡትን ምላሽ ስለሚያብሰለስሉ በሚሰጡት መልስ እንጂ በሰሙት ነገር አይደሰቱም፡፡ ምላሽ መስጠት የሚፈታቸው ችግሮች እንዳሉ ሁሉ መስማት የሚፈታቸው ችግሮችም አሉ፡፡ ለሐኪሙ ችግሩን አረፍ ብሎ ሲያስረዳ የሚፈወስ ስንት በሽተኛ አለ፡፡ ሰሚ ባለሥልጣን አግኝቶ ጉዳዩን ሲያስረዳ የተፈጸመለት ያህል የሚደሰት ስንት ባለ ጉዳይ አለ፡፡
በሚዲያ ላይ የወጣን ሃሳብ ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ ተቀብሎ ከዚህ ቦታ አግኝተን ይህንን ይህንን አስተካከልን ቢባልኮ ነውር የለበትም፡፡ ያም ሚዲያ እንደሚሰማ ይገባውና የተሻለ ሃሳብ ያቀርባል፡፡ ያም እንኳን ባይቻል ሃሳቡን ወስዶ ነገሩን ማሻሻሉ ኅብረተሰቡ ሃሳቡ የሚሰማለት መሆኑን እንዲያምን ያደርገዋል፡፡
በነገራችን ላይ በማኅበራት፣ በፓርቲዎች፣ በባለ ትዳሮች፣ በጓደኛሞች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች ሊፈቱ ከሚችሉባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ ለመስማት መቻል ነው፡፡ ሌላው ምን ይላል? ምን ያስባል? የሚለውን ለመስማት ቢቻል ኖሮ ሁለቱም ስለ አንድ ሃሳብ በተለያየ ቋንቋ እየተናገሩ መሆኑን ባወቁ ነበር፡፡ አንድ ሊቅ ሰው ሁለት ጆሮ እና አንድ አፍ የተሰጠው ብዙ እንዲሰማ እና ጥቂት እንዲያወራ ነው ብለው ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ተገላቢጦሹን እናገኘዋለን፡፡
ሁለት የተጋጩ ባለ ትዳሮች፣ ጓደኛሞች ወይንም ደግሞ የፓርቲ አባሎች በተጋጩበት ነገር ላይ ያላቸው ሃሳብ ተመሳሳይ ሆኖ ይገኛል፡፡ አንዱ የሚጠላውን ሌላው ይጠላዋል፣አንዱ የሚያምንበትን ሌላውም ይቀበለዋል፡፡ ለማስታረቅ እንኳን የልዩነት ነጥብ ይጠፋል፡፡ ታድያ ችግሩ ምንድን ነው? ቢባል ሁሉም ወገን ‹‹ልክ ልኩን ለመንገር››፣ ነጥብ ለማስቆጠር ያለበለዚያም ተሰሚነት ለማግኘት ሲባል ብቻ ይነጋገራሉ እንጂ እየተሰማሙ ስለማይነጋገሩ ሊግባቡ አይችሉም፡፡ ‹‹ስልቻ እና ቀልቀሎ›› እያሉ ሲነታረኩ ይኖራሉ፡፡
አንድ በሥልጣን ላይ ለአምስት ዓመታት ያገለገለ ወዳጄ ‹‹ባለ ሥልጣን ስትሆን ትልቁ ችግርህ የምትነግረው እና የሚያዳምጥህ ሰው አለመኖሩ ነው›› ብሎኛል፡፡ ገርሞኝ ‹‹ባለ ሥልጣንንማ ሁሉ ይሰማዋል›› አልኩት፡፡ ንግግር ስታደርግ ወይም መመሪያ ስትሰጥ እንጂ ሰው በመሆንህ ያለህን ብሶት ማን ይሰማሃል›› ነበር ያለኝ፡፡ አንዳንዴ ጊዜ ሰጥቶ፣ እህ ብሎ፣ አንገቱን ከልቡ እየነቀነቀ የሚሰማ ሰው ኦያምራችሁም፡፡
ለጆች ቁም ነገረኞች እንዲሆኑ ከፈለግን አንዱ መንገድ እነርሱን መስማት መቻል ነው፡፡ ልጅ ስለሆኑ ልንነግራቸው ብቻ አይገባም፡፡ ልናዳምጣቸውም ይገባል፡፡ ምን እንደ ሚያስቡ፣ ምን እንደሚያውቁ፣ ምን እንደ ሚያምኑ ማወቅ የምንችለው ስንሰማቸው ብቻ ነው፡፡ እንዲሰሙን የምንፈልገውን ያህል እንድንሰማቸውም ይፈልጋሉ ፡፡ ልንነግራቸው እንደሚያስፈልግ ሁሉ ሊሰሙም ይገባል፡፡ የሚያዳምጣቸው ካገኙ የሚያዳምጡ ይሆናሉ፡፡ ከማዳያምጡ ቤተሰቦች ተገኝተው የሚያዳምጡ ባለሥልጣናት እንዲሆኑ መጠበቅ ከንቱ ተስፋ ነው፡፡
ለብዙ ዘመናት የተካበተ ልምድ አለውና ገበሬውን እናዳምጠው፡፡ ግብርናን በኛ ዘመን የተጀመረ አናስመስለው፡፡ በዘመናዊው ሞያ መተንተን ቢያቅተዉም ያካበተዉ ልምድ አለው፡፡ የኛን ከመንገራችን በፊት የርሱን ብናዳመጠው ከምናስተምረው በላይ የምንማረው መኖሩንም በተረዳን ነበር፡፡ እኛ ሳይንስ ነው ብለን የምናስተምረው ትምህርት እኮ በሆነ ሀገር ያሉ፣ የታደሉ እና ሰሚ ያገኙ ገበሬዎችን ተሞክሮ ነው፡፡ የኛም ገበሬ ሰሚ ካገኘ እኮ ብዙ ሳይንስ አለው፡፡
አዚህ ዳላስ ውስጥ ባጋጠመኝ አንድ ታሪክ ልሰናበታችሁ፡፡ አንድ ሆቴል አለ፡፡ ወደ ውስጥ ሲገቡ በግድግዳው ላይ ለዓይን የሚታክቱ ከረባቶች ተሰቅለው ታገኛላችሁ፡፡ እዚያ ሆቴል ስትገቡ የሆቴሉ አስተናጋጆች ተሰብስበው መጥተው በመዝሙር ነው የሚቀበሏችሁ፡፡ እናንተ በአቀባበላቸው ተደስታችሁ ከነከረባታችሁ ወደ ውስጥ ስትዘልቁ አንድ አስተናጋጅ መጥቶ በመቀስ ከረባታችሁን ይቆርጠዋል፡፡ ለምንድን ነው ብትሉ ስትገቡ የተዘመረላችሁ መዝሙር ‹‹እዚህ ሆቴል ውስጥ ከረባት አድርጎ መግባት ክልክል ነው፤አድርጎ የሚገባ ሰው ካለ በመቀስ ይቆረጣል›› የሚል መዝሙር ነው የሚዘምሩት፡፡
የሆቴሉ አስተናጋጅ እንደነገረኝ ብዙዎቹ አይሰሙትም፡፡ እና ከረባታቸውን ያጣሉ፡፡
ኤሊኖይስ፣ ቺካጎ፣ ኦሐሬ አውሮፕላን ማረፊያ

1 comment:

Anonymous said...

please, do not post unread articles . It becomes habit on deje selam.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)