March 10, 2008

“መጪው ዘመን እንዳይቀድመን እንነሣ”

The Reporter Wednesday, 05 March 2008
“መጪው ዘመን እንዳይቀድመን እንነሳ” በሚል የተዘጋጀውና የካቲት 24 ተከፍቶ እስከ መጋቢት 2 ቀን 2000 ዓ.ም የሚቆየው ዐውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በመታየት ላይ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማህበረ ቅዱሳን ዕሥራ ምእቱን በማስመልከት ያዘጋጀው ዐውደ ርዕይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሁለት ሺህ ዓመታት ጉዞ የሚያስቃኙ ትዕይንቶች፣ ቤተክርስቲያኒቱ ለሀገር ያበረከተችው ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና መንፈሳዊና አገልግሎቶች እየቀረቡበት ነው፡፡

በዐውደ ርዕዩ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ማን ናት? እንዲሁም አምልኮተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሐዋሪያዊ ተልዕኮ፣ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር፣ በስነ ጥበብ በሕዝብ አስተዳደርና በሕግ ቀረፃ ያበረከተችውና በልማትና ብልፅግና ያላት አስተዋፅኦ፣ በተፈጥሮና በአካባቢ ጥበቃና በቱሪዝም ዘርፍ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ነገ እና ማህበረ ቅዱሳን የተመለከቱ ዘጠኝ ትዕይንቶች የቀረቡበት ነው፡፡

ዲያቆን ሰሎሞን አስረስ የዐውደ ርዕይ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደገለፁልን ዐውደ ርዕዩ ሲዘጋጅ በዋነኛነት ዕስራ ምእቱን ወይም የሚሌኒየሙን በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀና እስካሁን ከቀረቡ ዐውደ ርዕዮች ለየት የሚያደርገው ከዚህ በፊት ቤተ ክርስቲያን ያሏትን ሀብቶች በንዋያተ ቅድሳትና በሌሎች ደረጃ በዝርዝር ያስረዱበት ነበር፡፡ የአሁኑ ዐውደ ርዕይ ከዚህ በፊት ከቀረቡት የሚለየው የቤተ ክርስቲያኒቷ ታሪክ በሁለት ሺህ ዘመናት ምን እንደነበረ፣ የቤተክርስቲያኒቷ ብቻ ሳይሆን በሀገራችን የቤተክርስቲያኒቷ ታሪክ የሀገሪቷ፣ የሀገሪቱ ታሪክ ደግሞ የቤተክርስቲያኒቷ ስለሆነ ታሪኩን ለሕዝቡ በደንቡ ለማስረዳትም ታስቦ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎች ዓለማት የሚለዩዋት ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች አሏት፡፡ ከነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በትክክል ለሕዝቡ የሚቀርብበት ነው፡፡ “የዘመን አቆጣጠራችን የራሳችን ብቻ መሆኑን የማስረዳትና ከሌሎች የሚለይበትንም ምክንያት ማስገንዘብ” ዓላማችን ነው ብለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ በዋነኛነት በስነጥበብ ዘርፍ ከዓለም ድንቅዬ የተባሉ ጥበቦች ያሉባት አገር መሆኗን በስነ ሥዕል፣ በስነ ዜማ፣ በስነ ፅሁፍ፣ በኪነ ሕንፃ የኢትዮጵያ ታሪክ ምን ይመስላል? ከሌሎች ልዩ የሚያደርገንስ ምንድን ነው? እንዴትስ ጠብቀነው መሄድ እንችላለን የሚለው የሚታይበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ ኢትዮጵያ ታላላቅ መሪዎችን ማፍራት የቻለች አገር ናት፡፡ እነዚህን መሪዎች በማፍራት አንፃር ቤተክርስቲያኒቷ ትልቅ ሚና ተጫውታለች፡፡ አገራቸውን የሚወዱ፣ ለአገራቸው የሚሞቱ፣ ራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡና አገራቸውን አስጠብቀውና ነፃ አድርገው የሚኖሩ ሆኖም የሌሎችን ድንበር ዘለው የማይሄዱ ትልቅ ታሪክ ያላቸውን መሪዎች አፍርታለች፡፡ ብዙዎቹ መሪዎች ከቤተክርስቲያን የወጡ ነበሩ፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያኒቷ አስተምህሮ ለመሪዎቹ ሰብዕና ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡

በሕግ ረገድም ቢታይ አሁን ፍትሐ ብሔር፣ የወንጀል ሕግ የሚባሉት ረቅቀው ባልወጡበት በዛን ዘመን ሕግ በማፅደቅ፣ ሕዝቡን በማስተዳደር፣ በመዳኘትና በመሸምገል ብዙ አስተዋፅኦ አድርጋለች፡፡ ለዚህም “ፍትሐ ነገሥት” ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ለአሁኑ ትውልድ ትምህርት በመሆኑ ዐውድ ርዕዩ አንዱ የማሳያና የማስተማሪያ መድረክ ነው፡፡

ቤተክርስቲያኒቷ በልማትና በብልፅግና ያላት አስተዋፅኦን አስመልክቶ ብዙ የተሳሳቱ አመለካከቶች ሲንፀባረቁ ይታያሉ፡፡ ቤተክርስቲያኒቷ ሰው ሥራ እንዲፈታ የምታስተምር፣ ማግኘት ትክክል እንዳልሆነ እንደምታስተምር ተደርጎ የማየት ነገር አለ፡፡ ትምህርቷ ሰው ሰርቶ ማደግ ሌላውንም መርዳትና መደገፍ እንደሚኖርበት ነው፡፡ ሰርቶ ባገኘው ግን ወንጀልን መፈፀም እንደሌለበት ትምህርቶቿ ሁሉ የዕድገት መሆኑን ግንዛቤ የሚገኝበትም ነው፡፡

በነበሩት ሁለት ሺህ ዓመታትና ከዚህ በፊት በነበሩት ጊዜያት ቤተክርስቲያኒቷ ከነበራት አስተዋፅኦ በተጨማሪ ወደፊት ይህንን ጠብቆ ለማቆየት ምን መሰራት አለበት የሚለው የሚነሳ ጥያቄ በመሆኑ ለዚህም አቅጣጫ የሚያመላክትበት ነው፡፡

ትላንት ምን ነበር፣ ምን ልዩ የሚያደርግ ነገር አለ፣ ምን አበርክተናል እና ወደፊት ደግሞ ይህ ትውልድ ምን መስራት ይኖርበታል የሚለውን የሚያሳዩበት ዐውደ ርዕይ መሆኑን ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

ከዐውደ ርዕዩ ጎን ለጎን በኤግዚቢሽን ማዕከሉ አዳራሽ የፊታችን ቅዳሜና እሑድ ዐውደ ጥናቶች ይኖራሉ፡፡

ሶስተኛው ሺህ ሲነሳ አብዛኛው ተረካቢ ቀጣዩ ትውልድ በመሆኑም አሁን የተደረሰበትን ጨምሮ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የሕፃናት ቀን መዘጋጀቱን ያመለከቱት ዲያቆን ሰሎምን፣ በቅርብ ቀናትም በስድስት ከተሞች ውስጥ ዐውደ ርዕዩ መታየት እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡


በምሕረት ሞገስ

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)