January 23, 2008

በሃይማኖትና በጎሳ ስበብ የሚጫረውን እሳት ለማጥፋት . . .

The following article is prepared by Reporter Newspaper. It seems the issue we have been trying to discuss quite for some time seems to have got recognition. But still, the source of the problem is not getting proper attention. Let us call a spade a spade. Fanatic islam is trying to annihilate Christianity in Ethiopia.
......
በቤተልሔም ነጋሽ
በሃይማኖት ሽፋንና የጎሳ ልዩነትን ምክንያት በማድረግ በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች ግጭቶች ተከስተው ንብረት መጥፋቱና የሰው ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡ በተለይ ባለፈው ዓመት በጅማና አጋሮ አካባቢዎች ተከስቶና በየአካባቢው ተዛምቶ ጉዳት ያደረሰውን የሃይማኖትን ልዩነት መሰረት ያደረገ ክስተት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የተለያዩ ብሔሮችና እምነት ተከታዮች ተሰባጥረው የሚኖሩባቸው የተለያዩ የአገራችን ክልሎች አስከፊ ከሆኑ ግጭቶች እንዲላቀቁ የመንቀሳቀስ ዓላማ ይዞ የተቋቋሙ የሰላምና ልማት ፎረሞች በዘርፉ እየተደረጉ ካሉ ጥረቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡


ፎረሞቹ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ከኖርዌይ ቤተክርስቲያን የእርዳታ ድርጅት ጋር በመተባበር ያቋቋማቸው ናቸው፡፡

ፎረሞቹ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በተለይም ከዚህ ቀደም የጎሳና የሃይማኖት ግጭቶች በተከሰቱባቸውና ተጋላጭ ናቸው በሚባሉ አካባቢዎች የተቋቋሙ ናቸው፡፡ በዚህ ሳምንት ሰኞና ማክሰኞ እነኚሁ 13 ፎረሞች በአዲስ አበባ ተገናኝተው ስላከናወኗቸው ተግባራት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ለፎረሞቹ የወጣው ዝርዝር የሥራ አፈፃፀም መመሪያ ረቂቅ ላይም ተነጋግረዋል፡፡

ከተለያዩ የእምነት ተቋማት፣ የሴቶችና የወጣት ማህበራት እንዲሁም ከመንግስትና ከተለያዩ የሲቪል ማህበራት የተውጣጡ አባላት ያሏቸው ፎረሞች ስላከናወኗቸው ተግባራት እንዲሁም በየአካባቢያቸው ስላለው ሁኔታ ከተወሰኑት ጋር ቆይታ ለማድረግ ችለናል፡፡

መጋቢ ኃይላት ፍቅረሰላም ወረደ የሸካ ቤንች ማጂ ዞን ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅና የአካባቢው ፎረም ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው ፎረሙ የተመሰረተው ከታህሳስ 21 እስከ 23 በሚዛን ከተማ በኮሚሽኑ አማካኝነት የሰላም ግንባታ መርሃ ግብር ከተካሄደ በኋላ ነው፡፡ ከተሳተፉ ሰዎች መካከል ሰባት አባላት ያለው ኮሚቴ ተቋቁሞና በአካባቢው ያለውንና የሚፈጠረውን ግጭት የኮሚቴው አባለት እያወያዩ እንዲፈቱ፣ ግጭት ከመፈጠሩ በፊትም ምልክቶች ካዩ ቅድመ ማስጠንቀቂያ በማድረግ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት፣ የጎሳ መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በመሆን ጉዳዩን ለመፍታት እንዲቻል መስራት ጀመረ፡፡

ኮሚቴው በመጠኑ መንቀሳቀስ የጀመረ ሲሆን ባለፈው ጊዜ በአጋሮ አካባቢ ተከስቶ የነበረው ችግር ተጽዕኖ ስለነበር ህብረተሰቡን አሰባስቦ በቤተሰብ ደረጃ ሳይቀር የሚፈጠሩ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለሃይማኖት አባቶችና ለፎረሙ አባላት መረጃ አንዲሰጡ አስተምረዋል፡፡ ይኸውም ችግሮች ሲከሰቱ አስቀድሞ ለፎረሙ አባላት መረጃ እንዲደርስ ለማድረግ ነው፡፡

አቶ ሀብተማርያም ካዝቴት የቤንች ማጂ ዞን የአገር ሽማግሌ በበኩላቸው ለግጭቶች መንስኤ የሚሆነው በአካባቢው የተማረ የሰው ኃይል አለመኖሩና ማንአለብኝነት፣ አንዱ ጎሳ ከሌላው እኔ እበልጥ ማለቱ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በትንሽ ነገር ተነሳስቶ መዛት መገዳደል፣ ቤት ማቃጠል የመሳሰሉትን መፈፀም የተለመዱ ናቸው፡፡

በአብዛኛው የጠብ ቀስቃሾች የሆኑት ወጣቶች የሰላምና ልማት ፎረሙ በሚያዘጋጃቸው ስብሰባዎች አለመገኘታቸው ሥራውን ለማስኬድ እንቅፋት መሆኑን አቶ ሃብተማርያም ይገልፃሉ፡፡ ጠብ የሚጭሩ ሰዎች የእነሱ መጎዳት ብዙ ቤተሰቦችን የሚጎዳ መሆኑን ለመገንዘብ አለመቻላቸው በዞኑ ወንድማማቾች ሳይቀር የሚገዳደሉበት አጋጣሚ ሳይቀር መኖሩን ይገልፃሉ፡፡ ይህንን በተመለከተ በአካባቢው ግጭቶች እንዳይከሰቱ የመከላከልና የባህላዊ እርቅ ሥርዓትን የማስፋፋት ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ይገልፃሉ፡፡

የግጭት አፈታትን በተመለከተ ከተለያዩ የእምነት ተቋማት የተውጣጡ አባላት ያሉት በመሆኑ የፎረሙ አባላት በሄዱበት ሁሉ ጠብ የፈጠሩ ሰዎች ሰላማዊ ሁኔታን ለመፍጠር ዝግጁ ሆነው እንደሚያገኛቸው መጋቢ ኃይላት ፍቅረሰላም ሲገልጹ በዚህ ምክንያት ግጭት የመፍታት አቅም እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡

እንደ መጋቢ ኃይላት ፍቅረሰላም ገለፃ በዞናቸው አብዛኛው የሚነሱ ግጭቶች በህፃናትና በወጣቶች ተጀምሮ ቤተሰቦቻቸው ወደ ሃይማኖት አሳድገው ሲያቀጣጥሉት የሚፈፀም ነው፡፡ በተጨማሪም በቤተሰብ፣ በግጮሽ ቦታ፣ በሴቶች ምክንያት የሚነሳ ነው፡፡ ቤንች ማጂ ዞን ከ8 በላይ ብሔረሰቦችና አርብቶ አደሮች፣ ነጋዴዎች የሚኖሩበት በመሆኑ በሥራ ሂደት የሚፈጠሩ ጠቦች ይኖራሉ፡፡

የሰላም ግንባታው ኮሚቴ ከተቋቋመ በኋላ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ የተሰጠው የሥራ ዝርዝር አለመኖሩ የፎረሙን ሥራ ሲያጓትት፣ የቢሮ ችግርና የቁሳቁስ አለመሟላት ተጨማሪ ለሥራ እንቅፋት ሆነዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ ታረቀኝ ከሊሙ አውራጃ አጋሮ ከተማ የመጡ የአገር ሽማግሌና የአካባቢው የሰላምና ልማት ፎረም አባል ናቸው፡፡ ፎረሙ የተቋቋመው በኅብረተሰቡ ራስ አነሳሽነት እንደሆነ ሲገልፁ ባለፈው ዓመት ከመስከረም እስከ ታህሳስ የቆየው የአካባቢው ጠብ እንዲበርድ ፎረሙ ሚና ተጫውቷል ይላሉ፡፡ በአካባቢው ጉዳት የደረሰባቸው በመጠኑም ቢሆን መረዳታቸውንም ይጠቅሳሉ፡፡

እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለፃ በአጋሮ የተነሳው ግጭት ምክንያት በኢሉባቡር ደምቢ የሚባል አካባቢ ጭሪ በምትባል ቀበሌ በመስቀል ደመራ ምክንያት የተፈጠረ አለመግባባት ነው፡፡ በዚህ ውጤት ከቀያቸው መፈናቀል ለደረሰባቸው ጭምር ፎረሙ አገልግሎት መስጠቱንም ተናግረዋል፡፡

አሁን መጠነኛ የሆነ ሰላም ቢኖርም ለአጋሮው ግጭት መቋጫ እንዳልተበጀለት አቶ ሙሉጌታ ይገልፃሉ፡፡ "ያሉትን አሰባስበን ማን አጥፍቷል? የሚለውን አነጋግረን ተቻችለን እርቀ ሰላም እንዲወርድ ማድረግ ነበረብን" ይህንን ማድረግ ደግሞ የሚችሉት አሁን ሁኔታው ከተረጋጋ በኋላ ማንሳት መቀስቀስ ይሆናል ብለው መተዋቸውን ይገልፃሉ፡፡

የአጋሮ ፎረም ፀሐፊ አቶ ወ/ጊዮርጊስ ገ/ስላሴ እንደሚሉት ፎረሙ በጥቅምት ወር በወረዳው የተፈጠረውን ችግር ለማጣራት ከመንግስት /ከወደረዳው አስተዳደር/ የተወከሉ ኃላፊዎች ባሉበት ቦታው ድረስ ሄደው ህዝቡን አነጋግረዋል፡፡ ጥፋቱ ከዚህ ተነሳ ለማለት አዳጋች ሲሆን በአሁኑ ወቅት ችግር የለም፡፡

የሃይማኖት ሃላፊዎች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አቶ ወ/ጊዮርጊስ ሲገልፁ "በየመስጊዱና በየቤተክርስቲያኑ የሚሰጡ ትምህርቶችን በተመለከተ የእምነት ቤቱ አስተዳዳሪዎች እንዳመለከቱ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ አንዳንዶች አላስፈላጊ ትምህርት እንዳይሰጡ ለማድረግ ኮሚቴው እየሰራ ነው" ብለዋል፡፡

ሁለቱ የፎረሙ አባላት የመንግስት አካላት ጭምር በፎረሙ /የወረዳ ካቢኔዎች/ አባል በመሆናቸው ጥሩ ተቀባይነት ቢኖርም የኮሚቴው አባላት የሚንቀሳቀሱበትን ዓላማ ጉዳዬ ነው ብለው የመትጋት ነገር እንደሚጎድል ይገልፃሉ፡፡

አቶ ሙኪሳ ያሳ የጅማ ዞን የሰላምና ልማት ፎረም ሰብሳቢ ናቸው፡፡ የጅማ ፎረም ከተቋቋመ በኋላ ወደ ሥራ እንዲገባ ባለመደረጉ ሥራ አልጀመረም፡፡ ሆኖም ፎረሙ ከተቋቋመ በኋላ የሥራ ኃላፊዎችና ባለስልጣናትን አግኝተው ዓላማውን ለማስረዳት እንደሞከሩ ይገልፃሉ፡፡ በወረዳው ፀጥታ ጽ/ቤት ከተመሰረተው ኮሚቴ ጋር አብሮ ለመስራ የሚቻልበትን ሁኔታ መነጋገራቸውንም ያስረዳሉ፡፡

አካባቢው ለግጭት ተጋላጭ እንደመሆኑ በፎረሙ ደረጃ ለግጭት ምክንያት ይሆናሉ ብላችሁ የገመታችኋቸው ጉዳዮች ምንድ ናቸው ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ አቶ ሙኪሳ "ከተማው የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና የተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮች መኖሪያ ነው፡፡ በከተማው የጅማ ዩኒቨርሲቲና የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ አሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢ ያሉ ወጣቶች በጎሳ ላይ የተመሰረተ ግጭት የሚፈጥሩበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ከኅብረተሰቡ የመነጨ ሳይሆን የተለየ ፖለቲካ አቋም ያላቸው ወጣቶች ሊያመነጩት ይችላሉ" ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ለምሳሌ ባለፉት ሳምንታት በጅማ ዩሚቨርሲቲ የተነሳውን ግጭት አስመልክቶ ጥቂት የኦሮሞ ብሔረሰብ ተማሪዎች የፈረንጆች አዲስ አመትን ለማክበር ከዩኒቨርሲቲው ፈቃድ ጠይቀው ሲከለከሉ ውጪ ወጥተው ሁከት ለመፍጠር በመሞከራቸው የተከሰተ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

በሃይማኖት ልዩነት የሚፈጠሩ ግጭቶችን አስመልክቶ ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ በመቻቻል ሊኖሩ የሚችሉበትን መንገድ ለማስተማር እንደሚገባ አቶ ሙኪሳ ሲገልፁ በጅማ ዞን ሥር ካሉት 17 ወረዳዎች ውስጥ በተለይ ከአራት እስከ አምስት የሚሆኑት ትኩረት ተሰጥቶ ካልተሰራ በሃይማኖት ሽፋን ለሚፈጠር ግጭት ተጋላጭ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ፎረሞቹን በሚያስተባብረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የማህበራዊ አገልግሎትና የሰላም ግንባታ ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ ይልቃል ሽፈራው የፎረሞቹ ምስረታ ዋና ዓላማ በተለያዩ የእምነት ተቋማት የተሰበሰቡ የተለያዩ ብሔሮች ተወላጆች የሆኑ የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ለልማት በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ልማት እንዲኖር ሰላም መስፈኑ የግድ እንደሆነና በተለይ ወጣት የአዲሱ ትውልድ አባላት ኅብረተሰቡ ጥንት ከነበረው የሰላም ጽንሰ ሃሳብ እየወጣ በመሆኑ ለሰላም ግንባታ መስራት የግድ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

በተጨማሪም የአለመቻቻል ተግባራት ሲታዩ የግጭት ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችን ማከናወን (ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ማድረግ"፣ ግጭቶች ሲከሰቱ በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን መንገድ ማፈላለግና የባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓት ማካሄድ ሌሎች ዋና ዋና ተግባራት እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ይልቃል ገለፃ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋና የጎሳ ልዩነት የጠብ መነሻ መሆናቸው ቀርቶ አንድ ቋንቋ የሚናገሩና የአንድ ሃይማኖት ድርጅት ተከታዮች ሳይቀሩ የሚጋጩበት ሁኔታ በመኖሩ በሰላም ላይ መስራቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)