December 11, 2008

አዳዲ ገብቶ «አላህ አክበር» ሲል የተገኘው ሙስሊም በአንድ ዓመት እሥራት ተቀጣ

የፎቶ ግራፍ ባለሙያ መስሎ ወደቤተ መቅደስ የገባው ሙስሊም
በአንድ ዓመት እሥራት ተቀጣ
(ሕይወት ቦጋለ)
በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ በሌመን ወረዳ በሚገኘው አዳዲ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቤተ መቅደስ ውስጥ የፎቶ ግራፍ ባለሙያ በመምሰል ገብቶ «አላህ አክበር» ሲል የተገኘው የእስልምና እምነት ተከታይ በአንድ ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ፡፡

የሌመን ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ተስፋዬ አባተ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ ኅዳር 21 ቀን 2001 ዓ.ም ከቀኑ 4 ሰዓት ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብቶ «አላህ አክበር» በማለት የቤተ ክርስቲያኑን ሥርዓተ ጸሎት በማወኩ በምእመናን ትብብር በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል፡፡

ግለሰቡ ኅዳር 22 ቀን 2001 ዓ.ም በቀርሳና ማሊማ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ በዕለቱ የአንድ ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደበት መሆኑን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ፤ እጅ ከፈንጅ በተያዘ ጉዳይ አፋጣኝ ውሳኔ በመሰጠቱ ፍ/ቤቱ ሊመሰገን እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

«በሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ አብረን ብንሆንም በአምልኮ ቦታችን ግን የተለያየን መሆኑ እየታወቀ ግለሰቡ የክርስትና እምነት ተከታይ ሳይሆን በቤተ መቅደስ ውስጥ ድፍረት የተሞላበት ድርጊት መፈጸሙ ጠብ አጫሪነት መሆኑን ያመለክታል» ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ የሃይማኖት መቻቻል እንዲሰፍን ጥረት በሚደረግበት ወቅት ከፍተኛ ወንጀል ለፈፀመው ለዚህ ግለሰብ የተሰጠው ፍርድ ከጥፋቱ ክብደት አንፃር ሲታይ አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡

ቦታው ታሪካዊ እንደመሆኑ መጠን በርካታ የውጭ ሀገር ሰዎች ወደ ቦታው እንደሚመጡ የጠቆሙት የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፤ ለወደፊቱ በቀጣይ ጥበቃውን በማጠናከር ልዩ ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ መልአከ ምሕረት አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ተረፈ በበኩላቸው፤ በወቅቱ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንደነበሩ ጠቁመው፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ የተፈጸመው ድፍረት የተሞላበት ድርጊት የቤተ ክርስተያንን ህልውና ከመድፈር ባሻገር ሰላም ለማደፍረስ ሆን ተብሎ የሚደረግ ጠብ ጫሪነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ የተነሣውን ውዝግብ በትዕግሥት ማለፍና በሕግ አግባብ መከታተል እንደሚገባ ለምእመናን በመግለጽ መረጋጋት እንደተቻለም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ቤተ ክርስቲያን ቅሬታ እንዳላትና ድርጊቱ ለሌሎችም መቀጣጫ ሊሆን በሚችል መልኩ ከበድ ያለ የፍርድ ውሳኔ እንዲሰጠው በአቃቢ ሕግ በኩል ይግባኝ ለመጠየቅ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡ ቀደም ሲልም በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ግለሰቦች ድፍረት የተሞላበት ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙን ዝግጅት ክፍላችን መዘገቡ የሚታወስ ነው ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር


ምንጭ፡- ማኅበረ ቅዱሳን

1 comment:

asaph said...

እናንተ የእግዚአብሄር ቤተመቅደሶች ናችሁ
ቤተመቅደስ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቶስ በማመን ዳግም የተወለደ ክርስቲያን ነው

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)