November 24, 2006

የአቶ መለስ መግለጫ፡- ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ›› እንዳይሆን

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኅዳር 14/ 1998 ዓ.ም ለምክር ቤቱ ባሰሙት ንግግር በምዕራብ ኢትዮጵያ በእስልምና ስም የተካሔደው ጭፍጨፋ ላይ ማብራሪያ (ፒዲኤፍ ፋይሉን አዚህ ይመልከቱ) ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸው መሠረት ብጥብጡ በተነሣባቸው የጅማና ኢሉ አባ ቦራ ዞኖች 13 ክርስቲያኖችና 6 ሙስሊሞች ሲገደሉ÷ 37 ሰዎች ቆስለዋል፡፡ ንብረትንም በተመለከተ አምስት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል÷ ስድስቱ ላይ የማቃጠልና የመዝረፍ ሙከራ ተደርጎባቸዋል÷ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት ተዘርፈዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም 600 መኖሪያ ቤቶች በእሳት የጋዩ ሲሆን ስድስት የፕሮቴስታንት ቤተ ጸሎቶች ወደ መስኪድነት ተቀይረው እንደነበር አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ማብራሪያቸውን በመቀጠል እንደተናገሩት ከሆነ ‹‹ይህንን ቀውስ የፈጠሩት አክራሪ እስላሞች በሙሉ የአካባቢው ተወላጆች አይደሉም››፡፡ ይልቁንም እርሳቸው እንደገለጽዋቸው ‹‹የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ኃይሎች›› ናቸው፡፡ ጉዳዩ በሁለቱ ዞኖች መረጋጋቱን ያስረዱት አቶ መለስ በሌሎች አካባቢዎች ግን የተለያዩ መረጃዎችን በሲዲ በማባዛት የሚያሰራጩ ‹‹ጸረ ሰላም›› ኃይሎች አሉ ብለዋል፡፡ እነዚህም ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለንም ብለዋል፡፡
ማንኛውም አገሩን የሚወድ ሰው የዚህ አገር በቀል ያልሆነ ችግር መብረድና መፈታት በእጅጉ ያስደስተዋል፡፡ የፈረሱት ቤቶችና አብያተ ክርስቲያናት ዳግም በደቦ መሠራት÷ ከቀዬያቸው የተሰደዱ ምዕመናን መመለስ÷ እምነታቸውን በስለት አስፈራርተው ያስቀየሯቸው ሰዎች ወደቀደመ እምነታቸው መመለስመልካም ዜና ነው፡፡ ነገር አሁንም በደንብ ሊጤን የሚገባው ትልቅ ነገር እንደተረሣ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም ብለን እንደዘገብነው መንግሥት ሲዲ የሚያሰራጩ ያላቸውን በማሰስና በማሰር ብቻ እንዲሁም አክራሪ ናቸው ያላቸውን አንዳንድ ሰዎች በመያዝ ለችግሩ እልባት የሚሰጥ የመሰለው ይመስላል፡፡ ማንም ሰው ስለዚህ ጉዳይ ድጋሚ እንዳይናገር በማፈን አለባብሶ ለማለፍም ይፈለጋል፡፡
ችግሩን ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት ‹‹የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው››÷ ወይም ‹‹የሻዕቢያ መንግሥት የሚያቀናብረው ድርጊት›› ብቻ አድርጎ መቁጠሩ ትልቅ ስሕተት ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ አስቀድሞ ከደረሰባት አደጋ ይልቅ ይህ ችግሩን የማድበስበስ ተግባር ይጎዳታል የሚል እምነት አለን፡፡ የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማገልገል ደፋ ቀና የሚያበዙ አገልጋዮቿ በአክራሪነት ስም ከመንግሥት ዓይን ውስጥ ገብተዋል፡፡ ነገ በአንዱ ባለስልጣን ትዕዛዝ እነዚህ አገልጋዮች ወደ እስር ሊወረወሩ ወይም ሌላ የከፋ አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል፡፡
ሌላው ትልቁ የሚያሳዝነው ጉዳይ ደግሞ በቤተ ክህነቱ በተለያየ ሥፍራ የተቀመጡ አንዳንድ ግለ ሰቦች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የነርሱን አጓጉል ተግባር ይቃወሙ የነበሩ ኦርቶዶክሳውያንን እያስለቀሙ ለማሳሰር የሚያደርጉት መሯሯጥ ነው፡፡ ሕዝብ የሚቀበላቸው ሰባክያነ ወንጌልን÷ ለቤተ ክርስቲያን ቅንዓት ያላቸው ማኅበራትን በ‹‹አክራሪነት›› በመወንጀል ‹‹ለማስመታት›› ትልቅ ዘመቻ በመካሔድ ላይ ይገኛል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ መጎዳት ሳይሆን ጊዜያዊ ጥቅማቸውን ብቻ በማስቀደም ወንድሞቻቸው ወይም የሃይማኖት ልጆቻቸው ላይ ክፉ ጉዳት እንዲመጣ ቀን ከሌት በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ነገሮችን በማስተዋል እንዲመለከት ማሳሰብ መልካም ይመስለናል፡፡ ገና ለገና ‹‹መረጃው ከቤተ ክህነቱ ሹክ የተባልኩት ነው›› በሚል ከምኑም የሌሉ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ የማይገባ ርምጃ እንዳይወስድ መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ እንዲህ ሆኖ ከተገኘ ግን የበለጠ ችግሩን በማባባስ መብረጃ ወደሌለው ቀውስ መግባት ሊመጣ ይችላል፡፡ ዛሬ ራሳቸውን የኢሕአዴግ ባለሟሎች አድርገው በማቅረብ ቤተ ክርስቲያኒቱን የግል መጫወቻቸው ለማድረግ የሚሞክሩ ግለሰቦችን አጓጉል ምክር በመስማት መንግሥት ቤተ ክርስቲያኒቱንና ልጆቿን መጉዳት የለበትም፡፡
ስለዚህ የአክራሪ እስላሞቹ ጥቃት በ‹‹ጸረ ሰላም ኃይሎች›› እና በ‹‹ሻዕቢያ›› ላይ ብቻ ተላክኮ ዋናው የአክራሪነት እንቅስቃሴ ግን ተድበስብሶ እንዳያልፍ ትልቅ ስጋት አለን፡፡ ተ.መ.ድ በቅርቡ እንዳሳወቀው እኛም ቀድመን እንደምናውቀው ሳዑዲ አረቢያን በመሳሰሉ መንግሥታት የሚደገፍ የአክራሪዎች እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ውስጥ በመስፋፋት ላይ መሆኑን መንግሥት አላየሁም አልሰማሁም ሊል አይችልም፡፡ ይህ ማለት ግን እስላሞችን በሙሉ የሚመለከት እንዳልሆነ ማንኛውም ሙስሊም ወገናችን ይረዳዋል፡፡ የምንቃወመው የዋሐቢያና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቃሷቸውን ‹‹ሐርጀያ(?)››ዎችን ነው፡፡ እነዚህ የእስልምና ቡድኖች የሚያምኑት ክርስትናን ከምድረ ኢትዮጵያ ጠራርጎ በማጥፋት ነው፡፡ እርሳቸው እንዳሉትም ሳይሆን ስለጉዳዩ በተጠሩ ስብሰባዎች ላይ ሳይቀር÷ የኦሮሚያ ም/ፕሬዚዳንት ባሉበት÷ የዛሬ መቶና ሁለት መቶ ዓመት በፊት የተፈጸሙ ታሪካዊ ክስተቶችን በማንሣት ለመከራከር የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ይህ ነገሩን በጥሞና እንድንመለከተው ያስገድደናል፡፡ የፈረሱ ቤቶችን በመሥራትና ጥቂት ግለሰቦችን አስሮ ቶሎ ወደ እስር ቤት በመወርወር ብቻ ችግሩ የሚፈታ አይመስልም፡፡ መንግሥት ጉዳዩን በሥርዓቱ ያጥናው፡፡ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ›› እንዳይሆን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)