December 25, 2008

ብራና የኢትዮጵያ ሥነ ጽሕፈት መነሻ

ያለፉት የኢትዮጵያ ሁለት ሺሕ ዓመታት ዘርፈ ብዙ ታሪክ ተመዝግቦ የቆየው በብራና መጻሕፍት ውስጥ ነው፡፡ ዘመናዊ የወረቀት ሕትመት ወደ አገሪቱ እስከገባበት 19ኛው ምእት ድረስ መጻሕፍት ሲጻፍበት፣ ደብዳቤ መላላኪያ ሆኖ ያገለግል የነበረው የብራናው ውጤት ነበር፡፡

የብራና መጻሕፍት አዘገጃጀትና ሀገረሰባዊ እምነት በተመለከተ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የንባብና የውይይት ክበብ ታኅሣሥ 5 ቀን 2001 ዓ.ም. የዳሰሳ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

በደቡብ ጎንደር እስቴ ወረዳ ስላለው የብራና አዘገጃጀትና እምነት አቶ ታምራት ኃይሉ የዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል፡፡

ብራና ከበግ፣ ከፍየል፣ ከጊደር፣ ከፈረስ ቆዳ ደደቡና ጠጉሩ ተፍቆ የተዘጋጀ መጻፊያ ያልተቀጻ፣ በነጭ ኆጻ ታጥቦ የጠራ፣ የበራ ማለት እንደሆነ አጥኚው አለቃ ደስታ ተክለ ወልድን ጠቅሰው አመልክተዋል፡፡

የብራና ሥራ መቼና እንዴት በኢትዮጵያ እንደተጀመረ ባይታወቅም፣ እስካሁን በተገኘው መረጃ መሠረት ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ይታመናል፡፡

ብራና በውጩ ቃል ፓርችመንት ወይም ቨሌም (ጥጃ) የሚለው የሙያ ቃል በስፋት ይታወቅ የነበረው ቀደም ባለው ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በመሆኑ ከሀገራቱም ጋር የባህልና የንግድ ግንኙነት ስለነበረ ከእነዚህ ሀገራት መጣ ቢባል እንደሚያስኬድ ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ደግሞ በ6ኛው ምእት ዓመት በስደት ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ዘጠኙ ቅዱሳን ለሙያው መተዋወቅ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን በመጥቀስ ለብራና መተዋወቅ የራሷን አዎንታዊ ሚና ተጫውታለች የሚሉም ወገኖች አሉ፡፡

ዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ የመጀመሪያ ሥራቸው የነበረው መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ግእዝ ማስተርጎም ስለነበር ለዚህ ይሆን ዘንድ የእንስሳትን ቆዳ መጠቀም ዓይነተኛ ዘዴ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ የብራና ሥራ የሚካሄደው ሶስቱን የክረምት ወራትን ሳይጨምር ዓመቱን ሙሉ ነው፡፡ የክረምት ወራት ለብራና የማይመረጠው ቆዳው ቶሎ ስለማይደርቅ ነው፡፡

የብራና ሥራ ሂደቱ አንድ ተብሎ ተጀመረ የሚባለው አንዳንዶች ከእርድ ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ቆዳው ውሀ ውስጥ ከተዘፈዘፈ በኋላ ነው ይላሉ፡፡ አንድ ለብራና ሥራ ቆዳው ተፈልጎ የሚታረድ እንስሳ ከመታረዱ በፊት መታጠብ እንዳለበትና የሚታረድበትም ሥፍራ ጽዱ መሆን እንደሚኖርበት ነው የሚታመነው፡፡

ከዚህ በኋላ ቆዳው ለብራና ማውጫ በተዘጋጀ ማፈፊያ ካራ መሳይ በብረት መሣሪያና በመረመሚያ ድንጋይ ይታሻል፡፡ ከዚህ በኋላ ቆዳው ፀሐይ ላይ ወይም እሳት ወይም ጭስ ባለበት አካባቢ ይሰቀልና እንዲደርቅ ይደረጋል፡፡ ቀጥሎ በመጥረቢያ (አነስ ባለ) በቆዳው ላይ የቀረው ፀጉር ይላጫል፡፡

የቁም ጽሕፈት በብራና ላይ የሚጻፍበት የራሱ የሆነ ስልት አለው፡፡ ጽሑፍ የሚያርፍበት የብራና ክፍል ዓምድ ይባላል፡፡ አርእስት የሚባለው ከመጽሐፉ በላይ በኩል የሚገኘው ባዶ ቦታ ሲሆን፣ ኅዳግ የመጽሐፉ ግርጌ ከቀለሙ በታች እጅ የሚያርፍበት ነው፡፡ ጥሩ ቁም ፀሐፊ እነዚህን በሚገባ ጠብቆ መጻፍ አለበት፤ አለበለዚያ ይወቀስበታል፡፡

የብራና መጻሕፍት የሚጻፉበት የቀለም ዓይነት በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው፡፡ ዋና ዋናዎቹም ሦስት ናቸው፡፡ በቁም ጽሑፍ ለሚጻፉ መጻሕፍት በዋናነት የሚያገለግሉትና ለጽሑፍ ውበት የሚሰጡት የቀለም ዓይነቶች ቀይ፣ ጥቁር፣ ሰማያዊ ወይም ወርቃማ ናቸው፡፡

ሌላው የብራና ጥሬ ዕቃ ብርዕ ነው፡፡ ብርዕ ወይም መቃ ከደረቀ የሸምበቆ ተክል የሚሠራ የቁም ፀሐፍያን መሣሪያ ነው፡፡ ባህላዊ ብዕር ከተለያዩ የተክል ግንዶች ሊሠራ ይችላል፡፡ በቁም ፀሐፍያን ዘንድ የታወቀውና የተለመደው የሸምበቆ መቃ ነው፡፡

የብራና አሠራር አድካሚና ውስብስብ መሆኑን ያወሱት አቶ ታምራት፣ ሂደቱን ጠቅለል ባለ መልኩ እንደሚከተለው አቅርበውታል፡፡ የቆዳው ፀጉሩ ያለበት ውጫዊ ክፍልና ውጪያዊው ሥጋ ያለበት ክፍል እንዲሁም ውስጣዊው የሥጋ ክፍል ይታጠባል፡፡ በዚያም ባለሙያዎቹ ወጥረው በፀሐይ እንዲደርቅ በማድረግ እንዲለሰልስ በመረመሚያ ድንጋይ ያሹታል፡፡

ሂደቱ ይጀምራል የሚለው ከእርዱ በኋላ ነው፡፡ የእንስሳው ቆዳ ከውጭ በኩል ፀጉር፣ ከውስጥ በኩል ደግሞ ከቆዳው ላይ ተጣብቆ የቀረውን ሥጋ የብራናው ባለሙያ ይፍቅና ያፀዳዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ይወጥረዋል (በመወጠሪያ እንጨት ወይም ብረት"፡፡ በመጨረሻም በሻካራ ድንጋይ ቆዳው ይለሰልስና ለጽሕፈት አገልግሎት ይውላል፡፡

ድንጋዩ በቆዳው ላይ የሚገኙትን ቆሻሻና የሥጋ ቅሪት እየገፈፈ ካነሳው በኋላ እንደገና ቆዳው በማፈፊያ (ካራ) ደህና ተደርጎ በባለሙያው እንዲላግ ይደረጋል፡፡ ቆዳው በደንብ ከደረቀ በኋላ ፀጉሩ በመጥረቢያ ይላጫል፡፡ መጥረቢያው ለመያዝ እንዲመች አጭር ተደርጎ የተሠራና ጫፉ ብራናውን እንዳይቀድ ዳርና ዳሩ ዘንበል የተደረገ ነው፡፡

ብራናው ከደረቀ በኋላ ባለሙያው በሰንጢ ወይም በካራ ቆርጦ ከመወጠሪያው ላይ ያላቅቀዋል፡፡ ከዚያ በሚጻፈው መጽሐፍ መጠን እየተለካ ይሰመራል፡፡ መስመሩን ጠብቆ በወስፌ ውግ ይሰራለታል፡፡ ውግ ማለት ከአርዕስቱ እስከ ኅዳጉ ያሉት መስመሮች ጠባብና ሠፊ እንዳይሆን በወስፌ በብራናው ዳር ላይ የሚደረጉ ምልክቶች ናቸው፡፡

ሌላው አቶ ታምራት ያነሱት ነጥብ የብራና ሥራ ከሀገረሰባዊ እምነት ጋር ያለው ቁርኝት ነው፡፡ ቀዳሚው ለብራና ሥራ ዋነኛ ግብዓት ስለሆነው ቆዳ አመራረጥ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ፈረስና አህያ እርኩሳን ናቸው፡፡ የእነሱ ቆዳ በምንም ሁኔታ ለቅዱስ መጽሐፍ ሊውል አይችልም በብራና ሥራ ታሪክ ውስጥ ይህ አመለካከት ስር የሰደደ ነው፡፡

ሌላው የእምነቱ መገለጫ የቀለም መረጣ ነው፡፡ ቀይ ቀለም በተለምዶ ጥቅም ላይ የሚውለው የእግዚአብሔር፣ የክርስቶስ፣ የማርያም፣ የቅዱሳንና የሰማዕታትን ስም ብቻ ለመጻፍ ነው፡፡ ቀይ ቀለም የቅዱስነት መገለጫ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

በእስቴ ወረዳ ለብራና መስሪያ የሚመረጠው ቆዳ የፍየል ብቻ እንጂ የጋማ ከብቶች አይመረጡም፡፡ ሲያብራሩትም እንዲህ ብለዋል፡፡ "የጋማ ከብት ለብራና ይሆናል ማለት ሀሰት ነው፡፡ ሲነገር ግን እንሰማለን፡፡ በድሮ ጊዜ በትላልቅ የፍየል ቆዳ የተሰሩ ትላልቅ መጻሕፍት የሚመለከቱ ሰዎች ትልቅነቱን ለመግለፅ ይሄስ የፈረስ ቆዳ ነው ይላሉ፡፡ ልክ አሁን የአንድ ሰውን ትልቅነቱ ለመግለጽ ዝሆን ያህላል እንደምንለው ማጋነን ማለት ነው፡፡"

ለብራና መጽሐፍ ሥራ ተመራጭ የፍየል ቆዳ ቢሆንም የጾታም ምርጫ አለው፡፡ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፣ "ለብራና መጽሐፍ የምንመርጠው የሴት ፍየልን ቆዳ ነው፡፡ ምክንያቱም የሴቷ ቆዳ የመለጠጥና የመሳብ ባህሪ አለው፡፡ ዘፍዝፈን አውጥተን ስንወጥረው ይሳባል፡፡ የወንዱ ግን አይሳብም" በማለት ልዩነታቸውን አስረድተዋል፡፡

በእስቴ ወረዳ ያለው የብራና መጻሕፍት ዝግጅት እስከ አሁን ድረስ አለመጥፋቱ የማኅበረሰቡን እምነት፣ አስተሳሰብና ለሙያው ያለውን ጥልቅ ግንዛቤ ያሳያል፡፡ "የብራና ሥራ ጠፋ ማለት ሃይማኖታችን ጠፋች ማለት ነው፤ ብለው አባቶቻችን ነግረውናል፣ እኛም ጥቅም ባናገኝበት እንሰራዋለን" በሚል ሃይማኖታዊ ስሜት እየተሰራ ያለው ሙያ እንደ በፊቱ ራሱን ችሎ ኑሮን ለመምራትና መተዳደሪያ ሊሆን እንዳልቻለ መረጃ አቀባዮች ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የብራና መጻሕፍት ዝግጅት ጥንታዊ ትውፊቱን ሳይለቅ በብዛትና በጥራት በማዘጋጀት ሙያው በወጣቱ ትውልድ ልቦና ውስጥ ሰርፆ የኑሮ መሠረት ሊሆን እንዲችል ለማድረግ አጥኚው የደረሱበትን ውጤት በአስተያየት መልክ አቅርበውታል፡፡

የክልሉ መንግሥት የብራና መጻሕፍት ዝግጅት በቋሚነት እየተሰራ ያለበትን ቦታ ትኩረት ሰጥቶ በማስተዋወቅ ቦታው የብራና መጻሕፍት ዝግጅት ማዕከል በማድረግ ለጎብኚዎች ሁኔታዎች ቢመቻቹ፣ ሙያው ባህላዊ ገጽታውን ሳይለቅ መሥራት እንዲቻል በባለሙያዎች ጥናት ቢደረግና ስልጠና ቢሰጥ፣ በብራና መጻሕፍት ዝግጅት ሙያ ላይ መሰማራት ከሚያስገኘው መንፈሳዊ እርካታ በተጨማሪ ዳጎስ ያለ ገቢ የሚያስገኝ እንደሆነ ወጣቱ ትውልድ እንዲረዳና ወደ ሙያው እንዲሳብ የተጻፉትን መጻሕፍት ውጪ ሀገር ድረስ ወስዶ በማስተዋወቅና በመሸጥ ገበያ የማፈላለግ ሥራ ቢሠራ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በእስቴና በመሳሰሉት አካባቢዎች ብቻ ተወስነው ያሉትን የብራና መጻሕፍት ሙያ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማትና አድባራት ውስጥ ማሰራት የምትችልበት ሁኔታ ቢፈጠር፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ ያለባቸውን የሀገሪቱን ታሪካዊ የወረቀት መዛግብት በብራና በማጻፍ ቅርስን ሳይበላሽ የማቆየት ተግባሩን ቢወጣ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለተማሪዎቻቸው የሚሰጧቸውን የትምህርት ማስረጃ ዲግሪ፣ ዲፕሎማና ሰርተፍኬት በብራና ላይ አሰርተው ቢሰጡ ባለሙያዎቹን ተጠቃሚ በማድረግ ዓመት ሙሉ ከሙያቸው እንዳይርቁ ከማድረጉም በላይ የእያንዳንዱን ተማሪ ሕይወት ከብራና ጋር ማስተሳሰር ይቻላል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ በዳሰሳው ጊዜ በተደረገው ውይይትም አንዳንድ ነጥቦች ከተወያዮች ተነስተዋል፡፡

አወያዩ አቶ ሔኖክ ያሬድ፣ የብራና ሥርወ ቃላዊ መነሻው "ብርሃና" ከብርሃን ጋር የተያያዘ ነጭ የጽሕፈት ሰሌዳ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሕፈት ከድንጋይ ላይ ጽሑፍ (ጽሑፈ እብን) ወደ ብራና የተለወጠው በዘመነ አክሱም ከክርስትና መባት ጋር መሆኑ፣ በተለይ ከ3ኛው እስከ አምስተኛው ምእት ዓመት በዘመነ ፍሬምናጦስ ቅዱሳት መጻሕፍት ሲተረጐሙ የተጻፉት በብራና ላይ መሆኑ ይህም ከዘጠኙ ቅዱሳን (ተስዓቱ ቅዱሳን) በፊት መሆኑ በታሪክ መመዝገቡን አመልክቷል፡፡

የብራና መጽሐፎቻችን ከሃይማኖታዊው ጉዳይ ባሻገር ልዩ ልዩ ፖለቲካዊና ታሪካዊ ጉዳዮች፣ የዘመን አቆጣጠር ሰንጠረዦችና ሥዕሎች ተመዝግበውበት ይገኛል፡፡ ከክርስትናው ሌላ የአይሁድም፣ የእስልምና እምነት የሚመለከቱ ቅዱሳት መጻሕፍትም ተጽፈውበታል፡፡ ቅዱስ ቁርዐን በግእዝም፣ በአማርኛም በብራና መጽሐፍ ተጽፎ በቅርስነት መተላለፉን አስተያየት ሰጪው ገልጿል፡፡

በብራናው ላይ በጥቁርና በቀይ ቀለም አስተባብሮ መጻፍ በዘመናዊው የአማርኛ ሥነ ጽሑፋችንም ውስጥ እየታየ መሆኑን አቶ ሔኖክ ሲገልጽ፣ ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን በተረጐማቸው የሐምሌትና ማክቤዝ ድርሰቶች ላይ ቀይ፣ ጥቁርና ሰማያዊን እያፈራረቀ ሲጠቀም፣ አዳም ረታ "ግራጫ ቃጭሎች" በተሰኘው ልብ ወለድ ድርሰቱ ውስጥም የቀለማቱ ትውፊትን እናገኛለን፡፡ በቅርቡም የታላላቆቹን ምዕራባውያን የቅኔ (ግጥም) ሥራዎች ወደ አማርኛ የመለሰው ዶክተር ዳዊት ዘኪሮስም እንደ ብራናው ትውፊት ሰማያዊ፣ ቀይና ጥቁር ቀለማትን አሰባጥሮ ተጠቅሟል፡፡

ሦስተኛውን ሺሕ ዓመት (ሚሌኒየም) በጀመርንበት በ2001 ዓ.ም. የጥበብና ሰብዓዊ ጥናቶች ሕዳሴን ለማምጣት ነባሮቹን፣ ብራናን የመሳሰሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልዱም የማንነቱን አሻራዎች እንዲያውቅ ማድረግ የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ የትውልድ ማንነት በትውልድ ውስጥ ይተላለፋልና፡፡ ነውን ለማወቅ ነበርን ጠይቅ ነውና፡፡

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)