December 11, 2006

ግልጽ ደብዳቤ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ

ግልጽ ደብዳቤ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡ ‹‹የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ›› (ምሳሌ 23፡10) ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ተደፋፍሬ ያለአቅሜና ችሎታዬ ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ በመነሣሣቴ አስቀድሜ ይቅርታዎን እጠይቃለሁ፡፡ ቡራኬዎ እንዲደርሰኝም ዝቅ ብዬ እለምናለሁ፡፡ ለቤተ ክርስቲያኔ ያለኝ ፍቅር ጥልቅ ባይሆንና አሁን ያለችበትም ሁናቴ እጅግ የሚያሳስብ ባይሆን ኖሮ ወደ ላይ ተንጠራርቼ ለቅዱስነትዎ ጦማር ለመላክ ባልተገዳደርኩ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እናት ቤተ ክርስቲያን ካለችበት ችግር አንጻር ምዕመናንም ባለን ድርሻ የሚታየንን ብንናገር ለክፋት አይሰጥም በሚል ከኅሊናዬ መክሬ ለመጻፍ ወሰንኩ፡፡


The rest of the post comes between the span ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን
ቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ ዘመናት ከደረሱባት መከራዎችና ስደቶች ተርፋ ለዚህ ትውልድ የደረሰችው በጠንካራዎቹ አባቶቻችን ተጋድሎና በደሙ በመሠረታት በመድኃኒተ ዓለም ክርስቶስ ቸርነት እንደሆነ እናንተ አባቶቻችን ዘወትር የምታስተምሩን የታሪክ እውነት ነው፡፡ የግራኝ አህመድን ሰይፍ፤ የዮዲትን እሳት፤ የነአልፎንሱ ሜንዴዝና ተከታዮቹን ቅሰጣ አልፋ እነሆ ለእኛ ደርሳለች፡፡ ተጋድሎ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ጸጋ ነውና አባቶቻችን ያለፉበት መከራ ዛሬም መልኩን ቀይሮ መከሰቱ አልቀረም፡፡ በቅርቡም የዜና ማሠራጫዎችን ያጣበበው የወገኖቻችን ጭፍጨፋ አንዱ አብነት ነው፡፡ ነገር ግን ለእኔ ደብዳቤ መጻፍ ምክንያት የሆነኝ እርሱ አይደለም፡፡ ምክንያቴ ‹‹የጓዳውን ወደ አደባባይ›› እንዳይሆን እንጂ በለሆሳስ በመናፈስ ላይ ያለው በአሜሪካ ጵጵስናን ለተወሰኑ መነኮሳት የመስጠቱ ዜና ነው፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን
እግዘኢብሔር ዕድሜና ጤናውን ሰጥቶዎት እዚህ እስከደረሱበት ጊዜ ድረስ ብዙ መከራዎችን አሳልፈዋል፡፡ እግዚአብሔር በሚያውቀው ምስጢር ከአገርዎ ተሰደው በባዕድ ምድር ለመኖርም ተገደዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ተስፋ ሳይቆርጡ አገልግሎትዎን በማስፋት የተበተንን ልጆችዎን በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዝርወት ላለችውም ቤተ ክርስቲያንም ዓይንና ልብ ሆነው የክርስቶስ ወንጌል እንዲስፋፋ በማድረግ ላይ ነዎት፡፡ ይህንን ሐዋርያዊ አገልግሎትዎን ታሪክ ዘወትር ሲያስታውሰው እንደሚኖር ጥርጥር የለኝም፡፡ በዚህ ነቅ በማይወጣለት አገልግሎትዎም ቅዱሳን አበው ያገኙትን ክብር እንደሚያገኙ በአምላኬ እምነት አለኝ፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ይሁን እንጂ ከፍ ብዬ የጠቀስኹት ጵጵስናን የመስጠቱ ዜና ይህንን መልካም ስምዎን የሚያጠፋ፤ ታሪክዎን የሚያጎድፍ፤ ጠቢቡ ‹‹የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ›› (ምሳሌ 23፡10) ሲል በምድራዊቱ ድንበር አንጻር የተናገረውን የአበው ሃይማኖታዊ ድንበር የሚያስፈርስ፤ በታሪክ ዘንድም ተወቃሽ የሚያደርጎት ከባድ ፈተና ነው፡፡ ይህንን ለማድረግዎት አሳማኝ መጽሐፋዊ ማስረጃ እንኳን ቢኖርዎት ጉዳዩ ለጊዜው በአስተዳደር የተለያያችሁትን አባቶች እናንተም ካለፋችሁ በኋላ ትውልድ ተስማምቶ አንድ እንዳይሆን የሚያደርግ በመሆኑ ውሳኔዎትን እንደ ገና እንዲያጤኑት ዝቅ ብዬ እለምናለኹ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን
ዘመኑ ሰዎች በኅሊናቸው የሚመሩበት ሳይሆን በእልህና በግትረኝነት የሚመላለሱበት በመሆኑ አገር ቤት ባለው አስተዳደር የሚሠራው ተደጋጋሚ ስሕተት እርሶንም ወደ ተሳሳተ ውሳኔ እንዳያደርስዎት መስጋቴን ልደብቆት አልፈልግም፡፡ እነርሱ እንደዚህ ስላደረጉ እኛም እንደዚህ እናደርጋለን የሚለው አስተሳሰብ ሌላ ጥፋት ያመጣ ካልሆነ በስተቀር ለቤተ ክርስቲያናችን የሚፈይድላት ምንም ነገር አይኖርም፡፡ የፈረሱ ገዳማቷን አይሠራላትም፡፡ የተበተኑ ልጆቿንም አይሰበስብላትም፡፡ በምዕራቡ ዓለም የአበው ጳጳሳትን ቁጥር በማብዛት ብቻ ስብከተ ወንጌል አይስፋፋም፡፡ ስለዚህ ቅዱስ አባታችን ይህንን የታናሽ አገልጋዮን ቃል ባለማቃለል በተለመደው በሳል አመራርዎ ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያጤኑት እለምናለሁ፡፡ ነገሩ ከመጀመሪያውኑ ያልታሰበና ተራ ወሬም ከሆነ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን ብዬ በደስታ እቀመጣለኹ፡፡ ነገሩ በርግጥም የታሰበ ከሆነ ግን ክፉ ጠባሳ ትተው እንዳያልፉና በ‹‹አባ መርቆርዮስ ዘመን ይህ ተደረገ›› እየተባሉ በታሪክም በመጥፎ እንዳይነሱ፤ መጽሐፍ ‹‹ከመልካም ሽቱ መልካም ስም ይሻላል›› (መክብብ 7፡1) እንዲል ስለስምዎ ብለው ነገሩን በጥሞና ያስቡበት የምለው ከትልቅ ይቅርታ ጋር ነው፡፡ እልህ ቤት አይሠራም፡፡ ባጠፋሁ ይቅር ይበሉኝ፡፡
የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረሰኝ
ታናሽ አገልጋይዎspan tags

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)