April 17, 2008

ሺኖዳ እስከዛሬ ለምን አልጐበኙም?

REPORTER Sunday, 13 April 2008: በኢትዮጵያ፣ ፖለቲካ ውስጥ ሃይማኖት የተገለለ እንደሚሆን መነገር ከጀመሩባቸው ዓመታት ወዲህ ጭምር፣ የፖለቲካውን እግር ዱካ ያልተከተለበት ጊዜ የለም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ፖለቲካው የሃይማኖቱን ፈለግ የሚከተልበት ጊዜ ሞልቷል፡፡
በአንዳንድ ሃገሮች በአብዛኛው የአስተዳደሩ መሠረት፣ ሃይማኖት የሚሆነበትም ጊዜ አለ፡፡ እንደግብፅ ባሉ ሃገራት ምንም እንኳ ቀደምት የሆነው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የሚገኝበት ቢሆንም የአስተዳደሩ መሠረት የእስልምናውን እምነት መሠረት ያደርጋል፡፡ በዚህ መሠረት ለሚያደርገው ግንኙነት የግብፅን መንግሥት አቋም፣ ሌሎቹ እምነቶች ጭምር እንዲደግፉት ይደረጋል፡፡ የግብፅ መንግሥት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በተለያየ መንገድ ቸልተኛነቱ ለሚያሳየው መቀመጫውን እስክንድርያ ያደረገውን የወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ተሿሚ እምነት ተከራካሪ ሆኖ ይቀርባል፡፡
የማርቆስ እጣ ናቸው የሚባሉት የኮፕት ኦርቶዶክስ ተከታይ የሆኑት የኢትዮጵያና የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያኖች የመንግሥታቶቹ ቅርበትና ርቀት ግንኙነታቸውን ሲወስነው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ የመንግሥታቱ የፖለቲካ ግንኙነት በሻከረ ቁጥር በእምነት አንድ ነን የሚሉት የሃይማኖት መሪዎች በዚያው ረድፍ ሲኳረፉ ቆይተዋል፡፡

የአሁኑ የግብፅ የኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ ቅዱስ ሺኖዳ III የኢትዮጵያ ጉብኝት የሻከረውን ለማለስለስ ወይም የተቋረጠውን ግንኙነት ለመቀጠል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን እንደማመሳከሪያ አድርጎ ሊወስድ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሁለቱ እምነት መሪዎች ውሳኔ ከሃገራቸው መንግሥታት ያፈነገጠ ሊሆን ስለማይችል መንግሥታቱ ቅሬታ ከገቡ የዛሬው ሸርክና ነገ ወደ መኮራረፍ ያመራ ቢመስል ሊያስገርም አይችልም፡፡ በተደጋጋሚ እንደታየው ደግሞ በአባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ባመጣው መዘዝ የግብፅ መንግሥት ፖሊሲ በኢትዮጵያ ላይ ሁልጊዜም የጥርጣሬና የማዳከም መሆኑ በተለያዩ ጥናቶች ተነግሯል፡፡

ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ ራሷን የገነጠለችው ኤርትራ የልዩነቷና ራሷን የመቻሏ ማረጋገጫ ያደረገችው አዲስ የሾመችውን ሊቀጳጳስ በእስክንድርያው ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ የፓትርያርኩን ማዕረግ ማሰጠት ነበር፡፡ በጊዜው ከአንድ ቤተክርስቲያን በተለዩትና ጵጵስናና ሊቀጵጵስናን ከተቀበሉበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አለያይቶ ወደ እስክንድርያ መሄዳቸው የመንግሥት ፖለቲካ ውሳኔ ውጤት መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ውሳኔውም ቢሆን የኤርትራን መገንጠል ከመጀመሪያው ጀምሮ ለሚደግፈው የግብፅ መንግሥት የሚያስደስትና ለግንኙቱም ማጠንከሪያ እንዲሆን የታሰበ ነው፡፡ ነገር ግን የግብፅና የኤርትራ መንግሥት መነቃቀፍ ሲጀምር የጳጳሳቱ ግንኙነትም ፈዘዘ፡፡

የአሌክሳንድሪያ - ፓትርያርክ አባ ሺኖዳ III የሚመሩት ሲኖዶስ ረጅም ግንኙነት ከመሠረቱት ከኢትዮጵያ ይልቅ ወደ ኤርትራ ማድላታቸው አንድም ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በጵጵስና ማዕረግ መቻላቸውና የቤተክርስቲያኒቱ ጥገኝነት በመቅረቡ የሚናደዱበትን ታሪክ በኤርትራ በኩል ያስመሰሉት ስለመሰላቸው ይሆናል፡፡ አንድም ከላይ እንደተገለፀው የግብፅ መንግሥት ፖለቲካ ስለሚያስገድዳቸው ይሆናል፡፡

በአቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘ ኢትዮጵያ የሚመራው ሲኖዶስና በአቡነ ሺኖዳ የሚመራው ሲኖዶስ ብዙም ሰላምና ፍቅር ያላቸው አልነበሩም፡፡ የኤርትራን ጦርነት ተከትሎ የመንግሥታቱ አሰላለፍ የጥቅም ክርክር፣ የፕሮቶኮል ቅድሚያ አንዱ ለሌላው የሚሰጠውን ክብር በመቀነሱ ፍቅራቸው የፀና አይደለም፡፡

ሰባት ሚሊዮን አማኞች ያሉት የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እስካሁን ድረስ በእየሩሳሌም በሚገኘው የኢትዮጵያ ገዳም ይዞታነት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ እንዲያውም ከፍላጎት አልፈው የኢትዮጵያን ገዳማት እየተጻረሩ የግብፅ መነኮሳት በማስቸገር ላይ ናቸው፡፡ ይኸ አተካራ እስካሁን መፍትሄ አላገኘም፡፡ ገዳማቱን ግብፆች ለማግኘት ባይቻላቸው በኤርትራ በኩል ባለመብት ለመሆንም ፍላጎት እንዳላቸው አሁን ድረስ በውስጣቸው ያለና የሞቀ ፍላጎታቸው ነው፡፡

ከላይ እንደተገለፀው የግብፅ መንግሥት እንደ እነዚህን መሰል የጥቅም ጥያቄ ሲነሱ ዋና ተከራካሪ ሆኖ ሲቀርብ ይታያል፡፡ ቤተክርስቲያኗን የመጠበቅ ኃላፊነቱንም እንዳለበት የሚያሳየው የዚያን ጊዜ ይሆናል፡፡

የአሁኑ ፓትርያርክ ሺኖዳ ጉብኝት የቤተክርስቲያኖቹን ተከታዮች ፍቅር ለማስተሳሰር ቢመስልም፣ በመካከላቸው ያለውን የጥቅምና የመንግሥታት ፍላጎት በምን መንገድ እልባት እንደሰጡት ለጊዜው አይታወቅም፡፡ መፍትሔ የሰጡት ባለመሆኑም ልባዊ ግንኙነት ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ውስጥ መቀመጡ አይቀርም፡፡

የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኢትዮጵያን በአፌሴል ሲጎበኝ የአሁኑ ጉብኝት ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ ሦስተኛ ሊባል የሚችለው 1960ዎቹ የዓለም አብያተክርስተያናትን መሪዎች ኢትዮጵያ ስታስተናግድ ለጉባኤ ፓትርያርኩ መገኘታቸው ነው፡፡

አንደኛው በጊዜው ከ88 ዓመት በላይ የነበሩት የፓትሪያርክ ዮሐንስ ጉብኝት 1921 የተፈፀመ ሲሆን ሁለተኛው የአሁኑ የ84 ዓመት አዛውንት አቡነ ሺኖዳ ጉብኝት ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት ከአሌክሳንድርያ በሚሾም ሊቀ ጳጳስ ትተዳደር በነበረችው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንና የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪ ይኸን ያህል ዓመታት ኢትዮጵያን አለመጎብኘት በራሱ ግንኙነቱን መሳሳቱን ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጥገኛ ሆና ስትኖር ለመጀመሪያ ጊዜ ራሷን እንድትችል በተደረገው በ1940ዎቹ መጨረሻ ነበር፡፡ እዚያ ደረጃ ለመድረስ የአፄ ኃይልሥላሴ መንግሥት በትዕግሥትና በአስተዋይነት ችሎታውን የአሳየበት ተግባር መፈፀሙ ግብፆቹ ራሳቸው እየተናደዱበትም ቢሆን የሚመሰክሩት ነው፡፡

አቡነ ሺኖዳ III በሃገራቸው ከፍተኛ ፈተና ውስጥ በገቡበት ጊዜ ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሃገራቸው በአክራሪዎች እየተናጠች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ክርስቲያኖቹ የግድያ ሰለባ ሆነዋል፡፡ የቤተክርስቲያናትን ጥቅም ማጥፋትና የአማኞች ማንጓጠጥና መገለል በሰፊው የሚታይበት መሆኑን በጋዜጦች ታትሟል፡፡ በቅርቡ አንድ ጋዜጣ አንድ ካህን ራቁቱን ወሲብ ሲፈፅም ፎቶግራፍ እስከማውጣት ደርሷል፡፡ በዚህ ልባቸው የቆሰሉት ግብፃውያን ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ቢቃጡ፣ ዙሪያ ገባ ፖለቲካውን ያጡት አባ ሺኖዳ አርፋችሁ ተቀመጡ የሚል መማፀኛ ለመንፈስ ልጆቻቸው ከማቅረብ በላይ ሊያልፉ አልቻሉም፡፡

ሁኔታዎች አስቸጋሪ በሆኑበት ወቅት በትዕግሥት ሁኔታዎች እንዲረጋጉ ከማድረግ ያለፈ፣ በመንግሥት ተደማጭነት የላቸውም ቢባልም እጅግ ጠንካራ በሆኑት የግብፅ ክርስቲያኖች ልብ ፓትርያርክ ሺኖዳ የተከበሩና የተፈቀሩ መሆናቸው ይነገራል፡፡

በቅርቡ ወደ እንግሊዝ በሄዱበት ወቅት የፀጥታ ሃይሎች በአይሮፕላን ጣቢያ እንዲፈተሹ መጠየቃቸው ብዙዎች ተከታዮቻቸውን አስቆጥቷል፡፡ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በድርጊቱ የእንግሊዝ የፀጥታ ሃይል ይቅርታ እንዲጠይቅ ጠይቋል፡፡

ከ40 ሚሊዮን በላይ ተከታይ ባላት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እጅግ ከፍ ያለ አቀባበል እንደሚጠብቃቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይኸም ጥንታዊውን ግንኙነት በማሰብ እንጂ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ፍቅር ብቻ መሠረት በማድረግ አይደለም፡፡

የአሁኑ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ፣ እንደ አቡነ ሺኖዳ ሁሉ በፖለቲካው መደፈቅ አልቀረላቸውም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከመንግሥት ውሳኔ ጋር ራሳቸውን ለማስጠጋት በመፈለጋቸው ከሕዝቡ ቅሬታ አትርፈዋል፡፡ የሁለቱ የእምነት መሪዎች የሚያመሳስላቸው በመንግሥት ሰፊ እጅ መደቆሳቸው ሲሆን የሚያለያያቸው አንደኛው በችግር ሌላው በውዴታ መቀበላቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ መሪዎች የግብፅን መሪዎች ሲያስተናግዱ እንደ 1920ዎቹ ጳጳስ እንዲሾሙላቸው ለመማፀን አይደለም፡፡ በዚያን ጊዜ ፓትርያሪኩ አቡነ ዮሐንስ ለእጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ ጵጵስና እንዲሰጡ ለማድረግ በመንግሥት ደረጃ ስንት ድካም ተከፍሎበት ነበር፡፡ ዛሬዎች የቤተክርስቲያን መሪዎች የሚያስቸግራቸው በእየሩሳሌም ገዳም ባለቤት ላይ ያለውን አታካራ የመቅጨት ጥያቄ ይሆናል፡፡ ያም ቢሆን የግብፅ መንግሥት እጅ አለበት፡፡ ስለዚህ ሁሉም ነገር ውስብስብ ነው፡፡ ግን በተለምዶ እንደሚደረገው ርችት ተኩሶ በፈገግታ መቀበልና መሸኘት አይቀርም፡፡ ግን ለጉብኝታቸው የሁዳዴው ፆም የተመረጠው ስለምን ይሆን?

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)