August 21, 2008

‹‹በሀገረ ስብከት›› ሥር ወይስ ‹‹በሲኖዶስ›› ሥር?

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በውጪው ዓለም ያላት አገልግሎት ትልቅ የመከፋፈል አደጋ ላይ መውደቁ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ፖለቲካና ሃይማኖት መሳ ለመሳ ተሰልፈው፣ ፖለቲከኛው ዐውደ ምሕረቱን ተቆጣጥሮ፣ ሀገር ቤት በመንግሥት ወንበር ላይ የተቀመጡት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከቁጥጥራቸው ሥር አለመውጣቷን እያረጋገጡ ሲጓዙ፣ ከሀገር ውጪ ያሉት ተቃዋሚዎችም በበኩላቸው እንዲሁ የራሳቸውን ድርሻ ወስደው በውጪ ካሉት አብያተ ክርስቲናት አብዛኞቹን የፊጥኝ ቀፍድደው ይዘዋቸዋል፡፡ በሕዝብ ስም፣ በቤተ ክርስቲያን ስም ቤተ ክርስቲያኒቱ የፖለቲከኞች መጫወቻ ሆናለች፡፡ በአንድ በኩል ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በታሪካችን ታይቶ በማይታወቅ መልክ እናታችን ቤተ ክርስቲያንን የሌቦች ዋሻ ሲያደርጓት፣ እነ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ በበኩላቸው ‹‹ሲኖዶስ›› አቋቁመናል እያሉ አደጋ ጋርጠውባታል፡፡ ይህንን አደጋ ለመጋፈጥ ቆርጦ የተነሣ ማንኛውም አካል የመንደር ሬዲዮኖች አሉባልታ ሰለባ ስለሚሆን አንድም እርምጃ ሳይራመድ ተሽመድምዶ ይቀራል፡፡ አንድነትን የሚፈልግ፣ መለያየትን የማይቀበል፣ በተለይም የነ አባ መርቆርዮስንና የነ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያምን ተገንጣይ ‹‹ሲኖዶስ›› የሚቃወመውን በሙሉ ‹‹ወያኔ›› ብለው በመፈረጅ ያሸማቅቁታል፡፡ ይህም እስከ ዛሬ ጥሩ ውጤት አምጥቶላቸዋል፡፡ አሁን ግን ዘዴያቸው ‹‹እየተነቃበት›› ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ‹‹አንዲት ቤተ ክርስቲያን፣ አንድ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ስደተኛ ሲኖዶስ የሚባል የለም›› የሚሉትና በትክክለኛው መንገድ ላይ አሉ የሚባሉት ክፍሎች ራሳቸው ያሉበት ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ግልጽ እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡ ለብዙ ዓመታት በቅዱስ ሲኖዶስ አንድነት በማመን ራሳቸውን ከአዲስ አበባው አስተዳደር እንዳልተለዩ ሲገልጹ የቆዩ አያሌ አብያተ ክርስቲያናት በተለይ በዲሲና አካባቢው ይገኛሉ፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ሥር መሆናቸውን የሚገልፁበት ብቸኛው መለያቸው ‹‹በቅዳሴ ወቅት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን›› ስም ማንሣታቸው ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ምንም ዓይነት የአስተዳደር አንድነት የላቸውም፡፡ ገንዘብ ቢሰበስቡ ለራሳቸው፣ ሠራተኛ ቢቀጥሩ ራሳቸው፣ ቢሰበሰቡ ቢበተኑ ራሳቸው፣ ሁሉን አድራጊ ፈጣሪዎች ራሳቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር ነን እያሉ ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡
ነገር ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ካለፉት ዓመታት ወዲህ በአሜሪካ 3 አህጉረ ስብከት በማቋቋም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን መመደብ ከጀመረ ወዲህ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በስም ብቻ የቤተ ክርስቲያን መሆናቸውን ከመግለጻቸው በስተቀር በተግባር ግን ከ‹‹ገለልተኞች›› እና ከ‹‹ስደተኞቹ›› ያልተለዩ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ አልፈው ተርፈው የሀገረ ስብከትን ህልውና በመጋፋት ራሳቸውን ‹‹በቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ያለን አብያተ ክርስቲያናት›› እያሉ መጥራት ጀምረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በርግጥ እንዲህ የሚባል መዋቅር አላት?

ቃለ ዐዋዲያችን እንደሚያመለክተው የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ግንኙነት የሚፈጥሩት አህጉረ ስብከት ናቸው እንጂ አጥቢያዎች አይደሉም፡፡ አሜሪካ ያሉት የኛ ቅምጥሎች ግን ተስፈንጥረው፣ ሀገረ ስብከቱን ዘለው ‹‹ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ነው ግንኙነታችን፣ ተጠሪነታችንም ለሲኖዶሱ ነው›› ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ያፈርሳሉ ብለን እንኮንናቸዋለን፡፡ እኛስ እንዲህ መዋቅሯን ሽባ ስናደርገው ምን ማድረጋችን ይሆን፡፡ ገና ለገና ከፓትርያርኩ ጋር ቅርበትና ወዳጅነት አለን ተብሎ ቤተ ክርስቲያንን መናቅ ከሌሎች በላይ ይጎዳት ካልሆነ ምን ያደርጋት ይሆን፡፡ ስለዚህ ይህኛውም አዲሱ ዘዴ ‹‹በሲኖዶስ ሥር ነኝ፣ በሀገረ ስብከት ስር አይደለሁም›› የሚለውም ተራ ማጭበርበሪያ ነውና ተስተካከሉ!!!

አንባቢ ‹‹እንደዚህ የሚያደርጉት እነማን ናቸው›› ብሎ ራሱን እንዳይፈትን ይህንን የሚያደርጉት ለረጅም ዘመን አንድ አስተዳደር መኖሩን ሲቃወሙ ኖረው ጵጵስና ፍለጋ አቅጣጫቸውን ቀይረው አዲስ አበባ በገቡት በአባ ሰረቀ ወልደ ሳሙኤል የሚመሩት የዲሲ አካባቢ ካህናት መሆናቸውን መግለጹ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ ካህናት በቄስ ይስሐቅ ወልደ ማርያም ሬዲዮ አዘጋጅነት ድምጻቸውን በማሰማት ይህንን አዲስ ‹‹መዋቅር›› ሲለፍፉ እየሰማን ነው፡፡ ከፍ ብለን ያስቀመጥነውን መዋቅር እንመልከትና የነዚህን ሥርዓት አልባ ሰዎች እንቅስቃሴ እንመርምረው፡፡ ዘዴያቸው ብዙም እንደማያስኬዳቸው የተረዱት አይመስሉም፡፡ አንድ ቀበሌ ‹‹ከከፍተኛዬም፣ ከወረዳዬም፣ ከአውራጃዬም ጋር አልገኛኝም፤ ተጠሪነቴ ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ነው›› እንደማለት ያለ ሎጂክ እየተከተሉ መሆናቸው አልገባቸው ይሆን ወይስ ምእመኑን ‹‹አይነቃብንም›› ብለው ንቀውታል?

የነዚህን ሰዎች የወደፊት ዕቅድና ሥራቸውን ወደፊት እንዳስፈላጊነቱ እንመለስበታለን፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፡፡

1 comment:

Anonymous said...

Kebzuhanu tesewro yeneberwin ewineta silegeletchu Egziabhair Yistachu!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)