November 16, 2008

መንግሥት በዝግ ሒሣብ ያስቀመጠው ገንዘብ በአንዲት ግለሰብ ስም ወጣ

Sunday, 16 November 2008
በታምሩ ጽጌ

የቀድሞ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን (በአሁኑ ወቅት በግብናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር አደጋ መከላከልና ዝግጁነት እና ምግብ ዋስትና ዘርፍ) በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ በዝግ የሂሳብ ቁጥር EOC/DICAC 0171859036000 (3100) ያስቀመጠውን ገንዘብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በአንዲት ግለሰብ ስም እንዲወጣ ማድረጉን ምንጮች ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡በነሐሴ ወር 2000 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ በተፃፈና በሁለት ከፍተኛ የጠቅላይ ቤተክህነት ኃላፊዎች (ጳጳሳት) ፊርማ በግለሰቡ ስም እንዲወጣ የተደረገው ገንዘብ 1 ሚሊዮን 832 ሺ 900 ብር መሆኑን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ በሲፒኦ ቁጥር 1684470 እ.ኤ.አ ኦገስት 13 ቀን 2008 ወጥቶ በተመሳሳይ ቀን ወደ ወጋገን ባንክ አራዳ ቅርንጫፍ ገቢ መደረጉን ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡

ገንዘቡ የተገኘው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መጋቢት 1ዐ ቀን 1989 ዓ.ም. በቁጥር ተ80-አጠ3/01/06 በተፃፈ ደብዳቤ በተላለፈ መመሪያ መሠረት ከቀድሞ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች /መያድ/ መካከል ባለው የሥራ ውልና የሥራ ግንኙነት በእርጅናና በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት መስጠት ያቋረጡ ተሽከርካሪዎች በጨረታ ተሸጠው መሆኑን ምንጮቹ አብራርተዋል፡፡

በተላለፈው መመሪያ መሠረት ተሽከርካሪዎቹ ከተሸጡ በኋላ የተገኘውን 9 ሚሊዮን 876 ሺ 909 ብር ከ32 ሣንቲም ለኬር፣ ለኮንሰርን፣ ለኖርዌይ ሕፃናት አድንና ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደየድርሻቸው ከተከፋፈለ በኋላ በዝግ አካውንት ተቀምጦ ኘሮጀክት ኘሮፖዛል ሰነድ አዘጋጅተው የኘሮጀክት ውል ከፈፀሙና በፌደራል የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ቢሮ ሲደገፍ በቢሮው በኩል እንዲሰጣቸው የተፈቀደ መሆኑን ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የተጠቀሰውን ገንዘብ ለአማራ ክልል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ቢሮ እንዲያስረክብ ቢታዘዝም ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ለክልሉ መንግሥት ደብዳቤ መፃፉን ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡

ኮሚሽኑ ለክልሉ መንግሥት በፃፈው ደብዳቤ ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ የሚያከናውነው በውሃ ልማት ኘሮግራም ላይ መሆኑን ጠቅሶ የውሃ ጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽን መግዣ ገንዘቡን እንዲፈቅድለት መጠየቁን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን የኮሚሽኑን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ባፋጣኝ ለተወሰነለት አካል እንዲያደርስ የማያደርግ ከሆነ ተገቢውን የመፍትሄ እርምጃ እንደሚወስድ ገልፆ ደብዳቤ እንደፃፈለት ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ ለኮሚሽኑ የፃፈው ደብዳቤ ምላሽ ሳያገኝ ቆይቶ፣ መስከረም 9 ቀን 2001 ዓ.ም. ለግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር ለአደጋ መከላከልና ዝግጁነት እና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ደብዳቤ መፃፉን ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡

ኮሚሽኑ በፃፈው ደብዳቤ የተሻለ የወለድ ጥቅም ለማግኘት በሚል ከንግድ ባንክ ወደ ወጋገን ባንክ መቀየሩን ገልፆ በዝግ አካውንት ተቀምጦ የበረውን 1 ሚሊዮን 833 ሺ 174 ብር አራት ኪሎ ቅርንጫፍ የነበረው የሂሳብ ቁጥር 3100..0171859036000) እንዲዘጋ መጠየቁን ምንጮቻችን አስረድተዋል፡፡

በግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር አደጋ መከላከልና ዝግጁነት እና ምግብ ዋስትና ዘርፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ጉዳይ አስተባባሪ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ በፃፈው ደብዳቤ በዝግ አካውንት ያለውን ሂሳብ እንዲገልጽለት ጥቅምት 14 ቀን 2001 ጠይቆ ጥቅምት 27 ቀን 2001 ዓ.ም. ገንዘቡ መኖሩን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ እንደደረሰው ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

አስተባባሪው አቶ አስመላሽ ገ/ሕይወት ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው ገንዘቡ ለምግብ ዋስትና ድጋፍ የተሰጠ በመሆኑ ኮሚሽኑ ለሌላ ተግባር ማዋል እንደማይችል ገልፀዋል፡፡

“አንዱ በዝግ ያስቀመጠውን ሌላው አካል ማንቀሳቀስ ይችላል?” ተብለው ለተጠየቁት፣ “ገንዘቡን እንዲቀመጥ ያደረገው አመዝኤ ነው፡፡ እንዲንቀሳቀስ የሚፈቅደውም አመዝኤ ነው፡፡ ወደ ወጋገን ባንክ ተዛውሯል የሚባለው ሊሆን አይችልም” በማለት አቶ አስመላሽ ተናግረዋል፡፡

“በዝግ አካውንት የተቀመጠ ገንዘብ ወለድ ይከፈልበታል?” ተብለው ለተጠየቁት “በዝግ አካውንት የሚቀመጥ ገንዘብ ወለድ የለውም፡፡ ባንክም ሊያንቀሳቅሰው አይችልም” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ንጉሱ ለገሰን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው፤ “እኛ ለልማት በማሰብ፣ በቀናነት ሰርተናል፡፡ ገንዘቡ የኛው ነው፡፡ አልጠፋም፡፡ ለተሻለ ልማት ለማዋል በቀና አስተሳሰብ ሰርተናል” ብለዋል፡፡

በክልሉ የተሻለ ሥራ ለመስራት፣ በተለይ ውሃ ለማውጣት ተጨማሪ ማሽን ለመግዛት ጠይቀው እንደነበር የገለፁት ዶ/ር ንጉሱ፣ እሳቸውም ሆኑ ሁሉም ሰራተኛ ከክፋትና ወይም ከሌላ አስተሳሰብ በመነጨ አካሄድ ሳይሆን በትክክልና ስለዕውነት በልዩ ሙያዊ ፍቅርና በትጋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

1 comment:

Anonymous said...

It is good to have the source, which is Reporter.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)