June 17, 2007

የምናካሒደው ጸረ ዘረኝነት ትግል በጎጠኞች አጀንዳ እንዳይጠለፍ

(ከእውነት ይበልጣል - ewenety@yahoo.com)
በሀገራችን ማዶ የሚኖሩ መንደርተኞች እርስ በርሳቸው ቡዳ እየተባባሉ ይተማማሉ አሉ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን የመሸበት እንግዳ አሳድሩኝ ብሎ ከአንዱ ቤት ይገባል፡፡ የዛሬን አያድርገውና፣ የእግዜር እንግዳ ነውና አስተናጋጆቹ እግሩን አጥበው፣ መኝታውን አሰናድተው፣ የሚበላ የሚጠጣውን ሰጥተው፣ ኋላም አረፍ ብለው ሲጨዋወቱ እንግዳ ሆዬ አንድ ጥያቄ ያነሳል፡፡ ‹‹ኧረ እዚያ ማዶ መንደር ያሉ ሰዎች ቦዶች ናቸው ይባላል፣ እውነት ነው›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ከቤቱ ሰዎች አንዱ መልሶ ‹‹እንጃ፣ እኛ እነርሱን ቡዳ ናቸው እንላለን፣ እነርሱም እኛን ቡዳ ናቸው ይሉናል፡፡ እውነቱ ምን እንደሆነ አዳርህን አይተህ ትመሰክራለህ›› ቢለው ሰውየው ፈርቶ ሌሊቱን አውጣኝ አውጣን ሲል አደረ ይባላል፡፡ ይህችን ተረት ያስታወሰኝ ነመራ ዋቀዮ ቶላ የተባሉ ጸሐፊ ‹‹የጎንደር ምንቸት ውጣ፣ የትግሬ ምንቸት ግባ - ዘመነ መሳፍንት በቤተ ክህነት›› በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጽሑፍ ነው፡፡ ጸሐፊው የማይነካውን ለመንካት ያገኙት ድፍረት እኔንም ቀሰቀሰኝና ብዕሬን አነሣሁ፡፡
TO READ MORE, PLEASE CLICK ON THE TITLE ABOVE.

ዛሬ ከኤች. አይ. ቪ በበለጠ ኢትዮጵያውያንን እየለከፈ ያለው የጎጠኝነት መንፈስ በእነማን ላይ ያደረ ዛር ነው ቢባል ‹እኔ ከደሙ ንጹሕ ነኝ› የሚል ከተገኘ ሳያስገርም አይቀርም፡፡ይህ የጎጥና የወንዝ ዛር የታሪካችን አካል መሆኑ የማይካድ ቢሆንም እንዲህ እንዳሁኑ ግን በሚገባ የተካደመበትን፣ ድቤ ያስደለቀበትን፣ እንዲያውም ሀገርን ከመውደድና ከማፍቀር ጋር የተቆራኘበትንና የተሰበከበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ ለመሆኑ ይህ ችግር ከየት መጣ፣ የነማን ችግር ነው ቢባል ከላይ እንደተጠቀሱት ባላገሮች ‹አንተ አንተ› እያሉ ከመጠቋቆም በስተቀር የችግሩን ምንጭ ለማሳየትም ሆነ መፍትሔውን ከራስ ለመጀመር የደፈረ ያለ አይመስልም፡፡ ጉዳዩን አንስቶ ለመነጋገርም እንደ ነመራ ዋቀዮ ቶላ ዓይነት ‹ደፋሮችን› በብዛት ማግኘት ይጠይቃል፡፡ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ኑሮ ደረጃ ይህ ነው ሊባል የሚችል ልዪነት በሌላቸው፣ በአጠቃላይ ሲታይ የተመሳሳ ሃይማኖት ተከታዮች በሆኑ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል (ኧረ ይልቁንም በተመሳሳይ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል) እየተገነባ ያለውን ግንብ መሠረት የጣለው ማን ነው፡፡ የቆየ የታሪካችን ጠባሳ ከሆነስ መጪው ትውልድ እንዳይስቅብን እንዴት እናስተካክለው፡፡ ቢያንስ ይህንን አሳፋሪ የመለያያ ግንብ እየገነቡ ያሉትን የ‹ፖለቲካ› እና የ‹ሃይማኖት› ሰዎች ሳናፍርና ሳንሞዳሞድ ነፍሳችን እንደምትጸየፋቸው እንዴት እንንገራቸው፣ የሚለው ብዙ ሊያወያየን የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ከዚሁ አዙሪት ሊወጣ ያልቻለው ፖለቲካችን ለጊዜው ይቆየኝና ስለ ቤተ ክህነቱ ትንሽ ልበል፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተፈጠረውን ልዩነት በተመለከተ መንፈሳዊዎቹን ሕግጋት እየጠቃቀሱ ምእመኑን ግራ ማጋባቱ ይቀጥል እንጂ መነሻውም ሆነ መድረሻው ግን ከላይ ያነሳሁት የጉጥና የወንዝ ጉዳይ እንደሆነ ከዚህም ያለፈ እንዳልሆነ የቤቱን ‹ምሥጢር› የሚያውቁ ሁሉ ያውቁታል፡፡ በሀገር ቤት ያለችው ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ምንም አንደበተ ጎልዳፋ፣ ልብሰ አዳፋ ቢሆኑም፣ ቤተ ክህነቱም ከነመፈጠራቸው ባያውቃቸውና ቢዘነጋቸው፣ እነርሱ ግን ከደሃው ገበሬ ምእመን እየተረዳዱና የወር የዓመት ደሞዝ ሳይጠይቁ በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ምእመናንም የማንንም ‹መመሪያ› ሳይጠብቁ ካህናቱን እያከበሩና እየታዘዙ ያላቸውን ሁሉ እየሰጡ በንጹህ ልቡና አምላካቸውን ይማጠናሉ፡፡ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም ማንነታቸውንና ሥራቸው የማያውቀው የአብነት መምህራንም በዓታቸውን ሳይለቁ ያገኙትን ተማሪ ያስተምራሉ፡፡ተማሪዎቹም ዛሬም እንደ ጥንቱ እየለመኑ ይማራሉ፡፡መምህራኑም ከልመናው ቁራሽ ተካፍለው ይበሉ እንደሆን እንጂ የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ የሚላቸው ቤተ ክህነት የለንም፡፡ እንዲህ ተቸግረው ተምረው ለፍሬ የሚበቁትን ደቀመዛሙርትም በተማሩበት ለሥራ የሚያሰማራቸው የለም፡፡ ይልቁንም አፈጮሌዎቹ ወይም ባለዘመዶቹ ናቸው ሁሉን በሁሉ አድርገው የተቆጣጠሩት፡፡ ከዚያም አለፍ ካለ እንዲሁ በችግርም ሆነ በሌላ ምክንያት ትምህርታቸውን ከቅዳሴ በላይ ያልዘለቁት፣ ከመምህሮቻቸው የተማሩትን ትህትና ይዘው ከተማ የገቡት ካህናትና መነኮሳት በየከተማው ያለውን ድፍረትና ፈሪሃ እግዚአብሔር ማጣት እየተመለከቱ (መጀመሪያ ተገርመው ሲመለከቱ ቢቆዩም) ኋላ ግን እነርሱም የዚሁ ነገር ሰለባ ይሆናሉ፡፡ መነኮሳቱም በየመጻሕፍቱ ያንቡት እንጂ አይተውት ለማያውቁት ጾር ይጋለጣሉ፡፡ አንዳንድ የከተማ ዲያቆናት ቢደፍሩ የማያስገርመው እነማንን እያዩ እንዳደጉ ስለሚታወቅ ነው፡፡
እነዚህ ከየቆሎ ቤቱ እየፈለሱ ከተማ የገቡ ካህናት ወደ ቤተ ክህነቱ ‹ሲስተም› የሚገቡት የወንዛቸውን ሰው የሆነ የደብር አስተዳዳሪ ወይም ማዘዣ የሚጽፍላቸው የቤተ ክህነት ባለሥልጣን ሲያገኙ ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን ምን ሊቅ ቢሆኑ፣ ምን መንፈሳዊ ቢሆኑ ዞር ብሎ የሚያያቸውም አያገኙም፡፡ የደብር አስተዳዳሪ የሆነ የወንዛቸውን ሰው ወይም የቤተ ክህነት ባለሥልጣን ካገኙ ግን ትምህርታቸውም ሙያቸውም አይጠየቅም፡፡ የሚሸጎጡበት ሥፍራ ይፈለግላቸዋል፡፡ እንዲህ እያሉ እስከላይኛው ማዕረግ የማይደርሱበት ምክንያት የለም፡፡ ከላይ ወደታች የሚወርደውም ምደባ ይህንኑ የወንዘኝነት መሥፈርት የተከተለ ስለሚሆን በየዘመኑ በጎሪጥ የሚተያዩና ለበቀል ጊዜ የሚጠባበቁ ወንዘኞች እየተፈጠሩ እነሆ ሀገር ሳይገድባቸው አቋቋሙን ከትግራይ-ከጎንደር፣ ቅኔውን ከጎጃም፣ ትርጓሜ መጻሕፍቱን ከሸዋ እያሉ የተማሩ ሊቃውንት ወደ ኋላ ተመልሰው የጎንደር፣ የጎጃም፣ የሸዋ እየተባባሉ (ሌላው ቢቀር ከመቶው እጅ አብዛኛው ከነዚህ ጎጦች ውጪ መሆኑን ዘንግተው) የእውነተኛይቷን ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ዓላማ እያደናቀፉ መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከጨበጠበት ጊዜ አንስቶ በሃይማኖት እየተሳበበ የምንሰማው ውዝግብም የዚሁ የእንብላው አትበሉም የ‹ጎጠኞች› ሽኩቻ ውጤት ነው፡፡ የነበረውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ አራተኛውን ፓትርያርክ አስፈራርቶ ወይም በማግባባት ሥልጣናቸውን እንዲለቁ በማድረጉ ረገድ ግንባር ቀደም የነበሩት ለቦታው ራሳቸውን ያጩ ከላይ በተገለጸው መንገድ ዙሪያቸውን የከበብዋቸው ‹የመነድራቸው ልጆች› እንደነበሩ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ይህንን ፓትርያርክ የመቀየርን ውሳኔ በማሳለፉ ረገድ የሚሰጠው ማንኛውም ዓይነት ማስተባበያ (በሕይወት ላይ የተቃጣ አደጋ እንኳን ኖሮ ቢሆን) ራስን ከኃላፊነት ለማሸሽ የሚደረግ ዘዴ ከመሆን የማይዘል በመሆኑ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ በወቅቱ የነበሩ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ (በሕይወት ያሉትም ያለፉትም) ኃላፊነቱን ሊወስዱ ይገባል፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ እንዳስተማረን ‹ብዙ ከተሰጠው ብዙ› ይጠበቃልና፡፡ እነዚህ አባቶቻችን (ዛሬ ተቃዋሚ ለመምሰል የሚሞክሩትን ጨምሮ) በፈጸሙት ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ቤተ ክርስቲያናችን ስትበጠበጥ መኖር የለባትም፡፡ በነፍስም በሥጋም የሚያስፈርደውን ይህንን ታሪካዊ ስሕተት የፈጸሙት ራሳቸውና ራሳቸው ብቻ ኃላፊነቱን ሊወስዱ ይገባልና፡፡
ወደ ጎጡ ሽኩቻ ስንመለስ በወቅቱ በቤተ ክህነቱ በተነሳው ብጥብጥ ሥልጣን ላይ ለመውጣት በተደረገው ሽኩቻ በወቅቱ በነበረው የአንድ ወንዝ ልጆች የበላይነት አንጀታቸው አርሮ የነበሩት በሙሉ ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› በሚለው አሳፋሪ የመጠቃቂያ ዘዴያችን መመሪያነት በወቅቱ የፖለቲካው ድጋፍ ከነበራቸው የዘመናችን ባለ ተራ ወንዘኞች ጋር አበሩ፡፡ በአራተኛው ፓትርያርክ ወንበር ራሳቸውን ለማስቀመጥ ያሰፈሰፉትም ሆነ የሌሎቹ ሕልም ሳይሳካ ቀርቶ የ5ኛው ፓትርያርክ ማንነት ሲታወቅ ሁሉም ከእንቅልፉ ባነነ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ቀድሞ ነገሩ ሁሉ ሲወጠንና ሲወጠወጥ ያልተነሳው ‹‹በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ አይሾምም›› የሚለው ‹‹የመታገያ አንቀጽ›› ተፈልጎ የተገኘው፡፡ ጥያቄው በወቅቱ ይህንን ሕግ ጠቅሰው በሚገባ ያልተከራከሩና አስፈላጊውን መስዋዕትነት ያልከፈሉ አባቶች ዛሬ ጊዜና ቦታ ሲመቻችላቸው የፈለጉትን ያህል ጮክ ብለው ቢናገሩ እንዴት እናምናቸዋለን ነው፡፡ እሺ ይህም ይሁን ብለን (ቢያንስ በሃይማኖት አባትነታቸው አክብረናቸው) ብንቀበላቸው፣ በለመዱት መንገድ በውጭ የሚገኘውንም ምእመን በወንዝ ሲከፋፍሉት ስናይ ምን እንበላቸው፡፡ ሳያፍሩና ሳይፈሩ በቃልና በጽሑፍ የእነርሱ ጎጥ ከሌላው የተሻለ ቅዱስ እንደሆነ ሊነግሩን የሚሞክሩትን ግብዞች አባቶች ብለን እንዴት እንከተላቸው፡፡ (በሌላም በኩል ደግሞ በቀድሞዎቹ ጎጠኞች የተተካው አሁን ያለው አስተዳደር ካለፉት ምንም ሳይማር ከታች እስከ ላይ ያለውን መዋቅር ከራሱ ጎጥ በወጡ ካህናትና መነኮሳት ለመሙላትና ይባስ ብሎ ክህነቱም ሆነ ትምህርቲ በሌላቸው ‹‹የወንዛቸው ጎረምሶች›› ቤተ ክርስቲያኒቱን በማዘረፍ ላይ መሆናቸው እጅጉን ያቃጥላል፡፡)
በተለይም ደግሞ በቀላሉ የዚህ የጎጥ በሽታ ሰለባዎች ለመሆን የበቁት ቀድሞውንም በአብዛኛው ስለማኅበራዊ ግንኙነት እንጂ ስለሃይማኖት ብዙም በማይደንቃቸው ግለሰቦች የተመሰረቱትና የፖለቲካ መድረክ በተደረጉት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ ከእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት አብዛኞቹ የቀድሞዎቹ የቤተ ክህነት የጎጥና የመንደር ‹‹ሃይማኖት›› አራማጅ መነኮሳትና ካህናት በማንአለብኝነት ባቋቋሙት ‹ስደተኛው›ና ‹ሕጋዊው ሲኖዶስ› በሚሉት የአንድ ጎጥ ኮሚቴ አንመራም በማለት አቋም መያዛቸው አግባብ ቢሆንም ይህንኑ አቋማቸውን በግልጽ ለምእመናን አሳውቀው ያለውን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንጂ የቅዱስ ሲኖዶስን አንድነት እንደማይቃወሙ ለመግለጽ ብዙ ጊዜ ፈጅቶባቸዋል፡፡ ዛሬም ግን አልረፈደም፡፡ በያዙት አቋም ጸንተው ቤተ ክርስቲያን የምትጠናከርበትን ብሎም አንድነቷን ድጋሚ የምትቀዳጅበትን መንገድ በመፈለጉ ላይ የበለጠ መጣር አለባቸው፡፡ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ራሳቸውን ከማንኛውም ጎጠኛ አመለካከት ለማጽዳት መጣር አለባቸው፡፡ ምእመናንም መርዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአገር አንድነት ስሜት ሳይሆን የጎጠኝነት ስሜት የተጠናወታቸው የሃይማኖ ካባ ለባሾች በፖለቲካው ትግል ከጎናችን የቆሙ ቢመስለንም ከእኛ ጋር አለመሆናቸውን መረዳት አለብን፡፡ ይልቁንም በሥልጣን ላይ ያለውን የመለስ ዜናዊ አምባገነናዊ አስተዳደር ለመቀየር በሚደረገው ትግል አጀንዳው በነዚህ ሰዎች ጎጣዊ አስተያየት እንዳይጠለፍና አገሪቱና ቤተ ክህነቱ ከወያኔ ያልተናነሱ ጎጠኞች እጅ እንዳይወድቁ ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ከአንድ ጎጥ የተሰባሰቡ ዘረኞች ጎጠኛውን ወያኔን ለመዋጋት ሞራላዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ብቃት የላቸውም፡፡ ወያኔን መጥላት ብቻ ኢትዮጵዊ አያደርግም፣ አገር ወዳድም አያሰኝም፡፡ ሌላውን ዘረኛ ለመዋጋት የምንነሳ ሁላችን በመጀመሪያ ከውስጣትችን የተደበቀውን የዘረኝነት በሽታ አውጥን እንጣል፡፡ ራሳችንን ከዚህ ነውር እንጽዳ፡፡ እንንጻ፡፡ ለዚህም ከራሳችን ጀምሮ መውሰድ ስለሚገባን እርምጃ አስቀድመን እንወያይ እላለሁ፡፡
ቸር ይግጠመን፡፡

1 comment:

Anonymous said...

My brother God bless you
Kale hiwot yasemah.
thank you very mach

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)