November 23, 2006

ዳቦ ተርበን - ካኪ ታርዘናል÷ የሰውነት ክብርና ኢትዮጵያዊ ኩራትስ ተጠምተናልን?


(ነመራ ዋቀዮ ቶላ)
ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሣሱኝን የሚከተሉትን ሦስት ነገሮች በመጀመሪያ በማቅረብ ነው ከሐተታ ይልቅ ጥያቄ ወደሚያበዛው ጽሑፍ የምገባው፡፡ እነሆ፡፡
ሀ. አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው የሰሞኑ ዜና
1. አዲስ አበባ ስቴዲየም ዙሪያ የነበሩ ውብ ዛፎች በእግር ኳስ ፌዴሬሽን ትዕዛዝ ተጨፈጨፉ ብሎ የነገረን ሪፖርተር ጋዜጣ ነው፡፡ ኅዳር 1998 ዓ.ም ነው ይህ የሆነው፡፡
2. የአንበሶች ማሳደጊያው የአዲስ አበባ ‹አንበሳ ግቢ› አስተዳደር ብርቅዬ የሆኑና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዘራቸው በመመንመን ላይ የሚገኙ አንበሶችን በመርዝ ገደላቸው ሲሉ ቢቢሲና ሌሎች የዜና ማሠራጫዎች አስነበቡን አሰሙን፡፡ ... ‹‹Rare Abyssinian lion cubs are being poisoned at a zoo in Ethiopia's capital, Addis Ababa, and their bodies are then sold on to be stuffed. The zoo, founded by Ethiopia's former Emperor Haile Selassie, says it poisons a number of cubs each year because it does not have the space or money to look after them.›› ኅዳር ውስጥ የሆነ ነገር መሆኑ ነው፡፡ ገድለውም አንበሶቹን አድርቀው በጌጥነት ለሚያውሉ ድርግጅቶች እንደሚሸጡ አንዱ ኃላፊ ተናገሩ ይላል በተለይ ከቢቢሲ ያገኘሁት ዜና፡፡

ለ. ገጠመኝ
የዛሬ ሰባት ዓመት አዲስ አበባ ከጓደኞቼ ጋር ከምሳ በኋላ ሻይ ቡና ለመጠጣት ቁጭ ካልንበት ቡና ቤት ‹‹ጎጃም አዘነ›› የምትባለውን መጎናጸፊያ ቢጤ የደረበ ባለቁምጣ ወጣት ዕርጥባን ቢጤ እየለመነ መጣ፡፡ የፈለገ ያለውን ሰጠ የሌለውም ‹‹እግዜር ይስጥልኝ›› ብሎ ‹ተገላግሎ› ወሬውን ይጠርቃል፡፡ ያው ልጅ ከእኛ አለፍ ብሎ ያሉ ሰዎችን ሁሉ እየጠየቀ ቆይቶ ውጪ መናፈሻው ላይ ከተቀመጡ እስያውያን ጋር ደረሰ፡፡ አጥር መሰል ፍርግርግ ብረት አጠገብ ተቀምጠው እርሱ ከአጥሩ ውጪ ቆሟል፡፡ ያለውን ከሌለው÷ የኔ ቢጤውን ከደህናው መለያ ድንበር መሆኗ ነው፡፡ እጁን ዘረጋላቸው፡፡ በልመና፡፡ እስያውያኑ ተያይተው ሲያበቁ አንደኛው ከቦርሳው ዳቦ አውጥቶ ከብረቱ አጥር ለይ አስቀመጠው፡፡ በእጁ ሊሰጠው ሲችል፡፡ መጠየፉ ለመሆኑ ምንም ማስተባበያ አልነበረም፡፡ በደምሥሬ ሄዶ የነዘረኝን ስሜት አላውቀውም፡፡ ዳቦውን ሊያነሣ የነበረውን ልጅ ጮኬ እንዴት እናደስጣልኩት ሳስበው ዛሬም ይገርመኛል፡፡ በማውቀውም በማላውቀውም እንግሊዝኛና አማርኛ እስያውያኑ ላይ ወረድኩባቸው፡፡ እነርሱም በተራቸው ተሸማቅቀው ዳቧቸውን ከቦርሳቸው ከተቱ፡፡ ለተስፈኛውም ጓደኞቼ የሚሰጡትን ሰጥተው ተለያየን፡፡ የዚች ዳቦ ነገር ብዙ አሳሰበኝ፡፡ እንዲያው እንዴት ቢንቁን ነው ያውም አገራችን ላይ ዳቦ ለማቀበል እንኳን የሚጠየፉን አልኩኝ ለራሴ፡፡ እነዚያ እንግዶች ይህንን ያደረጉት አገራችን ላይ ያውም ሕዝብ በተሰበሰበበት መዝናኛ መሆኑን ሳስበው ‹‹በእውነት ዳቦ ተርበን - ካኪ ታርዘናል÷ የሰውነት ክብርና ኩራትስ ተጠምተናልን?›› ብዬ ማስታወሻ ዲያርዬ ላይ አሰፈርኩኝ፡፡ ቀኑ ሚያዚያ 22/ 1992 ዓ.ም ምሳ ሰዓት ላይ ነበር፡፡
ሐ. የተፈጠሩብኝ ጥያቄዎች
ሦስቱን ነገር ገጣጥሜ ለማየት ሞከርኩ፡፡ መናቃችንና ከሰውነት በታች መዋረዳችን ሳያንስ ሊጠበቁ የሚገባቸውን ሀብቶቻችንን እየተከታተልን የምናጠፋ እስክንመስል ድረስ የራሳችን ጠላቶች መሆናችን ግርም የሚል ክስተት ነው፡፡ በብዙ መከራ ያደገ ዛፍ አንዲት ትንሽ ቆርቆሮ ከለለች ብሎ መጨፍጨፍ÷ ውድ የእንስሳ ዘርን የበጀት እጥረት ገጠመኝ ብሎ በመርዝ መፍጀት÷ በምርጫ ሰበብ የራስን ወገን በጠራራ ፀሐይ ልቡንና ግንባሩን በጥይት አረር እየነደሉ መጣል÷ ከጎረቤት ጋር ጦርነት ገጥሞ በወራት ውስጥ ብቻ ከ70 ሺህ በላይ ወጣት መጨረስ/ ማስጨረስ ወዘተ ወዘተ፡፡
ነገሩን ሲመለከቱት እጅግ ግርም የሚል የዕብደት ዓይነት ቲያትር ይመስላል፡፡ ምን እየሆንን ነው? ምንስ እያደረግን ነው? ይህ የዕብደት አዙሪት ማብቂያው የት ላይ ነው? በፖለቲካ አስተሳሰብ ተለያይተን በጥይት ተተጋትገን÷ በዘር ተለያይተን ታቦት ሳይቀር በዘራችን ስም አቁመን÷ ቤተ ክርስቲያናችንን ለወንዛችን ልጆች ብቻ አድርገን÷ አሁን ደግሞ ይባስ ብለን ክርስቲያን ከእስላም ብለን ሰይፍ መዘን ተገዳድለን ... እንዲህ ሆነን እስከመቼ እንዘልቀው ይሆን?
በሰከነ ኅሊና ለማሰብ ለሚሞክር ሰው አገሪቱ እንደ አገር÷ ሕዝቡም እንደ ሕዝብ የገቡበትን ቀውስ በግልጽ ይመለከታል፡፡ ቀውሱ ያለው በአንድ ዘርፍ ብቻ አይደለም፡፡ በሁሉም በኩል ነው፡፡ የፖለቲካው መቸም ግልጽ ነው፡፡ ነገሩ ከዚያ የሰፋና የጠለቀ ነው፡፡ በትምህርት በኩል ልጆቻችን አገሪቱ ደርሳ የማታውቅበት ዓይነት ደረጃው የወረደ የትምህርት ፖሊሲ ተጠቂዎች ሆነዋል፡፡ በመንግሥት የተበላሸ ፖሊሲ ትውልድ እየጠፋ ነው፡፡ ዕድሜ ለወ/ሮ ገነት ዘውዴና ግብረ አበሮቻቸው፡፡ በዘርና በጎሳ በኩልም የአንድ አገር ልጆች እርስ በእርሳቸው በጠላትነት ተፋጠው ለመቆም በቅተዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን የባቢሎን ታሪክ የሚያስታውስ ሁናቴ ላይ ደርሰናል፡፡
ባቢሎናውያን በቋንቋቸው ተግባብተው ፈጣሪያቸውን ግንብ እየገነቡ÷ መንበረ መንግሥቱን ለመናድ ድንጋይ መቆለል ያዙ፡፡ ይህ የትዕቢት ድርጊታቸው ያናደደው ፈጣሪ (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሥላሴ) እንዲህ አለ፡፡ ‹‹ኑ እንውረድ÷ አንዱ የአንዱን እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው›› (ዘፍጥረት 11፡7-9)፡፡ ዛሬም በአገራችን የሆነው ይህን አይመስልምን? አንዱ ከአንዱ ጋር እንዳይግባባ÷ ይልቁንም አንዱ ለአንዱ የጠላትነት ስሜት እንዲኖረው÷ ሁሉም የራሱን ቋንቋ ብቻ እንዲያውቅ የማድረግ ዘመቻ ተዘምቶብናል፡፡ የእናት አባት ቋንቋዎቻችንን ማወቃችንና በአፍ መፍቻ ቋንቋችን መማራችን መልካም ሆኖ ሳለ ከፋፍሎ መግዛትን በሚመስል ኮሎኒያሊስታዊ ዘዴ የሰሜኑን ከደቡቡ÷ የምዕራቡን ከምስራቁ በቋንቋ አጥር ማጠር ትልቅ ግፍ ይመስለኛል፡፡ ከዚህም አልፎ በቋንቋ ሊቃውንት ምርምር ላይ ባልተመረኮዘ መልኩ (ሁሉን የሚያውቁ በሚመስላቸው ካድሬዎች ስብከት) የተለያዩ የአገሪቱ ዜጎች የአገራቸውን ኢትዮጵያዊ ፊደል እንዳይጠቀሙ ተከልክለዋል÷ ይልቁንም የላቲኑን ፊደል የራሳቸው አድርገው እንዲቀበሉ ሆነዋል፡፡ በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠር አንድ ትውልድ የራሱን ፊደል ማንበብ የማይችል በአውሮፓውያኑ የፊደል ገበታ አፉን የፈታ ለመሆን ተገዷል፡፡ ለመሆኑ የላቲኑ ፊደልን ድምጾቹ ከኢትዮጵያዊው ፊደል በላቀ (የግእዝ ወይም የአማርኛ ፊደል አለማለቴን ልብ በሉልኝ÷ የነርሱ ብቻ አይደለምና) ለኦሮምኛ ይቀርበዋልን? የትኛው ሊቅ ነው ያረጋገጠው? ለሲዳማውና ለሱማሌው የራሱ ኢትዮጵያዊ ፊደል ጠላቱ ነውን? ከዚያስ ይልቅ የበታችነትን የሚያላብሰው አፍሪካዊ ያልሆነው የባዕድ ፊደል ይሻለዋልን? ብዙ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ችግሩ መልሱ ቀላል ሆኖ ሳለ መተግበሩ ግን ከባድ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡
ዛሬ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና አገራዊ ኩራትን ሊያመጣና ሕዝቡን ወደ ትልቅ ዕድገት ሊያሸጋግረው የሚችለው ሀብት በሙሉ በጥቃት ውስጥ ነው፡፡ ሕዝቡም የዚህ ሰለባ ነው፡፡ አንድ ኃላፊ ብቻውን በአገራችን ብቻ ያለ አንድን ብርቅዬ እንስሳ በመርዝ ለመፍጀት ያደረሰው የዚህ ሥር የሰደደ አላዋቂነትና ለራስ ሀብት ዋጋ ያለመስጠት አባዜ ነው፡፡ እኚህ ኃላፊ የመንግሥት በጀት ቢያጥራቸው ሌላ ዘዴ ለመፈለግ ምክረዋል? ቢያንስ ቢያንስ የሀብቱ ባለቤት ለሆነው ሕዝብ ነግረዋል? ርዳታ ለጋሾችንና የተፈጥሮ ሀብት ተንከባካቢዎች አማክረዋል? ይህንን ለማድረግ ዘግይተው ሲያበቁ አንበሶቹን በመርዝ ለመግደል ምን አፈጠናቸው? የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑም እንደዛው፡፡ በጠቅላላው ስንመለከተው ዳቦ መራባችንና የምንለብሰው ካኪ ቢጤ እራፊ ጨርቅ መታረዝ ብቻ ሳይሆን የሰውነት ክብርንም እያጣን መሔዳችን ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡
ቸሩን ያሰማን፡፡ አሜን
(የዚህን ጽሑፍ አዘጋጅ potsdamer2005@yahoo.de በሚለው ኢ-ሜይል ማግኘት ይቻላል፡፡)

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)